Saturday, 28 March 2015 09:08

የእንድማጣ ኢየሱስ ት/ቤት ትዝታ

Written by  ከጌድዎን ግምጃ
Rate this item
(3 votes)

(ለቅላቂዎችና አስለቅላቂዎች)

    የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ የእንድማጣ ኢየሱስ ት/ቤት የሚገኘው በደብረ ማርቆስ ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል የአሁኑ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ካለበት አካባቢ ነው፡፡ ት/ቤቱ የተመሰረተው ለጥ ብሎ ከሚታየውና ሣር በበዛበት የውሰታ ወንዝ ሜዳ ላይ ነው፡፡ የውስታ ወንዝ ከላይ ከደጋው እየወረደ መስኩን ለሁለት ሰንጥቆ የሚጓዝ አነስተኛ ወንዝ ነው፡፡
ዋለልኝ አዘነ የተባለ ዘፋኝ እንዲህ ሲል ውሰታን ያነሳሳዋል፡-
ደገኛ በቆሎውን ይለዋል አምባላይ፣
ቤቷ ደብረ ማርቆስ ከውሰታ በላይ፡፡
ድምፃዊው ሙሉቀን መለሰ ደግሞ
እንድማጣ ማርያም እጥጓ ደርሼ
ወይ አለመታደል መጣሁ ተመልሼ
ብሎ ዘፍኗል፡፡ ነገር ግን እንድማጣ ኢየሱስ እንጂ እንድማጣ ማርያም የምትባል ቤተክርስቲያን በአካባቢው የለችም፤ አልተሰራችም፡፡ ይልቅ በዋናው በደብረ ማርቆስ ከተማ አከማ ማርያም የተባለች ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የጥንት ገዥዋ ደጃች ተድላ ጓራ በዐረፉበት ወቅት
የውሽ ወስደው  ጣሉት ደጃዝማች ተድላን፡፡
ይነሳ ነበር አከማ ቢሆን
ተብሎለታል፡፡ ይኸውም ደጃች ተድላ ጓሉ መቀበር የነበረበት የውሽ ሚካኤል ሳይሆን አከማ ማርያም ነበር ለማለት ነው፡፡ ምስጢሩም አከማ ቢሆን ኖሮ ይነሣ ይታወስ ነበር ለማለት ነው፡፡
እንድማጣ ኢየሱስ የት/ቤቱን ዳገታማ ቦታ አልፎ ከሜዳው ላይ ይገኛል፡፡ ከዳገቱ ሥር ደግሞ የአንደኛ ደረጃው ትምህርት ቤት ይገኛል፡፡ ት/ቤቱ የተመሰረተው ረግረጋማና ለምለም ሳር በበዛበት ቦታ ላይ ነበር፡፡ በቦታው ረግረጋማነት ት/ቤቱ እየሰመጠ ስለአስቸገረ፣ ዛሬ በአጭር ርቀት ከደረቁና ከዳገታማው ሥር ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በ1961 ዓ.ም አሀዱ ብዬ ትምህርት ቤት የገባሁት 3ኛ A ነው፡፡ በወቅቱ የስም ጠሪ መምህራችን ወ/ት ሙሉቀን ታደሰ ትባል ነበር፡፡ የሞጣ ሰው እንደሆነች አልፎ አልፎ ስታወራ እሰማ ነበር፡፡ በጊዜው ት/ቤቱ የተደራጀው ከአምስተኛ እስከ 6ኛ ክፍል ሲሆን ያኔ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያህል ነበር የሚታዩት፡፡
ሦስተኛ ክፍል ገብቼ ለመማር የምችል መሆኔን የሚገልጽ ሰርተፊኬት የሰጡኝ አቶ ሸዋቀና ዘውዴ የተባሉና በጊዜው የጎልማሶችና ማይማን ኃላፊ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ በወቅቱም፡
ትምህርት ተስፋፋ ከፍ ከፍ ባለ ዘዴ፣
