Print this page
Saturday, 21 March 2015 10:15

“አውራው ፓርቲ አሳይቶ የነሳን አበዛዙ--” (ወዶ እኮ አይደለም!)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)
  • “ገዢው ፓርቲ ሰለቸኝ” የሚል ራሱን በፍጥነት ከድህነት ያውጣ!
  • “ኢህአዴግ ሥልጣን የሚፈልገው እኛን ከድህነት ለማውጣት ነው”

   ከቅርብ ጊዜ  ወዲህ አውራ፣ ገናና፣ ህዝባዊ፣ ልማታዊ፣ አብዮታዊ፣ ድሃ ተኮር፣… ወዘተ የሚሉ ቅፅሎች እንደ ጉድ የተጫኑለት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የሥልጣን መንበሩን ከተቆናጠጠ ይኸው ሩብ ክ/ዘመን ሊያስቆጥር ነው! (በገዢዎች ሳይሆን በተገዢዎች የጊዜ ሰሌዳ ማለቴ ነው!) እኔ የምፈራለት ግን ምን መሰላችሁ? ዕድሜው እየጎለመሰ በሄደ ቁጥር የሚያከብራቸው በዓላት እየበረከቱ ስለሚመጡ ከልማታዊነት እንዳያቦዝነው ነው፡፡ (ግንቦት 20፣ የህወሃት 40ኛ ዓመት፣--የኢህአዴግ የብር ኢዮቤልዩ…ወዘተ!) በዓላት እኮ ለኒዮሊበራሎች እንጂ ለልማታዊ ፓርቲዎች ብዙም አይመቹም፡፡
በነገራችን ላይ --- ኢህአዴግ ሌላ ተጨማሪ 30 እና 40 ዓመታት አገሪቱን የመግዛት ህልም እንዳለው በየአጋጣሚው እየገለጸ ነው፡፡ (ኢዴፓ “መመኘት መብቱ ነው” ያለው መሰለኝ፡፡) እኔ ደግሞ “የያዝከውን ያበርክትልህ” ልለው አስቤ ነበር፡፡ (ሥልጣን ግን መቅኖ የለውም፤የዘንድሮ 100 ብር በሉት!) እውነቱን ለመናገር---ኢህአዴግ ስልጣኑን ለምን ማራዘም እንደፈለገ በቅጡ ባላውቅ ኖሮ ጨሼም አላባራ ነበር፡፡ (መረጃ ፈውስ ነው!)
እናላችሁ--ኢህአዴግ ይህችን 30 እና 40 ዓመት የሚፈልጋት (በልማታዊ መንግስት አቆጣጠር 3 ዓመት ብትሆን ነው!)  ለግል ጉዳዩ ሳይሆን የህዝቡን ምቾት ለማደላደል ብቻ ነው (ከተጠራጠራችሁ በውሸት detecetor ፈትሹኝ ብሏል!) እንደውም እኮ---ህዝቡን ከድህነት አረንቋ አውጥቼ ሰው ካላደረግሁት፣ እንቅልፍ በአይኔ አይዞርም ብሎ ተፈጥሟል አሉ፡፡ (እኛንም እንቅልፍ ሊነሳን ነዋ!)
አንዳንድ “ፍንዳታ ፖለቲከኞች” ግን እቺን ለ30 ዓመት ሥልጣን የማስረዘም ጉዳይ ፈጽሞ አልወደዷትም፡፡ ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ? “ኢህአዴግ ሌላ 50 ዓመት ከጨቀጨቀንማ ላይፍ ቦሪንግ ይሆናል!” (ግዴለም ሲበስሉ ይረዱታል!) እኔን ከሁሉ ያስገረመኝ ግን ኢህአዴግን ለመንቀፍ ሁሌም ቢላቸውን ስለው የሚጠብቁ አቃቂረኞች አሉት የተባለው ነው፤ “ኢህዴግ ሞናርኪ ሊሆን ነው!” (ተጨማሪ 30 ወይም 40 ዓመት መጠየቅ ንጉሳዊ አገዛዝ ያሰኛል?) እነዚህን እኮ ነው ኢህአዴግ “የሰፊው ህዝብ ጠላቶች---”የሚላቸው! (የእኔ ጠላት ሊላቸው አይችልማ!)
