Saturday, 28 March 2015 09:16

ገንዘቡ ያለው ከታች ነው!

Written by  ብሩህ አለምነህ
Rate this item
(0 votes)

ጥድፍ ጥድፍ የሚሉ እግሮች፣ ቅልጥፍጥፍ የሚሉ እጆች፤
ቁርጥ ቁርጥ የሚሉ ትንፋሾች፣ እዚህና እዚያ የሚያማትሩ አይኖች፤

ጋዜጠኛው በወ/ሮ ውቢት ሁኔታ እጅግ ተገርሟል፡፡ የድምፅ መቅረጫውን እያስተካከለ ወ/ሮ ውቢትን አሁንም አሁንም ያያታል፡፡ ወ/ሮ ውቢት ተወልዳ ያደገችው እዚሁ ምስራቅ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ እንደሆነ አስቀድሞ አውቋል፡፡ የዕድሜዋ ነገር ግን ቸግሮታል፤ “መቼም ዕድሜዋ ከ40-45 ዓመት ሳይሆን አይቀርም፣” የሚል ግምት ለራሱ ሰጠ፡፡ ሆኖም ግን በሰውነቷ ቀልጣፋነት በጣም ተደንቋል፡፡ ወ/ሮ ውቢት ከእንጀራ መጋገር ጀምሮ እስከ ማሸግና በመኪና መጫን ድረስ ያሉትን የስራ ሂደቶች ሁሉ የምትከታተለው በጣም በፍጥነት ነው። ወ/ሮ ውቢትን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ላያት ሰው፣ “እረፍት የሌላት ንብ” ትመስላለች፡፡
ጋዜጠኛውን ሌላው በጣም የገረመው ነገር፣ ወ/ሮ ውቢት ሰራተኞቿን በሙሉ የምትጠራው በቁልምጫ መሆኑ ነው፤ ሚስጥሩን ለማወቅ ጓጓ፡፡ ከሚያያቸው ነገሮች በመነሳትም ብዙ ጥያቄዎችን ማስታዎሻ ደብተሩ ላይ መመዝገብ ጀመረ፡፡ ጥያቄውን ፅፎ ቀና ሲል ወ/ሮ ውቢት በችኮላ እሱ ወደተቀመጠበት ቢሮ ስትመጣ ተመለከተ፡፡
“እሺ ወ/ሮ ውቢት ትንሽ ፋታ ካገኘሽ አሁን ቃለ መጠይቁን ማድረግ እንችላለን?” አለ   ጋዜጠኛው ማስታዎሻ ደብተሩን እየዘጋ፡፡
 “ይቅርታ ልጠይቅህ ነው የመጣሁት፤ እየጨረስኩ ነው፤ትንሽ አንድ 20 ደቂቃ ስጠኝ፤ መኪኖቹን ሸኝቼ እመጣለሁ፤” ብላው ወ/ሮ ውቢት ተመልሳ ሄደች፡፡
“እረ ምንም ችግር የለም ወ/ሮ ውቢት ጨርሰሽ ነይ፤ እኔ እንደሆንኩ ስራ አልፈታሁም፤ ስራችሁን ከርቀት ሆኜ እየተከታተልኩ ነው።” አለ ጋዜጠኛው፣ በልቡ (20 ደቂቃ! 20 ደቂቃ ደግሞ ምናላት! ቀኑን ሙሉ የሚገትሩን እንዳሉ ባወቅሽ፤) እያለ፡፡
ጋዜጠኛው የወ/ሮ ውቢትን ጨዋነትና ሰው አክባሪነቷን አደነቀ፡፡ በጣም የገረመው ነገር ግን ለቃለ መጠይቅ አለመጨናነቋ ነው፡፡ “በጣም ብዙ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጌያለሁ፡፡ ሁሉም ግን ጋዜጠኛን የሚፈሩና ለቃለ መጠይቅም በጣም የሚጨናነቁ ሲሆኑ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የሚናገሩትን ነገር ሁሉ በቃላቸው እስከ ማጥናት የሚደርሱ አሉ፡፡ የወ/ሮ ውቢት ግን እጅግ የተለየ ነው፡፡” አለና ለራሱ፣ ሰዓቱን ሲመለከት የተባለው 20 ደቂቃ እያለቀ ነው፡፡ የመጨረሻ ዝግጅቱን እያደረገ ሳለም ወ/ሮ ውቢት ወደ እሱ እየመጣች መሆኑን ተመለከተ፡፡
“ይቅርታ እንግዲህ የስራ ሰዓት ሆነና ደጅ አስጠናሁህ፤” አለች ወ/ሮ ውቢት የቢሮዋ ወንበር ላይ እየተቀመጠች፡፡
“እረ ምንም አይደለም ወ/ሮ ውቢት፣ እንዲያውም የስራችሁን ሁኔታ እያየሁ መቆየቴ ብዙ ጥያቄዎችን እንዳስብ አድርጎኛል፡፡”
“ዛሬ መላቀቅ የለም በለኛ!”
