Monday, 02 March 2015 09:32

የዘንድሮው እውነታ “ግን” በምትል አፍራሽ ቃል የታጠረች ናት!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ይበልጣል ይበልጣል ነው፤ ምልክቱም (›)
ያንሳልም ያንሳል ነው፤ ምልክቱም (‹)
እኩል ነውም ራሱን የቻለ ነው፤ ምልክቱም (=)
የ“ግን” ጉዳይ ግን ሌላ ነው፡፡ ይበልጣል “ግን” እዚህ ጋ ደግሞ ያንሳል፡፡ ያንሳል “ግን” እዚህ ነጥብ ላይ ግን ማነሱን በልጦታል፡፡ ይኼ ነው የዘንድሮው እውነታ ወለፈንድነት፡፡ ወለፈንድነቱ ራስ ምታት ሆኖብኛል፡፡ የራስ ምታቶቼን አይነት በምሳሌ ማሳየት ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ “ግን” ምን ዋጋ አለው?  ምሳሌ ቢበዛ መፍትሄ አይገኝ፡፡ መፍትሄ ቢገኝስ? … መፍትሄ ቢገኝም ግን እኔ ማማረሬን አላቆምም፡፡
ማሳያ አንድ፡- ብሔራዊ ትያትር ቤት
(የትያትር ዋጋ ከ15 ብር ወደ 40 ከመሸጋገሩ በፊት የተፃፈ)
የትያትር ቤት መግቢያው ሰዓት እኔ በበሩ እያለፍኩ ከነበርኩበት ቅፅበት ጋር ባይገጣጠሙ ኖሮ “ባቢሎን በሳሎን”ን ገብቼ ባልታደምኩ ነበር፡፡ ትያትር ቤት መንፈሳዊ ቦታ መሆኑን ከዚህ ቀደም በአርቲስት አንደበት ሲመሰከር ብሰማም፣ ባለሙያ ለራሱ እውነት ሲል የሚሰብከው ፕሮፓጋንዳ ነበር የሚመስለኝ፡፡
ብሔራዊ ትያትር ቤት ብሔራዊ ሳይሆን አለማቀፋዊ የጥበብ መንፈስን መሸከም የሚችል ህንፃ ነው፡፡ ክፍያው አስራ አምስት ብር መሆኑን ሳይ “ግን” የምትለዋ የቅሬታ ቃል ተመልሳ  ነገሰችብኝ፡፡ ለጥበብ አፍቃሪዎች ጥበብን ከንግድ በማስቀደሙ የትያትር ቤት አስተዳደሩን አመሰገንኩ፡፡ “ግን ትያትር ቤቱ በምን አቅሙ ያድጋል? አዲስ ትያትሮች በምን በጀት ያስተናግዳል? … ግን ቢያንስ የማይረባ ፊልም በሀምሳ ብር ከሚያሳዩ ፊልም ቤቶች ይሻላል፡፡ በአነሰ ገንዘብ የበለጠ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ … “ግን” ስለመስጠቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ትያትሩ ከመጀመሩ በፊት ሳንድዊች ገዛሁ፡፡ ሳንድዊቹ የፆም ነው፡፡ ትያትር ቤቱ ብሔራዊ ስለሆነ ብሄራዊ የፆም ቀኖች መከበር አለባቸው፡፡ “ግን” መብላት የፈለግሁት የስጋ ሳንድዊች ነበር፡፡ በጥበብ አምልኮ አስራ አምስት ብር መክፈሌ ኪሴን ደስ ቢለውም፣ ለፆም ሳንድዊች አስራ አምስት ብር መጠየቁ አበሸቀኝ፡፡ ሁለቱ በምንም በኩል እኩል አይደሉም፡፡
ባቢሎን በሳሎን › (ይበልጣል) ከሩዝ ሳንድዊች!
