Saturday, 28 March 2015 09:11

“ገብሬ እና እኔ” ምናባዊ ወግ (cyber sonata)

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

“…እና ከመሀል ልጀምርላችሁ”
አንድ ሙዚቃ ከፈትኩኝ፡፡ ሙዚቃውን ላፕቶፕ ላይ ተጭኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ላፕቶፑ ደግሞ ተሰብሮ የተጠገነ ነው፡፡ የሰበርኩትም እኔ ነኝ፤ ያስጠገንኩትም እኔ ነኝ፡፡ ካስጠገንኩት በኋላ እየወደድኩት መጣሁ። በፊት እጠላው ነበር፡፡ ጊዜዬን ስለሚያባክንብኝ…መጥፎ ፊልሞች ሳይበት እንድውል ስለሚያደርገኝ…ከመፅሐፍት ጋር ሊነጣጥለኝ ደባ ይሸርባል ብዬ በስህተትም ቢሆን ስለማምን ወዘተ…፡፡ እየናቅሁት ስሸከመው ቆይቼ አንድ ቀን እብደት ያባውን ሆድ ብቅል አወጣው፡፡ ላፕቶፔን ሰበርኩት፡፡
ሰብሬው የተገላገልኩ መስሎኝ ነበር፡፡ ሳምንት ሳያልፍ እነዚያ ያስጠሉኝ ፊልሞች ይናፍቁኝ ጀመር። በላፕቶፑ ምክንያት የተራራቅኋቸው መፅሐፍት…ብርቅ የሆኑብኝ ስርቃቸው እንጂ ሳቀርባቸው ይሰለቻሉ፡፡ በተለይ አዳዲስ ሽፋን ያላቸው መፅሐፍት… የፊደሎቻቸው ጠረን አላስቀርብ አለኝ። በሰለቹኝ መጠን ሰባራው ላፕቶፔ ይናፍቀኝ ጀመር።
ስለዚህ ለመስበር አንድ ደቂቃ ያልፈጀው ተግባር ለመጠገን ብዙ ወራትን ወሰደ፡፡ ብዙ ገንዘብም አስወጣኝ፡፡ ከሀኪም ቤት ወጥቶ ቤቴ ሲገባ ላፕቶፑ ከጦር ሜዳ ቆስሎ የመጣ ወንድሜን ይመስለኝ ጀመር፡፡ በጥንቃቄ እየከፈትኩ፣ በጥንቃቄ እየዘጋሁ አስተኛው ጀመር፡፡ ጉረኛነቱ ቀንሷል፡፡ ሳይሰበር በፊት “አቅሜ አይችልም፣ አራዳ ነኝ” እያለ ያናፋ ነበር፡፡
እና ከእለታት አንድ ቀን ከበሽተኛ እንቅልፉ ቀሰቅሼ ሙዚቃ እንዲከፍት ጠየቅሁት፡፡ ማዘዝ ድሮ ቀርቷል፡፡ በፍጥነት ካዘዝኩት ፈዞ ይቀራል። ስለዚህ ጠየቅሁት፡፡ አይዞህ አትቸኩል… ቀስ ብለህ… “Take five” እያልኩ… በቀላል ጃዝ አስመስዬ ረቂቅ ሙዚቃ እንዲከፍትልኝ አዘዝኩት። እና ከዚህ በፊት ያልሰማሁትን ሙዚቃ ከፈተልኝ፡፡
