Saturday, 28 March 2015 09:04

ለጠ/ሚኒስትሩ የሞ ኢብራሂምን 5 ሚ. ዶላር ተመኘሁላቸው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

የኦህዴድ ድንገተኛ የርችት “ተኩስ” ክፉኛ አስደነገጠኝ

ባለፈው ረቡዕ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ገደማ የሰማሁት ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እንዴት ክው እንዳደረገኝ አልነገራችሁም፡፡ ስንት ሃሳብ----ወደ አዕምሮዬ መጣ መሰላችሁ? (ለአንድዬም ቴክስት ሜሴጅ አድርጌአለሁ!) ግን የምን ተኩስ ይሆን? የእርስ በእርስ የውስጥ ሽኩቻ? ወይስ አንዱ ጥርስ የነከሰብን የአሸባሪ ቡድን አዲስ አበባ ላይ መሽጎ? ብቻ ምን ልበላችሁ ---- ስጋት፣ ፍርሃት፣ ድንጋጤ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ድንዛዜ ወዘተ------ በቅጽበት መንፈሴንና ስሜቴን ተቆጣጠሩት፡፡ ሞባይል አንስቶ መደዋወልም እኮ የአባት ነው፡፡ ግን ማን ከድንዛዜ ያውጣኝ?
የተኩሱ ድምፅ ሲጨምር ነው ድንገት ከተቀመጥኩበት ተስፈንጥሬ መስኮቱ ጋ የደረስኩት። መስኮቱን በጠባቡ ከፈት አድርጌ ወደ ውጭ አጮለቅሁ፡፡ ድንጋጤዬ ወደ መገረም ለመቀየር ቅፅበት አልፈጀበትም፡፡  (“ሰርፕራይዝ ኤንዲንግ” ያለው አጭር ልብወለድ በሉት!) ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ ነገርየው ተኩስ አልነበረም፡፡ ፌሽታ፡፡ ልደት፡፡ ኦህዴድ ለ25ኛ ዓመቱ ያስተኮሰው ርችት!! (ለመሆኑ ርችት ስንት ገባ?)
እናላችሁ---ወደ መስቀል አደባባይ ግድም ያለው ሰማይ፣ በሚፈነዳው የርችት ህብረቀለማት ዓለሙን ሲያይ አመሸላችሁ፡፡ እኔ ግን የርችቱ አምራች ናት ብዬ የጠረጠርኳትን ቻይና በሆዴ ወቅስኳት፡፡ ምናለ የሪችትን ድምፅ ከጦር መሣሪያ ድምጽ ለየት ብታደርገው?! እንዴት---- የፌሽታና የጥይት ድምጽ እስኪያሳሳት ድረስ አንድ ይሆናል? በሌሊቱ ሰማይ ላይ የቀለማት ምትሃት የሚሰራ የሚመስለውን የሪችት ተኩስ ጥቂት ከተመለከትኩ በኋላ መስኮቴን ዘጋሁ፡፡ ወደ መቀመጫዬ ስመለስ የደርግ 10ኛ ዓመት የአብዮት በዓል ትዝ አለኝ፡፡ (አቤት የርችት መዓት!)