“እንደዛ ነው እንግዲህ ወ/ሮ ውቢት፤” አለ ጋዜጠኛው፣ በልቡ (ወ/ሮ ውቢት ስራ ብቻ ሳይሆን ቀልድ አዋቂና በራሷም የምትተማመን ሴት ናት፤) እያለ፡፡
“አይ ይሁን እንግዲህ፤ አሁን መጀመር እንችላለን፡፡” አለች ወ/ሮ ውቢት፡፡
“ስራ እንዴት ነው ወ/ሮ ውቢት?” አለ ጋዜጠኛው የድምፅ መቅረጫውን እያበራና የማስታዎሻ ደብተሩን እየከፈተ፡፡
“ስራ ጥሩ ነው፤ ከዕለት ወደ ዕለትም ስራችን እየሰፋና ብዙ ደንበኞችንም እያገኘን ነው፡፡”
“ወ/ሮ ውቢትን እንዲህ ፊትለፊት ሳያት በስራዋ ደስተኛ፣ ጤነኛና በራሷም መተማመን ያላት ሴት ትመስላለች፤ እውነት ነው?”
“እውነት ነው!” ብላ ጀመረች ወ/ሮ ውቢት ፈገግ እያለች፡፡ “እውነት ነው! በምሰራው ስራ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሁልጊዜ የማስበው፣ ስራው እንዴት አሁን ካለበት ደረጃ ወደሚቀጥለው ከፍተኛ ደረጃ እንደሚደርስ ነው። ስራው ተስፋፍቶ ተጨማሪ ሰራተኞች መቀጠር፣ ተጨማሪ መኪኖችም መገዛት አለባቸው፡፡ በምሰራው ስራ በጣም ደስተኛ ስለሆንኩ ነው መሰለኝ ጤንነቴም ተስተጓጉሎ አያውቅም፡፡”
ወ/ሮ ውቢት ስትናገር አትጨነቅም፤ የምታወራው ከጋዜጠኛ ፊት ሳይሆን ልክ ከአንድ የቅርብ ባልንጀራዋ ጋር የምታወራ ነው የምትመስለው፡፡
“እንጀራ ሲጭኑ የነበሩት መኪኖች ያንቺ ናቸው?” ጋዜጠኛው ጠየቀ፡፡
“አንደኛው በድርጅታችን ሀብት የገዛነው መኪና ሲሆን፤ ሌላኛውን ግን ተከራይተነው ነው፡፡ በቅርቡ ግን የራሳችንን ተጨማሪ መኪና እንገዛለን፡፡”
ጋዜጠኛው ተገረመ! ‘እንጀራ በመሸጥ ይሄንን ያህል ደረጃ ይደረሳል’ የሚል ሃሳብ እንኳን በእውኑ በህልሙም አስቦት አያውቅም፡፡ ብዙ ሰው እንጀራ መሸጥ ከኑሮ ችግር የተነሳ የሚሰሩት ስራ እንደሆነ ስለሚያስብ፣ በእንጀራ መሸጥ ለሚተዳደር ሰው ከንፈሩን ይመጣል እንጂ እንደዚህ ትልቅ የሀብት ምንጭ ይሆናል ብሎ የሚያስብ የለም፡፡
“ወ/ሮ ውቢት አሁን ስንት ሰራተኞች አሉሽ?”
