Monday, 16 March 2015 09:38

ተቃዋሚዎችም የየራሳቸው “ደደቢት” አላቸው!

Written by 
Rate this item
(21 votes)

ኢህአፓም “አሲምባ”ን ማስጎብኘት ይችላል----

  ልጅ ያሬድ የተባለው ታዋቂ ኮሜዲያን ሰሞኑን በዋሽንግተን ሆቴል (የአዲስ አበባው ነው!) ባቀረበው የኮሜዲ ምሽት ላይ የታደመችው የሥራ ባልደረባዬ ሰምታ ካጣጣመቻቸው ቀልዶች ውስጥ  ጥቂቶቹን ስለነገረችኝ እኔም ለናንተ ላጋራችሁ፡፡ (“sharing is caring” አሉ!)
ወደ ልጅ ያሬድ ቀልድ፡- አንድ የሆነ ሰፈር ነው አለ፡፡  ሌላው ጋ 3 ብር የሚሸጠውን አንድ እንጀራ 4 ብር ነው የሚሸጡት ---- ለምንድን ነው እዚህ ሰፈር  4 ብር የሚሸጠው ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ምን ቢሉት ጥሩ ነው --- እኛ ሰፈር ውሃ ስለሌለች ሊጡን በሃይላንድ ውሃ ነው የምናቦካው፡፡ (የጨረሰች  ቀልድ!)  
ባለፈው ሳምንት ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ስለ ህወሃት 40ኛ ዓመት በዓል ሳወጋችሁ አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳነት እየተጠቀመበት ነው የሚል ክስ መሰንዘራቸውን ጠቅሼ ነበር (ነገርዬው ባይሆን ለወቀሳ እንጂ ለክስ እንኳን አይበቃም!) የሆኖ ሆኖ ---- ተቃዋሚዎች ለምን እንዲህ ያለ ወቀሳ ሰነዘሩ ብዬ ሳሰላስል ሁለት መላ ምቶች ብልጭ አሉልኝ፡፡ አንደኛው፤ ህወሃት ለምን ለበዓሉ አልጠራንም የሚል የአበሻ ቅያሜ ቢጤ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ አይፈረድባቸውም፡፡ ለምን መሰላችሁ ----- ሱዳኖችንና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን በሰበብ አስባቡ እየጋበዙ ለአገር ቤት ተቃዋሚ ጀርባ መስጠት ያናድዳላ፡፡ (ቀላል ያጨሳል!)  
በነገራችሁ ላይ በእንዲህ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች (የህወሃት 40ኛ ዓመትን ማለቴ ነው!) ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የፖለቲካ ኩርፍያ (የኩርፍያ ፖለቲካም ያስኬዳል!) ለመስበር መትጋት እኮ ብልህነት ነው፡፡ (አረ ብልጥነትም ጭምር!) ፖለቲከኞቻችን ሌላው ቢቀር … ለአዲሱ  ትውልድ የሚያስረክቡትን አገር ማሰብ አለባቸው፡፡ (ኩርፍያ የሞላት አገር ማን ይረከባል!)
እናላችሁ----በተለይ የመንግስትን ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ ተነሳሽነቱን መውሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡    (ከተቃዋሚም ቢገኝ አንጠላም!) አያችሁ ቢገባን እኮ---ለሰላምና ለፍቅር መሸነፍ ከማሸነፍ እኩል ነው፡፡ (ኧረ ኩርፊያው ይሰበር!) አሁንስ እኔ ለእነሱ ደከመኝ… (ስፖንሰር ከተገኘ “ኩርፊያው ይሰበር” የሚል የ6 ወር አገራዊ ንቅናቄ ለመጀመር አስቤያለሁ!)
ሁለተኛውን መላ ምት እንኳ ሳምንትም ጠቀስ አድርጌዋለሁ (የአርቲስቶች ደደቢትን መጎብኘት ማለቴ ነው!) ዛሬ ግን ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ይዤአለሁ፡፡ ባለፈው ጠቀስ እንዳደረግሁላችሁ ተቃዋሚዎች በዚህ ነገር ደስ የተሰኙ አይመስሉም፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቀመበት የሚል ወቀሳ የመጣው፡፡ (ሁሉ ነገር በአስተማማኝ ግምት ላይ የተመሰረተ ነው!)
