Monday, 02 March 2015 09:35

ታላቁ የአድዋ ድል

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(4 votes)

“የዓለም ታሪክ ተገለበጠ”

ከፈረሠኞች አሉ በልዩ
መሀል አገዳ የሚለያዩ፤
*   *   *
አየሁት አድዋን እንደ ኮከብ ደምቆ
የበቀለበትን ሠው መሬት ላይ ወድቆ፤
*   *   *
የአድዋ ሥላሤን ጠላት አረከሠው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሠው፤
*   *   *
ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ፤
*   *   *
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤
*   *   *
ታላቁ የአድዋ ጦርነት የአፍሪቃውያን ትውልዶች ታላቅ የነፃነት ተጋድሎ ነው፡፡ ሞትና ባርነት የተቀበሩበት፤ እውነትና ፍትህ አሸንፈው ህይወት የዘሩበት፡፡
ልክ የዛሬ አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ ዓመት፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም “ጥቁር ህዝብ ትልቅ ትል ነው ቅንቡርሥ ነው እንጂ ነፍሥ ያለው ሠው አይደለም” ብለው አፍሪቃን በሽሚያ የተቀራመቱ የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች ከመላው ኢትዮጵያ ዳር እስከዳር ተወጣጥቶ አድዋ በዘለቀ አንድ መቶ ሺህ የገበሬ ሠራዊት የተቆጣ ክንድ አድዋ ላይ ድባቅ ተመቱ፡፡
እንግሊዞች ፡- የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፤ ታላቅ የትውልድ ኃይል አፍሪቃ ውስጥ ተቀሠቀሠ…አሉ፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ፤ “ኢትዮጵያውያን ባበደ መንፈሥ ተዋግተው የአውሮጳን ቅኝ ገዢዎች አሸነፉ”…በማለት ፅፈዋል፡፡
በመቶ ሺህ ከሚሠላው የገበሬ ሠራዊት ሃያ ዘጠኝ ሺህ የሚሆነው ፈረሠኛ ነው፡፡ በአድዋ ገመገሞች ፡- በረቢ አርእየኒ በሸልዶ ተራራ በማርያም ሸዊቶ…የሚያብረቀርቅ ጐራዴያቸውን አየር ውስጥ እየቀዘፉ፣ የጋሻቸውን እምብርት ምድር ላይ እያጠቀሡ ሠማይ ደርሠው ምድር እየተመለሡ ከሚያሽካኩ ሠንጋ ፈረሶቻቸው ጋር እየፎከሩ እየሸለሉ….ያበጠውን የአውሮጳ ኃይል የዶጋ አመድ አደረጉ፡፡ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሠዓት ግድም የመጀመሪያዋ ጥይት ፈነዳች፡፡ የመጀመሪያዋ ጥይት የፈነዳችው ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሠዓት ግድም ነው የሚሉ የታሪክ ሊቃውንትም አሉ፡፡
በቅዱሥ ጊዮርጊስ በዕለቱ ቀኑ ማልዶ የተጀመረው ከባድ ጦርነት ከቀኑ አምሥት ሠዓት አካባቢ አሸናፊውን ወይንም ድል አድራጊውን ኃይል ለየ፡፡ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነው የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ሠራዊት ከኢትዮጵያ የተቆጣ ጀግና የገበሬ ሠራዊት ጋር ግማሽ ቀን እንኳን በመተጋተግ ለመዋጋት አልቻለም፡፡ ከቀትር በፊት በጄኔራል ባራቴሪ የሚመራው አውሮጳዊ ሠራዊት ተፍረከረከ።
ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ያለቀው አልቆ፣ የቆሰለው ቆሥሎ የተረፈው መሸሽ ሲጀምር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች እያሣደዱ ፈጁት፡፡ ከሚሸሹት መሃከል አንዱ ጄኔራል ባራቴሪ ነው፡፡ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተማርኳል፡፡ ሃምሣ ስድሥቱም የኢጣሊያ መድፎች በኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት ተማርከዋል፡፡ አብዛኞቹ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ ጥቂቶቹ ከጄኔራል ባራቴሪ ጋር ሸሽተው ከማምለጣቸው በቀር ከሞት የተረፉት ቆሥለዋል፤ ተማርከዋል፡፡
የምርኮ ጓዙን ወደ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ አምሥት መቶ አጋሠሥ አስፈልጓል፡፡ የኢጣሊያ ኮሎኒያሊስት ቁስለኞችን በማከምና በመርዳት፣ ምርኮኞችን በመመገብና ውኃ በማጠጣት እቴጌ ጣይቱ ብርቱ ኃላፊነት ተወጥተዋል፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከምሽቱ አራት ሠዓት ላይ ድል አድራጊው የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት እንዳማርያም (ቅድሥት ማርያም ቤተ ክርስቲያን) ተሠባሥቦ፣ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን የሠጠውን (ድል እንዲያደርግ የረዳውን) አምላክ አመሠገነ፡፡
በማግሥቱ የካቲት 24 ቀን 1888 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሠዓት ላይ ምርኮኞች በዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ ድንኳን አጠገብ እንዲያልፉ ተደረገ፡፡ ምርኮኞቹ ሲያልፉ በቆራጥ አፍሪቃዊ የገበሬ ጄኔራሎች የተመራው የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ሁሉ እየፎከረ እየሸለለ አሣለፋቸው፡፡ ከሚፎክሩትና ከሚሸልሉት አንዱ ፈረንሣዊ የጦር መሣሪያ ጠጋኝ ኦርዲናንስ ካፒቴን ነው፡፡
የኢጣሊያ ምርኮኞች ለአገራቸው ምድር ከበቁ በኋላ ጄኔራል አልቤርቶኒ በፃፈው መፅሐፍ ላይ…”እየፎከሩ እየሸለሉ ከነበሩት ጥቁር አፍሪቃውያን መሀከል አንዱ እንደኛው አውሮጳዊ ፈረንጅ ነው”…ብሎአል፡፡ ከአገሩ ከፈረንሣይ ለጦር መሣሪያ ጥገና ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ይህ ፈረንሣዊ ካፒቴን ኦርዲናንስ “አሁን ጊዜው የጦርነት ስለሆነ ወደ አገርህ ተመለሥ” ቢሉት ቢሠሩት አሻፈረኝ ብሎ ከእኛ ጋር አድዋ ድረስ የዘመተ ነው፡፡
አድዋ ላይ የተዋጋንባቸው ሠማንያ ሺህ አሮጌ ጠመንጃዎች በምሥጢር የተገዙትም ከፈረንሣይ አገር ነው፡፡ አርመናዊ የትውልድ ሥረ መሠረት ኢትዮጵያዊ መንፈሥና ነፍሥ ያላቸው ሠርኪሥ ቴሪዝያን፤ አሮጌዎቹን ሠማንያ ሺህ ጠመንጃዎች ከአውሮጳ ወደ አፍሪቃ አሻግረው በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ያሥገቡ ነጭ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡትም እኒህ ፅኑዕ የኢትዮጵያ ወዳጅና ነጭ ኢትዮጵያዊ ሠርኪስ ቴሪዝያን ሲሆኑ፡- ካስገቧቸው መኪናዎች አንዱ በአሁኑ ጊዜ አምስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ለላንቲካ ቆሞ ይታያል፡፡ “እንደ ሰርኪስ ባቡር” ተብሎ የተዘፈነው ስለዚህ ነው፡፡
 በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ የአውሮጳ ወራሪዎችን ያሸነፈችው በዋናው ወታደራዊ ውጊያ ብቻ ሣይሆን፤ ጥበብና ብልሀት በተመላ የአገር አስተዳደር ፖለቲካ የበላይነት - በወታደራዊ መረጃ ብልጫ  እና በሥልጡንና በበቃ ዲፕሎማሲያዊ አሠራር ጭምር ነው፡፡
ከሁለት መቶና ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት፡- የሶስት ማዕዘን ንግድ (Triangular Trade) በሚባለው የታሪክ ምዕራፍ፤ አውሮጳውያን ገዢዎች ጥቁር አፍሪቃውያንን በሠንሠለት አስረው እንደ ከብት እየነዱ በሴኔጋል በኩል ጐሬ ደሴት ላይ ያደርሷቸዋል፡፡ ሠባ ኪሎ ግራም ከመዘኑ ጥርሥና ጡታቸው ጤናማ ከሆነ፣ ወደ አሜሪካና ወደ ካሪቢያን ያሻግሯቸዋል፡፡ ይህንን መመዘኛ ካላሟሉ ለባህር አውሬ ይጥሉዋቸዋል፡፡ ጐሬ ደሤት ላይ እነዚያ ቁምጥማጭ ሠንሠለቶች ከዘግናኝ ትዝታዎቻቸው ጋር ዛሬም ድረሥ አሉ፡፡ ገዢዎቹ እያደር ለምን ጉልበታቸውን ብቻ አገራቸውንና ሀብታቸውን ጭምር ለምን አንዘርፍም ብለው ያሠቡ ይመስላል፡፡
ስለዚህ ነው በ1880ዎቹ መጀመሪያ ግድም ጀርመን አገር በርሊን ከተማ የተሠባሠበው የአውሮጳ ኮሎኒያሊስት ጥምር ኃይል አፍሪቃን በሽሚያ ለመቀራመት የወሠነው፡፡ ዕድል ከተባለ፤ እንዳለመታደል ሆኖ ለኢጣሊያ እኛ ደረሥነው፡፡
ቢያብጥ ቢደነድን ቢከመር እንደ ጭድ
ደንዳናውን እንዶድ ይቆርጠዋል ማጭድ፤
ያንን ለአያሌ መቶ ዓመታት ሲጠራቀም የኖረ እብሪትና እብጠት አድዋ ላይ በተንነው፡፡  ጥቁር ህዝብ ትልቅ ትል ቅንቡርሥ ሣይሆን ነፍሥ ያለው ሠው ከሠውም ሠው,ኧ ጀግና መሆኑን አድዋ ላይ ለዓለም ሁሉ ያሣየነው እኛ ነን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን።
ታላቁ የአድዋ ድል፤ በዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና አስደንጋጭ ለውጥ አምጥቶአል፡፡ ልክ እንግሊዞች እንዳሉት፡- “የዓለም ታሪክ ተገለበጠ! አዲስ የትውልድ ኃይል አፍሪቃ ውስጥ ተቀሠቀሠ፡፡
ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በአካል ባልተገኙበት የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ታላላቅ የአፍሪቃ የጐሣ መሪዎች ጉባኤ ላይ የነፃነት ተጋድሎውን እንዲመሩ ሊቀመንበር ተደርገው ተመረጡ፡፡ የኢጣሊያው ንጉሥ ኢማኑኤል ኤምቤርቶ የልደት ቀን የሀዘን ቀን እንዲሆን ተወሠነ፡፡ ጄኔራል ባራቴሪ ጦር ፍርድ ቤት ቀርቦ ማዕረጉ ተገፈፈ፡፡ ፍሎሬንስ ሚላን ሮም ናፖሊ…የተሠኙት የኢጣሊያ ከተሞች በመንግሥታቸው ላይ በተቆጡ “ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር” የሚል መፈክር ባነገቡ ሠልፈኞች ተጥለቀለቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ በየአገራቱ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎዎች በቁጣና በኃይል ተቀሠቀሡ…
ለአድዋ ጦርነ መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል አንቀፅ አሥራ ሠባት ነው፡፡