“ግን” ከአስራ አምስት ብር ያነሰ ዋጋ ያለው ሳንድዊች የትም ሰፈር የለም’ኮ፡፡ የትያትሩን ሂሳብ ከሳንድዊቹ ማስበለጥ የአስተዳደሩ ፈንታ መሆን ነበረበት፡፡ በሳንድዊች መጠን እንዳይተመን ወይንም አንድ ፊቱን ትያትሩን በነጻ ጋብዞ የጥበብን ነፃነት ማስመስከር ይሻል ነበር፡፡ ጥበብ ከሳንድዊች መብለጡን የብር ተመን ጭራሽ ባለመጠየቅ … ማስረገጥ፡፡ ትያትር ይበልጣል ከሳንድዊች፡፡ ግን መብለጡን የሚያሳየው ያነሰ ብር በመቀበል ነው፡፡ “ግን” ይሄም ወለፈንድ ነው፡፡
ትያትሩን በተመስጦ ተከታተልኩት፡፡ ትያትረኞቹ ከእስክሪፕት በላይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን ከዚህ ቀደም በፊልም ወይንም የቴሌቪዥን ድራማ ላይ አይቻቸዋለሁ፡፡ ግን በመድረክ ላይ እንዳላቸው ብቃት አይደለም በእስክሪን ላይ ከዚህ በፊት የተረዳሁዋቸው፡፡ ትያትር ላይ በካሜራ የሚቀረፅም ኤዲት የሚደረግም የለም፡፡ ትክክለኛ ብቃት ነው፡፡ ትክክለኛ ብቃት ባለው ትያትር ቤት ውስጥ ትክክለኛ ብቃት ባላቸው ተዋንያን ሲከወን አየሁ፡፡ ሳንድዊቹን ከግማሽ በላይ መብላት አቅቶኝ በሶፍት ጠቅልዬ የማስቀምጥበት ቦታ አጣሁ፡፡ ትያትሩን “ግን” በሙሉ አጣጣምኩት፡፡ አጣጥሜ ስጨርስ ቆሜ ለአስደነቁኝ ሁሉ አጨበጨብኩ፡፡ እነሱም በጭብጨባ የሚረኩ መሰለኝ፡፡ ግን ጭብጨባ እህል አይሆንም፡፡ ሳንድዊች ትያትር እንደማይሆነው ሁሉ፡፡ ግን በእንደዛ አይነት ፍቅር ገጸ ባህሪዎቹ የሚተውኑት ጭብጨባ ፍቅር ቢሆን ነው፡፡ ፍቅር ደግሞ እርካታ፡፡
ግን እነዚህ አርቲስቶች በደንብ እንዲሰሩ አዲስ ትያትር ተፅፎ በአዲስ ትያትር ቤቶች ውስጥ አይታይም? ለምን በአገሩ ላይ አይስፋፋም፡፡ ትያትር › ከፊልም፡፡ “ግን” ፊልም ብዙ ብር በማስገባት ትያትርን ይበልጠዋል፡፡
ማሳያ ሁለት፡- መሰረተ ልማት
መብራት፣ መንገድ፣ ስልክ፣ መጠለያ አዎ ተስፋፍተዋል፡፡ መስፋፋት መጠናከር ነው፡፡ መጠናከር ከመዳከም ይበልጣል፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ መዳከም ከመጠንከር ስለማነሱ? መብራት እንደ ድሮ በወር እየሄድኩ መብራት ኃይል መክፈል ቀርቷል፡፡ ካርድ እገዛለሁ፤ የመቶ ብር ካርድ ከሶስት ወር በላይ ያስጠቅመኛል፡፡ “ግን” መብራት ብዙ ጊዜ የለም፡፡ ለምን እንደማይኖር ለማጣራት ያደረኩት ሙከራ በሙሉ ወደ መልስ ሳይሆን ወደ መቀየም ነው ያመራኝ፡፡ የመቶ ብር ካርድ ለመሙላት ስሄድ የሚቆረጠው ገንዘብ የተለያየ የሚሆንበት ምክኒያት አልገባኝም፡፡ አንዳንዴ ስድስት ብር፣ ሌላ ጊዜ ሀያ ሰባት ብር ከመቶው ላይ ታክስ ተብሎ ይቆረጣል፡፡ ምክንያቶች ግልፅ ስላልሆኑ ለግልፅ ነገርም ምክኒያት የመጠየቅ አቅሜን አጥቼዋለሁ፡፡