“ባጠቃላይ ዘጠኝ ሰራተኞች አሉኝ፤ ሁለት ጥበቃዎች፣ አምስት እንጀራ ጋጋሪዎችና ሁለት ሹፌሮች፡፡ ሁሉም ታዲያ ስራ ወዳድና በጠባያቸውም የተመሰገኑ ናቸው። እንጀራ ጋጋሪዎቹ ወደኔ ድርጅት ከመምጣታቸው በፊት ወላጆቻቸውን በቤት ውስጥ ስራ ከመርዳት ውጭ ምንም ዓይነት ሌላ ገቢ የሚያገኙበት ስራ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ አሁን በወር ጥሩ ደምወዝ እከፍላቸዋለሁ፡፡ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውንም በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ስራው የበለጠ ሲስፋፋ ደግሞ ልክ እንደነዚህ ዓይነት ተጨማሪ ሰራተኞችን እንቀጥራለን፡፡”
“ቅድም ስራችሁን ስከታተል አንድ የገረመኝ ነገር ነበር፤ ሰራተኞችሽን የምትጠሪያቸው በቁልምጫ ነው። ለምንድነው? በአሰሪና ሰራተኛ መካከል እንደዚህ ዓይነት ነገር ብዙም የተለመደ ነገር አይደለም ብዬ ነው፡፡
 “ስለምወዳቸው እኮ ነው! በባህሪያቸውና በስራቸው በጣም ያስደስቱኛል፡፡ በርግጥ ሰራተኛን የማቅረብና እንደዚህ በቁልምጫ የማቅረብ ነገር በባህላችን እምብዛም የተለመደ ነገር አይደለም። አሰሪ ሁልጊዜ የሚቆጣ፣ ደምወዝ የሚቀጣና ከስራ የሚያባርር ስለሆነ በሰራተኞቹ ዘንድ የተፈራ ነው፡፡ ጥያቄው ግን፣ ስራ መሰራት ያለበት በዚህ መንገድ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ በዚህ መንገድ ስራ ሊሰራ ቢችልም፣ አስደሳችና ውጤታማ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ ሰራተኛው በስራው እየተደሰተ አብሮ ከድርጅቱ ጋር ማደግ አለበት እንጂ ድርጅቱ ከሰራተኞቹ ተነጥሎ ሊያድግ አይችልም፡፡ እኔ አነሱን እያስከፋሁና እያሳቀኩ የማገኘው ገንዘብ አያስደስተኝም፡፡ ሰራተኞቼን የማቆላምጣቸው በእኔና በእነሱ መካከል ክፍተት እንዳይፈጠርና በመካከላችን መግባባት፣ መቀራረብና መዋሀድ ስለሚያመጣ ነው፡፡”
ጋዜጠኛው በወ/ሮ ውቢት ንግግር ፈዟል። ማስታዎሻ መያዙን ትቶ በጥሞና ያዳምጣታል። የቱን ፅፎ የቱን ይተወዋል፤ ድምፅ መቅረጫው ይጨነቅበት፡፡ ወ/ሮ ውቢት ንግግሯ ውበት ያለውና የሚያሳምን ነው፡፡
“ወ/ሮ ውቢት ስንት ልጆች አሉሽ? የባለቤትሽና የልጆችሽስ ሚና በስራሽ ላይ ያለው አስተዋፅዖ መንድነው?”
