Print this page
Monday, 09 March 2015 11:57

አርቲስቶቹ የህወሐት 40ኛ ዓመት ይደገም ቢሉስ?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)

ሁሌም ምርጫ ሲደርስ ብቅ ብቅ የሚሉ (በኢቢሲ ማለቴ ነው!) ፊታቸው “የቁጣ አስተማሪ” የሚመስል አንዳንድ ግለሰቦች አላጋጠማችሁም? ፖለቲከኞች ወይም ባለሥልጣናት እንዳይመስሏችሁ። (እነሱ አይቆጡም አልወጣኝም!) እነዚህኞቹን “የምርጫ ዬኔታ” ይሏቸዋል፡፡ ይሄ ስያሜ ለምን እንደተሰጣቸው አላውቅም፡፡ ምናልባት ቁጣ ቁጣ ስለሚላቸው ይሆን? የሚገርመው ደግሞ እየተቆጡ የሚያስተምሩን እንዴት ምርጫውን ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ---እንደምናደርገው ነው፡፡ (ሰላማዊ ምርጫ --- በቁጣ?!)
 እኔ የምለው ግን --- አንዳንድ ግለሰቦች “የቁጣ ፈቃድ” አላቸው እንዴ? ወይስ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል? ከምሬ እኮ ነው---መቼም አንድ ግለሰብ (ለብቻው) 90 ሚሊዮን ህዝብን ለመቆጣት የግድ ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ ፈቃድ ካለው ህግ አክባሪ ስለሆንን እንታገሰው ይሆናል፡፡ ያለዚያ ግን ---- (ምንም!!)  
በነገራችን ላይ ---- የህወሓትን 40ኛ ዓመት በዓል እንዴት አያችሁት? እንግዲህ በዓሉ ለአንድ ወር ያህል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ ባለፈው እሁድ ተጠናቋል፡፡(አንድ ወር አላነሰችም?) የሸገር 125ኛ ዓመት የተከበረው እኮ ዓመቱን ሙሉ ነው (ዓመትም ተንዛዛ!) አንድ ነገር ልንገራችሁ--- የዘንድሮን ምርጫ ልዩ የሚያደርገው፣ የህወሐት 40ኛ ዓመት በተከበረ ማግስት በመዋሉ ነው፡፡ (የEBCን ዜና ቀማሁት አይደል!) አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ… የዘንድሮን የህወሐት በዓል ልዩ  የሚያደርገው ምንድን ነው ብትባሉስ? (ከ40ኛ ዓመቱ ውጭ ማለቴ ነው!) ቀላል እኮ ናት! (ሮኬት ሳይንስ አደረጋችሁት እኮ!) ልዩ የሚያደርገዋ---የህወሐት የቀድሞ ታጋዮች (አሁንማ ባለ ስልጣን ሆነዋል!) ከአርቲስቶች ጋር የሆድ የሆዳቸውን ማውራታቸው ነው!! (መሞዳሞድ ሌላ ነው!)
ተቃዋሚዎች በዓሉን አስመልክቶ የሰነዘሩት ትችት ግን አልገባኝም፤ “ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቅሞበታል” ሲሉ ሰማሁ፡፡ (So what?) …ገና ለገና  በግንቦት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ በየካቲት በዓል ላይከበር ነው? (“ማን ላይ ቁጭ ብለሽ ማንን ታምያለሽ” አሉ!) ከዚህም የባሰውን ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ “የህወሐት በዓል አድዋን አደበዘዘው” አሉና አረፉት! (በጉዴ ወጣ! ማለት አሁን ነው!)
በጣም ግርም ያለኝ ምን መሰላችሁ? ህወሐትም ሆነ በአጠቃላይ ኢህአዴግ እስከዛሬ ሲተቹበት የነበረው ዋና ጉዳይ ----- ምስጢረኞች ናቸው፤ ሆዳቸው አይታወቅም እየተባሉ  ነበር፡፡ እናም የህወሐት የቀድሞ ታጋዮች፣ 40ኛ ዓመቱን በማስመልከት ምድረ አርቲስትን ሰብስበው ደደቢት ድረስ ወሰዱ፡፡ ዋና ዋና የትግል ቦታዎችን አስጐበኙ። የትግሉን ገድል ተረኩ፡፡ ከ20 ዓመት በላይ ከርችመውት የቆዩትን ገበና ወለል አድርገው ከፈቱ። (ልብን ከፍቶ እንደ መስጠት እኮ ነው!) እና ይሄ  ጥፋቱ ምንድነው? (የምርጫ ቅስቀሳ ያስብላል!?)