ይሄውላችሁ----እኔ ግን አንድ ሁነኛ መላ አለኝ፡፡ “ኢህአዴግ ሰለቸኝ” የሚል ወገን ሁሉ ራሱን በብርሃን ፍጥነት (ብርሃን እንደ ልብ ባይገኝም!) ከድህነት መንጭቆ ያውጣ! ምክንያቱም የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች “ሚድል ክላስ” ከተፈጠረ በኋላ ፓርቲው ይከስማል ብለዋል፡፡ (በሞጃ መራሽ ፓርቲ ይተካል ማለት ነው!) አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግን በኢህአዴግ ጥያቄ ከመቃጠላቸው የተነሳ “ወራጅ አለ!” እያሉ ነው፡፡ ለመሆኑ ማነው ኢህአዴግን “የድህነት ነፃ አውጪ ያደረገው” ሲሉም አበክረው ይጠይቃሉ፡፡ (ይሄን እንኳን ራሱ ቢመልሰው ይሻላል!)
የሆኖ ሆኖ እንዳለመው ከሆነለት፣ኢህአዴግ ጦቢያን ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ በመግዛት ሪከርድ ይሰብራል ማለት ነው፡፡ ይሄን ሃሳብ ለሚነቅፉ ወገኖች ሁሌም የሚጠቅሰው ደግሞ ጃፓንን ነው - (በምርጫ ክርክሩም ደረቱን ነፍቶ እየተናገረ  ነው!) ጃፓን ዛሬ ያለችበት ደረጃ የደረሰችው ለ100 ዓመት በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ብቻ እየተመራች ነው በማለት። እኔ የምለው----የሥልጣን ትራንስፎርሜሽኑ ሲጀመር (የ30 እና 40 ዓመቱን ማለቴ ነው!) ባሎት (ምርጫ) ከእነአካቴው    ይቀራል ማለት ነው? (ለህዝብ ከበጀ ለምን ጥንቅር አይልም!)
በነገራችሁ ላይ በዛሬው የፖለቲካ በፈገግታ ወጋችን የምናስተናግደው ከህዝብ የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ (እንዳቅሚቲ’ኮ የህዝብ አምድ ነው!) እናላችሁ … አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠ ጀምሮ አሳይቶ የነሳን “በረከቶች” ተቆጥረው አያልቁም … በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እስካሁን አሳይቶ ያልነሳን ነገር ቢኖር --- “አብዮታዊ ዲሞክራሲ”ን  ብቻ ነው ብለዋል - ፍርጥም ብለው፡፡ (ርዕዮተ ዓለሙን ማለታቸው ነው!) በነገራችን ላይ አሳይቶ መንሳትና አይቶ ማጣት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው!  (አንድዬ ከሁለቱም ይሰውረን!)
አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ኢህአዴግ አሳይቶ ነሳን ከሚሉት ውስጥ የግል ጋዜጦች መመናመንን ይጠቅሳሉ፡፡ ከምርጫ 97 በፊት የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፃው ፕሬስ ትሩፋቶች፣ ከአሁኑ ዘመን በጣት የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች ጋር በማነፃፀር ያጡትን እያሰሉ በቁጭት ይንገበገባሉ፡፡ (በእንስራ አሳይቶ በጣሳ መስጠት ብለውታል!) እንደ ዘንድሮ “የምርጫ ታዛቢው ራሱ ህዝቡ ነው!” ከመባሉ በፊት በየአምስት ዓመቱ ባህር ተሻግረው የሚመጡትን ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች (በተለይ የአውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረትና የካርተር ፋውንዴሽን) በምልሰት ወደ ኋላ ተጉዘው በማስታወስም የተቆጩ አልጠፉም፤አውራው ፓርቲ እያሳየ የነሳን አበዛዙ… በሚል፡፡ “ታዛቢዎቹ ምርጫውን ባይታዘቡ እንኳ ለአገር ገፅ ግንባታ ሲባል መጋበዝ ነበረባቸው ባይ ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በዘንድሮ ምርጫ የማይታዘበው እንደተባለው በአቅም እጥረት ሳይሆን አንድም ባለ መጋበዙ አንድም ደግሞ መንግስት ህብረቱ የሚያቀርበውን የምርጫ ሪፖርት ስለማይቀበል እንደሆነ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡)
አምና መንግስት በመሰረተባቸው ክስ የተዘጉትን ከ6 የማያንሱ የግል መፅሄቶችና የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም  የተሰደዱ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች--- የምርጫ መቃረብ ምልክቶች ናቸው ሲሉ ዓለምአቀፍ የፕሬስ መብት ተሟጋቾች ተችተዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ግን ከምርጫም ጋር ሳይነካኩ በቀጥታ ከራሳቸው መብት ጋር ነው ያያዙት፡፡ መረጃ የማግኘትና ሃሳባችንን በነጻ የመግለፅ መብታችንን አሳይቶ ነሳን (የፈረደበት ኢህአዴግን ነው!) የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የጋዜጦች ቁጥር ከ100ዎች ወደ አስሮች ሲያሽቆለቁሉ ---የባሰ አታምጣ ብለን በጸጋ መቀበላችን ባዶአችንን አስቀርቶናል ሲሉ ክፉኛ ይቆጫሉ፡፡ (የፕሬስ አብዮት አስበው ነበር እንዴ?)
