Monday, 09 March 2015 11:58

“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ፡፡ ተግሣፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!”

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከበደ ሚካኤል
(አዝማሪና ውሃ ሙላት)
   አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይሆናል፡፡ የሚከተለው ተረት የዚያ ዓይነት ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ የአማርኛ መምህር ስለግጥም አስተማሩና
“ቆቅ በሚለው ቃል አንድ ግጥም ፃፉ”
አሉና የክፍል ሥራ ሰጡ፡፡
አንድ ሁልጊዜ የሆነ ያልሆነ ጥያቄ እየጠየቀ የሚያስቸግራቸው ተማሪ አለ፡፡ ይህ ተማሪ እምብዛም አማርኛ የማይሳካለት ነው፡፡ በሌላ ትምህርት “ኤ” እያገኘ በአማርኛ ግን ይወድቃል፡፡ አማርኛ ክፍል ውስጥ መከራከሩን ደሞ ይቀጥላል፡፡ እልኸኛ ልጅ ነው፡፡ ለምሳሌ መምህሩ፤ “መተከዣ ምግብ ታውቃላችሁ?” ይላሉ፡፡ የሚመልስ ሲጠፋ፤ ራሳቸው ይመልሳሉ፡፡
“መተከዣ ምግብ ማለት እንደ ቆሎ፤ ቋንጣ፣ ዳቦ ቆሎ ወዘተ ያለ እየተጫወትን በዝግታ የምንበላው ነገር ነው” ይላሉ፡፡ ይሄኔ ያ ልጅ እጁን ያወጣል፡፡
“ዶሮ ወጥስ መተከዣ ምግብ አይሆንም?” ይላቸዋል፡፡
“አይ ዶሮ ለምሣ ወይ ለራት ርቦን በፍጥነት የምንበላው ነው፤ መተከዣ ምግብ አይደለም” ይላሉ፡፡
“ቀስ ብዬ ብበላውስ?” ብሎ ድርቅ ይልባቸዋል፡፡
“እንግዲያው የእኔ ልጅ ዶሮ ለአንተ…መተከዣ ምግብ… ይሁንልህ!” ይሉታል፡፡
ሌላ ቀን “ቅዳሜና እሁድን የት አሳለፋችሁ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡
ያ ሞገደኛ ተማሪ እጁን ያወጣና፤
“ካምቦሎጆ” ይላል፡፡
“የመግቢያ ክፍያው ስንት ነበር?”
“አይ በከንቱ ነው የገባነው” ተማሪዎቹ ይስቃሉ፡፡
“በከንቱ አይባልም” ይላሉ የኔታ፡፡
“እሺ በባዶ?”
“በነፃ ብትል ይሻላል የኔ ልጅ”
“በዜሮስ ብለው?”
“ይሁንልህ” ይሉታል፡፡
ዛሬ እንግዲህ “ቆቅ” በሚለው ቃል ግጥም ግጠሙ ብለዋል - የኔታ፡፡ ሁሉም ተማሪ አንድ አንድ ስንኝ እየፃፈ ሰጠ፡፡ ያ ሞገደኛ ተማሪም ፅፎ ሰጥቷል፡፡
የኔታ አርመው ስም እየጠሩ መለሱ፡፡ ስምንት ከአሥር፣ ዘጠኝ ከአሥር ያገኙ አሉ፡፡
ያ ሞገደኛ ተማሪም ወረቀቱን ተቀበለ፡፡ ግን ማርክ አልተሰጠውም፡፡
“የኔታ፤ የእኔ ለምን አልታረመልኝም?” አለና ጠየቀ፡፡ እስቲ አንብበው የፃፍከውን ግጥም፡፡
ልጁ ማንበብ ጀመረ፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆቅ
አፋፍ ለአፋፍ ስታሽሟቅቅ” ብሎ ጨረሰ፡፡
የኔታም “ማሽሟቀቅ” ምን ማለት ነው?” አሉና “ትርጉሙ ካልታወቀኮ ለግጥሙ ማርክ ለመስጠት አይቻልም” አሉት፡፡
“እሺ ላስረዳዎት፡፡ ማሽሟቀቅ ማለት በመንፏቀቅ ና በማሽሟጠጥ መካከል ያለ ነገር ነው”
“በል በል በል …አንድ ከአሥር አግኝተሃል፡፡ ይህም ለተማሪ ዜሮ ስለማይሰጥ ነው፡፡ ቅ እና ቅ መግጠሙን ማወቅህ ይበቃል” አሉት፡፡
*    *    *