ሙዚቃ ከቅርብ አመታት ወዲህ ብዙም ግድ የማይሰጠኝ ነገር ሆኖብኝ ቆይቻለሁ፡፡ ነብሴ ከጆሮዬ ርቆ ተደብቆ ነበር፡፡ በተለይ ሙዚቃ የማጫወት ስልጣን ለሁሉም ግለሰብ እና በሁሉም ስፍራ እንዲባልግ ከተኮነንን ወዲህ፣ ጆሮዬ የጩኸት ፍሳሽ ማስወገጃ መሳሪያ እንጂ ከነብሴ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖረው አድርጌ ደፍኜዋለሁ። ጆሮ ጩኸትን የሚያስገባ እና ምንም የማድመጥ ሙከራ ሳያደርግ የሚያስወጣ ነገር ሆኗል ለኔ፡፡
ጆሮዬን ወደ ጉበት ቀይሬው ቆይቻለሁ። የድምፅ መርዝ ነፍሴንም ሆነ አእምሮዬን እንዳይጐዳ እንደአገባቡ ማስወጣት ብቻ ነበር የየውሎ አላማዬ።
ምናልባት ላፕቶፕ ከመሰበሩ በፊት በላዩ ላይ የተጫኑትን በሙዚቃ ስም የተሰየሙትን ፋይሎች ለመክፈት ሙከራ የማላደርገው በራሴው እጅ ራሴኑ እንዳልጐዳ ስለምፈራ ሳይሆን አይቀርም። ግን አስታውሳለሁ መጠጥ ጠጥቼ ስሰክር ብቻ ጩኸቶቹን በጆሮዬ ላይ ያሻቸውን እንዲሆኑ ነፃ እለቃቸው ነበር፡፡ ስሰክር ስለ ሁለቱም ጉበቶቼ ደንታ ስለማይሰጠኝ፣ በራሴው እጅ የራሴው ጤና ላይ አልኮል እለቅበታለሁ፣ በራሴው እጅ ራሴው ጆሮ ላይ ደሞ  ጩኸት፡፡ መጠጥን እንደምጠላው ላፕቶፔን መጥላቴ ምክንያቱ ከዚህ ግንኙነት የመነጨ ሳይሆን አይቀርም፡፡
መጠጡ እና ሙዚቃው በሂደት እንደሰባበሩኝ፣ እኔም በሂደት የመጠጥ ጠርሙሱን እና ላፕቶፑን ሰበርኳቸው፡፡ በላፕቶፑ ጠርሙሱን ወይንም በጠርሙሱ ላፕቶፑን የትኛውን ለየትኛው መስበሪያ እንደተጠቀምኩ አላውቅም፡፡ ድምጽ በሚያወጣው ላፕቶፕ እብደት የሚያወጣውን ጠርሙስ ወይንስ ተገላቢጦሽ?
ብቻ ጠዋት ስነቃ…ሦስታችንም ተሰባብረን ወድቀናል፡፡ ከፍተኛ ጩኸት የጆሮዬን ጉበት፣ ከፍተኛ መጠጥ የሆድ እቃዬን ጉበት ከጥቅም ውጭ አድርገውታል፡፡ ከውስጥ እቃዎቼ ውጭ የሚላወስ እኔነት ካለኝ እሱም ገንዘቤን የማገኝበት ስራዬ ነበር። ስራዬንም በራሴ እጅ ቆርጬ ጥየዋለሁ፡፡ ስራዬ በሙሉ ያለው ላፕቶፔ ላይ ነው፡፡ ላፕቶፕ ከሌለ ስራ የለም፡፡ በራሴ እጅ ራሴን እንደ ዳማ እየዘለልኩ በልቼ ጨርሻለሁ፡፡ ራሴን በልቼ በውድቀቴ ላይ ነግሻለሁ፡፡ ስለዚህ ስራ ለተወሰነ ጊዜ አቆምኩ፡፡
ስራ ሳቆም ገንዘብ ቆመ …ገንዘብ ሲቆም አልኮል መጠጣት ቀረ፡፡ ገንዘብ ሲቆም ወደ ከተማ መውጣት ቀረ፡፡ ወደ ከተማ መውጣት ሲቆም ጩኸት ቀረ፡፡ ጩኸት ሲቀር የተደበቀችው ነፍሴ ቀስ እያለች ወደ ጆሮዬ ብቅ ማለት ጀመረች፡፡