አሁን ደግሞ በቀጥታ የምናመራው ወደ “ቀልድ ርችት” ይሆናል፡፡ እናላችሁ---የዓለም መሪዎች በሙሉ በአንድ ቀን ይሞቱና ራሳቸውን ሰማይ ቤት ያገኙታል። ምንጮች እንደሚሉት፤ሳጥናኤል እንደዚያን ዕለት ጮቤ ረግጦ አያውቅም፡፡ ከመሪዎቹ መካከል አንድም እንኳን የጸደቀ የለም፡፡ ሁሉም ምድባቸው ሲኦል እንደሆነ ተነገራቸው፡፡ (የምድርን ገነት ሲያጣጥም የኖረ ሁላ ገሃነም ወረደ!) እንዳልኳችሁ… አሟሟታቸው ድንገተኛ ስለነበር ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ አልተሰናበቱም፡፡ ምንም የተናዘዙት ነገርም የለም (መሪዎች እንሞታለን አይሉማ!) እናም ፕሬዚዳንቶቹ፤ ወደ አገራቸው አንድ አንድ የስልክ ጥሪ ያደርጉ ዘንድ ሰይጣንን አስፈቀዱት፡፡ ሰይጣንም ያለ አመሉ ሲበዛ ደግ ሆነላቸው፡፡ (“የዘላለም ፍሬንዶቼ ናቸው” ብሎ ይሆን?) የመጀመሪያው ደዋይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ (በምድር ላይ ኃያል፣ በሰማይም ኃያል ነው!) ከዚያ የሩሲያ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይ ወዘተ… በየተራ ደወሉ፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ከሲኦል ወደ ምድር ስልክ ለመደወልም ውራ ነበሩ፡፡ (እዚህም ውራ፤ እዚያም ውራ!) ሆኖም ከማናቸውም አገራት መሪዎች የበለጠ ረዥም ሰዓት ያወሩት እነሱ ናቸው፡፡ (ብዙ የቤት ጣጣ አለባቸዋ!) ሁሉም ደውሎ ሲጨርስ ሰይጣን፤ “Friends, you know there is no free lunch” አለና ከእያንዳንዳቸው ላይ የስልክ ሂሳብ መቀበል ጀመረ። (ሲኦልም ቴሌ አለ እንዴ?!) ወዲያው ከአሜሪካ፣ እስያ፣ አውስትራሊያና አውሮፓ ፕሬዚዳንቶች ላይ (ከእያንዳንዳቸው) 500 ዶላር ቆነደዳቸው። ለረዥም ሰዓት በስልክ ያወሩትን የአፍሪካ መሪዎች ግን (እያንዳንዳቸውን) 50 ዶላር ብቻ አስከፈላቸው። ይሄን የታዘቡት የቀሩት አገራት ፕሬዚዳንቶች በጣም ተናደው፤ “ክፍያው ኢ - ፍትሃዊ ነው!” በማለት ሲኦልን ቀወጡት። ሰይጣን በጋኔላዊ ጩኸቱ ሲያምባርቅባቸው ትንሽ ገታ አሉ፡፡ ከዚያም “ጋይስ…ምንድነው የምትሉት… የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች እኮ የአገር ውስጥ ጥሪ ነው ያደረጉት!” አለና ገላገላቸው፡፡ (ትንፍሽ ያለ አልነበረም!)
አያችሁ… ሲኦልና የአፍሪካ አህጉር የሚገኙት በአንድ ክልል ውስጥ ነው (ለዚህ ነው Local call ነው የተባለው!) በእርግጥ የአፍሪካ ሲኦልነት ለህዝቦቿ እንጂ ለአምባገነን መሪዎቿ አይደለም፡፡ (ለህዝቡ ሲኦልን ፈጥረው፤እነሱ ገነት ውስጥ ይኖራሉ!) የአፍሪካ ሲኦልነት አምባገነን መሪዎቿ እንደሚቦተልኩት፤ የኒኦሊበራሊዝም አቀንቃኞች የአህጉሪቷን ገፅታ ለማጠልሸት የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ እንዳይመስላችሁ። አህጉሪቷ የሲኦል እኩያ ናት፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ድሃና ኋላቀር አህጉር፡፡ በሚሊዮኖች የሚገመቱ ህዝቦቿ በጦርነትና በበሽታ አልቀዋል፡፡ ከ240 ሚ. በላይ አፍሪካውያን በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ናቸው (“ምግብማ ሞልቷል--” በሚዘፈንባት አፍሪካ!) መከራዋ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ እስካሁን 17 ሚ. አፍሪካውያን በኤችአይቪ/ኤድስ ያለቁ ሲሆን ዛሬም ከ25ሚ. ህዝብ በላይ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ነው፡፡ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው አፍሪካዊ፤ ፊደል የማይቆጥር የዕውቀት ጨዋ ነው፡፡ (ከቆጠረማ አርፎ አይገዛም!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… አፍሪካ የምድር ሲኦል የሆነችብን የአያት ቅድመ አያቶች እርግማን ስላለብን አይደለም፡፡ የእግዜር ቁጣም እንዳይመስላችሁ። ተፈጥሮም እንዳልበደለችን ተዝቆ የማያልቅ የምድሪቱ ሃብት ምስክር ነው፡፡ የአፍሪካ ጠላቶች ቅኝ ገዢዎቿ አይደሉም፡፡ (ኧረ በስንት ጣዕማቸው!) ከራሷ ማህፀን ወጥተው የስልጣን ሱሰኝነት አምባገነን ያደረጋቸው የራሷ ልጆች ናቸው - ቀንደኛ ጠላቶቿ!! እስቲ ልጠይቃችሁት… አውሮፓውያን ከአፍሪካ ምድር መዘበሩ ከተባለው ሃብት ይልቅ አምባገነን መሪዎቿ የመዘበሩት አይልቅም? (የትና የት!)
