Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 January 2012 12:21

የቤት ሠራተኞችን የሚያስቀጥረው ኤጀንሲ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
  • የደሞዙ ስኬል ከ400-2500 ብር ነው
  • የቤት ሠራተኞች ከቅጥር በፊት ሥልጠናና የጤና ምርመራ ያደርጋሉ
  • ካፌና ሬስቶራንቶች ከ8 ሰዓት በላይ በማሰራት የሠራተኞችን መብት ይጥሳሉ

በማኔጅመንት በዲፕሎማ የተመረቀችው ወ/ት ትሁት ክንፈሚካኤል ወደ ንግድ ሥራ ከመግባቷ በፊት በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥራ ሰርታለች - በፀሃፊነት፡፡ በአፍሪካና በአውሮፓ አገራት እንደኖረች የምትናገረው ትሁት፤ ወደ አገሯም ተመልሳ የሴቶች ፀጉር ቤት መክፈቷን ታወሳለች፡፡ ያኔ ነው በፀጉር ቤትዋ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች የማግኘት ችግር የገጠማት፡፡ ይሄንንም ችግሯን ወደ ቢዝነስ የመቀየር ሃሳብ ብልጭ አለላት፡፡ በውጭ አገራት ያየችውን ሥራ አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች ተመክሮም በአገሯ ላይ ለመሞከር ጥናት ጀመረች - ከሁለት ዓመት በፊት፡፡ በአገራችን የቤት ሠራተኞችን በአረብ አገራት የሚያስቀጥሩ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ቢኖሩም ለአገር ውስጥ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አለመኖራቸውን ያስተዋለችው ትሁት፤ ሙሉ ትኩረቷን አስተባብራ ወደ ስራው እንደገባች ትናገራለች፡፡

በእርግጥ የቤት ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሙያዎችና የትምህርት ዘርፎች የተመረቁ ሥራ ፈላጊዎችንም ለተለያዩ መ/ቤቶችና ድርጅቶች ታስቀጥራለች፡፡ በአዲስ አበባ ባካሄደችው ጥናት 10ሺ የሚደርሱ የቤት ሠራተኞች እንዳሉ ማረጋገጧን የገለፀችው ትሁት፤ “ብቃት የሰው ሃይል ኤጀንሲ” በሚል ስያሜ ያቋቋመችው ድርጅቷ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ከሦስት ወር እንዳስቆጠረ ትናገራለች፡፡የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ከወ/ት ትሁት ክንፈሚካአል ጋር በድርጅቱና በሚያከናውናቸው ሥራዎች ዙርያ ያደረገችው ቃለመጠይቅ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

የቤት ሠራተኞችን በአገር ውስጥ በማስቀጠር የናንተ የመጀመርያው ኤጀንሲ ይመስለኛል፡፡ ከቅጥር በፊት የምትሰጡት ስልጠና አለ?

ለቤት ሠራተኞች የስነ ምግባር ትምህርት እንሰጣለን፡፡ የጤናም ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ለቤት ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን በሌላ የሥራ ዘርፍም ለምሳሌ ለቢሮ ሥራ የሚያመለክቱትንም የምክር አገልግሎት እንሠጣቸዋለን፡፡ የቢሮ ስርአትን በተመለከተና ለአለቃቸው መስጠት የሚገባቸውን አክብሮት እናስተምራለን፡፡ አሠሪያቸውን ወይም ቀጣሪያቸውን ማክበር እንዳለባቸው እና ስራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ እንመክራለን፡፡ ለቤት ሠራተኞችም ይሔንን እናደርጋለን፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ወደ አረብ አገር ለመሔድ ልባቸው የተነሳሳ በመሆኑ የቤት ሠራተኞችን እንደልብ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ አብዛኞቹ ሠራተኞች ያልተረዱት ነገር የእኛ አገርም ከአረብ አገር ክፍያው ብዙም የማይራራቅ መሆኑን ነው፡፡ በዚያ ላይ በአገራቸው የደህንነት ስጋት ሳያድርባቸው፣ በራሳቸው ቋንቋ እየተናገሩ ጥሩ ደሞዝ አግኝተው መብታቸውም ተጠብቆላቸው መስራት ይችላሉ፡፡ እዛ እየሄዱ ብዙ ችግር፣ ድብደባ፣ በደል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የጤና እክል እየደረሰባቸው ነው የሚመጡት፡፡ ስለዚህ አገራቸው ላይ ቢሰሩ ይሻላቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ እኛ ጋ የሚያመለክቱ ሥራ ፈላጊዎች በምግብ ዝግጅት የተመረቁ ቢሆኑም ካፌና ሬስቶራንት ከመቀጠር ይልቅ መኖሪያ ቤት ይመርጣሉ፡፡ ክፍያው የተሻለ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ በእርግጥ የእኛ ስራ በቤት ሠራተኞች ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ለተለያዩ ድርጅቶችና መ/ቤቶች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተመረቁ ብቁ ሠራተኞችን እናቀርባለን፤ እናስቀጥራለን፡፡