በዳሬክተራችን ሸዋቀና ዘውዴ
እየተባለ ደብረ ማርቆስ ውስጥ ይወደሱ ነበር። እንድማጣ ኢየሱስ የተባለው አዲሱ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እየተቀበለ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያስተምራል መባልን እንደሰማሁ አቶ ሸዋቀና ዘውዴ የሰጡኝን ሰርተፊኬት ይዤ ወደ ት/ቤቱ ሄድኩ፡፡ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር አጭርና ጠይም መልክ ያላቸው አቶ ጋሻው ከበደ ነበሩ፡፡ በጠባያቸው ኮስተር ረጋ ያሉ አስተዋይ ሰው ናቸው፡፡ ሁኔታዬን አይተውና ገምግመው ለ3ኛ ኤ ስም ጠሪዋ ለወ/ት ሙሉቀን ታደሰ ማስታወሻ ጽፈው፣ የይግባ ፍቃድ ፈርመው ሰጡኝ፡፡
ወደ ት/ቤቱ የሄድኩት ጋቢ ለብሼ ስለነበር፣ “ከነገ ጀምሮ ጋቢ ለብሰህ እንዳትመጣ” በማለትም አስጠነቀቁኝ፡፡ በነጋታው በእድሜ ከእኔ ከሚያንሱ ልጆች ጋር መስመር መስመር ይዞ ከተዘጋጀው ግንዲላ ላይ ስቀመጥ ሁሉም አትኩረው አዩኝ። ያኔ በክፍል ውስጥ ልጆቹ የሚማሩት በተጠረበ ግንዲላ ላይ በመቀመጥ ነበር፡፡ ከ1ኛ እስከ ስድስተኛ ያሉት ክፍሎች ሊሾ ስላልተደረጉ በየሳምንቱ ዐርብ ዐርብ በክፍል አለቆች አማካይነት እበት ከየቤቱ እየመጣና ከሜዳም እየተለቀመ ክፍሎች ሁሉ የጤፍ አውድማ እስኪመስሉ ድረስ ይለቀለቁ ነበር፡፡ በየቀኑ በመውጫ ሰዓት ላይ በተመደበው ተረኛ ይጠረጉና ይጸዱም ነበር፡፡ አስለቅላቂዎችና አስጠራጊዎች የየክፍሉ አለቆች ሲሆኑ ለቅላቂዎችና ጠራጊዎች ደግሞ ተማሪዎች ናቸው፡፡
እኔ 3ኛ ክፍል ስገባ፣ የክፍል አለቃው በፈቃዱ ለሽተው ይላል ነበር፡፡ በክፍሉ ቁጥር አንድ ረባሽ ደግሞ አቤ ኅብስት ይባላል፡፡ አቤ ኅብስት ፊቱ ሾል፣ ዓይኑ ደቀቅ ያለ ቁመተ ረጅም ተማሪ ነበረ። ከሁሉም ተማሪ ጋር በመጣላትም ይታወቃል። ሁልጊዜ ይከሰሳል ይከስሳል፡፡ በፍቃዱ ለሽተው ደግሞ ገራገርና ቅንም ስለሆነ ሳይቀጣ ያልፈዋል። በዚህ ድርጊቱ በፈቃዱ ለሽተው ተሽሮ እኔ አለቃ ሆንኩ፡፡፡
አቤ ኀብስት በየቀኑ መረበሽና መክሰስ ይወድዳልና እኔን በክፍሉ የስም ጠሪዋ በወ/ት ሙሉቀን ታደሰ ዘንድ ከሰሰኝ፡፡ እርስዋ ፊት እንደቀረብኩ፤ “ዐቃጣሪ” ብዬ ሰደብኩት፡፡ ለካንስ እንዲህ ተብሎ አይሰደብም ኖርዋል፡፡ እትየ ሙሉቀን ቱግ አለችና ጣቶቼ ደም እስኪያንጠባጥቡ ድረስ ገረፈችኝ፡፡ እኔም በተራዬ የክፍል አስለቅላቂ ሆኜ ስሰራ፣ አቤ ኅብስት ሳይለቀልቅ በመቅረቱ አስገርፌዋለሁ፡፡ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ላሉ ክፍሎች ዋናው የተማሪዎች ተጠሪና አስለቅላቂ ደግሞ ሙሉነህ ሰውነቴ የሚባል ተማሪ ነበር፡፡ በተለይ መምህራን ቀብር ሲሄዱ በየክፍሉ እየገባ ት/ቤቱን ይቆጣጠር ነበር፡፡ ሙሉነህ ረጅም፣ ቀጭንና ጠባዩ የተመሰገነ ልጅ ሲሆን ልክ እንደኛ ሁሉ ቁምጣውን ለብሶ በባዶ እግሩ ነበር የሚጓዘው። ሰውነቱ ቀጭን ስለሆነ ቁምጣው ከአሁን አሁን ሾልካ መሬት ላይ የምትወድቅ ትመስል ነበር፡፡