ከአዲስ አበባ በስተሠሜን ወደ ወሎና ትግራይ ስንሄድ,ኧ ከደሴ ከተማ አለፍ ብሎ ውጫሌ ከተማ ልንደርስ ስንል በስተግራ በኩል ከአምባሠል ተራራ ግርጌ ንጉሥ ይሥማ የሚባል ቦታ አለ፡፡ ከአድዋ ጦርነት በፊት የኢትዮጵያ መሪዎችና ቆራጥ የገበሬ ጄኔራሎች በዚህ ሥፍራ ነበሩ፡፡ የውጫሌ ውል የተደረገው እዚህ ቦታ ነው፡፡ የውሉ አንቀፅ አሥራ ሠባት የአማርኛ ቅጂ፡- “ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ ይቻላታል” ሲል፤ የጣሊያንኛ ቅጂው ደግሞ ፡- “ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ አለባት” ይላል፡፡ አማርኛው ፡- ከፈለገች…የሚል ሥሜት ይሠጣል፡፡ ኢጣሊያንኛው፡- ኢትዮጵያ ብትፈልግም ባትፈልግም ከሌላው አገር ጋር በኛ በኩል ነው መገናኘት ያለባት…ነው የሚለው። የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሣይሆን ልዕልናዋን ይነካል፡፡…ተገዙ፤ ለኢጣሊያ ተንበርከኩ!...ዓይነት መንፈስ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መሪዎች ለኢጣሊያው መልዕክተኛ የአንቀፅ አሥራ ሠባትን የኢጣሊያንኛ ቅጂ አስተካክል አሉት፡፡ በጅ አልል አለ፡፡
ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ ለጦርነት በተሠናዳ ልብ ንግሥት ባለቤታቸውን፡- “ጣይቱ መዘግየት አደገኛ ነው”…..አሉ፡፡ ጦርነት የግድ እና አይቀሬ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የኛ መሪዎች ጥበብና ብልሀት በተመላ የፖለቲካ አስተሣሠብ የኢጣሊያን ሸፍጥና ትንሽነት በልጠው ተገኙ፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ድል የተቀዳጀችው ውጫሌ ላይ በፖለቲካ ነው፡፡ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ ክተት አወጁ፡፡ መላው ኢትዮጵያ ዳር እስከ ዳር ተነቀነቀ፤ ተነቃነቀ፡፡
አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ ተጉዞ አድዋ ግድም እሚገኙ ገመገሞች የዘለቀው ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆን የተቆጣ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት የውጊያ መንፈሡ ሣይቀዘቅዝ አገልግሉ ሣይቀል…በፍጥነት ጦር መግጠም አለበት፡፡ ፈጥኖ ወደ ውጊያ መግባት፡፡ በፍጥነት ጦር ለመግጠም ፡- ወይ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ሠራዊት ወደኛ መምጣት አለበት፤ ወይንም ደግሞ እኛ ወደ ቅኝ ገዢዎቹ ምሽግ መሄድ አለብን፡፡ ወደነሡ ምሽግ መሄድ የሚያስከትላቸው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁናቴዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ ምሽግ ላለ አንድ ወታደር የሚመጠነው ሶስት አጥቂ ወታደር ነው፡፡ ሶስት ለአንድ፡፡ ከምሽግ መውጣት ብዙ መስዋዕትነት ያስከፍላል፡፡ የግድ ከሆነ ግን የግድ ነው፡፡
ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት ኢንቲጮ አካባቢ የተወለዱ ኢትዮጵያዊ ጐልማሣ ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት ምሽግ ተጠሩና ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነትና አደራ ተቀበሉ፡፡ ከእሣቸው ጋር ሌሎች ለኢጣሊያ መንግሥት የሚሠልሉ የኤርትራ ተወላጆች ፌርማቶሪዎች ባሉበት፡- በኢትዮጵያ ሠራዊት ውሥጥ የተሥቦ በሽታ መግባቱ፤ ሠራዊቱ ቀለብ መጨረሡ…በይፋ ተለፈፈ፡፡ ይሄንኑ እነባሻዬ አውአሎም የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ሠራዊት ወደሠፈረበት ቀጠና ዘለቁና የሆነውን ሁሉ ለጄኔራል ባራቴሪ ነገሩት፡፡ “ተስቦ በሽታ ገብቷል…ቀለብ አልቋል…፤ ስለዚህ፡- ጊዜው አሁን ነው” ብለው የልብ ልብ ሠጡት፡፡