ዝም ብዬ ሳስበው ግን በህወሐት ላይ ለተሰነዘረው ትችት ተጠያቂዎቹ አንዳንድ ስሜታዊ አርቲስቶች ይመስሉኛል፡፡ ደደቢትን ከጐበኙ በኋላ አንዳንዶቹ በEBC ሲሰጡት የነበረውን አስተያየት ሰምታችኋል? አብዛኞቹ ባዩት ነገር የምር መደነቃቸውን ከገፅታቸውም ከአንደበታቸውም ተገንዝቤአለሁ። ጥቂቶቹ ግን ትወና ቢጤ ሳይሞካክሩ አልቀሩም (ተሰጥኦ ለመቼ ነው!) ግን እኮ  ገና መጀመሪያውኑ ተነግሯቸው ነበር፡፡ “ለጉብኝቱ የመጣችሁት እንድትዘምሩልን አይደለም፤ ሁሉም ሰው ያሻውን ሃሳብ ሊይዝ ይችላል” በሚል፡፡ አንዳንድ አርቲስቶች ግን ማሳሰቢያው የገባቸው አልመሰለኝም  (ቀላል ዘመሩ እንዴ!)
በነገራችን ላይ ከበረሃ ትግል ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ ግቢ ወደ ቤተመንግስት ግቢ የመግባት ዕድል ያገኙት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በዚህ የህወሐት 40ኛ ዓመት በዓል ላይ “የታጋይነት ማዕረግ” ተሰጥቷቸዋል፡፡ (“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” አሉ!) ማዕረጉ የክብር ይሁን የምር ግን አልተነገረንም፡፡ የምር ከሆነ እኮ “ታጋይ ኃይለማርያም” ይባሉበታል ማለት ነው፡፡ የክብር ከሆነ ግን  “የክብር ታጋይ” ነው  የሚባሉት (የክብር  ዶክትሬት እንደማለት!)
አያችሁ---የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው ዩኒቨርስቲ ተገብቶ----ትምህርት ተከታትሎ…ጥናትና ምርምር ሰርቶ -- አይደለም፡፡ በተሰማሩበት ሙያ ለአገር ያበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ተመዝኖ ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ይመስለኛል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ታጋይ የተባሉት ለ17 ዓመት ጠብመንጃ አንግተው ስለታገሉ አይደለም፡፡ (እሳቸው ከብዕርና ከጠመኔ ውጭ ምንም አያውቁም!) እዚህ ጋ መረሳት የሌለበት ቁምነገር ምን መሰላችሁ? እርግጥ ነው አቶ ኃይለማርያም ከትግል ጋር አይተዋወቁም። እርግጥ ነው ጥይት አልተኮሱም፤ እርግጥ ነው ፈንጂም አላፈነዱም፡፡ ግን የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን (መሬት ይቅለላቸውና!) ተክተው ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል ቃል የገቡት፣ ኃላፊነት የተሰጣቸውም ለእሳቸው ነው፡፡ (ታጋይ መባል አይበዛባቸውም!)
ለነገሩ በኢህአዴግኛ፤ ሥልጣንና ሹመትም እንደ ትግል ወይም መስዋእትነት ነው የሚቆጠረው፡፡ አቶ ኃይለማርያም፤ በጠ/ሚኒስትርነት የተሾሙ ሰሞን አዲሱን ስልጣናቸውን እንደ ትግል እንደሚያዩት መናገራቸው ትዝ ይለኛል፡፡ (አገር መምራትን እንደ ትግል ማሰብ አይገርምም?) ኢህአዴግ እኮ ልማት ማካሄዱንም፣ መልካም አስተዳደር ማስፈኑንም፣ የህግ የበላይነትን ማስጠበቁንም፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማጐልበቱንም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ማስከበሩንም…ወዘተ (ከሀ-ፐ በሉት) እንደ ትግል ነው የሚቆጥረው፡፡ (የትጥቅ ትግል አልወጣኝም!)
አንዳንዴ ሳስበው ግን እውነቱን ነው እላለሁ፡፡ ከምሬ ነው…እነዚህ የተጠቀሱትን ጨምሮ…ኪራይ ሰብሳቢዎችን መጋፈጥ… ድህነትን ታሪክ ማድረግ… ፍትሃዊ የሃብት ሥርጭትን ማስፈን…(ሁሉንም እኩል ማደህየት እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን!) የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ማጠናከር (“ማን ነበር አክትሞለታል” ያለው?!) ወዘተ… ቀላል ትግል እኮ አይደለም፡፡ እንዴ…ደርግን የሚያህል ግዙፍ ኃይል በትጥቅ ትግል ለመጣል እኮ 17 ዓመት ብቻ ነው የፈጀው (ትንሽ ናት አልወጣኝም!) ቀደም ብዬ ያነሳኋቸው የአገር ችግሮች ግን ይኸው ከ20 ዓመት በኋላም “መች ተነካና!” እያስባሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ካያችሁት .. የኢህአዴግ ሥልጣን እውነትም መስዋዕትነት የሚከፈልበት ትግል ነው ሊባል ይችላል፡፡ (ተቃዋሚዎች አልገባቸውም!)