አንድ ጊዜ ደሞ ለት/ቤቱ ማስፋፊያ ገንዘብ ይዋጣ ተብሎ የሀብታም ቤተሰብ ብር 150፣ መኸከለኛ 100፣ በጣም ዝቅተኛ 50፣ ከዚህ ያነሰው ብር 30 እንዲከፍል በወላጆች ኮሚቴ ጭምር ተወሰነ፡፡ እና እኔም በጊዜው ብር 50 እንድከፍል ተጠይቄ ነበር። ነገር ግን ደብረ ማርቆስ ምንም ዓይነት ቤተሰብ እንደሌለኝ ለወላጆች ኮሚቴ ሊቀመንበር ለአቶ ይኩኖ ነግሬ በነጻ እንድማር ፈቅደውልኝ መማሬን ቀጠልኩ፡፡
በወቅቱ ከነበሩ መምህራን ውስጥ አቶ ሙሉቀን፣ አቶ ዘለቀ፣ ወ/ት ሙሉቀን ታደሰ (ብቻ በጊዜው በት/ቤቱ ውስጥ ወንድም ሴትም ሆነው 3 ሙሉቀኖች ነበሩ) እንደገና የመዝሙር መምህራችን ጋሽ ጫኔ አይረሱኝም፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት ት/ቤቱ የተሰራው ሳር በበዛበት ቀዝቃዛ ቦታ ላይ ስለነበር ጧት ጧት ብርዱ ሲያንቀጠቅጥ ለጉድ ነው፡፡ ትንሽ ያረፈደ ተማሪ ደግሞ (መቼም የዘበኛ ደግ የለውምና) ኃይለኛና ጨካኝ በነበሩት በአባ ደምሴ፣ እጅና እግሩ ይገረፋል፡፡ እያለቀሰ ወደ ክፍል የሚገባው ተማሪ ብዙ ነበር፡፡ ተማሪ ሁሉ ደስ ይለው የነበረው ረፋዱ ላይ በመዝሙር ክፍለ ጊዜ ወደ ውጭ ሲወጣ ነው፡፡ በት/ቤቱ ሳር ላይ በባዶ እግር እየተሯሯጡ መጫወት በጣም ያስደስት ነበር፡፡
የመዝሙር አስተማሪው ጋሽ ጫኔ አጠር ያለና ቀይ ሲሆን ሁልጊዜ በኮትና ሱሪው ላይ ነጭ ጋቢ ደርቦ ይመጣል፡፡ መስኩ ላይ ያስቀምጠንና መዝሙር አስመርጦን ዘምሩ ይለናል፡፡ መዝሙሩን ሞቅ አርገን መዘመር ስንጀምር፣ “እንዳታቋርጡ መጣሁ” ይለንና በእንጨት አጥሩ በኩል ሾልኮ ወደ አንዱ አረቄ ቤት ይገባል፡፡
እኛም መዝሙሮችን እያማረጥን እያጨበጨብን እንዘምራለን፡፡ እኔም ከአስለቅላቂነቴ በተጨማሪ አዘማሪ ነበርኩ፡፡ ያኔ ጋሽ ጫኔ ከሚያስዘምረን መዝሙሮች ውስጥ ትዝ የሚለኝ፡-
“ሰንደቅ ዓላማችን ስንላት በዜማ፣
ግሩም ያላት ግርማ ግሩም ያላት ግርማ፡፡”
“ለባላገሮች ቤት አላቸው፣
ይደሰታሉ በአዝመራቸው፡፡”
“ደስ ይበልሽ ጎጃም
ፍኖተ ሰላም፡፡”
“መንግሥት እንደ ዳዊት ቡራኬ
እንደ ሴም፣
አንዲት የተሰጠው ማንም ሰው የለም፡፡”
“ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ፣
መልካም ባለሙያ፡፡”
ከመዝሙር መዝሙር እያማረጥን ስንዘምር ጋሽ ጫኔ ሙክክ ብሎ፣ ዓይኑ በርበሬ መስሎና አንደበቱ ተኮላትፎ ይመጣል፡፡ ከዚያም ወደ ክፍላችን እንድንገባም ያባርረናል፡፡ ቀድሞ የእንድማጣ ኢየሱስ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የነበረበት ቦታ በረግረጋማነቱ ምክንያት ፈርሶና ሜዳ ሆኖ ሳየው የቆየ ትዝታ ቀስቀሶብኝ ነው ይህችን ጽሑፍ የተከተብኳት፡፡ ቦታው እድለኛ ሆኖ ከበላዩ ዩኒቨርሲቲ መከፈቱም በእጅጉ ያስደስታል፡፡ እሰየሁ ብያለሁ!!

Read 2527 times