“ሦስት ልጆች አሉኝ፤ የመጀመሪያዋ ልጄ የዩነቨርሲቲ ተማሪ ስለሆነች አሁን ከአጠገቤ የለችም፡፡ ሁለቱ ልጆቼ ግን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ በስራዬ ውስጥ ሁልጊዜ አብረውኝ አሉ፡፡ ተማሪዎች ስለሆኑ ግን ሙሉ በሙሉ በዚህ ስራ ውስጥ እንዲገቡ አልፈቅድላቸውም፡፡ በተረፈ የባለቤቴ እገዛ ግን ተነግሮ አያልቅም፡፡ እኔና ባለቤቴ አንድ መ/ቤት ውስጥ አብረን ነበር የምንሰራው፡፡ የቢሮ ስራዬን ትቼ ወደዚህኛው የግል ስራ የገባሁት ከባለቤቴ ጋር ተነጋግረንና ወስነን ነው፡፡ እኔ እንጀራውን እየጋገርኩ የማቀርብበትን ሆቴል ያገኘልኝም ሆነ ለስራዬ መነሻ የሚሆን ገንዘብ ከመ/ቤቱ ተበድሮ የሰጠኝ ባለቤቴ ነው፡፡ ባጠቃላይ ልጆቼም ሆኑ ባለቤቴ ከእኔ ስራ ጋር በአንድ ቅኝት ውስጥ በመጓዛችን ነው ዛሬ ለዚህ ደረጃ የበቃነው፡፡”


ከቢሮ ስራ ወደ እንጀራ ጋጋሪነት! ጋዜጠኛው በጣም ተደነቀ፡፡ ይሄ በህብረተሰባችን ወስጥ እንግዳ የሆነና እንደ እብደትም የሚቆጠር ውሳኔ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ከዚህ የወ/ሮ ውቢት ውሳኔ ጀርባ ያለውን ውጣ ውረዷንና ቆራጥነቷን ማወቅ ፈለገና ሌላ ጥያቄ አነሳ፣
“ከባድ ውሳኔ ይመስለኛል ወ/ሮ ውቢት! የቢሮ ስራ ትቶ በእንጀራ ጋጋሪነት ለመሰማራት መወሰን በኛ ማህበረሰብ ውስጥ ከባድ ነው፤ ትልቅ ቁርጠኝነትና በራስ መተማመንን ይጠይቃል፡፡ በዚህ በኩል የስራ ባልደረቦችሽን አማክረሽ ነበር? ምን አሉሽ?”
“ቢሮ ውስጥ አብረውኝ የሚሰሩ ጓደኞቼን አማክሬያቸው ነበር፡፡ ቃል በቃል ‘ይሄ እብደት ነው!’ ነበር ያሉኝ፡፡ ‘ሰው እንዴት የተከበረ የቢሮ ስራውን ትቶ ልክ እንደ ችግረኛ አመድ ለአመድ ልርመጥመት ይላል፤ ምን ቸግሮሽ ነው እንጀራ ሸጬ ልኑር የምትይው!’ ብለው በጣም ተቆጡኝ፡፡ እኔ ግን የስራውን አዋጪነት ቀደም ብዬ ከባለቤቴ ጋር በደንብ አይተነዋል፡፡ ደግሞም ከድሮ ጀምሮ በውስጤ የሆነ ነገር ነበር፤ ይሄውም የራሴን የግል ስራ እየሰራሁ በእሱ ማደግን ከድሮ ጀምሮ የምመኘው ነገር ነው፡፡ እናም እስከዚያ ቀን ድረስ ውጤታማ የምሆንበትን ስራ እያጠናሁ ነው የቆየሁት፡፡ በአንድ ነገር ላይ ካመንኩበት ደግሞ የሚያቆመኝ ነገር የለም፡፡ ያንን ነገር ካላሳካሁት እረፍት የለኝም፤ ነጋ ጠባ ውስጤ ተሰንቅሮ ይነዘንዘኛል። ይሄ እንግዲህ የግል ባህሪዬ ነው፡፡ ጓደኞቼ ከውስጥ የሚነዘንዘኝን ነገር አያውቁትም፡፡ እነሱ ነገሮችን የሚያዩት ከራሳቸውና ከማህበረሰቡ አስተሳሰብ አንፃር ነው፤ ለዚህም ነው፣ ‘እብደት ነው!’ ያሉኝ፡፡
ጋዜጠኛው ወ/ሮ ውቢት የቢሮ ስራዋን ከመልቀቋ በፊት የነበረባትን የሃሳብ ሙግት በአይነ ህሊናው መቃኘት ጀመረ። እውነትም ከባድ ውሳኔ ነው! ወ/ሮ ውቢት ከዚህ የሀሳብ ሙግት በኋላ በስተመጨረሻ ወደ ተግባር የተሸጋገረችበትን ቅፅበት ለማወቅ ጓጓና ሌላ ጥያቄ አስከተለ፣
“እና በስተመጨረሻ የቢሮ ስራሽን ለቀሽ ወደ እንጀራ መጋገር ስራሽ እንድትገቢ ያስቻለሽ ቅፅበት ምንድን ነበር?”
