Monday, 09 March 2015 11:36

ጊዜ ክፉውን ጥሎ፣ ደጉን ይዞ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ለአድማሶች፣ እንኳን ለአሥራ አምስተኛ ዓመታችሁ አደረሳችሁማ!
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሳችሁ…” መባባል አሪፍ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ለመባል ዕድሉን ያላገኙትን ማሰቡ ጥሩ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ጥያቄ አለን፣ በ‘ድሮ አራድነት’ና በ‘‘ዘንድሮ አራድነት’…አለ አይደል…ፊልሞች ይሠሩልንማ! ልክ ነዋ…ነገሮች ግልጥና ግልጥ ይሁኑልና! የአራዳነት ‘ዴፊኒሽን’ ተለውጦ ከሆነም ይገለጥና መቀመጫ ሳጥናችንን እንወቅማ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የድሮ እንትና የድሮዋን እንትናዬን ለማጥመድ የነበረው ‘ውጣ ውረድ!’ ልጄ ዘመን ተለወጠና ስሟን ሳያውቅ ‘እሷን የሚያውቅበት’ ጊዜ ላይ ደርሰነው አረፍን! ቂ…ቂ…ቂ…  
እናላችሁ… በፊት አስቀድሞ ስሟ፣ የማን ልጅ እንደሆነች፣ ‘ጉልቤ ብራዘር’ ይኑራት፣ አይኑራት… ምናምን ይጠናል፡፡ ቀጥሎ በርቀት በ‘ዓይኑካ’ መከታተል አለ…ከዛ ‘መመኘት’ በህልም ማየት ምናምን አለ፣ ቀጥሎ ብጣሽ ወረቀት በትንሽ ልጅ አስይዞ መላክ አለ፣ መልስ መጠበቅ አለ…(እንደዛም ሆኖ እኮ ላይሳካ ይችላል!) “እሺ…” የተባለ ቀን…ምን አለፋችሁ… የሆነ ‘ኖቤል’ ምናምን ቢያሸንፍ እንኳን እንደዛ ደስ አይለውም፡፡ ደግሞ እኮ እሺታው ‘ሻይ ለመጠጣት’ ብቻ ነው፡፡ በድሮ አራዶች ሻይ እንጠጣ ማለት ሻይ እንጠጣ ነው፡፡ እና ዘቢብ ኬክና ቡና በወተት ሳይጋብዝ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሻገር!
ከዛላችሁ…ከተወሰኑ ሳምንታት የዘቢብ ኬክና… አለ አይደል… እንደ እሱዬው ‘ኤኮኖሚክ ስታተስ’ ከባቅላባ ግብዣ በኋላ ደግሞ ጉዞ ሐምሌ አሥራ ዘጠኝና፣ ብሔረ ጽጌ ይሆናል፡፡ እሱኛው የፐሮጀክት ፌዝ ቂ…ቂ…ቂ… ለመጠናቀቅ ወራት ሊፈጅበት ይችላል፡፡ ‘ተጠናቀቀ’ የሚባለው …‘ኪሶሎጂ’ (ያውም ‘በስሱ’!) ላይ ሲደረስ ነው፡፡ በድሮ አራድነት እንደ ነብር ዘሎ መከመር የለማ! ቂ…ቂ...ቂ.
ከዛ ምን አልባት ከአሥራ አንድ ወር ምናምን በኋላ… “ለምን ብቻችንን…” ምናምን ይባላል፡፡ ዕድሜ ለሦስት ብር…. ከሰፈር በሁለት አውቶብስ ወደሚኬድበት አካባቢ ጉዞ ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ… የሰፈር ሰው፣ የሂሳብ ቲቸር፣ የጓደኛ እህት…ምናምን እንዳያዩ ይፈራላ! እንደ ዘንድሮ… ወላጆች ራሳቸው እንትንዬው በር ላይ አድርሰው… “በሉ ይቅናችሁ…” ብለው የሚመለሱ የሚመስልበት ዘመን አልነበረማ!
ከተገባ በኋላ መጀመሪያ እንጨት ወንበሩ ላይ፣ ቀጥሎ ‘ቤዱ’ ጫፍ…ምናምን እየተባለ እየተዳኸ መሀል ይደረሳል፡፡ እናላችሁ… እንዲህ፣ እንዲህ እየተባለ ‘ዓይን ይበራል!’
(እነ እንትና…ያ በብርጭቆ ወረቀት ተፈግፍጎ ከፋይ ይመስል የነበረው የወታደር ጫማ እስኪወልቅ የሚፈጀው ጊዜ ትዝ ይላችኋል! እኛ የቻይና ሸራ እናደርግ ስለነበር እናውቀውም! ቂ…ቂ…ቂ…)
እንደ ዘንድሮ ቢሆን ከነጠላ ጫማ የማትሻል ጫማ ነገር ያለካልሲ ጠለቅ አድርጎ… በእጅ ‘ተፈታ፣ አትፈታ’ ብሎ መታገል አያስፈልግም፡፡ እግርን ወርወር ሲያደርጉት ጫማዋ ተስፈንጥራ ትወልቃለቻ! ጊዜ የለማ! ‘ሌላዋ ተረኛ’ ብሔራዊ ትያትር አካባቢ ‘ወክ’ እያደረገች ሊሆን ይችላላ!
የምር ግን…አለ አይደል…ዘንድሮ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በቃ ሰዉ ‘የናሽናል ጂኦግራፊ’ ዘጋቢ ፊልም ከልክ በላይ የሚያይ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ፊልሞቹ ላይ እንደምናያቸው አንበሶችና ነብሮች ‘ዘሎ ጉብ’ ሆኗላ!
