Monday, 09 March 2015 11:41

የአዲስ አድማስ የ15ኛ ዓመት እንግዳ) ጋዜጣና ቡና የሚያቀርበው ካፌ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    “ከወፍራም ቡና ጋር አብሮ የሚሄደው ነገር ምንድን ነው?” ብዬ ስጠይቃችሁ፤ ምን ቡና አለ?! ብላችሁ ወደ ወትሮው ምሬታችሁ እንድትገቡ አልፈልግም፡፡ ከወፍራም ቡና ጋር የሚሄደው ነገር ንባብ ነው፡፡ ጋዜጣ ወይንም መፅሔት አሊያም መፅሐፍ ከያዛችሁ ማለፊያ ነው፡፡ … ታዲያ ቡና እያጠጣ ጋዜጣ በራሱ ሂሳብ ገዝቶ አንብብልኝ የሚል ካፌ ከተገኘ ይኼ ሰው ባለውለተኛነቱ … ለቡና ጠጪ እና ለንባብ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን … ከንባቡ ጀርባ ላሉት የጋዜጣና መፅሔት ፀሐፍት (የፃፉት እንዲነበብላቸው ለሚፈልጉ) እንዲሁም ለቡና ገበሬዎችና ቡና ነጋዴዎች (ያመረቱት እንዲጠጣላቸው ለሚመኙትም) ጭምር ነው፡፡ ቡናን ፉት እያሉ ንባብን ማጣጣም የሚችሉበትን ካፌ ገርጂ ያገኙታል፡፡
የመብራት ኃይል ካፌ ባለቤት አቶ ፀጋዬ ወንድሙ ራሳቸውን ያስተዋውቁንና ስለ ካፌያቸው ያወጉናል፡፡  

ፀጋዬ ወንድሙ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት እዚህ አዲስ አበባ ለገሀር አካባቢ ነው፡፡ በስፖርት ውስጥ በሩጫ እሳተፍ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ወደ ውጭ የመሄድ አጋጣሚ ፈጠረልኝና ወደ ጣሊያን አመራሁ፡፡ ጣሊያን ለሁለት አመት ያህል ከቆየሁ በኋላ ወደ ካናዳ ተሻገርኩ፡፡ እዚያም ለ14 አመታት ኖርኩ፡፡ ካናዳ በነበረኝ ቆይታ በሩጫው ዘርፍ እወዳደር ነበር፡፡ በመጨረሻ ከ8 አመት በፊት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ካፌ ከፍቼ መስራት ጀመርኩ፡፡
ካናዳ ምን እየሰራህ ነበር የምትኖረው?
ያው መጀመሪያ በሩጫው ምክንያት ነው ከሀገር የወጣሁት፡፡ ካናዳ ከሄድኩኝ በኋላም አንድ ድርጅት ወክዬ እሮጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የካናዳ የአየር ንብረት ትንሽ ስለከበደኝ በሩጫው መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው የተለያዩ የዕለት ተእለት  ስራዎችን እየሰራሁ ለ14 አመት ቆየሁ፡፡ የካናዳ ዜግነት ስላለኝ በፈለግሁት ጊዜ በመመለስ መኖር እችላለሁ። ነገር ግን ወደ አገሬ ስወጣ ለራሴም ገቢ የሚፈጥር፣ ህብረተሰቡንም የሚያግዝ ሥራ መስራት አለብኝ ብዬ ስለሆነ እየሰራሁ ነው፡፡
ከካናዳ መጥተህ እንዴት የካፌ ስራ ውስጥ ገባህ?
ከልጅነቴ ጀምሮ በተለያዩ ቢዝነሶች የመሰማራት እድሉ ነበረኝ፡፡ ሞተር ብስክሌት እና መኪና አለማምድ ነበር፡፡ መኪና ወደ ካፌ ቢዝነስ ልገባ የቻልኩት ግን  በካናዳ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ከጓደኞቼ ጋር እየተገናኘን የተለያዩ ነገሮችን የምንወያየው በካፌ ውስጥ ነበር። ካፌ ውስጥ ገብተን ጓደኞቻችንን በምንጠብቅበት ወቅት ታዲያ የእለቱን ጋዜጦችና መጽሔቶች ካፌው ያቀርባል ቴሌቪዥንም ይከፍታል፡፡ ወጣቶችም ይሁኑ አዛውንቶች ወደዚህ ካፌ ሲመጡ ከህትመት ውጤቶች ላይ መረጃዎችን እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፡፡ ወጣቶች በተለይ አጓጉል ቦታ ጊዜያቸውን ከማሳለፍ እዚህ እያነበቡ፣ ቴሌቪዥን እየተመለከቱ የሚቆዩበት መንገድ ተመቻችቷል፡፡ ሥራ ፈላጊዎች ሳይጉላሉ ከጋዜጦች ላይ ክፍት የሥራ ቦታዎችን ያያሉ፡፡ እዚህ ክፍት የስራ ቦታ አይተን ስራ አገኘን የሚሉ ብዙ ደንበኞች ያጋጥሙኛል፤ ይሄ ያስደስተኛል፡፡
ከካፌ ሌላ ቢዝነስ አለህ?
በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ እየሰራሁ ነው።  ገልባጭ መኪኖች አሉኝ፡፡ ከሚኒባስ ስራ ነው ወደ ገልባጭ የቀየርኩት፡፡
የየዕለቱን ጋዜጣ በማቅረብህ የካፌ ሥራህ አልተጐዳም? ደንበኞች ጋዜጣ ሲያነቡ ለረዥም ሰዓት መቀመጫ ይይዛሉ ብዬ ነው……
ለገንዘብ ብዬ የሠውን ፍላጐት መጫን ስለሌለብኝ ደንበኞቼ እንዲያነቡ ፈቅጃለሁ፡፡ መፍቀድ ብቻ አይደለም፤ የሚያነቡትንም እያቀረብኩ ነው፡፡ ያለምንም የሰአት ገደብ ማንበብ ይችላሉ፡፡ ይህንን ሳደርግ እኔም የማገኘው ጥቅም አለ፡፡ ሰው ጋዜጣ ለማንበብና ክፍት የስራ ቦታዎችን ለማየት ሲል ከተለያዩ ሰፈሮች ወደ እዚህ ካፌ ይመጣል፡፡ ጋዜጣውን ለማንበብ ሲቀመጥ ደግሞ ማዘዙ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አንድ ደንበኛ የመሳቢያ መንገድ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ጋዜጦችን ማቅረቤ ለቢዝነሱ የሚሰጠው ጥቅም አለ ማለት ነው…
በብዙ ካፌዎች ግን እንዲህ ያለ ነገር አልተለመደም። እንደውም “ጋዜጣ፣ መፅሐፍ ማንበብ ክልክል ነው” የሚሉ ማሳሰቢያዎች የሚለጥፉ ሁሉ ያጋጥማሉ፡፡
እንግዲህ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ፍልስፍና፣ የራሱ የሆነ አተያይ ይኖረዋል፡፡ እነዚያ ሰዎች ለምን እንደዚያ እንዳደረጉ አላውቅም፡፡ እኔ ግን ባለኝ እውቀትና የአስተሳሰብ ደረጃ አንድ ሰው መረጃ ማግኘት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እየተከናወኑ ያሉ አዳዲስ ነገሮችን ሊያውቅና መረጃው ሊኖረው ይገባል የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን ከሚያገኘው መረጃ ባሻገር ከተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች አዳዲስ መረጃዎችን እያገኘ፣ እግረ መንገዱን የማንበብ ባህልን እያዳበረ እንዲሂድ ባለኝ ፍላጐት ነው ይህንን ተግባር እያከናወንኩ ያለሁት፡፡
በካፌው ውስጥ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲነበቡ በማድረግህ ምክንያት የገጠመህ ቅሬታ ወይ ትችት አለ?
በሁኔታው የሚደሰቱ እንዳሉ ሁሉ የሚከፉ ሊኖሩ የሚችሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ እኔ ግን አምኜበት የማደርገው ስለሆነ “እገሌ ስለከፋው ማስነበቤን ላቁም” የምልበት ምክንያት አይኖረኝም፡፡ የሚደሰተውን እያስደሰትኩ መቀጠል ነው የኔ ሃላፊነት፡፡
ሰው አንድ ጋዜጣ ገዝቶ ሊያነብ ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉንም የየዕለቱን ጋዜጣ ገዝቶ ሊያነብ አይችልም፡፡ ያንን ለማድረግ የኑሮውም ሁኔታ ላይፈቅድለት ይችላል፤ ስለዚህ እኔ ሁሉንም የየዕለቱን ጋዜጦች በማቅረብ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለህብረተሰቡ በመፍጠር ከሌላው አለም ያገኘሁትን ተሞክሮ በአቅሜ ለዚህ ህብረተሰብ እያካፈልኩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ለምን ጋዜጣ ታስገባለህ ተብዬ የተጠየቅሁበት ጊዜ ሁሉ አለ፡፡ ሰው ቁጭ ብሎ ሲያነብ ችግር ለመፍጠር የተሰባሰበ ወይም ተቃውሞ ሊመስል ይችላል፡፡
በዚህም ምክንያት በተለያዩ አካላት ጋዜጣ እንዳላስነብብ ተነግሮኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ጋዜጦችን ሳመጣ መርጬ እንደማላመጣና ሁሉንም አይነት ጋዜጦች እንደማመጣ፣ ዓላማዬም ህብረተሰቡ መረጃ እንዲያገኝና የማንበብ ባህል እንዲያዳብር መሆኑን፣ ይሄም ከውጭ አገር ያገኘሁት ተሞክሮ እንደሆነ አስረድቻቸዋለሁ፡፡  
ከህብረተሰቡ ምን አይነት ምላሽ ታገኛለህ?