እንዲህ ከተሸሸገችበት ወደ ጆሮ አፋፍ ወጥታ ብቅ በማለት ላይ ሳለች አንድ አጋጣሚ መጣ፡፡ እጄን መልሶ የሚሰጠኝ አጋጣሚ፡፡ እጅ የሚሰጠኝ አጋጣሚ ጩኸትን መልሶ የሚሰጠኝ አጋጣሚም መሆኑ አልጠፋኝም፡፡ ላፕቶፔ ሲጠገን ነፍሴ እንደሚበላሽ፣ ላፕቶፔ ሲጠገን ኪሴ እንደሚሞላ እና ሰላሜ እንደሚጐድል አውቀዋለሁ፡፡ ግን ጉድለቴ ናፈቀኝ። ነፍሴም ሰብቶ አስጨነቀኝ፡፡ ገዳም ሊያስገባኝ ሆነ። ‘ኦሽ’ን ሊያደርገኝ ያስፈራራኝ ጀመር። ላፕቶፑ ተጠገነ፡፡
ጉበቱ ባለቀ ጆሮዬ ውስጥ በቀስታ የመጀመሪያውን ሙዚቃ ከፈትኩ፡፡ ነፍሴ ሰብቷል፡፡ የሚያርፍበት ነገር ያስፈልገዋል፡፡ በአይን የሚገባውን ንባብ፣ ከአፍ የማያልፈውን ፀጥታ ለወራት አጣጥሟል፡፡ ነፍሴ በጆሮዬ በኩል ብቻ ተርባለች፡፡
ሰባራው ላፕቶፕ ሲጠገን… እንደኔው ረጋ ያለ ሆኗል፡፡ ፍጥን - ፍጥን አይልም፡፡ ክፈት ሲባል ብዙ ያስባል፤ ያሰላስላል፡፡ “መክፈት ጥሩ ነው አይደለም?” ዝጋ ሲባልም ያስባል “መዝጋት ጥሩ ነው አይደለም?”
እኔ እና ላፕቶፔ አንዳችን ሌላችንን ሰብረን፣ እርስ በራሳችንን ተሰባብረን፣ እርስ በራሳችን ተጠጋግነን ተመልሰን አንድ ቤት ገብተናል፡፡ ሁለታችንም ረጋ ያልን ሆነናል፡፡ ላፕቶፑ ከዚህ በፊት እንደ እቃ ነበር። የእቃ ስም ነው የነበረው፡፡ የጅምላ ስም የጅምላ ጠባይ፡፡ አሁን ግን መንፈስ አበቀለ፡፡ የሰው ባህርይ አወጣ፡፡ ዝግ አለ፡፡ አርቆ አስተዋይ ሆነ፡፡ እቃን አሰላሳይ የሚያደርገው “ቫይረስ ሲጠቃ ነው” የሚሉትን አላመንኳቸውም፡፡
“HP” የሚል የእቃ ስሙን ቀይሬ “ገብሬ” ብዬ ክርስትና አነሳሁት፡፡ “ገብረ - እኔ” ነው። በውስጡ ያመቃቸውን ሙዚቃዎች አስመርጦ አንዲቱን በዝግታ ከፈተልኝ፡፡
የፒያኖ ሙዚቃ ነው። ያዘነ ሙዚቃ። ባዘነ ሙዚቃ አንደበት የሚተረክ፡፡ ተሰብረው የተጠገኑ ጣቶች የሚወለውሉት ሙዚቃ። ጣቶቹ ፒያኖውን በደንብ ያውቁታል፡፡ ማለት የፈለጉትን ያናግሩታል። በል ተብሎ የታዘዘውን ብቻ ሳይሆን ማለት የፈለገውንም ነው ማዜም የሚችለው። ላፕቶፔ የፒያኖውን እና የተጫዋቹን ሀዘን ቀስሞ አስደመጠኝ። ነብሴ አደመጠች፡፡ አድምጣ ተነካች። ለካ ለማድመጥ ማዘን ያስፈልጋል፡፡ ድሮ፤ የሬሳ መሸኛ ይመስለኝ የነበረው የክላሲካል ሙዚቃ፣ በአዲስ መንፈስ ራሴን እንድቀበል አደረገኝ፡፡ የተሸኘው ሬሳ የበፊቱ ቅብጥብጥነቴ ነበር፡፡ የበፊቱ ቅብጥብጥነቴ ከቅብጥብጡ አዲስ ኮምፒውተር ጋር ተሸኝቷል፡፡ አዲሱ እርጋታዬ ረጋ ካለው ላፕቶፕ ጋር ተወልዷል።