ለነገሩ እስቲ ራሳችሁን በተቃዋሚዎች ቦታ አድርጋችሁ አስቡት፡፡ (ለአፍታ የእነሱን ጭንቅላት ልዋስ!) እናላችሁ--ለምሳሌ አርቲስቶችን ደደቢት ድረስ ወስዶ ማስጎብኘት ለምን አስፈለገ? (ያውም በምርጫው 11ኛ ሰዓት ላይ!) ግን እኮ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት ለራሱ ለህወሃት ነው! የጉብኝቱ ዓላማ እንደተባለው ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው? (እንዴት አሁን ትዝ አላቸው?) ወይስ በምስኪንነት ሆድ አባብቶ አሊያም በጀግንነት ቀልብ ማርኮ የአርቲስቶችን ድምፅ ለመግዛት ነው? እኒህ ሁሉ ጥያቄዎችና መላምቶች  የእኔ አይደሉም … እኔ ለእነሱ የመታሁት መላ እንጂ!! (ራሴን በተቃዋሚዎች ጫማ ውስጥ አስገብቼ ማለት ነው!)
እናም ማንም ተቃዋሚ የሆነ (ያውም ደግሞ ያኮረፈ!) ከላይ ከቀረቡት ውስጥ ልቡ ወደ ሁለተኛው ጥያቄና መላ ምት እንደሚያደላ ሳይታለም የተፈታ ነው!! እናም ለዚህ ይሆናል የህወሃትን 40ኛ ዓመት  ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቀሙበት የሚለው ክስ (ይቅርታ ወቀሳ!) የመጣው፡፡ አሁን ወደ መፍትሄው እንግባ፡፡ የእኔ ሃሳብ ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎችም ልክ እንደ ህወሃት የየራሳቸውን “ደደቢት” ለአርቲስቶች እንዲያስጎበኙ ዕድል መስጠት! (ከከተማ ሳይወጡ ደደቢት!) ግን ምን መሰላችሁ? ምንም እንኳን ተቃዋሚዎች እንደ ህወሃት በረሃ ገብተው ባይዋጉም አልታገሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና ማግኘት፣ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ አዳራሽ ወይም ሆቴል መከራየት፣ በየክልሉ ካሉ ትናንሽ የወረዳ ንጉሶች ጋር መወዛገብ፣ ሰላማዊ ፈቃዱ ህገወጥ ነው ከሚል የጸጥታ ኃይል ጋር መጋፈጥ (ዱላና ድብደባን ያካትታል!) ------ እኒህ ሁሉ የትግሉ አካል ናቸው፡፡
 ሌሎችም የትግል ቦታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ---ተቃዋሚዎች ፓርቲያቸውን ለመመስረት ሃሳብ የጠነሰሱበት ሥፍራ፣ በኢህአዴግ ካድሬ ተዋከብን የሚሉበት ቦታ፣በየጊዜው እነሱ ወይም ጓዶቻቸው የታሰሩበት፣(ቃሊቲ፣ዝዋይ፣ማዕከላዊ--ወዘተ) እነዚህ ሁሉ የእነሱ የትግል ቦታዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጋሩት አንድ የድል ቦታም አላቸው -የህዝብ ማዕበልን የሚያስታውሳቸው፡፡ መስቀል አደባባይ!! (የ97 ምርጫን ልብ ይሏል!) አያችሁ----ተቃዋሚዎችም ለአርቲስቶች ሊያስጎበኙት የሚችሉት ከበቂ በላይ የትግል ቦታና ታሪክ  አሏቸው፡፡ (የየራሳቸው ደደቢት እንደማለት!) በነገራችሁ ላይ የትጥቅ ትግሉን ያሸነፈው ኢህአፓ ቢሆን ኖሮ---- አርቲስቶቹ የሚጎበኙት ደደቢትን ሳይሆን አሲምባን ይሆን ነበር፡፡
 እናላችሁ … ተቃዋሚዎች አርቲስቶችን ሰብስበው የየራሳቸውን “ደደቢት” ቢያስጎበኙ ኩርፊያውን ለማርገብ የሚያግዝ ይመስለኛል፡፡ (አርቲስቶች የህዝብ ሃብት ናቸው ብዬ እኮ ነው!) በነገራችሁ … ላይ የህዝብ ሃብት ያልሆነ ነገር እኮ ፈልጋችሁ አታገኙም! ለምሳሌ መሬት የህዝብ ሃብት ነው (ይቅርታ እና የመንግስት!)፣ ቲቪና ሬዲዮ ጣቢያም የህዝብ ሃብት ነው፡፡ የኢህአዴግ ኢዶውመንቶች ራሳቸው - የህዝብ ሃብት ናቸው፡፡ የሥልጣን ባለቤት ማነው? ህዝብ ነው!! የመንግስት ሹማምንት የማን አገልጋይ ናቸው? የህዝብ!! ግን እኮ አርቲስቶች ሃብታቸውን ሲጠየቁ----ሃብታችን ህዝብ ነው ይላሉ፡፡ (ከምራቸው እንዳይሆን!)

Read 5323 times