ከመሰረተ ልማት ሁሉ በጣም ያደገው ስልክ ይመስለኛል፡፡ ግን ያለ ስልክ ድሮ የማገኛቸው ሰዎች፣
 አሁን ስልክ እያለ የበለጠ የመራቃቸው ነገር ይገርመኛል፡፡ ሰውን በግንባር ከማግኘት በፌስቡክ ማግኘት መቀራረብ ነው ወይንስ መራራቅ? የሚለው ጥያቄ ራሱ ግልፅ አልሆነልኝም፡፡
መንገድም ተመሳሳይ ነገር አለው፡፡ መንገድ መዘርጋት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የምኖረው ድሮ ስማቸውን ሰምቼ በማላውቃቸው አካባቢዎች ነው፡፡ መንገድ መሰራቱ ጥሩ ነው ግን ከሰፈሬ አርቆኛል፡፡ መንገድ መሰራቱ ጥሩ ነው፤ ግን መንገዱን የሚያክል ፎቅ አብሮት ይገባል፡፡ መንገዱን እና ፎቁን የማናክለው እኛ ጥቃቅኖቹ ከአካባቢው መራቅ ተገድደናል፡፡ ቅርብ የነበርነው ስንርቅ፣ ራቅ ያሉት ደግሞ ቀርበዋል፡፡ አድገናል ግን ተራርቀናል፡፡ ተለውጠናል ግን ተጠፋፍተናል፡፡ በልፅገናል ግን ደስታ የለንም፡፡ ስልክ ሁላችንም አለን ግን ኔትወርክ አይሰራም፡፡ መብራት በአዳዲስ አካባቢዎች ተስፋፍቷል ግን ከነባሮቹ አካባቢዎች እየተቀነሰ ይመስል ፊተኞቹ ኋለኞች ሆነዋል፡፡ እድገት አለ! ግን …፡፡
ማሳያ ሶስት፡- ባንክ፣ ዴሞክራሲ እና ቢራ
ቅድም መፃፍ ስጀምር “ይበልጣል ይበልጣል ነው” ብያለሁ፡፡ ይህ ድምዳሜ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ሊያወዛግበን አይገባም፡፡ ለምሳሌ “ከእኩይ መልካም ይበልጣል” የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ላይ ለመጨባበጥ የምናቅማማ ከሆነ ስለ መብለጥ እና ማነስ ደረታችንን ነፍተን መናገር አንችልም፡፡
ወደ መልካም የሚደረስባቸው አማራጮች ግን እየተፎካከርን ለመለየት መጣር ግዴታችን ነው፡፡ ማን ከማን ይበልጣል? ብለን የምንወዳደረው ሁላችንንም ወደሚያስተሳስር ብልጫ ለመድረስ መሆን አለበት፡፡ ወደ ሰው ልጅ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት ወይንም ወደ ደስታ ለማምራት ማን ከማን ይበልጣል ተባብለን ልንሽቀዳደም እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን ከየትኛው የሰው አይነት የትኛው የበለጠ ነው ማለታችን አለመሆኑን ከፅንሰ ሀሳብ ጀምረን ማጣራት ይጠበቅብናል፡፡
ከህዝብ እና ከመንግስት ማን ይበልጣል?
ህዝብ ነው እንደምትሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ “ግን” … መንግስት ህዝብን ይቆጣጠራል፡፡ ህዝብ መንግስትን ይመርጣል፡፡ ግን መንግስት በህዝብ እኩልነት ስም የበላይ ይሆናል፡፡
ከግለሰብ እና ከማህበረሰብ ማን ይበልጣል?
