Monday, 09 March 2015 11:46

ለመሆኑ ሳቅ የማን ናት?

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

የእግዚአብሔር ወይንስ የሰይጣን?.... ሰይጣን ምን አባቱ ቆርጦት ይስቃል! ስራውን ሰርቶ ሲጨርስ የት ተወስዶ እንደሚጣል እያወቀ ይቆዝም እንጂ ምን ያስቀዋል!...
ሳቅማ የሰው ልጅ ብቸኛ አንጡራ ሀብቱ ናት። ፍርሐቱን የሚያሸንፍባት….ከአቅሙ በላይ ውድ አድርገው የሸጡለትን ህይወቱን ቀለል፣ ረከስ የሚያደርግባት እፎይታው፡፡ ሳቅማ የእኔ ናት፡፡ ግን ታዲያ ለምንድነው ስቄ የማላውቀው?
መሳቅ ስላለብኝ የማሳቂያ ምክንያት መፍጠር አስፈልጐኛል፡፡ ግን እኮ ሳቅ ምክንያት አያሻውም፡፡ የአመለካከት መንገድን መቀየር ብቻ ነው ዋናው ነገር። ትንሽ መጃጃል ማለቴ ነው፡፡ ጨካኝ መሆን ሳይሆን መጃጃል፡፡
“በማን ላይ ነው የምትስቀው…..ምን ያስቅሀል?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ቢሆንም፤ ምክንያት መፍጠር አያስፈልገኝም፡፡ በሁላችሁም ላይ እና በሁሉም ነገር ነው የምስቀው፡፡ የሳቅ ት/ቤቱ ራሱ ያስቀኛል፡፡ ስለ ሳቅ የምፅፈው ራሱ እየሳቅሁ አለመሆኔ በውስጤ ያስቀኛል፡፡ “እያረሩ ማሳቅም” የሳቅ አይነት ነው…ኮርሱ በሳቅ ት/ቤታችን ስለመስጠቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
እንደ ሃይማኖት ተቋሞች ሳቅን በድብቅ የሚያወግዝ ያለ አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪን መፍራት ዋነኛው መርህ በሆነበት ስፍራ ሳቅ ሊፈቀድ አይችልም፡፡ ቀጥ ባለ በአናቱ ብቻ የሚታወቅ ነገርን ዘቅዝቆ በማየት ድፍረት ነው ሳቅ የሚፈጠረው፡፡ ጠንካራ እምነትን ወደ ጥርጣሬ በሚለውጥ እይታ ውስጥ እንቆቅልሽ ይወለዳል፡፡ መገልፈጥ ሳቅ አይደለም…ከጥርስ መደርደር ባሻገር…  ሀሳብም ሲደመርበት ቀልድም ሳቅ ይሆናል፡፡
ሳቅ መገልፈጥ አይደለም፡፡ ጥሩ ሃሳብ ያስፈልገዋል። ለጥሩ ሃሳብ ደግሞ ጥሩ እውቀት አስቀድሞ መኖር አለበት፡፡ ሃሳብ እና እውቀት ኖሮት የነፃነት ፍርሃት ያለበት ሳቅን ከቀልድ ውስጥ ሊያመነጭ አይችልም፡፡ … ምናልባት የኔም የሳቅ ድርቀት ከእዚህ ጉድለቶች በአንዱ ምክኒያት ይሆናል፡፡
ለመንፈሳዊያኑ ሳቅ የስጋ ሀጢአት ተደርጐ በግልፅም ባይሆን መወሰዱ አይቀርም፡፡ ሳቅን ከተሳቀበት ምክንያት ነጥሎ ማየት አይቻልምና፡፡ በሙዝ ልጣጭ ተንሸራትቶ የወደቀው ሰው ላይ መሳቅ…መስቀል ተሸክሞ ከወደቀው መሲህ ላይ ከመሳቅ ጋር ረቂቅ የሆነ ትስስር አለው፡፡ የፈረንሳይ የካርቱን መጽሔት አዘጋጆች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉትም በዚሁ የሳቅ ግንኙነት ነው፡፡