ከፍተኛ የነዳጅ ምርት በማምረት ከዓለም በ4ኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ናይጄሪያ ---- የሆነውን አልሰማችሁም? የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ አንድ ማለዳ ላይ 20 ቢ. ዶላር እምጥ ይግባ ስምጥ  አይታወቅም አሉ፡፡  (መቼም “ሰላቢ” አልወሰደውም!)
ከአፍሪካ የነጭ ቅኝ ገዢዎችን ለማስወጣት የታገሉ የአህጉሪቷ የነፃነት ሃዋርያቶችን ሳስብ ግርም ይለኛል፡፡ (ማን ነበር “ነፃነት የማያውቁ ነፃ አውጭዎች” ያለው?!) እንዴ … አህጉሪቷ ነፃነቷን በተጎናፀፈች ማግስት እኮ ነው የሲኦል እኩያ የሆነችው - ዕድሜ ለአፍሪካ አምባገነኖች!! የሻዕቢያ የ30 ዓመታት የነፃነት ትግል ለኤርትራ ህዝብ ምን ፋይዳ አመጣለት? (ኢትዮጵያን እንዲጠላ ከመደረጉ ውጭ!) በእርግጥ ወዲ አፈወርቂ ላለፉት 23 ዓመታት ስልጣንን ርስታቸው አድርገው ህዝቡን ሲገዙ ቆይተዋል፡፡ (ኤርትራ ለእሳቸው ገነት፤ ለህዝቡ ሲኦል ናት!) ኤርትራውያን ዛሬ ኢሳያስ አፈወርቂ ነፃ አወጣኋት የሚሏትን አገር ጥለው እየተሰደዱ ያሉት ቅኝ ገዢ ወደተባለችው ጦቢያ ነው። ሌሎችም የአፍሪካ ህዝቦች እንደዚያው!
በነገራችን ላይ ስልጣንን የሙጥኝ ብለው ለረዥም ዓመታት ከዘለቁ የዓለማችን 20 ፕሬዚዳንቶች (Top 20) መካከል 10ሩ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ ነው (እንደብርቅዬ የዱር አራዊት! ከአህጉራችን ምርጥ አምባገነን መሪዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የ90 ዓመቱ የዕድሜም የስልጣንም ባለፀጋ፣ የዚምባቡዌው መሪ ሮበርት ሙጋቤ ናቸው።  ፕሬዚዳንቱ አገሪቱ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ጀምሮ ላለፉት 34 ዓመታት ህዝቡን አንቀጥቅጠው ገዝተዋል። ይሄም ሳያንሳቸው…በቅርቡ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ተረክበዋል፡፡
አንድ ነገር ልንገራችሁ አይደል… በአፍሪካ ህብረት ከምር ተስፋ የቆረጥኩት ሙጋቤን ሊቀመንበር አድርጐ የሾመ ዕለት ነው (ሊቀመንበርነቱን ለሚስቴ አውርሻታለሁ እንዳይሉ ብቻ!) ወዳጆቼ…አያደርጉትም ብላችሁ ጥርጣሬ እንዳይገባችሁ! እንኳን የህብረቱን ሊቀመንበርነት የአገር መሪነቱን እኮ ለውድ ባለቤታቸው ሊያወርሷት ጉድ ጉድ እየተባለ ነው፡፡ (ግን እንዴት አመኗት?!)