“በእንደዚህ አይነት የሃሳብ ሙግት ላይ እያለሁ ድሮ የማውቃት አንድ ጓደኛዬን በአጋጣሚ መንገድ ላይ አገኘኋትና ስለኑሮና ቤተሰብ ማውራት ጀመርን፡፡ እሷ አሁን በምትኖርበት አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴነት ተደራጅታ እየሰራች እንደሆነና ጥሩ ገቢም እንዳላት ነገረችኝ። እኔም የቢሮ ሰራተኛ መሆኔንና ሆኖም ግን ስራዬን ለቅቄ እንጀራ በመጋገር ለተለያዩ ሆቴሎች በማስረከብ ስራ ላይ ለመሰማራት ማሰቤን ነገርኳት፡፡ ከባለቤቴ ቀጥላ ይሄንን ሃሳቤን የደገፈችው ብቸኛዋ ሰው ይቺ የድሮ ጓደኛዬ ናት፡፡ ከምክሮቿ ውስጥ ሁሉ ግን ውስጤን ያቀጣጠለውና ሁልጊዜም ከውስጤ የማልረሳው አንድ ነገር አለችኝ፣ “አትሞኝ! ሰው ሁሉ ጨዋታው ያለው ከላይ ይመስለዋል፤ አይደለም፡፡ ገንዘቡ ያለው ከታች ነው!” ይሄ አነጋገሯ በቋፍ ላይ የነበረውን ሃሳቤን እንዲለይለት አደረገኝ፡፡ ውስጤ በጣም ተቀጣጠለ! በነጋታው የቢሮ ስራዬን ለቀኩ፡፡ ከዚያም አንድ እንጀራ ጋጋሪ ቀጠርኩና ስራዬን ተያያዝኩት፡፡”
ጋዜጠኛው ወ/ሮ ውቢትን የሚሰማት በአግራሞት ነው። “ስራ ፈጣሪ ሰዎች የመክሰር ኃላፊነትን (Risk) ለመውሰድ ደፋሮች ናቸው”፤ የሚለው አባባል ትዝ አለው፡፡ ጋዜጠኛው ሌላ ጥያቄ አነሳ፣
“እና ወ/ሮ ውቢት ትናንትናና ዛሬ እንዴት ናት?”
“ውቢት ትናንትና በትንሽ ቢሮ ውስጥ ተቀጥራ የምትሰራ ነበረች፤ ዛሬ ግን ዘጠኝ ሰራተኞችን ቀጥራ ከተማውን ሁሉ እንጀራ የምትመግብ ናት። ውቢት ትናንትና ወሩን ሙሉ ሰርታ ትንሽ መቶ ብሮችን የምትጠብቅ ነበረች፤ ዛሬ ግን በወር በመቶ ሺ ብሮች የምታንቀሳቅስ ሰራተኛ ሆናለች፡፡ ውቢት ትናንትና ጠዋት ሁለት ሰዓት ወደ ቢሮዋ ገብታ ማታ አስራአንድ ሰዓት ላይ ወደ ቤቷ የምትመለስ ሴት ነበረች፤ ዛሬ ግን ከሌሊት እስከ ሌሊት በትጋት የምትሰራ ባተሌ ሆናለች፡፡ ውቢት ትናንትና ረጅም ኪሎ ሜትሮችን በእግሯ የምትኳትን ሴት ነበረች፤ ዛሬ ግን ከአንድም ሁለት መኪኖች ግቢዋን አጣበውታል፡፡ ውቢት ትናንትና እንደማንኛውም ሰው የምትታይ ነበረች፤ ዛሬ ግን በአርዓያነቷ ብዙ ሴቶችን ለስራ የምታነሳሳ ተምሳሌት ሆናለች። ትናንትና ውቢት ለራሷ የዕለት ጉርስ ብቻ የምትደክም ሴት ነበረች፤ ዛሬ ግን ከራሷ አልፋ ለማህበረሰቡና ለትውልዱ የምታስብ ባለ ራዕይ ሆናለች፡፡ ይሄ ሁሉ ለኔ ደስታን ይሰጠኛል፡፡”
ወ/ሮ ውቢት ወደ ስኬት የመጣችባቸው ዓመታት በጣም ቅርብ ቢሆኑም ዘመኖቿን እንዲህ ውብ በሆኑ ንፅፅሮሽ ማቅረብ መቻሏ ጋዜጠኛውን አስገርሞታል፡፡ ንግግሯ መሳጭና ውስጥንም የሚያነቃቃ ነው፡፡
“ወ/ሮ ውቢት ወደ ፊት ምን ታልማለች? ለሴት እህቶቻችንስ ምን ምክር አላት?” ጋዜጠኛው ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡፡
“ውቢት ወደ ፊት ብዙ ነገር ታልማለች፤ ይሄንን ስራችንን  በማስፋት ለህብረተሰቡ ተጨማሪ የስራ እድሎችን መፍጠር እንፈልጋለን። እንዲሁም አሁን እንጀራ ከምናስረክባቸው ሆቴሎችና ካፌዎች በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ ሌላ ቅርንጫፍ በመክፈት ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግም እያሰብኩ ነው፡፡
ለእህቶቻችን የምመክራቸው ብዙ ነገር አለኝ። በመጀመሪያ ውስጣቸውን በደንብ ማዳመጥ አለባቸው፤ በሃሳባቸው የመጣው ነገር በእርግጥም ከውስጣቸው ፈንቅሎ የመጣ ነገር መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለባቸው፡፡ ይሄንን ውስጠት ካዳመጡ በኋላ በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ወይም የቤተሰብ አባላትን ማስረዳትና ማሳመን አለባቸው። አንድ ሴት በውስጧ ልትሰራው በምታስበው ነገር ላይ ቤተሰቧን ማካተትና የእሷ አጋዦች እንዲሆኑ ማድረግ አለባት፤ ምክንያቱም በስራዋ ላይ የሚያበረታቷትም ሆኑ ብትወድቅ የሚያነሷት እነሱ ናቸው፡፡ ገንዘብ ዋጋ የሚኖረው እነዚህን ሁሉ ቅድመ ሁኔታዎች ካስተካከልክ በኋላ ነው። ከዚህ በኋላ በሙሉ እርግጠኝነት ወደምታልመው ስራ መግባት አለባት፡፡ ሃሳቧን፣ ጊዜዋን፣ጉልበቷንና ገንዘቧን ሁሉ በዚያ ነገር ላይ አተኩራ የምትሰራ ከሆነ በእርግጠኝነት ለውጥ ታመጣለች፡፡
እዚህ ላይ ግን ‘ትኩረት’ ስለሚባለው ነገር ትንሽ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ አንበሳ ሲያድን አስተውለህ ታውቃለህ?” ወ/ሮ ውቢት ጋዜጠኛውን ድንገተኛ ጥያቄ ጠየቀችው፡፡
“በቴሌቪዥን አይቻለሁ፤ ያው በተለመደውና ማንኛውም ሰው በሚያይበት መልኩ ነው እኔም የማየው፡፡” ጋዜጠኛው መለሰ፡፡ ወ/ሮ ውቢት በዚህ ነገር ላይ ምን ዓይነት አዲስ ምልከታ ልታሳየው እንደሆነ ለመስማት ጓጉቷል፡፡
“ብዙ ሰው ከአንበሳ የተሳካ አደን ጀርባ ስላለውና ‘ትኩረት’ ስለሚባለው ነገር ብዙም አያስተውልም። አንበሳ ለአደን ከመሮጡ በፊት የተወሰነ ጊዜ ወስዶ የሜዳ አህዮችን እንቅስቃሴ ያስተውላል፤ ከእነሱም ውስጥ አንዷ ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ሊያድናት የፈለጋትን የሜዳ አህያ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደገና ለብቻው በአትኩሮት ይከታተላል። በስተመጨረሻ የሚንደረደረው ያተኮረባትን የሜዳ አህያ ብቻ ለመያዝ እንጂ በመንገዱ ላይ ያጋጠሙትንና የቀረቡትን የሜዳ አህዮች ለመያዝ አይደለም፤ ይሄንን ማድረግ ለእሱ ትኩረትን መበተንና ጉልበትንም ማባከን ነው፡፡ ሁሉም የሜዳ አህዮች የሚበሉ ቢሆኑም እሱ ግን አንዷ ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ መላ ጉልበቱንና ኃይሉን የሚያውለው ያተኮረባት የሜዳ አህያ ላይ ነው፡፡ ጉልበቱንና ኃይሉን የሚያገኘው ደግሞ ከትኩረቱ ነው፤ እናም ይሳካለታል፡፡