ሳቅ የሰው ልጅ የግል ንብረቱ ናት፡፡ የማህበረሰብ አይደለችም፡፡ ማህበረሰብ ተግባብቶ በሳቀው ቀልድ ሌላ የሚያስኮርፈው አካል ከበስተጀርባ አለው፡፡ ሳቅ ብቻውን አይደለም፡፡ የተሳቀበት ነገር እና ምክኒያቱ አብሮት አለ፡፡ የሳቀው ከተሳቀበት እኩል ደስተኛ እንዲሆን አይጠበቅም። ሳቅ የነፃነት መገለጫ ነው፤ ግን የአንዱ ነፃነት ሌላውን በማብሸቅ አርነቱን የሚቀዳጅ ነው፡፡ መንግስት በቀለደው ቀልድ ህዝብ አይስቅም፡፡ ይገለፍጥ እንደሆን እንጂ…
ስለዚህ ሳቅ የግለሰብ ናት፡፡ “On the road” የተባለ የጃክ ኬሩዋክ ድርሰት ላይ አንድ ገፀ ባህርይ አለ፡፡ ምግብ እየተመገበ ተጎልቶ ከነበረበት መአድ ምን አይነት ቀልድ በጭንቅላቱ እንደተፈጠረ ባይታወቅም…ከጠረጴዛው ተነስቶ መሳቅ ጀምሮ…እየተንደፋደፈ እስከ ከተማዋ ጠረፍ ድረስ ቀኑን ሙሉ ሲስቅ ዋለ፡፡ የዚህ ኔግሮ ሰውዬ ሳቅ በአይነቱ ለየት የሚልብኝ የሳቁ ምክንያት በደራሲው ባለመገለፁ ነው፡፡ ሳቅ የግለሰብ ንብረት መሆኗንም ለእኔ ያረጋግጥልኛል፡፡ ከራስ ጋር ብቻ የሚሳቅ ሳቅ… ለሳቂው ለራሱ ቅኔ ነው፤ ለተመልካች ግን እብደት፡፡
“ምን አሳቀህ?” ተብሎ ጥያቄ ከቀረበ በኋላ የሳቁ ባለቤት ዕይታ እና ሳቁን ለመዋስ እየሞከረ ያለው ሰው እየታ ካልተጣጣሙ…ቅራኔ ሊከሰት ይችላል፡፡ ወይ የሳቅ ነፃነት ጉልበቱ ይደክማል፡፡ የሳቅ ሙሉ ነፃነት ግለሰብ አእምሮ ውስጥ ያለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወጥቶ ለሌላ ለማቀበል ማለዘብ እና መደራደር ይገደዳል፡፡
ሁሉም ቀልድ ከፍ ተደርጐ የሚታይ ነገርን ዝቅ በማድረግ የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ እስታሊን፣ ሌኒን እና ትሮትስኪ “Animal farm” ላይ ያሉትን አሳሞች ይሆናሉ። ሰራተኛው መደብ ፈረስ ተደርጐ ይመሰላል። ከፍታው ላይ ክብራቸውን ያደላደሉት እንጂ ሲወድቁ የሚያስቁት ውዳቂውማ ድሮውኑ ትራጀዲ ነው፡፡ … ድሮውኑ ጉድጓድ ውስጥ ባሉት ለመሳቅ ያስቸግራል፡፡
ከፍታው ላይ በነበረበት ሰዓት ይፈራ የነበረው ነገር በሳቅ ዝቅ ብሎ ትንሽ እንዲረክስ፣ የደረበው ጭንብልም ተቀዶ እንዲወድቅ ይሆናል፡፡ በዚህ የሳቅ ሂደት ከፍታው ላይ ለነበረው ነገር፣ ሰው፣ አምላክ ከቀልዱ በፊት የነበረው ፍርሐት ከሳቁ በኋላ አይኖርም፤ ወይንም ዋጋው ይረክሳል። ሳቅ ተነግሮት መሳቅ ባይፈልግ እንኳን አምልጦት የሳቀ፣ ለሳቀበት ነገር ከዚህ በፊት ይሰማው የነበረውን ፍርሐት…ክብር በመጠኑም ቢሆን አጥቷል፡፡
ስለዚህም፤ ክብር እንዲረክስ በማይፈለግበት ስፍራ ቀልድ አይፈቀድም፡፡ ከቀልድ ወይንም ገላጭ እንቆቅልሽ ፍቺ ውጭ የሚወጣ ሳቅ ደግሞ ለአእምሮ ችግረኞች እና ቂሎች የተመደበ በመሆኑ … ቦታ አይሰጠውም፡፡
ሳቅ የነፃ ግለሰቦች እና የቂሎች ናት፡፡ ምናልባትም ነፃ ግለሰቦች ቂሎች ብቻ ናቸው፡፡
