Monday, 02 March 2015 09:31

ኮረዳዋ ወራቤና የስልጤው ደራሲ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


የስልጤ ዞንዋ ወራቤ ከተማ እንደ አገሩ በሠርጓ ዋዜማ ኮሶ ጠጥታ፣ ለሠርጓ የተዘጋጀች ኮረዳ መስላ ታየችኝ፡፡ ከአራትና አምስት ዓመት በፊት ያየኋት ጨቅላዋ ወራቤ አይደለችም፡፡ ዛሬ ጡቶችዋን ደረትዋ  ላይ ቀስራ፣ባል በውበት ፉጨት፣ በነፍስ ዜማ የምትጠራ ትመስላለች፡፡ ደምዋ መፍለቅለቅ፣ አይኖችዋ መናጠቅ እየጀመሩ ነው፡፡ ገና አሥር ዓመቷን በቅርብ ያለፈችው ወራቤ ስሟ ከየት መጣ? ከብዙ ሰዎች ድምር ሃሳብ ተጨምቆ የተገኘው የስልጤ ታሪክ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- ወራቤ ቀድሞ “ወርኮ” ነበር አንድ ስሟ፡፡ ወርኮ ደግሞ የገበያ ስም ነው፡፡ ገበያ ደግሞ የእንጀራ ምጣድ እንደ ማለት ነው - በኔ ትርጓሜ፡፡ እና በእንጀራ ወይም በዳቦ ስም ጠሯት፡፡ ለነገሩ ሕይወት ሁሉ በእንጀራ ምጣድ ለእንጀራ ተሽከርክራ አይደል ጣዕምዋን መጥጣ፣ ሥጋዋን ቆርጣ ስታበቃ፣ ከምህዋሩ የምትወረወረው!
እናም “ወርኮ” ያኔ ጥንት በደቡብ እስከ ከፋ፣ ከደቡብ ምዕራብ እስከ መተማ ለሚያልፉ የሲራራ ነጋዴዎች መተላለፊያ ነበረች፡፡ በጊዜው ጥጥ፣ ቡናና ዝንጅብል ታመርት ነበር፡፡ ቅመሞችዋም የብዙዎችን ልብ ነጥቀዋል፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ የባሪያ ንግድም የጦፈባት ገበያ ነበረች፡፡
“ወርኮ” የሚለው የስልጤኛ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “ዞር በል!” ወይም መክቶ መላሽ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ትርጉም የተሰጠው ደግሞ በሥፍራው የነበረውን ጦርነትና የጦርነቱን ጀግኖች በማሰብ ነው፡፡ ለወቅቱ ድል ደግሞ ስንኞች ተቋጥረው፣ በዜማ ተንቆርቁረዋል ይባላል፡፡ ልጃገረድዋ የእህል ወፍጮ ላይ መጇን ወደፊትና ወደኋላ እየገፋች፣ ጐረምሳው በዜማና በፉጨት በአየር ላይ አናኝቶታል፡፡
በስልጢኛ - “በሶመን ስላት
በመህሪባ ገባት
ኡሀም ባፍጥር ሳት
ለኩተሬ ታት
መጣን በለፋት
ሚን ቢቾ ደረሰ፣ ሚሽቱም ቲጃጄት”
በአማርኛው - “በፆም በሶላት፣
        በመግሪብ ሶላት ወቅት
ከኩተሬ በላይ፣ ጀግና መጥቷል አሉ
የቁርዐን ተማሪ (ደረሳ) ብቻ ሳይሆን ሴቷም ተዋግታለች፡፡
(ትርጉም - ከመጽሐፉ ደራሲ ከይረዲን ተዘራ)
ሌላኛው ትርጓሜ - በስልጢኛ ቋንቋ “ወራባ” ማለት ጅብ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ ጦረኞች ወደ ሌላ አካባቢ ወረራ ሲያደርጉ ጅብ ናቸው እንዴ? ለማለት “ወራባ” ሲሉ፣ በጊዜ ሂደት ያ - የጦር አውድማ፣ ያ - የጦረኞች ድንኳን “ወራቤ” ተብሎ ስያሜዋን ቀየረው ይላል - የስልጤ ታሪክ ፀሐፊ የከይረዲን ተዘራ መረጃ፡፡ ሌላው ደግሞ “ወረብ” ከሚል ቃል የመጣ ነው ይላል፡፡