በተሳሳተ ወይም በሌላ ቃል፤ አዋቂ ለመምሰል የሚጥሩ አያሌ ናቸው፡፡ ቃል ግን አይታበልም፡፡ አንዳንዴም ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው “ቃል የዕምነት ዕዳ ነው”፡፡ ቃልን በትክክለኛ አግባቡ በቦታው ማስቀመጥ ጥንቃቄንና ታማኝነትን የሚጠይቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡
እነሆ አዲስ አድማስ ጋዜጣችን አሥራ አምስት አመት ሞላው፡፡ ገና ከጅምሩ፣ ገና ማለዳ፤ “እኛ ጋዜጣ ብቻ ሳንሆን ኃላፊነት የሚሰማው ሥነ ጽሑፍ ነን” ብለን ነበር፡፡
ኃላፊነታችንን መወጣታችንን”፤ አንባቢያችን ይመሰክራል፡፡
“ባህላዊ ጋዜጣ ነንም” ብለን ነበር፡፡ እስከዛሬ ከሰባት መቶ በላይ ተረቶችን በመፃፍ በባህላዊ ርዕሰ አንቀጽ አፃፃፍ ዘዴያችን ዘልቀናል፡፡ “የጥበብ መድረክ ነንም” ብለን ነበር፡፡ አያሌ ግጥሞችንና አጭር ልቦለዶችን አስነብበናል፡፡ “የእርሶና የቤተሰብዎ ጋዜጣ ነንም” ብለን ነበር፡፡
አያሌ አንባቢያን እጅ ገብተናል፡፡ ከነጭና ጥቁር ፅንፍ ይልቅ እመካከል ለሚገኘው ግራጫው ቦታ ላይ ያለ ሠፊ ማህበረሰብ እናግዛለን ብለንም ነበር፡፡ ያገለገልን ይመስለናል፡፡ “በአንፃራዊ መልኩ ሀሳብ ላለው ሁሉ የሃሳብ መስጫ መድረክ እንጂ የፖለቲካ አቋም ማራመጃ አይደለንም” ብለንም ነበር፡፡ ቃላችንን አክብረናል፡፡ ለእኛም ቃል የዕምነት ዕዳ ነበር፡፡ ነው፡፡ ነገም ሌላ ቃል ነው! ነገን ያየነው ገና ትላንትና ነው፡፡
የተመሠረትነው በዕውቀት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ስሜታዊነት አያጠቃንም፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ በትምህርት ማነስ የተፈጠረውን ገዋ (Vacuum) እንሞላለን የሚል ዕምነት አለን፡፡ ዓላማችን ኢንፎቴይመንት ነው፡፡ Infotainment የInformation እና የEntertainment ቅልቅል ነው - መረጃ መስጠትና ማዝናናትን የያዘ ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ባህል ላይ ተመሥርተን ፖለቲካን ልናስብ እንችላለን እንጂ ፖለቲካን እንደ ባህል አንወስደውም (We are culturally political and not politically cultural)
ከአንባቢዎቻችን ጋር ረዥም መንገድ ተጉዘናል፡፡ የጋዜጣ ሥራ በተለይ ባላደገ  አገር በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ የሚተኙበት አይደለም፡፡ ይህን አለማወቅ የዋህነት የሆነውን ያህል፣ አውቆ መደነባበርም የዚያኑ ያህል ሜዳው ገደል እንዲሆን የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡ “አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” እንዲሉ፡፡ የተከፈተ በር አናንኳኳም፡፡ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ስንባል ግን “አስቀድሞ ነገር ለምን ተዘጋ?” እንላለን፡፡
“እሾክ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው” ብለን በምሬት ብቻ አገራችንን አናጣም፡፡ ይልቁንም፤
“አገርህ ናት በቃ
አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረሃት ንቃ!”