ከህወሐት 40ኛ ዓመት በዓል ጋር በተያያዘ የጀመርኩትን ወግ ሳልቋጭ ነው ወደ ትግል ትንተና የገባሁት፡፡ እናም የቀረችኝን ልጨርስላችሁ። አሁንም ጉዳዩ አርቲስቶችን ይመለከታል፡፡ (የህወሐትና የአርቲስቶችን ፍቅር ያዝልቅላቸው!?)
በነገራችሁ ላይ ይኸኛውንም በEBC መስኮት ነው የታደምኩት (ከአንዴም ሦስቴ!) ምን መሰላችሁ? የህወሐትን 40ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ለአርቲስቶች የተዘጋጀ የጥያቄና መልስ ውድድር ነው፡፡ ቦታው አዳማ ይመስለኛል፡፡ ወይም እርግጠኛ ለመሆን በEBC መስኮት!!
የጥያቄና መልስ ውድድሩ “11በ11” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ለምን? አንደኛ፤ ህወኃት የተመሰረተበት ቀን የካቲት 11 ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ጠያቂውን ጨምሮ በውድድሩ የተካፈሉት አርቲስቶች 11 ነበሩ፡፡ እናም 11 በ11 ተባለ፡፡ ምክንያቱ አላጠገባችሁም? (ደግሞ ለምክንያት!) የአሸናፊው ቡድን 5 አርቲስቶች በነፍስ ወከፍ 11ሺ ብር ነው የተሸለሙት፡፡ (የፓርቲ “ሞጃ” ይመቸኛል!) በእነዚህ ሁሉ በቂ ምክንያቶች የጥያቄና መልስ ውድድሩ “11 በ 11” ተብሏል፤ አለ - ውድድሩን የመራው አርቲስት ሸዋፈራሁ፡፡
ጥያቄና መልሱ ተጀመረ፡፡ በነገራችሁ ላይ ጥያቄዎቹ በህወኃት ትግል ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ (በትንሹ የ30 ዓመት ታሪክ ማለት ነው) እኔ የምለው… የእነ ህወሐት ገድል በታሪክ ትምህርት ውስጥ ተካተተ እንዴ? (እነ ፍልፍሉ እሳት ሲሆኑብኝ እኮ ነው!) ይታያችሁ… የታጋዮች የበረሃ ስም… ህወሐት ደርግን ድባቅ የመታባቸው ዘመቻዎች፤ ቦታዎች፣ ዓመተ ምህረቶች ወዘተ ሲጠየቁ ነበር፡፡ መጠየቃቸው አይደለም የሚገርመው።
መመለሳቸው ነው፡፡ ያውም እኮ ከአፍ እየነጠቁ ነበር የሚመልሱት፡፡ ቆይ… የአዲስ አበባ አርቲስትና ኮሜዲያን የህወሐትን ትግል እንዲህ የሸመደዱት መቼ ነው? ይሄውላችሁ… በመልሳቸው ፍጥነት የተገረምኩት እኔ ብቻ ብሆን ኖሮ ችግሩ ከእኔ ነው ብዬ ግለ-ሂስ አወርድ ነበር፡፡ ግን እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡
ራሱ የፕሮግራሙ አጋፋሪ፤ አርቲስቶቹ መልሱን እንደ እሳት ሲተፉበት ደንግጦ “አብራችሁ ታግላችኋል እንዴ?” አይል መሰላችሁ፡፡ (ደንግጦ አስደነገጠን!) እኔማ አውጥቼ አውርጄ ተውኩት እንጂ “ጥያቄና መልሱ …ተጭበርብሯል” ብዬ ለህወሐት ልጠቁም ዳድቶኝ ነበር (“ሃብታም በሰጠ …” እንዳልባል ፈርቼ ጭጭ አልኩ!)
ይልቅስ ምኑ ደስ አለኝ መሰላችሁ? ያሸነፈም የተሸነፈም መሸለሙ!! አሸናፊዎቹ (ቅሬታዬ እንዳለ ነው!) እያንዳንዳቸው 11ሺ ብር፤ በጠቅላላ 55ሺ ብር ሲሸለሙ፣ ተሸፊናዎቹ በነፍስ ወከፍ 5ሺ ብር፣ በድምሩ 25ሺ ብር አግኝተዋል፡፡ እኔ የምለው…አርቲስቶቹ ሽልማቱ ጥሟቸው የህወሓት 40ኛ ዓመት ይደገም ቢሉስ? (ምርጫ መሰላቸው?!)
እኛም እንግዲህ ግልጽ ማመልከቻ ለሚመለከተው ወገን አቅርበን ወጋችንን እንቋጭ … የግንቦቱ አገራዊ ምርጫ እንደ ጥያቄና መልስ ውድድሩ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ አሸናፊም ተሸናፊም የሚሸለምበት!! ያሸነፈ ደረቱን የማያሳብጥበት፤ የተሸነፈ አንገቱን የማይሰበርበት ምርጫ ያስፈልገናል። (“ታስፈልገኛለህ” አለች ዘፋኟ!)
እንኳን ለአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በዓል አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!

Read 5562 times