የአሁንዋ ወራቤ አቀማመጧ ለተፋሰስ አመቺ ነው፤ ለአይንም የሚማርክ መልክዓ ምድር አላት፡፡ በተለይ ኮምፕሬሲቫል ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሏ ታላቅ ግርማ አጐናፅፏታል፡፡ የዞኑ የባህል ማዕከልም በሳር ቤት ቅርፅ፣ አሣምረው ስለሰሯት በእጅጉ ታባብላለች፡፡ ነፍስ ትማርካለች፡፡ ቀለም ቅብዋም የባህል ልብሱ ላይ መሠረት ያደረገ ስለሆነ፣ ደግና ተገቢ ትርጓሜ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ያንን ቀለም በሆቴሉም፣ በካፌውም በሱቁም ላይ ማድረግ ግን አንዳች የውበት መፋዘዝና መንዛዛት ያመጣል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡
ወራቤ ሲጋጌጡ ይመላለጡ አይነት ለዛ ቢስነት ውስጥ እንዳትገባ ከወዲሁ ለውበቷ መጠንቀቅ የሚያሻት ይመስለኛል፡፡ አገር ምድሩን ተመሳሳይ ማድረግ ሌላው ቢቀር ቦታን ለማወቅ ያደናግራል፡፡ በዚያ ላይ ለዓይንም መሰልቸቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡ በተረፈ ብቅ ብቅ ያሉት አዳዲስ ህንጻዎች የወራቤ ጌጦች መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በርካታ ገልባጭ መኪናዎች ወደ ወራቤ እንደሚተሙ አስተውያለሁ - አሸዋ ለመጫን፡፡ አሸዋ የተፈጥሮ ሃብቷ ነው፡፡ ለሆነለት እኮ አሸዋም ወርቅ ነው፡፡  
የወራቤና የስልጤ ልማት ጥሩ መልክ ነው ብዬ የምጠቅሰው፣ ከየወረዳው የተውጣጡ ጐበዝ ተማሪዎችን ማደሪያ ቤትና ምግብ በማዘጋጀት ለማስተማር መትጋቷን ነው፡፡ ይህ ለነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ነው፡፡ አቅም በማጣት እንደ እሣት የሚነድዱ፣ እንደ መብረቅ ጨለማን የሚሰነጥቁ ወጣቶች፣ በእንጀራ ታንቀው እንዳይቀሩ መታደግ ያኮራል፡፡
በሠሞኑ የወራቤ ጉዞዬ ዋነኛው ትኩረቴ የነበረው አንድ የስልጤ ጐልማሳ ነው፡፡ ከድር አብዱ ይባላል፡፡  ትንሽ የሚያደናግር ሕይወት፣ የሚጐፈንን ትዝታ አለው፡፡ ወጣትነቱን በቀለም ቤንዚን ነድዷል፣ ጐልማሣነቱም አመድ አልዋጠውም፤ ዛሬም የጥበብ ፍም ነው፡፡ ጠጋ ላለው ይሞቃል፣ ላዳመጠው ደማቅ የነፍስ ዜማ ነው፡፡ ከድር አብዱ ከረጅም ዓመታት በፊት የጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪ ነበር፡፡ ሦስተኛ ዓመት ላይ አንድ መምህር “እግርህ ያነክሣልና መማር አትችልም” ብሎ እንዳባረረው ይናገራል፡፡  ከድር በውጤቱ አይታማም፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባው ከአንድ “B” በስተቀር “A” ዎችን ደርድሮ ነው፡፡
ግን ምን ያደርጋል-- በአንድ መምህር የተነሳ ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ ወደ ቀዬው ተመልሶ እርሻ ጀመረ፤ ጥሩ ገበሬ ወጣው፡፡ በተለይ ደግሞ በርበሬ ያመርት ነበር፡፡ ግን ብስጭቱ ሲቀሰቀስ መለኪያን ባልንጀራው ያደርጋል፡፡ የሕይወት ፉንጋ ፊት ሲያስጠላው፣ መለኪያ ውስጥ ውበት ያስሳል፡፡  