አይታወቅም፡፡ እንደ ስርዓቱ መልሱ ይለያያል፡፡ እንደ መለያየቱ መጠን የዴሞክራሲ ትርጓሜ ራሱ አንድም ከመስፋቱ የተነሳ ማሟላት የማይቻል ይሆናል፤ አልያም ከመጥበቡ ብዛት ትንፋሽ  የሚያሳጣ ሆኖ ያርፋል፡፡ ከእዝ ኢኮኖሚ ነፃ ገበያ ይበልጣል? ከነፃ ገበያ እና በመንግስት ቁጥጥር ከሚነዳ ገበያስ?
ሁሉም ግልፅ አይደሉም፡፡  
አንድ መአከላዊ ባንከል ካለበት የደርግ ዘመን፣ ወደ ብዙ የግል ባንኮች ዘመን ተሸጋግረናል፡፡ እንደ ባንኮቹ ሁሉ ከሜታ እና ከጊዮርጊስ ወደ አንበር እና ዋልያ ቢራ ዘመንም ደርሰናል፡፡ ባንኮቹ የብሄር መዋቅር ያላቸው ስለመሆናቸው ይወራል፡፡ “እንትና ባንክ የእንትኖች ነው … እንትና ባንክ አክሲዮን ለመግዛት እንትን መሆን ይኖርብሃል” … ወዘተ፡፡
በአጭሩ እንትን ባንክ አገልግሎቱ የበለጠ የሚሆንላቸው ለእነ እንትና ነው እንደማለት ነው፡፡ አገልግሎቱን ሳይሆን የማንነት እምነቱን ግንዛቤ ውስጥ ይዞ ነው አገልጋዩ የሚጠጋው፡፡
ምርጫ = ብሔር
ቢራም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአንድ ቢራ አፍቃሪ አንድ እንጂ ሌላ ክለብ አይደግፍም፡፡ ክለቡም ቢራውም የመጠጥ ምርጫውም ከማንነት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ከግለሰብ እና ከማህበረሰብ ማን ይበልጣል? ከተባለ በወቅታዊ ሁኔታ መልሴ “ብሔር” የሚል ይሆናል፡፡
ዲሞክራሲ ወደ ግለሰብ አልወረደም፡፡ ግን ዲሞክራሲ በግለሰቦች ምርጫ እና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አልነበረም ወይ?
ከቅርብ ጓደኛዬ አንዷ ባንክ ያስቀመጠችውን ብር ጠቅላል ልታወጣ ስትል “ግን ሁሉንም ባታወጪው ይሻላል” የሚል ምክር ተሰጣት፡፡ “ግን” የባንክ ሳይንስ ውስጥ እንዲህ አይነት ጣልቃ ገብነት ይፈቀዳል እንዴ? በሌላ ጊዜ እቺው ልጅ ከተረፋት ሶስት መቶ ብር ሁለት መቶውን ልታወጣ ስትል፣ የባንኩ ሰራተኞች እንደሳቁባት ነገረችኝ፡፡ እንግዲህ ባንኩን የመሰረተው ብሔር ገንዘብን በማጠራቀም እንጂ ባለመቀነስ የሚያምን ሊሆን ይችላል፡፡ … ግን ለግለሰቧ ደንበኛ ይህ እምነት ምን ያገባታል? በፈለገችው ጊዜ ገንዘቧን ማስቀመጥ፣ በፈለገችው ጊዜ ማውጣት የምትችለው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደው ባደጉ ልጆች የተመሰረተ ባንክ ስራ የጀመረ ዕለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ግን ይኼ ሁሉ ነገር ከባንክ ሳይንስ ጋር ምን አገናኘው? የባንክ ሳይንስ ከብሄር ሳይንስ ጋር ከተደባለቀ አዳዲስ አባዜዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
የብሔር ዴሞክራሲን ከግለሰብ ነፃነት ጋር ለማነፃፀር፣ ቢራ እና ባንክን እንደ ምሳሌ ማየቴ ስህተት አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም ከዛም በላይ ገፋ ማድረግ ይቻላል - የቁርኝት ሰንሰለቱን፡፡ እንትና የተወለደው የት ነው? ያደገውስ … የሚለው ጥያቄ መልስ ካገኘ … የሚጠጣውን ቢራ፣ የሚቆጥብበትን ባንክ፣ የሚገዛውን ጋዜጣ … እና የሚያደምጠውን ሀገርኛ ዘፈን ማወቅ ይቻላል፡፡