ሰዎች በተለይም ሴቶች ከዚህ የአንበሳ ተፈጥሮ ብዙ መማር አለባቸው፡፡ በመላው ህይወት ውስጥ እጅግ የላቀ ኃይል ያለው ‘ትኩረት’ የምንለው ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሀብቱ ትኩረቱ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ዓለም በተለያዩ የመረጃዎች ጎርፍ የተጥለቀለቀ ነው። ኢንተርኔቱ፣ሬዲዮው፣ቴሌቪዥኑ፣ጋዜጣው፣መጽሄቱ፣ወሬው..ሁሉበተለያዩ መረጃዎችና ዕውቀቶች የታጨቀ ነው፡፡ ትኩረትህን በእነዚህ ሁሉ መረጃዎች ላይ መበተን የለብህም፡፡ ልትሰራው በምትፈልገው በአንድ ነገር ላይ ብቻ አተኩር፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”
ወ/ሮ ውቢት በንግግሯ ጭራሽ እየተቀጣጠለች ሄደች። ጋዜጠኛው በተመስጦ ያዳምጣታል፤’በግል የንግድ ስራ ላይ እንዲሰማሩ እገዛ የሚደረግላቸው ሴቶች ከሁሉ አስቀድሞ አሁን ወ/ሮ ውቢት የምትናገረውን ንግግር ዓይነት በስልጠና መልክ ይሰጣቸው ይሆን?’ ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ ወ/ሮ ውቢት ንግግሯን ቀጠለች፣
“በጣም አስገራሚው ነገር ትኩረት ከፈጠራና ከስራ ጥራት ጋር እንዲሁም ከደስታ፣ ከብልፅግናና ከጤንነት ጋር ሚስጢራዊ ግንኙነት መኖሩ ነው፡፡”
ጋዜጠኛው ተገረመ! ‘ትኩረት’ ስለሚባለው ነገር እምብዛም አስቦበት አያውቅም፡፡ አሁን ከወ/ሮ ውቢት የሚሰማው ሁሉ አዲስ ነገር ሆነበት፡፡ ‘እና እነዚህ ሁሉ ነገሮች ‘ትኩረት’ በሚባለው ነገር የመጣሉ ማለት ነው?’ ጋዜጠኛው ተዓምር ሆነበት፡፡ “እንዴት ወ/ሮ ውቢት?” ጥያቄውን ሰነዘረ፡፡
“እኔ እንጀራ በመጋገር ስራ ላይ ከተሰማራሁ አራት ዓመት እንኳን አልሆነኝም፡፡ ሌሎች በዚሁ ስራ ላይ ረጅም ዓመታት የቆዩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉም ግን ስራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ ለስራው ያላቸው ትኩረትና ክብርም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ አንድ የማረጋግጥልህ ነገር ቢኖር ስራቸውን በዝቅተኛ ትኩረት፣ በምሬትና በእፍረት የሚሰሩ ሰዎች ስራው ላይ የቱንም ያህል ጊዜ ቢቆዩ አይሻሻሉም፡፡”
“ምናልባት የአቅም ማነስ ከሆነስ?” ጋዜጠኛው በመሀል ገባ፡፡
“ሁሉን ነገር ከአቅም ማነስ ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ባላቸው አነስተኛ አቅም እኮ ስራውን እየሰሩት ነው፡፡ ያችን አቅማቸውን ግን ትኩረት የሚያሳጧትና ምሬትም የሚያበዙባት ከሆነ እሷንም ያጧታል፡፡ ምሬት ማለት በራሱ የተበተነ ሃሳብና ፍላጎት ማለት ነው፤ ግማሽ ልብ እዚህ፣ግማሽ ልብ እዚያ፡፡ የሃሳብና የፍላጎት መበተን የሚያጋጥምህ ደግሞ በስራው እምነትና ደስታ ከማጣት ነው። ይሄንን ማወቅ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። በስራው እምነት ከሌለህና የተበተነ ፍላጎትም ካለህ የሚደረግልህ የገንዘብ ድጋፍ እንኳን ቢኖር በተበተነው ሃሳብህ ልክ ገንዘብህንም በማይረባ ነገር ነው በትነህ የምትጨርሰው፡፡ እኔ ወደ እንጀራ መጋገር ስራ ስገባ ባለቤቴ ከመ/ቤቱ የተበደረልኝ ብር በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እናም የተነሳሁት በጣም በትንሽ ብር ነው፡፡ እዛች አነስተኛ አቅም ላይ ግን መላው ትኩረቴን ጨመርኩበት፤ እያንዳንዷን ሽርፍራፊ ሳንቲምና ጊዜ ስራዬ ላይ ነበር የማውላት። ያለበቂ ምክንያት የማባክናት ጊዜና ሳንቲም ታንገበግበኛለች። ነጋ ጠባ፣ ሁልጊዜ የማስበው እንዴት ደንበኞቼን እንደማስደስት፣ እንዴት ስራው እንደሚያድግ ነበር፡፡ በአንድ ነገር ላይ ስታተኩር ያንን ነገር በትጋት የምትፈፅምበት ከፍተኛ ኃይል ማግኘት ብቻ ሳይሆን ያንን ነገር ከሌሎች ሰዎች በተለየና በላቀ ሁኔታ እንዴት ማከናወን እንዳለብህ ሁሉ አዳዲስ ሃሳቦች ይመጡልሃል፤ ባጭሩ የፈጠራ ሰው ትሆናለህ፤ ስራህም ጥራት ይኖረዋል። በዚህም ይበልጥ ደስተኛና ጤነኛ ትሆናለህ፡፡ ስራው እያደገ ሲሄድም ገቢህም በዚያው መጠን እያደገ ይሄዳል፡፡
እናም ሴቶች የትኩረትን ኃይል ማወቅ አለባቸው። መጀመሪያ በምን ዓይነት ስራ ላይ ቢሰማሩ በቀላሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ መለየት አለባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መላው ሃሳባቸውን በዚያ ነገር ላይ ብቻ ማተኮር አለባቸው፡፡ ሃሳብህ በተበተነ ቁጥር ገንዘብህና ኃይልህም አብሮ ይበተናል፡፡ አንድ ሴት መላው አትኩረቷን በምትሰራው ስራ ላይ ብቻ ስታሳርፍ ያ ስራ ለውጥ ማምጣት ይጀምራል፡፡ ስራዋም በፍጥነት ቀና ቀና ማለት ሲጀምር ታየዋለች፡፡ ወዲያውም የሌሎች ደንበኞችን አትኩሮት ማግኘት ትጀምራለች፤ ስራዋ ሌሎችን ሁሉ ይማርካል፡፡ ወደዚህ ከፍ ከፍ የማለት ደረጃ ላይ የምትደርሰው ግን መጀመሪያ ዝቅ ብላ ስትሰራ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጓደኛዬ እንዳለችው ነው - ገንዘቡ ያለው ከታች ነው!!”
ጋዜጠኛው ወ/ሮ ውቢትን የሚያዳምጣት በከፍተኛ ተመስጦ ነው፡፡ ትኩረት የሚባለውን ነገር እንዴት ከፈጠራና ከስራ ጥራት ጋር እንዲሁም ከደስተኛነት፣ ከብልፅግናና ከጤነኝነት ጋር ያገናኘችበት መንገድ ገርሞታል፡፡
የሆነ የሞቲቬሽን ትምህርት የሚከታተል እንጂ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግ አልመሰለውም። ወ/ሮ ውቢት የምትናገረው በንድፈ ሃሳብ ሳይሆን በተግባር ያለፈችበትን የህይወት ተሞክሮ ስለሆነ ምክሮቿ በእርግጠኝነትና በስልጣን የተሞሉ ናቸው፡፡ እንደ ወ/ሮ ውቢት ያሉ የንግድ ስራ ክህሎት ያላቸውን ሴቶች የስኬት ሚስጥር በሚዲያ ማቅረቡ በተለይ የተለያዩ እገዛ የሚፈልጉ ሴቶች ላይ የሚፈጥረውን የመነቃቃት ስሜት ሲያስበው በሚሰራው ስራ ተደሰተ፣ ኩራትም ተሰማው፡፡


Read 2557 times