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ስሟ በበጎ እየተገነባ የነበረችውን አገርም በአንዴ ጥላሸት በመቀባት የአገር ገፅ ግንባታውን አሳይቶ ነሳን ብለዋል፤ በምሬት። ጦቢያ በሰብዓዊ መብት አያያዝና በፕሬስ ነፃነት አጠባበቅ መቼም ቢሆን አመርቂ ውጤት አስመዝግባ ባታውቅም እንዳሁኑ ግን ውጤቷ በሁለት ዲጂት አሽቆልቁሎ አያውቅም ይላሉ፤ አቤቱታ አቅራቢዎቹ፡፡ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰርና ከአገር በማሰደድ ከአፍሪካ ተሽላ የተገኘችው በአንደኝነት ደረጃ ከተቀመጠችው ኤርትራ ብቻ ነው የሚሉት ምሬተኞቹ፤ ይሄም የአሳይቶ መንሳት ፍሬ ነው ብለዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በመልካም አስተዳደርና በሙስና በኩል ምንም አሳይቶ የነሳን ነገር ስለሌለ ተመስጌን ነው ይላሉ - የነበረው ችግር ተባብሶ ከመቀጠሉ ውጭ የተፈጠረ ነገር እንደሌለ በመጥቀስ። በ97 ምርጫ ማግስት በተቃዋሚዎች ተይዘው የነበሩት የፓርላማ መቀመጫዎች ተመናምነው አንድ ለመድሃኒት ብቻ መቅረቱንም አሳይቶ  የመንሳት ትሩፋት እንደሆነ አምርረው ይገልፃሉ፡፡ (ኢህአዴግ እንግዲህ ወንበሩን አይለቅላቸው!) በመጨረሻም እንደ አይቶ ማጣት ክፉ እርግማን የለም ሲሉ ጦቢያ ዳግመኛ አይታ እንዳታጣ እንፀልያለን ብለዋል - በአንድ ቃል!!
እኔ ግን ኢህአዴግ እነዚያን ሁሉ “በረከቶች” አሳይቶ የነሳን ሆን ብሎ አይመስለኝም፡፡ (ማንን ደስ ይበለው ብሎ?!)  አያችሁ … ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በአልባንያ ሶሻሊዝም የተጠመቀ ማርክሲስታዊ ድርጅት ነበር፡፡ ከዚያም ዓለምን ለመምሰል “ነጭ ካፒታሊዝም”ን እንደሚከተል ሲናገር ቆየ (ቢያንስ በኢኮኖሚው ዘርፍ!) ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የተሸጋገረው በኋላ ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ (ኒዮ-ሌኒኒስት የፖለቲካ ሞዴል ነው!) ከሌኒኒዝም፣ ከማርክሲዝም፣ ከማኦይዝምና ከሊበራሊዝም ውጭ የሚንቀሳቀስ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ አስቡት…ለራሱም ለኢህአዴግ እንኳን እንዴት እንግዳ የሆነ ርዕዮተ ዓለም እንደነበር! እናላችሁ … ምን እጠረጥራለሁ መሰላችሁ? (መረጃ ከሌለ መጠርጠር መብት ነው!) ገዢው ፓርቲው ሳያውቀው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሚፈቅደው ውጭ ብዙ “ነፃነቶች”ን ሲያሽረን ከርሟል። ከርዕዮተ ዓለሙ ጋር በቅጡ ሲተዋወቅ ደግሞ ነገሮችን መስመር ማስያዝ ነበረበት፡፡ “ኢህአዴግ  እያሳየ የነሳን በረከቶች አበዛዛቸው---” የሚለው አቤቱታ የተወለደውም በዚህ ሂደት ይመስለኛል። (“አይቶ ማጣት የወለደው----የእንትን ሠራዊት” የሚል እንዳይመጣ ፍሩልኝ!)