ማን ከማን ይበልጣል?! የሚለው መንፈስ ሁሉም የሰው ልጅ  በተለይ ደግሞ የሀገር ልጅ አንድ እንደሆነ በታመነበት ሁኔታ መልካም ፉክክር ነው፡፡ ማን ከማን ይበልጣል ብሔርን ወይንም በተለያየ የመድሎ እርከን ላይ ተቀምጧል ተብሎ የሚታሰብን ማህበረሰብ መሰረተ ያደረገ ከሆነ … “ግን” ጥርጣሬ ሳትጠራ “አቤት” ትላለች፡፡
“ሀገር እያደገ ነው፣ ሰው በተሻለ ነፃነት እየሰራ ነው፣ ብዙ አማራጮች ተፈጥረዋል”
… “ግን”
ማሳያ አራት፡- እንጀራ
ስም መደብለቅ (Name dropping) አይሁንብኝና በቅርቡ አዳም ረታ ስምንተኛውን መፅሐፉን ለማስመረቅ አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት ከእሱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የመገናኘት እድል አግኝቼ ነበር፡፡
እና ምን ይጠበስ? ካላችሁኝ …. ጥብስ ሳይሆን በሥነ-ፅሁፉ ላይ አዘውትሮ የሚጠቅሰውን እንጀራ ፍርፍር በፍላጎት አዝዞ “ግን” መመገብ አቅቶት ሲተወው ታዝቤ ነበር፡፡ እንጀራን “ሜታፎር” አድርጎ ድርሰቱን በእንጀራው ፍልስፍናው ውስጥ እየፈጠረ ያለው ደራሲ፤ እንጀራ ቀርቦለት ሳይበላ “በቃኝ” ሲል ትንሽ ብገረምም ችግሩ ያለው የት እንደሆነ ወዲያው ሳይገባኝ አልቀረም፡፡
ቢገባኝም ለእሱ “ግን” አልጠቀስኩበትም፡፡ አዳም ስለ እንጀራ የማይለወጥ ታሪክ እና ቅርፅ ሲጨነቅ፣ እንጀራ መበላሸቱን ልብ አላለም፡፡ እንጀራ ተበላሽቷል፡፡ መበላሸቱን በይፋ ያወጀው የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ነው፡፡
በፊት፤ ችግሩ፤ የጤፍ ዋጋ ጣራ መንካቱ ጤፍን ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች ጋር እየቀላቀሉ ስለሚጋግሩት ይመስለኝ ነበር፡፡ ጤፍን ከሩዝ … ከበቆሎ ወዘተ፡፡ ነገሩ “ግን” እንደዛ አይደለም፡፡ እረፍት ያጡ የእርሻ መሬቶች ላይ ያለ አፈር ሚኒራሉ ስለተሟጠጠም አይደለም፡፡ ወይንም በእርሻ መሬቶች ላይ የሚፈሰውም ማዳበሪያ አይመስለኝም… ለእንጀራው መበላሸት አስተዋፅኦ ያደረጉት፡፡
የእንጀራውን መበላሸት እኔ የማውቀው ወደ ውስጥ ሲገባ በሚፈጠረው ስሜት ነው፡፡ ተበልቶ ወዲያው ከሆድ ይጠፋል፡፡ ወይንም በጭራሽ     አይፈጭም፡፡ በተለይ ከሽያጭ የምገዛቸው እንጀራዎች ከጣዕማቸውም፣ ከሽታቸውም ብዙ እንከን ስላለባቸው አግልያቸዋለሁ፡፡ ምናልባት አዳም ላይም ይህንኑ ነገር ሳይሆን አይቀርም የታዘብኩት፡፡
“ግን” እንጀራ ይኼንን ያህል የአበሻ ማንነት አርማ ከሆነ፣ እንጀራው እየወደቀ አበሻ ቢነሳ… አነሳሱ ጥርጣሬ ያዘለ አይሆንም? … ድሮ እንጀራ ተበላሸ ማለት ሻገተ ነው፡፡ አዲሱ አበለሻሸት አዲስ ትርጓሜ ያስፈልገዋል፡፡… ግን እንጀራ ከተበላሸ ምን እንብላ? … ኢንዶሚን?!