በአንድ ወቅት የቢቢሲ ጋዜጠኛ “መቼ ነው ህዝቡን የሚሰናበቱት?” ብሎ ሲጠይቃቸው---- የሰጡትን ምላሽ ሰምታችኋል? (ተጫዋች እኮ ናቸው!) “ህዝቡ ወዴት ሊሄድ ነው?” ነበር ያሉት፡፡ (እሳቸውማ ከዘላለም ሥልጣናቸው ወዴት ይሄዳሉ!?) እንደ እነ ጋዳፊ በህዝብ አመፅ ከስልጣን ከመገርሰስ የተረፉት  ሙጋቤ፤ ከዚህ በኋላ እንኳ ገዳምም ቢገቡ ደንታ የላቸውም፡፡
ለረዥም ዘመን በአምባገነንነት ሥልጣን ላይ በመክረም የሚታወቁት ሙጋቤ ብቻ አይደሉም። በአስሮቹ የአምባገነን ምርጦች (Top 10) ውስጥ ከተካተቱት መካከል የኡጋንዳው መሪ ዩዌሪ ሙሴቪኒ (28 ዓመት!)፣ የሱዳኑ ኦማር ሃሰን አልበሺር (25 ዓመት!)፣ የካሜሩኑ ፖል ቢያ (32 ዓመት!) … ህዝባቸውን ወደ እስከሚጠላ አንቀጥቅጠው ገዝተዋል።
እንዲህ የአህጉሪቱን ታሪክ መበርበር ስትጀምሩ፣ አፍሪካን በእርግጥም የሲኦል እኩያ ያደረጓት የገዛ አምባገነን መሪዎቿ እንጂ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች እንዳልሆኑ ትረዳላችሁ፡፡ የሴራሊዮን፣ የኮንጐ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ ወዘተ … የእርስ በርስ ግጭትና እልቂት የተከሰተው እኮ በቅኝ አገዛዝ ዘመን አይደለም፡፡ በሰው በላዎቹ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጊዜ እንጂ!፡፡
ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ … የአፍሪካ ህዝብ እርግማን የለበትም፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሱዳናዊው የቴሌኮም ቢዝነስ ከበርቴ ሞ ኢብራሂም ያሉ አርቆ አሳቢ አፍሪካውያን የተፈጠሩት፡፡ እኚህ ባለፀጋ የአፍሪካ የመልካም አስተዳደር ሽልማት ፋውንዴሽንን በ2006 እ.ኤ.አ ያቋቋሙት የአፍሪካን ህዝቦች ከሲኦል ኑሮ ለመገላገል ነው፡፡ እናም ህዝቡን ከድህነት አላቆ፣ የኑሮ ደረጃውን አሳድጎ፣ ኮሽታ ሳያሰማ ሥልጣን ለለቀቀ የአፍሪካ መሪ፣ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይሸልማሉ (ዕውቅናው ሳይጨመር!) ዳጎስ ያለ ሲባል … ስንት ትገምታላችሁ? 5 ቢ. ዶላር ነው! (በአበሽኛ 100 ሚ. ብር!) ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ተሸላሚዎቹ በህይወት እስካሉ ድረስ በየዓመቱ 200ሺ ዶላር (2 ሚ. ብር በሉት!) ይሰጣቸዋል፡፡ (ጡረታ በሉት!) በነገራችን ላይ የዘንድሮን የአፍሪካ ስኬታማ አመራር ሽልማት ያሸነፉት የቀድሞው የናምቢያ መሪ ሂፌክ ፑንዬ ፓሃምባ ናቸው፡፡ በ2007 ሽልማቱን የሞዛምቢክ መሪ የነበሩት ጃኪውም አልቤርቶ ቺሳኖ ያሸነፉ ሲሆን በ2008 የቦትስዋናው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፌስቱስ ጎንቴባንዬ ሞጋ ሽልማቱን ወስደዋል፡፡ ማንዴላም በዚያው ዓመት የክብር ሎሬት ተሸላሚ ነበሩ፡፡
በ2011 ደግሞ የኬፕቨርዲ የቀድሞ መሪ ፔድሮ ዲ ቬሮና ሮድሪጉስ ፒሬስ የ5ቢ. ዶላር አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የሚገርማችሁ ነገር…ለሶስት ዓመታት (በ2009፣ 2012 እና 2013) ተሸላሚ ባለመገኘቱ ሽልማቱ  ተዘሏል፡፡ (ከስልጣን በሰላም የወረደ ከየት ይምጣ!) ሱዳናዊው ባለፀጋ ይሄን የመሪዎች ሽልማት እንዴት እንዳሰቡት እያሰላሰልኩ ሳለ ሌላ ድንገተኛ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ። (ዩሬካ!)