ጄኔራል ባራቴሪ የካቲት 21 ቀን 1888 ሠራዊቱን እንዳያንቀሣቅስ ዝናብ ያዘው፡፡ በማግሥቱ የካቲት 22 ማምሻውን በጥድፊያ ተንቀሣቅሶ ወደ አድዋ ገሠገሠ፡፡ በባሻዬ አውአሎም ሀረጐት እየተመራ አድዋ ግድም እሚገኙ ጉድባዎች ጋ እንደደረሡ፣ ሊነጋጋ ሢል አውአሎም ቱር ብለው መሮጥ ጀመሩ። ባራቴሪ፡ “አውአሎም! አውአሎም!” ብሎ ተጣራ፡፡ “ግሥ! እስሀ ዝዋልካዬ አያውለና” (ወግድ! ዛሬ እኔ አንተን አያድርገኝ) ብለው ዘለው ራሥ አሉላ አባ ነጋ ምሽግ ገቡ፡፡ ባራቴሪና ወራሪ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት በተቆጣ የእሣት አፍ ውሥጥ መሠሥ ብሎ ገባ፡፡ ወራሪው የአውሮጳ ጦር በጥቁር አፍሪቃዊ የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል የእሣት ላንቃ ውሥጥ ተመሠገ፡፡ ጣሊያኖች ድል የተነሡት በዚህ መልኩ ነው፤ በወታደራዊ ሣይንሥ የመረጃ ብልጫ፡፡
የኢጣሊያ ምርኮኞችና የምርኮው ጓዝ ከብዙ ቀናት ጉዞ በኋላ አገሪቱ ርዕሠ መዲና አዲስ አበባ ደረሠ፡፡ በአውሮጳ የኢጣሊያ ሹማምንት፡- “ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ አረመኔዎች ስለሆኑ ምርኮኞቻችንን ይገድላሉ፣ ያሠቃያሉ ብልቶቻቸውን ይቆርጣሉ”…እያሉ የኢትዮጵያን ሥም ያጐድፋሉ። ኢትዮጵያ ሁለት ትጉህና ብልህ ዲፕሎማቶቿን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ወላጅ አባት ራሥ መኮንን ጉግሣን እና ግራዝማች ዮሴፍን አውሮጳ አህጉር አስቀምጣ የኢጣሊያን ሹማምንት ሥም ማጥፋት ትመክታለች፡፡ ግራዝማች ዮሴፍ፤ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛና በኢጣሊያንኛ…እየተረጐሙ የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አቋምና አድራጐት ለዓለም ሁሉ ግልፅ ያደርጋሉ፡፡
በመጨረሻ ኢትዮጵያ የኢጣሊያን ምርኮኞች ግብር አብልታ አሥጨፍራ አሥደንሣ በጅቡቲ በኩል ወደ አገራቸው ወደ ኢጣሊያ በላከች ጊዜ፣ የኢጣሊያ ሹማምንት የኢትዮጵያን ሥም የማጉደፍ ዲፕሎማሲያዊ የቅጥፈት ዘመቻ እርቃኑን ቀረ፡፡ ጣሊያኖችን ለአራተኛ ጊዜ በለጥናቸው፡፡ በፖለቲካ ብልሀት፤ በዋናው የጦር ጐራ ወታደራዊ ግጥሚያ፤ በወታደራዊ መረጃ ብልጫ እና በዲፕሎማሲ…በልጠን አሸነፍናቸው፡፡
ታላቁ የአድዋ ድል!!
ታላቁ የአድዋ ድል፡- የኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን የመላው አፍሪቃውያን ክብርና ኩራት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ብቻ ሣይሆን የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦችና የመላው ዓለም የእውነትና የፍትህ ወገኖች ሁሉ ክብርና ኩራት ነው፡፡
አየሁት አድዋን እንደ ኮከብ ደምቆ
የበቀለበትን ሠው መሬት ላይ ወድቆ፤
ብሎ የገጠመው መዝገበ ጥበብ የምለው ኢትዮጵያዊው ሠዓሊና ገጣሚ መዝገቡ ተሠማ ነው፡፡
ይሄ ፅሁፍ ለጀግኖች አባቶቻችን ክብር፤ ለጀግኖች ወላጆቻችን ክብር …የተሠዋ ይሆን ዘንድ በመደነቅ ተበርክቶአል፡፡ ለክብራቸው ይቁምልኝ፡፡
ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli-Deo.Gloria!

Read 5211 times