አንዲት የቤት ሠራተኛ የስራ ቅጥር ፍለጋ ወደናንተ ኤጀንሲ ስትመጣ ሂደቱ ምን ይመስላል?

አንድ ሠራተኛ ወደ እኛ ስትመጣ የሚጠበቅባትን ግዴታ አስቀድመን እንነግራታለን፡፡ የጤና ምርመራ ማድረግና አሻራ መስጠት እንዳለባት እናሳውቃታለን፡፡ ኢንተርቪው  ትደረጋለች፡፡ ተያዥ የሚሆናት ሠው ስለ እሷ ምን ያህል እንደሚያውቅ እንጠይቃለን፡፡ ከዚያም ትምህርትና ስልጠና ይሰጣታል፡፡ የምግብ ሠራተኛ (አብሳይ) ከሆነች እንዴት ማብሠልና ማቅረብ እንዳለባት፣ ልጆች የምትይዝ ከሆነ እንዴት መያዝና መንከባከብ እንዳለባት፣ የፅዳት ሠራተኛ ከሆነች እንዴት ማፅዳት እንዳለባት ትምህርት እንሠጣለን፡፡ የቤት ሠራተኛ እፈልጋለሁ ብሎ በቅድምያ መጥቶ የሚመዘገበው አሠሪው ነው፡፡ ሠራተኛዋ ከመቀጠርዋ በፊት ግን ስንት ሰዓት እንደሚያሰሯት፣ የት እንደሚያስተኝዋት… ወዘተ አሰሪዎችን እንጠይቃለን፡፡ ከቅጥር በኋላም ክትትሉ ይቀጥላል፡፡ በየወሩ ሠራተኛውም አሠሪውም ጋር እየደወልን ችግር አለ ወይ ብለን እንጠይቃለን፡፡

የሠራተኞች መብት ጥሰት እንኳን በግለሰቦች ቤት በትላልቅ መ/ቤቶችና ድርጅቶችም እንደሚደርስ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የቤት ሠራተኞች መብታቸውን አውቀው እንዲያስከብሩ ምን ያቀዳችሁት ነገር አለ?

በተለይ ካፌና ሬስቶራንቶች እንደዚህ አይነት ጫና በሠራተኞቻቸው ላይ ያደርሳሉ፡፡  የሚከፍሉት ደሞዝ ግን ከሦስት መቶ ብር አይበልጥም፡፡ ደሞዝ የሚያሳንሱባቸው ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት ይበላሉ፡፡ ቲፕም ያገኛሉ በማለት ነው፡፡ እኛ ግን እንደዚህ አይነት የመብት ጥሰትና አግባብ ያልሆነ የሥራ ጫና ያሉባቸው ቦታዎች ሠራተኞችን አንልክም፡፡ ሁሉም ሠራተኞች በቀን ስምንት ሠአት መስራት እንዳለባቸው ነው የምናምነው፡፡ ድርጅትም ውስጥ ሆኖ የፅዳት ሠራተኞች ጠዋት ገብተው ማታ የሚወጡ እንዳሉ እናውቃለን - በቀን 12 ሰዓት ገደማ ማለት ነው፡፡ የቤት ሠራተኛን በተመለከተ… ለምሳሌ፡- ጠዋት ባለቤቶቹ ከመነሳታቸው በፊት እንዴት ሥራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ፕላን እንዲያወጡ እናደርጋለን፡፡ ቁርስ ሠርተው እስከ ምሳ ድረስ እንዲያርፉ፣ ከምሳ እስከ እራት ድረስ ደግሞ እንዲሁ እረፍት እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ አንዳንድ ሥራ የሚበዛበት ቤት ግን አለ፡፡ ሥራ መብዛቱ ችግር የለውም፡፡ ግን በሰራችው ልክ እንዲከፈላት እናደርጋለን፡፡ አብዛኞቹ አሰሪዎች ጨዋዎች ስለሆኑ የሰው ገንዘብ አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ ችግር አይፈጠርም፡፡ የእረፍት ጊዜያቸውን በተመለከተስ…