ከድር ላለፉት 20 ዓመታት ከትምህርት ጋ ከእነአካቴው አልተለያየም፡፡ ተማሪዎችን ያስጠናል፣ ያስተምራል፡፡ እሱ ያስተማረው ተማሪ ደግሞ ውጤቱ የታወቀ ነው፡፡ ስለ ዕውቀቱ ሀገር ይመሠክርለታል፡፡ ከድርን ከዚህ ቀደም አግኝቼው አውግቶኝ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከረጅም ዓመታት በኋላ ዳግም አወጋን፡፡ አሁን ከ1ኛ-8ኛ ክፍል የስልጢኛ ቋንቋ ማስተማሪያ መርጃ፣ ከ9-10ኛ ክፍል ማስተማሪያ መርጃ፣ በተጨማሪም ከ5-12ኛ ክፍል የስልጢኛ ቋንቋ ማስተማሪያዎች አጋዥ መጻህፍት አዘጋጅቶ አውጥቷል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከ150 በላይ ገፆች ያሉት ልቦለድ መጽሐፍ በስልጢኛ ቋንቋ ጽፏል፤ የግጥም ጥራዞችም አሉት፡፡ ግን አሁንም ትራሱ ሥር ሀሳብ እየበላቸው፣ የእርሱንም ሃሳብ እየበሉ ቀርተዋል፡፡
ከድር መፃፍ ብቻ አይደለም የሚወድደው፣ ማንበብ ሕይወቱ ነው፡፡ የስልጢኛ ቋንቋ አጋዥ ማስተማሪያዎችን ለመፃፍ በርካታ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መፃሕፍትን አንብቧል፡፡ ስለ ግጥም ሲፅፍ ዘይቤዎችን፣ ቋንቋ አጠቃቀምን፣ ምትንና ምጣኔን በወጉ አውቆ ነው፡፡
ከፃፋቸው ግጥሞች ውስጥ ጥቂት ስንኞችን ወስጄ በወዳጄ መሐመድ ሁሴን ትርጉም ላስነብባችሁ፡ -
ታወሠኝ ፍስኩ ቀን ደምቆ የማለዳው፤
የቄጠማ ምንጣፍ ለብሶ
ሽታው ሲናኝ እልፍኝ ጓዳው
ክትፎ ዓይቡ በየአይነቱ፣
ፌሽታ ሲሆን ተሰብስቦ ጐረቤቱ፣
ከእናት ጋራ መደሰቱ!
ብዙ ግጥሞቹ የፍቅር፣ የማህበራዊ ሕይወት፣ የባህል - ጣዕም ያጠቀሱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ  ተማሪዎችን ሲያስጠና የትምህርት ዓይነት መርጦ አይደለም፤ ሁሉንም ነው የሚያስተምረው፡፡ ፊዚክስ፣ ሂሣብ፣ እንግሊዝኛ፣ አማርኛ… ሁሉንም ያስጠናል፡፡
ከድር ባለፈ ነገር መፀፀት የሚወድ ሰው አይደለም፡፡ በትምህርቱ ያሰበበት ድረስ ባይገፋም ሌሎች ልጆች ላይ በሚዘራው ዘር ደስ ይሰኛል፡፡ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ፈጥሬያለሁ ይላል፡፡ የሚገርመው ግን በዚህ ዘመን አንድ ገጣሚና ደራሲ ብቅ ያለለት የስልጤ ሕዝብ፣ የዚህን አንድ ዕንቁ ድምጽ መስማት ያለመቻሉ ነው፡፡ ለሰዎች ጤንነት፣ ማሕበራዊ ደህንነት ያንን ታላቅ ሆስፒታል ያሠራ ሕዝብ፣ እንዴት አንድ የጥበብ ሻማ የሆነውን ጌጡን የመከራ ንፋስ እያጣፋ ብርሃኑን ሊነጥቅ ሲታገል ዝም ይላል? ይህ ነው ግራ አጋቢና አያዎ (paradox) የሚሆነው፡፡ ይህን ምጡቅ ምናብና አእምሮ የታደለን ወጣት፤ ዞኑ በርቀት ትምህርት እንኳ የተሻለ ሥልጠና እንዲያገኝ ሊረዳው እንዴት አልቻለም? ከዚያ ባለፈ የአካባቢው ተወላጆች ይህችን ቀላል ጥያቄ እንዴት መመለስ አቃታቸው? እንደ እኔ እንደ እኔ ግን ከድር አብዲ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለታላቅ ሀገራዊ ጥቅም የሚውል አቅም ያለው ብርቱ ሰው ነው፡፡ በሕይወት እያለ ሊጠቀሙበት የሚገባ ስለሆነም የእርሱ ጉዳይ ሁላችንንም ይመለከታል ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ንፋስ የሚያወላግደውን ብርሃን፣ መስታወት ሆነን ከመጥፋት እንታደገው፡፡  

Read 5020 times