በእርግጥ ኢህአዴግ ከነቃም በኋላ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንጂ ፖለቲካዊ ነገሩን በግልፅ አልነገረንም፡፡ (ፈርቶ ይሆናላ!) አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ መንግስት በተገደበ መልኩ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ርዕዮተ ዓለም መሆኑን በተደጋጋሚ ነግሮናል (ኧረ በተግባርም አሳይቶናል!) ያልተነገረን የፖለቲካው ነገር ነበር፡፡ እሱም ቢሆን ግን የሮኬት ሳይንስ አይደለም፡፡ ከእስከዛሬው የልማታዊ መንግስታችን ተግባራዊ ተመክሮ ተነስተን እንዲህ ነው ማለት አያቅተንም፡፡ እናላችሁ ---- አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲያስፈልግ መንግስት ያለ ገደብ ፖለቲካው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት የዲሞክራሲ ስርዓት ማለት ነው፡፡ (ከኖርነው ተነስተን ማለት ነው!)
እዚህ ጋ ግን አንድ እውነታ መዘንጋት የለብንም። መንግስት ኢኮኖሚው ውስጥ በተገደበ መልኩ ጣልቃ የሚገባውም ሆነ ፖለቲካው ውስጥ ያለ ገደብ ዘው የሚለው የሰፊውን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል ነው፡፡ (ኢህአዴግ ከህዝብ የወጣ፣ በህዝብ የተፈተነ፣ ህዝባዊ ፓርቲ መሆኑን እንዳትዘነጉ!) በ97 ምርጫ ማግስት ምን አደረገ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚፈቅድለት መሠረት፤ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ገደብ ጣልቃ በመግባት፣ ለህዝብ አይበጁም ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ድራሻቸውን አጠፋ (ያኔ የታገደው ሰላማዊ ሰልፍ ከ8 ዓመት በኋላ ተፈቀደ!)
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋናው መሠረታዊ ነገር ምን መሰላችሁ? ተጀምሮ እስኪያልቅ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አድራጊ ፈጣሪው መንግስት ነው፡፡  እናላችሁ … የግል ፕሬሱ ፅንፈኝነቱን ያለቅጥ አብዝቶት የፖለቲካ ሥርዓቱን ሲያዛባ መንግስት ዘው ብሎ ክስ በመመስረት … ከአንድ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መንግስት የሚጠበቅበትን ተወጣ፡፡ (የሚዲያ ተቋማቱ ተዘጉ፤ ጋዜጠኞች ከአገር ተሰደዱ!) ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ ችግራቸውን መፍታት ሲሳናቸው ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ ባጃቸው፡፡ ሌሎችም በምርጫው ሂደት የተከሰቱ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ (ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል እንጂ!)
የመንግስት ጣልቃገብነት በኢኮኖሚው (በተገደበ መልኩ!)… የመንግስት ጣልቃገብነት በፖለቲካው … የመንግስት ጣልቃገብነት በፕሬስ ነፃነት … የመንግስት ጣልቃገብነት በዲሞክራሲው … የመንግስት ጣልቃገብነት በሰላማዊ ሰልፍ… የመንግስት ጣልቃ ገብነት በፓርቲዎች እንቅስቃሴ … ወዘተ … ያለ ገደብ ይፈቅዳል - አብዮታዊ ዲሞክራሲ!! ይሄ ሁሉ ጣልቃ ገብነት ደግሞ መብት ለመግፈፍ ወይም ነፃነት ለማፈን አይደለም፡፡ የህዝቡን ጥቅም የበለጠ ለማስጠበቅ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የህዝብ አለኝታ ነው! (ወይም ነኝ ይላል!)


Read 3794 times