ምን መሰላችሁ? የ2016 የኢብራሂም የአፍሪካ መሪዎች ሽልማትን የአገራችን ጠ/ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንዲያሸንፉ እፈልጋለሁ፡፡ ዓላማዬ ጠ/ሚኒስትሩን በሰበብ ከስልጣን ለማስወረድ አይደለም (ዞሮ ዞሮ እኮ--በመተካካት መውረዳቸው እኮ አይቀርም!) ለማንኛውም የእኔ ሃሳብ … እሳቸውን በማሸለም የአገራችንን መልካም ገፅታ መገንባት ነው። (“Killing two birds with a stone” አለ ፈረንጅ!) አያችሁ…ጠ/ሚኒስትሩ የ5ቢ. ዶላር ሽልማቱን እንዳሸነፉ በየሚዲያው ዜናው ሲናኝ፣ ዓለም ስለ ጦቢያ ያለው አመለካከት ከመቅፅበት ይቀየራል፡፡ (“ካልታዘልኩ አላምንም” አሉ!)
እናም እቺ “ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን እንዲሁም የሃይማኖት መብት አቀንቃኞችን ወህኒ ቤት አጉራለች” ተብላ የምትታማ (ሃሜት ልማዳቸው እኮ ነው!) መከረኛ አገራችን፤ ስሟ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚታደሰው በእንዲህ ያለው መሬት አንቀጥቅጥ ክስተት ነው---ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼውላችሁ… ጠ/ሚኒስትሩ ድምጽ ሳያሰሙ ከስልጣን ወርደው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ተሸላሚ ሆኑ ማለት በአገሪቱ ላይ መልካም አስተዳደር ለመስፈኑ ጉልህ ማረጋገጫ ነው፡፡ ያኔ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ያለ የሌለ ሃብታቸውን ሰብስበው ጦቢያ እምብርት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እንደጉድ ይሽቀዳደማሉ፡፡ ያኔ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰደድ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተደጋጋሚ የምትወነጀለው አገራችን ክሱና ውንጀላው ሁሉ ይሰረዝላታል፡፡ ያኔ የቱሪስቶች ቁጥር ታይቶ በማይታወቅ መጠን ወደ ሰማይ ይመነደጋል። ያኔ የሰብዓዊና የልማት ድጋፎች ከኒዮሊበራል መንግስታት ይጎርፍልናል፡፡ ኢትዮጵያ የ“አፍሪካ ታይገር” መሆኗን እነ Economist, The Guardian, New York Times, Blumberg, Washington Post ወዘተ… በስፋት ይዘግባሉ፡፡ ይተነትናሉ፡፡ (ኢህአዴግም ህልሙ ተሳካለት ማለት እኮ ነው!)
ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን ግብ ካሳኩ በኋላ ከፈለጉ በ10 ሚ. ብር ቦንድ (የህዳሴ ግድብ) በመግዛት የግል ባለሃብቱን በአርአያነት ሊያነቃቁ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በላይ ህይወት፣ ከዚህ በላይ መስዋዕትነት፣ ከዚህ በላይ ጽናት፣ከዚህ በላይ እርካታ ከየት ይመጣል? ይሄ ሁሉ የሚሳካው ግን ፓርቲያቸው እሺ ካለ ነው። ኢህአዴግ እንደለመደበት ጠ/ሚኒስትሩን አልለቅም ብሎ ክችች እንዳይል ጸሎት ያስፈልጋል (ለቀድሞው ጠ/ሚኒስትርም አልበጃቸውም!)

Read 3889 times