ሁሉም እውነተኛ ሳቅ ውስጥ ከዚህ በፊት ተገልጦ የማያውቅ እውነት አለ፡፡ እውነቱ ግን የሳቁ ምክኒያት የሆነው ነገር ከዚህ በፊት ይታይ የነበረበትን መንገድ አደብዝዞ የሚፈካ በመሆኑ በሳቅ ውስጥ አዲስ ገፅታ ይዞ እውነቱ ሲወለድ የድሮውን ገፅታ ግን ይገድለዋል። የድሮው ገፅታው እንዲሞት የማይሹ በሳቅ እንዲረክስ አይፈቅዱም፡፡ በቀልድ መወጋት በጦር ከመወጋት የበለጠ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ የተወጋው ነገር እንዳለበት (አለሁ እንዳለበት) ከፍታ የአወዳደቁ ርቀት እና ህመሙ ይወሰናል፡፡
አንድ ህፃን ሊስትሮ በጥፊ ሲመታ ብዙ ሰው ሊስቅ ይችላል፡፡ አንድ ሽማግሌ ግን በጥፊ ቢመታ ቀልድ አይሆንም፡፡ ቀልድ እንዲሆን የማህበረሰብ ውሉ አይፈቅድለትም፡፡ የግለሰብ የውስጥ ግዛት ግን ብቻዋን ትስቃለች፡፡ ከፍ ካለበት ቦታ በሳቅ የወረደው ሁሉ ለግለሰቡን ፍርሐት በሆነ ነፃነት ተክቶ ነውና፡፡
ብዙ ፍርሃት እና መፈራራት በነገሰበት መንፈስ ውስጥ ለግለሰብ ከሳቅ የበለጠ ወጌሻ የለም፡፡ ሳቅ ከጥበባቱ መደርደሪያ ወጥታ (ወይ) ፋርማሲ መደብር መደርደሪያ ላይ መቀመጥ ሳይኖርባት አይቀርም፡፡ ፍርሐት እና መጠባበቅን ዋጋቸውን ረከስ አድርጋ… ቀልዳባቸው ትንሽ ነፃነት እና የእፎይታ የተናፈሰ አየር እንዲገባ መፍቀድ ትችላለች፡፡
ክርስቶስ ፍቅርን ሰበከ…ሞት እና መንግስት ደግሞ ፍርሐትን ሰበኩን፡፡ ሳቅ ምናልባት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፍርሐትን የሚያበዛ ጭንቅላት እና ትካዜን አጥብቀን እንድንይዝ የሚያደርግ ማንኛውም ተቋም ላይ በጥቂቱም ቢሆን መሳቅ መቻል ይኖርብኛል፡፡ ስንስቅ ፍርሐት አቅሙ ቀነስ ይልና ምናልባት ወደ ፍቅር የመሄጃ የማርያም መንገድ ሊሰጠን ይችል ይሆናል፡፡
ትሩማን ካፖት (Truman capote) የተባለ አሜሪካዊ ደራሲ “የገና ትዝታ” የምትል ምርጥ አጭር ልብወለድ አለችው፡፡ ልብ ወለዱ ውስጥ አንድ የመጠጥ ቤት ባለቤት የሆነ ሰውዬ አለ፡፡ ሰውየው በጣም ጨፍጋጋ ፊት ያለው፣ አንድ ቀንም ሲስቅ ተሰምቶ የማያውቅ አይነት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዚህ አስፈሪ ፊት ላለው ሰው “ha-ha” የሚል ስም አወጡለት፡፡ ስቆ ለማያውቅ ሰው የሳቅ ድምፅ ቅላፄን ስም ብለው ሰጡት፡፡ ስሙ ተጣበቀበት፡፡ እና ካፖት የሰውየውን ገፅታ ገልፆልን እየፈራነው እያለ ስሙን ሲነግረን ቀለል ይለናል፡፡ ገፀ ባህሪው በስሙ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም መልኩ የሚያስፈራ ግን መልካም ሰው ሆኖ የተቀረፀው፡፡