አምስተኛ ማሳያ፡- ሴቶች
ልዩነቶችን እኩል ማድረግ እንጂ አንድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ሴቶችን እኩል ለማድረግ የተሰሩት ስራዎች ጥሩ ናቸው፡፡ ግን ሴቶችን ሀያል ማድረግ ማለት ሁሉንም ሴት ማድረግ ስለአለመሆኑ መጣራት ይገባዋል፡፡ ልክ መንግስን የህዝብ ምርጫ ለማድረግ ህዝብን በመንግስት ካድሬዎች እና አፈቀላጤዎች መሙላት እንደመሰለው እንዳይሆን ማለቴ ነው፡፡
ልዩነቶች በእኩል ሁኔታ ቦታ መቀያየራቸው (ማለትም እናት የመሰሉ አባቶች እና አባት የመሰሉ እናቶች) መፈጠራቸው ለልጆቻቸው የተሻለ ወላጅነትን የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበት ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ “ግን” የታመነበት በማን ነው? … እናቶቻችን ስኬታማ ሴት እንዳልነበሩ በራሳቸው አንደበት ከሚናገሩት ይልቅ የእነሱ ባልሆነ እምነት የሚናገሩላቸው ተደማጭነት አግኝተዋል፡፡
ተፈጥሮ ይበልጣል ወይንስ ተሞክሮ? …
ተፈጥሮን የሚለውጡ ተሞክሮ እንዲጸድቅ የተደረገው ለሴቶች የተሻለ እድል እንዲሰጥ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ “ግን” ተሞክሮውን ፖሊሲ ያደረጉት ሰዎች ሴቶች እንዳይደሉ ይሰመርበት፡፡ “አንኳሩ የስልጣን ስፍራ ላይ የተቀመጡት አሁንም ወንዶች ናቸው፡፡ ሊቃነ ስልጣናቱ ለሚስቶቻቸው አሁንም የበላይ ናቸው፡፡ ለሚመሩት ህዝብ ያስተካከሉት ተሞክሮ በእነሱ ዘንድ መስራቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ የተስፋዬ ገ/አብ መፅሀፍ ስለነዚሁ ቁንጮዎች የሚለው ነገር እውነት ይሁን ሀሰት የሚያውቁ ይመዝኑት!
የተፈጥሮ ህግን ለማስተካከል መስራቱ … የወንድ ትምክህተኝነትን በሴት እኩልነት ለማስተካከል መጣሩ ተገቢ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ “ግን” እኩልነቱ ከላይ ነው መጀመር ያለበት፡፡ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሚስቶቻቸውን ከጓዳ አውጥተው ስፍራውን ይልቀቁላቸው፤ ከዛ ከእነሱ አርአያነት የተማረ ህዝብ በተግባር ይከተላቸዋል፡፡ ግን እውነት ተፈጥሮን ተሞክሮ ይቀይረዋል? … “ተፈጥሮን ተሞክሮ ወይ ያጣምመዋል ካልሆነ ያሳምፀዋል” ብለው ነው ያስተማሩን፡፡

Read 1935 times