እንደ ቤቱ ነው፡፡ አንዳንዱ በየሳምንቱ ቅዳሜ ሔዳ እሁድ ትምጣ የሚሉ አሉ፡፡ በወር አንዴ የሚሉም አሉ፡፡ በወር አንዴም እረፍት እንድትወጣ የማይፈልጉ አሠሪዎችም ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ሲያጋጥም እረፍቷ ወደ ገንዘብ እንዲቀየርላት እናደርጋለን፡፡

ሥራ ፈላጊዎችን የምትቀበሉበት መስፈርት ምንድነው?

መስፈርቱ ጤነኛ መሆን ነው፡፡ አንዳንድ ሠዎች የሚጥል በሽታ ወይም የአዕምሮ ህመም ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ደግሞ እሳት ላይ ሊወድቁና በራሳቸው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ፣ ህፃን ልጅ ይዘው ሊወድቁም ይችላሉና እነዚህን ለመቅጠር ይከብዳል፡፡ ከነዚህ ችግሮች ነፃ ከሆኑ ግን በህክምና አረጋግጠን ሊቀጠሩ ይችላሉ፡፡

ለምሳሌ ከክ/ሀገር ወይም ከገጠራማ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡትን ትቀበላላችሁ?

እንቀበላለን፡፡ ጀማሪዎች ስለሚሆኑ ደመወዛቸው ሊያንስ ይችላል፡፡ የአንዳንድ እቃዎችን ወይም ማሽኖችን አጠቃቀም ላያውቁ ይችላሉ፡፡ በተረፈ እንደማንኛውም ሥራ ፈላጊ እየተመላለሱ ትምህርት እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ እኛ በተለይ ስነ-ምግባር ነው የምናስተምረው፡፡ ልጆች ፊት ምን መናገር እንዳለባቸው፣ ከአሠሪዎቻቸው ጋር እንዴት እንደሚግባቡ፣ ንፅህና እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ትምህርት ሠጥተን የሚችሉትን እና የማይችሉትን የሥራ አይነቶች ለአሠሪዎቹ አሳውቀን እናስቀጥራለን፡፡ በክፍያ ደረጃም የሚችሉና የማይችሉ በሚል ይለያያል፡፡

የቤት ሠራተኞች በቀጣሪ አባወራዎች ወይም በቤተሰቡ ወንድ አባላት የፆታ ጥቃት እንዳይደርስባቸው የምትወስዱት የቅድመ-መከላከል እርምጃ አለ?

አስቀድመን ያለውን ሁኔታ እንጠይቃለን፤ እንመረምራለን፡፡ አሠሪውን ስለመኝታዋ እንጠይቃለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ለሠራተኛዋ መጠንቀቅ የምትችልበትን ሁኔታ ለመንገር ነው፡፡ ሠራተኞችም እንደዚያ የሚመስሉ ሁኔታዎች (ምልክቶች) ሲገጥማችሁ ጥቃቱ ሳይደርስባችሁ በፊት ንገሩን እንላለን፡፡

የቤት ሠራተኞችን ደሞዝ ማነው የሚከፍላቸው? የናንተንስ የአገልግሎት ክፍያ ማነው የሚከፍላችሁ?

እኛ ከሰራተኛው ኮሚሽን አንቀበልም፡፡ አሰሪዎች ለሠራተኛው ከሚከፍሉት ከአንድ ወር ደሞዙ ላይ ሀያ በመቶ እንዲከፍሉ እናደርጋለን እንጂ፡፡

በእኛ በኩል የሚቀጠሩት የቤት ሠራተኞች ትንሹ ደሞዝ 400 ብር ሲሆን ኤምባሲና የተለያዩ የውጪ አገር ዜጐች ቤት ውስጥ የሚቀጠሩት እስከ 2ሺህ 500 ብር ይከፈላቸዋል፡፡

 

 

Read 3402 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 12:32