የያኔው ‘ፕሮጀክት’ ከመስከረም እስከ ነሐሴ፣ የዘንድሮ ‘ፕሮጀክት’ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ!
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሰህ!” ለመባል ያብቃንማ!
የምር ግን…
አፈረሱት አሉ ውቤ በረሀን
እንደ እናት እንደ አባት ያሳደገንን፤
ዘፈን ብቻ መሆኗ ቀርቶ እውነት ሆነች አይደል! የፈረሰው ጣራና ግድግዳ ብቻ አይደለማ! የፈረሰው ‘ዘመን’ ነዋ!
አንዱንም በቴስታ ነበር ልማዳችን
አንዱንም በካልቾ ነበር ልማዳችን
ሚስት አገባንና
ልጆች ወለድንና
ፈሰሰ ሀሞታችን፤
ይባልበት የነበረበት ዘመን፡፡ የ‘ቤዱ’ ብቻ ሳይሆን የ‘ቡጢው’ ትውስታ ታትሞ የሚቀርበት ዘመን!
ዘንድሮ ልጄ ‘ሜሞሪ’ ሲባል የሚታውቀው የ‘ሞባይል ሜሞሪ’ ነው፡፡ ልክ ነዋ…መዝናኛዎቹ ከእነ ስማቸው እኮ…ቺቺኒያ!  እኔ የምለው እስካሁን ምነው ለቺቺኒያ ‘ፖፑላር’ የሆነ ነገር አልተዘፈነላትም!
ስሙኝማ…ቺቺኒያን ካነሳን አይቀር… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በአንዳንድ አውሮፓ አገሮች የቀለጡት መንደሮቻቸው ውስጥ የነገርዬው ‘ዊንዶው ሾፒንግ’ ነገር አለ አሉ፡፡ በቃ በ‘ዊንዶው’ በኩል አይቶ ‘በል፣ በል’ ካለው በ‘ዶሩ’ በኩል ይገባላ! አንድ ወዳጄ ሲነግረኝ…ሌሊቱ ሲገፋ ቺቺኒያ ውስጥ አንዳንድ ቤቶች በሮቻቸው እስከመጨረሻ ይከፈቱና እንትናዬዎቹ ፊት ለፊት በሚያስደነግጥ አቀማማጥ እንደ ‘ዓውደ ርዕይ’ አይነት… ብቻ ተዉት! ነገርዬው ግን… “እንደው የት እንደርስ ይሆን!” የሚያሰኝ ነው፡፡
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሰህ!” ለመባል ያብቃንማ!
እንግዲህ ደጃች ውቤ ምን አገር ሆነች
ያቺም ልጅ አገባች፣ ያቺም ልጅ ሄደች፤
ይባልበት የነበረ ዘመን፡፡
በዛሬዋ ቺቺኒያ… አለ አይደል… “ያቺም ልጅ አገባች፣ ያቺም ልጅ ሄደች…” ብሎ ነገር የለም፡፡ ልክ ነዋ…‘እነሆ በረከት’ በተባባሉ በአራተኛው ቀን… “ይቺን ልጅ የሆነ ቦታ አውቃታለሁ…” መሰለኝ… አይነት ነገር ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…
በአሥራ አምስት ዓመቷ ትገኝ በነበረች
እንደ ዳማ ከሴ መድኃኒት ነበረች፣
የተባለበት ዘመን አይገርማችሁም! ዘንድሮ ግን እንትናዬዎች በ‘ፊፍቲና በፊፍቲ ፋይቭም’…አለ አይደል…‘ዳማ ከሴ’ እየሆኑ ነው፡፡ ጊዜው ተለውጧላ! ቂ…ቂ…ቂ…  የተውኔትና የሲኒማ ሰዎች ‘የባለ ፊፍቲ ፋይቮቹን’ ዳማ ከሴዎች… አለ አይደል… የአሥራ አምስቷን ገጸ ባህሪይ ‘በእውን የተላበሱ’ ይሏቸው ነበር፡፡ (እነ እንትናዬ…ፊፍቲ ምናምን አልደረሳችሁም ብዬ ነው ‘እንደ ልቤ’ የምናገረው!)
እናላችሁ…
አደገች አደገች በቀሚሷ ሞላች
የእኔን የድሀውን አንጀት እየበላች፤    
አይነት ከወዲሁ ‘አፕሊኬሽን’ የሚገባበት ዘመን ነበር። እንደ ዘንድሮ ‘ሃራስመንት’ ምናምን የሚባሉት ቃላት ያልታወቁበት ዘመን ነበራ! እኔ የምለው… እነ እንትና… “ሽንኩርት ነች…” ይባል የነበረው ምንን ለመግለጽ ነው! ልክ ነዋ… እኛ ሽንኩርት የምናውቀው ሲከትፉት ዓይን እንደሚያቃጥል ነዋ!
እናላችሁ…ዘመን ሲለወጥ፣ ጊዜ ሲገሰግስ፣ ‘ኤጅ’ም እየጨመረ ሲሄድ…ክፉው ነገር እየቀረልን ደጉ ነገር እየተያዘ ይቀጥልልንማ! ጊዜ ክፉውን ጥሎ፣ ደጉን ይዞ ይቀጥልልንማ!
ለአድማሶች፣ እንደገና…እንኳን ለአሥራ አምስተኛ ዓመታችሁ አደረሳችሁማ!
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሰህ!” ለመባል ያብቃንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1767 times