ህብረተሰቡ በጣም ደስተኛ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ሄጄ ባጋጣሚ ጋዜጣ ተከራይቼ በማነብበት ወቅት የተለያዩ ሰዎች የኪራዩን ሒሳብ የሚከፍሉበት ጊዜ አለ፡፡ እኔ በመልክ እንኳን የማላውቃቸው ሰዎች “አንተ ሁሌ በነፃ እያስነበብከን እኛ የአንድ ቀን የጋዜጣ ኪራይ ብንከፍል ምን አለበት” ይላሉ፡፡ በካፌ ውስጥ ቁጭ ብለው የሚያነቡ አዛውንቶች ሲመርቁኝ ህብረተሰቡ በዚህ ተግባሬ በጣም ደስተኛ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ አንዳንዴ እንደውም “እዚህ ስናነብ ባገኘነው ክፍት የስራ ቦታ አመለክተን ስራ አገኘን፤ ደስ ብሎናል ካልጋበዝኳችሁ “የሚሉ ደንበኞች ሁሉ ያጋጥሙናል፡፡ ስለዚህ በምንሰጠው አገልግሎት ህብረተሰቡ ደስተኛ ነው ብለን እናምናለን፡፡
አንዳንዶች የተሻለ ደሞዝ ያለው ሥራ ማግኘታቸውን ሲነግሩንም ደስ ይለናል፡፡ ለካ እንዲህ እያደረግን ነው ብለን እንድናስብ የሞራል ድጋፍ ይሆነናል፡፡
በአንተ ተሞክሮ በህብረተሰቡ ውስጥ የማንበብ ባህል አለ ብለህ ታስባለህ?
እኔ እንዳየሁት ከሆነ አቅሙ እስካለውና ሁኔታዎች ተመቻችተው እስከቀረቡለት ድረስ ህብረተሰቡ የማንበብ ፍላጐት አለው፡፡ ማታ ካፌውን በምንዘጋበት ሰአት መጥቶ 10 ደቂቃ ለንባብ ብሎ የሚያስፈቅድ ደንበኛ ሁሉ አለ፡፡ ይሄ ህብረተሰቡ የማንበብ ፍላጐት እንዳለው ያሳየኛል፡፡ ሌላው የመግዛት አቅሙ ባይኖረው እንኳን ተከራይቶ ሲያነብ ይስተዋላል፡፡ ከሰው ከሚሰማው ነገር ይልቅ አንብቦ ለመረዳት ያለው ፍላጐት ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ እንደኔ አስተያየት ህብረተሰቡ የማንበብ ፍላጐት አለው ነው የምለው፡፡ እንደዚያ ካልሆነማ፣ ለምን የተለያዩ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን እየገዛሁ አስቀምጣለሁ? ሌላው ቀርቶ ስንዘጋ አንብቦ ያልጨረሰ ደንበኛ ካለ፣ ቤት ወስጄ ላንብብና ጠዋት ልመልስ የሚልበት አጋጣሚ ሁሉ አለ፡፡
ጋዜጣ ለምን ታስነብባለህ የሚል ጫና አሁንም ይደርስብሃል?
እኔ በግልፅ ተናግሬአለሁ፡፡ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዓላማ እንደሌለኝና ለሥራ የቆምኩ መሆኔን፣ ጋዜጣ አታስነብብም ከተባልኩ ካፌውንም እንደምዘጋ ገልጬአለሁ፡፡ እነሱም አንባቢው ጤነኛ እንደሆነና ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ሲያዩ ትተውኛል፡፡  አሁን ምንም አይነት ጫና የለብኝም፡፡ ይሄም የሆነው ሥራ የጀመርኩ ሰሞን ብቻ ነው፡፡
በልጅነትህ የማንበብ ልማድ ነበረህ?
ከልጅነቴ ጀምሮ የማንበብ ባህሉና ፍላጐቱ ነበረኝ ልልሽ አልችልም፡፡ የማንበብም ሆነ የማስነበብ ባህልን ያዳበርኩት ውጪ በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ ካናዳ ስኖር የማስተውላቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ በየካፌው የተለያዩ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ተደርድረው ለደንበኞች ይቀርባሉ፡፡ እነሱ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው በመረጃ የተደገፈ ነው፡፡ ስለዚህ የንባብ ነገር ካናዳና ጣሊያን በነበረኝ ቆይታ ያዳበርኩት ባህል እንጂ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረ አይደለም፡፡
የየዕለቱ የጋዜጦች ወጪህ ስንት ነው?
በየቀኑ የሚወጡትን ሁሉንም አይነት ጋዜጦች አመጣለሁ፡፡ በቀን ለጋዜጣና ለመጽሔት እስከ 50 ብር አወጣለሁ፡፡ በሳምንት እስከ 350 ብር ገደማ ይሆናል። ለአንድ አስተናጋጅ በወር የምከፍለውን ደሞዝ ማለት ነው፡፡    

Read 2509 times