እንላለን፡፡ እኛ ብቻ አዋቂ የሚል ግብዝነት የለብንም፡፡ የብርሃን ነጠብጣብ ሁሉም ሰፈር አለ፡፡ በየት በኩል እናብራ ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ተወርዋሪ ኮከብ እንዳለ ሁሉ ትልቁ ድብ እና ትንሹ ድብ አለ፡፡ የቡና ስባቱ መፋጀቱ ብንልም እንኳ፤ እንደ ቡና ከምንቀዘቅዝ (Decaffeination) እንደወይን አድረን ብንበስል (ብንመረቃ) እንመርጣለን፡፡ “ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል” ብንልም፤ ለምን ያለቅሳል? ከማለት አንቆጠብም፡፡ ያልተመለሱ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ሰብዓዊ ጥያቄዎችን እናስታውሳለን፡፡ የሕግ የበላይነት እከሌ ከእከሌ ሳይባል እንዲከበር እንወተውታለን፡፡ በምንም ሽፋን የሰው ልጅ እኩልነት እንዳይነካ መረጃዎችን ለመስጠት እንጥራለን…ትላንት እንዲያ ነበር፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው፡፡ ነገም ይቀጥላል፡፡
እነሆ! አሥራ አምስት ዓመታትን ተሻግረናል፡፡ በነዚህ ዓመታት ውስጥ የዛሬ አሥር ዓመት ትጉውን፣ ደጉን፣ ምሁሩን ሥራ አስኪያጃችንን (አቶ አሰፋ ጐሣዬን) አጥተናል፡፡ ምኔም እናስታውሰዋለን፡፡ ያልተዘመረለት ጀግና ነውና! ረቂቁን ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀብተማሪያምን፣ ሰፊ ማህበራዊ ዳሰሳን የተካነውን አብርሃም ረታንም አጥተናል፡፡ ነብሳቸውን ይማር!
እንደሌላው የህይወት መንገድ ሁሉ በጋዜጠኝነት ውጣ ውረድ ውስጥም ብዙዎች ይመጣሉ ብዙዎች ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናትም፣ ፓርቲዎችም፣ ታዋቂ ግለሰቦችም፣ ልዩ ልዩ ተቋማትም ወዘተ አሉ፡፡ ሁሎችም ይሰሙናል፤ ሁሉችም ከጥፋታቸው ይማራሉ ብለን አንጠብቅም፡፡ ለውጥ አድሮ አዳጊ ነው (incremental)፡፡ ዲሞክራሲም እንደዚያው፡፡ የብዙ ለውጦች እንቅፋት ጉራና ዝና ነው፡፡ ስለሆነም፡-
“ዝናኮ እንደንብ ነው
ዜማ አለው፣ ቃና አለው
መውጊያ እሾኩ ጉድ ነው!
የሰማያት ያለህ! ለካ ክንፍም አለው!”
የሚለውን ያልታወቀ ገጣሚ ፅሁፍ አበክረን እንገነዘባለን፡፡
በመጨረሻም ከደራሲ ከበደ ሚካኤል ጋር፤
“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሣፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ” ብንልም፤ በዚያ አናቆምም፡፡
“ምሥማር እንኳ ቢዘንብ፣ ከሰማይ ጣር ቁጣ
እንናገራለን፣ አድማጭ እስኪመጣ!” እንላለን፡፡
እስከዛሬ ላነበባችሁንና ነገም ለምታነቡን ምሥጋናችን ክቡርና የላቀ ነው!



Read 5940 times