የፍርሐት መንፈስ የነገሰባት ሀገር ላይ የሳቅ ት/ቤት መኖሩ ደስ ይለኛል፡፡ ት/ቤቱ እንደሌላው ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራት የጐደለበት እንዳይሆን ምኞቴ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ሲጎድል በግድ የሚስቁ ምሩቃን….መፍትሔ የማይፈጥሩ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ፡፡ መፍትሔው ሳቅ ነው፡፡ ከበድ ተደርገው የሚታሰቡትን ነገሮች ትንሽ ቀለል አድርጐ ክብደታቸው ልንሸከማቸው ከምንችለው መጠን በላይ እንዳይሆን ማበጀት፡፡
“የቡድን መብት ከግለሰብ መብት ይቅደም”፤ ግዴለም…ለግለሰብ ግን የመሳቅ መብት ይፈቀድ፡፡ ለመሳቅ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ ለመሳቃችን ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉት ደግሞ ፍርሐቶቻችን ናቸው፡፡ የግብር ፍርሐት አለብን፣ የእውቀት ፍርሐት፣ የእውነት ፍርሐት፣ መሪን የማምለክ ፍርሐት፣ የነፃነት ፍርሐት…ወዘተ፡፡ ቀልድ እና ሳቅ ግትርና ተወጥሮ ላይበጠስ የሚያጨናንቀን መንፈሳችንን ረገብ ካላደረገው … ህልውናችን ትርጉም የለውም፡፡ ሰው ለመሆን ሰውነትን ማጣት ነው ነፃነታችንን የሚነፍገን፡፡
የጥንት ሰው ሰማዩ አልደርስ ወይ አልገሰስ ሲለው ሳይሆን አይቀርም የፍጥረትን ረቂቅ ሚስጥር ራሱ በፈጠረው ቀልድ ረገብ ለማድረግ የሚሞክረው፡፡ እናም፤ ምድር እና ህዋ የሰባት ቀናት የፈጣሪ ሳቅ ውጤት ናቸው ብሎ ተረተ፡፡ የሰባተኛው ቀን የሳቅ ውጤት ደግሞ ራሱ ሰው ነው ይለናል - ተረቱ፡፡ ምናልባት ሃይማኖት በጣም ከሮ የሚሆነውን ሲያጣ ሊሆን ይችላል የቀልድ ፈጣሪው በራሱ አስመስሎ ወደ ፈጣሪ ጆሮ እቺን “ጆክ” ያስወነጨፋት፡፡ ምናልባት ፈጣሪ ፈታ ብሎ ስቆ ከፈጠረኝ፣ የእኔ ሌት ተቀን መጨነቅ የት ለመድረስ ነው? እንደማለት፡፡ ፈጣሪ በሳቅ ከሆነ ሰውን የፈጠረው…ሰው ተፈጥሮ ላይ ወይንም ራሱ ስቆ ማስተጋባት እንጂ… ማልቀስ ሞኝነት መሆኑንም ያስታውሰናል፡፡ ፈጣሪ በራሱ ቀልድ የሚስቅ ከሆነ ሞኝነት ሰማይና ምድርን የሚያስተሳስረው ብቸኛው ምስጢር ሳይሆን አይቀርም፡፡  ግን ክርስቶስ የአምላክን ባህርይ ለብሶ ስቆ ያውቅ እንደነበረ ብጠራጠርም፣ የሰውን ስጋ ሲለብስ ግን አልቅሷል፡፡ እየወደቀ እየተነሳ መስቀሉን ተሸክሞ ሲጓዝ የሳቁበትም ነበሩ፡፡ በሳቃቸው ስቃዩን ዝቅ አድርገው፣ በዛች ቅፅበት ፍርሐታቸውን መርሳት ችለዋል፡፡ የራሳቸውን የሞት ፍርሐት መሲሁ ከወረደበት ተመልሶ ሲወጣ የሳቁበተ ላይ ይስቅባቸው ይሆን?...ያስፈራል፡፡ እያስፈራም ግን በውስጡ አንድ ኮሜዲ ከጥቀርሻው የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ውስጥ አራግፎ መፍጠር እና ጊዜያዊ እፎይታ በሳቅ ውስጥ ማግኘት ሳይሻል አይቀርም፡፡
ሳቅ የሰው ልጆች አንጡራ ሀብት መሆኑን አምናለሁ፡፡ ጨለም ያለ መንፈስ በተጫነኝ ጊዜ ለጨለምተኛ መንፈስ ከብርሐን ይልቅ ሳቅ የበለጠ ተስፋን ይፈነጥቃል፡፡  

Read 7432 times