ላፕቶፑ የፒያኖውን ሙዚቃ ቀድቶ አይደለም የሚያስደምጠኝ፡፡ የተሰበረ አራዳ ማለት ራሱ ለካ ፒያኖ ነው፡፡ ሰባራ እቃዎች እና ሰባራ ሰዎች ለካ አንድ ናቸው፡፡ ሰው እና መኪና፣ ባርያና ጌታ አይደሉም ለካ፡፡ መኪናውን የሰራው ሰው ቢሆንም ሰው እና መኪና አንድ ላይ ሆነው ነው የሚነግዱት፡፡ ሰው እየነዳ አጋጨው ቢባል ወይንም መኪናው እየተነዳ ተጋጭ ቢባልም እንኳን፣ አደጋው ግን አንድ ላይ ነው የሚደርስባቸው፡፡ ከአደጋው በኋላ ይግባባሉ፡፡ መኪናውም ጋራዥ ሰውም ሆስፒታል ይገባል፤ አንድ ላይ በተጓዙበት የቅብጥብጥነት መዘዝ፡፡
ከላፕቶፑ ውስጥ የወጣው የሚያሳዝን ሙዚቃ፤ የሰው ብቻ ሳይሆን የእቃዎችም እሮሮ ነው፡፡ አንድ ላይ ነው የሚወድቁት፡፡ ሙዚቃውን የሚሰማው የደረሰው ሰው ብቻ አይደለም፡፡ እኔም እሰማዋለሁ። መስማት የቻልኩት ግን አሁን ነው፡፡ ሙዚቃውን የደረሰው ሰውን አይነት ሀዘን ሲደርስብኝ፡፡ ፒያኖው ከእንጨት ቢሰራም ሀዘንን የመግለፅ አቅም ስላለው ነው ሙዚቃውን ለማፍለቅ ያስቻለው፡፡ የመግለፅ አቅም ደግሞ የመረዳትም አቅም ነው፡፡
ላፕቶፔ ተሰብሮ ባይጠገን… ተሰብሮ የተጠገነ ፒያኖን ለቅሶ ማስተጋባት ባልቻለ ነበር፡፡ እኔም ተመሳሳይ ነኝ፡፡ ተጐድቼ ባልድን፣ ጐድቼ የማዳንን ጣዕም ባላወቅሁ ነበር፡፡ የሙዚቃ ትርጉም ራሱ በአጭሩ መጐዳት እና መዳን ነው፡፡ የጥበብ የመጀመሪያ ልሳን ሙዚቃ ነው፡፡ ሙዚቃን ለማድበስበስ ንግግር ሙዚቃን እየቆራረጠ፣ እየተንተባተበ ይገባል። መንተባተቡ የማያስታውቅ በውበት የተቀመመ ንግግር “ግጥም” ተብሎ ይጠራል፡፡
በመጥረቢያ ከተፈለጠ ዛፍ ውስጥ የሀዘኑ ቅርጽ የሚገለጥበት መንገድ ከተቸረው… ፒያኖ ሆኖ ስሜቱን ይገልፃል፡፡ ዛፉ…ዛፍነቱን በመጥረቢያ ስለት ሲያጣ ያዝናል፤ በአናጢ ህክምና ከሞተው ዛፍነቱ እና ሀዘኑ ተላቅቆ ፒያኖ ሆኖ ይወለዳል፡፡ ሳይወለዱ መሞትም ሆነ ሳይሞቱ መወለድ አይቻልምና፡፡
የአፈጣጠር ሞቱን ከአወላለዱ ጋር… ስቃዩን ከደስታው ጋር እየመዘነ ፒያኖው ያዜማል፡፡ ሰው ባይቆርጠው እንጨቱ አያዝንም…ሰው ፒያኖ አድርጐ ባይወልደው እንጨቱ አይዘፍንም፡፡
ሰውንም እንደ ዛፉ የሚቆርጠው ሀዘን ይገጥመዋል፡፡ ከሀዘኑ ሲያገግም ስንኝ ወይ የሙዚቃ ዜማ በውስጡ ያበቅላል፡፡ በውስጡ የበቀለውን ሀዘን ወደ ውልደት የሚቀይረው በመሳሪያዎች አማካኝነት ነው፡፡
እነዚያም መሳሪያዎች ግን እንደሱው ከድሮው ማንነታቸው ተቆርጠው በአዲስ ማንነት የበቀሉ እስካልሆኑ ድረስ በውስጣቸው መልዕክትን ማስተላለፍ አይችሉም፡፡ የሚያስተላልፉት መልዕክት የሰው ልጆችን የስጋ እና ደም እንጉርጉሮ ብቻ ሳይሆን… የራሳቸውንም የቁስ ነብስ እሮሮንም ጭምር ነው፡፡ ስለሚሆንም፤ ተሰብረው የተቃኑ የእቃ እና የሰው ነፍሶች በትብብር አዲስ ውበት ይፈጥራሉ፡፡
ቀርከሃ ጐብጦ ወንበር ይሆናል፤ ሰው ጐብጦ ይቀመጥበታል፡፡ አንዱ በመቀመጥ ሌላው በማስቀመጥ አዲስ ማንነታቸውን ያሳርፋሉ፡፡ ባልተቆረጠ እና በጋለ ሚስማር ባልተበሳ ሸንበቆ ዜማ አይወጣም፡፡ ሸንበቆውን የሚቆርጠው እና የሚበሳው ሰው መሳሪያውን ማበጀት የቻለው… ከራሱ ህይወት ውጣውረድ… የተቆረጠውን እና አለፍ አለፍ ብሎ በጊዜ እና እጣ-ፈንታ የጋለ ሚስማር የተበሳበትን ልምዱን በሸንበቆው ላይ ተርጉሞ ነው። በሸንበቆው ቀዳዳ የሚልከው እስትንፋሱ ከእኩል የህልውና ክፍተቱ እና የሀዘን ሽንቁሮቹ ጋር የተስማማ እስካልሆነ ድረስ ውበት አይደመጥም፡፡
ሙዚቃው በላፕቶፔ አንደበት ሲያንጐራጉር ከላይ ሹክ አለኝ፡፡ ወይንም ያለኝ መሰለኝ፡፡ ሙዚቃውን ደጋግሜ አደመጥኩት፡፡ መልዕክቱ አንድ ነው፡፡ ነፍሴ በጆሮዬ ወጥታ በሙዚቃው ውበት ላይ ትርጉሟን አገኘች፡፡ ባገኘችው ትርጉም ላይ በፀጥታ አርፋበት ቆየች፡፡ በፀጥታው ውስጥ እኔነቴን በሁሉም ነገር ላይ አንድ ሆኖ አገኘሁት፡፡
አልጋዬም፣ ወንበሬም፣ መስታወቴም እኔን ስለመሆናቸው እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ አሁን በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ እኔን መስለው የከበቡኝ እቃዎች ሁሉ…በሀዘን ውስጥ አደብ ገዝተው በፀጥታ የተዋጡ… ተሰብረው የተጠገኑ የስጋ ዘመዶቼ መሆናቸው ታወቀኝ፡፡  

Read 2027 times