Print this page
Saturday, 14 January 2012 12:07

የሀዲስ ዓለማየሁ ተረቶች “እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ”

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(2 votes)
  • ሦስቱ ልቦለዳዊ  ተረቶች ከወጡበት ዘመን አንጻር ሲፈከሩ ምን ይላሉ?
  • በብርሃኑ ገበየሁ ጥናታዊ ስራ የሀዲስ ተረቶች ለምን ይሆን ያልተካተቱት?

ፈር መያዣ-  የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ግንባታ ሲቋቋም መጠሪያውንና መታሰቢያነቱን ለታላቁ ደራሲያችን ለሀዲስ አለማየሁ ማድረጉን ምክንያት በማድረግ ባለፈው  ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ በሀዲስ ተረት ተረት የመሰረት መጽሐፍ ላይ መጠነኛ ሂሳዊ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ እንዲሁም ነፍሱን ይማረውና ታዋቂው የስነግጥም መምህርና የባህል አጥኚው ብርሀኑ ገበየሁ (ረዳት ፕሮፌሰር) በህይወት ቢኖሩ “ልቦለድ እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ” በሚል በሀዲስ ስራዎች ላይ ባቀረቡት ጥናታቸው ፣ ‹‹ተማሪዎቹ የጠየቋቸውን ጥያቄ የሚመልሱበት መድረክ ይሆን ይሆን?›› የሚል ትሁት ጥያቄ አንስቼ፣ ሂሳዊ መጣጥፉን ለተወዳጁ የስነጽሁፍ መምህር ለብርሀኑ ገበየሁ መታሰቢያ እንዲሆንልኝ ማለቴም ይታወሳል፡፡ ዛሬም ከሳምንት የሚቀጥለው ጽሁፍ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሶስቱ ልቦለዳዊ ተረቶች ከወጡበት ዘመን ጋር እየተፈካከሩ ሲፈከሩ

የሀዲስ አለማየሁ፣ “ተረት ተረት የመሰረት” መጽሐፍ፣ መጠነ ርዕያቸው (scope) በሚፈቅደው መሰረት፣ ከሌሎች የልቦለድ መጽሐፎቻቸው ያልተነሱ፣ እንደውም፣ ለሌሎቹ መነሻ የሆኑ፣ ረቂቂ ፍልስፍናዎች የታጨቁባቸው፣ በሌሎቹ ሥራዎች ላይ ጠንከር ያለ አሻራ ያሳረፉና ለደራሲው የአፃፃፍ ስልት መለዮ እስከ መሆን የደረሱ ተረቶች የያዘ፣ በወጉ ሊፈተሽ የሚገባው የላቀ ሥራ (masterpiece) እንደሆነ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

እስከ አሁን የተነሱትን ሀሳቦች ለማስረዳት፣ በብርሃኑ ጥናት የተገኙ የርዕዮተ ዓለም ማሳያ የሆኑ ጭምቅ ፍልስፍናዎችን ተረቶቹም እንደያዟቸው ለማስረገጥ፣ የተወሰኑ ተረቶችን መርጦ በማንበብና በዘመናቸው ከተከሰቱ ከተለያዩ ሁነቶች ጋር እያገናዘቡ በመፈከር ማስተንተን ይቻላል፡፡ በዚህ ጥናትም የተባሉትን ሀሳቦች ያስረዳሉ የተባሉ 3 ተረቶች ተመርጠዋል፡፡ በርግጥ በዋናነት “ዞሮ ዞሮ ዓለም ለዝንጀሮ” የሚለው ተረት ሆኖ በብዙ መልካቸው የሚመሳሰሉ፣ በተለይ በማዕከላዊ ጭብጣቸው አንድ የሆኑ ሌሎች ሁለት ተረቶችም በማንፀሪያነት ተወስተዋል፡፡ ተረቶቹ፣ ተጠያቂያዊ በሆነ መንገድ የተነሳንበትን ማዕዘን ብቻ በሚያስረዱበት አንጻር እንደሚከተለው እየተብራሩ ተፈክረዋል፡፡ በመጀመሪያ የምንመለከተው፣ “ዞሮ ዞሮ ዓለም ለዝንጀሮ” የሚለውን ተረት ነው፡፡ ይህ ተረት አንድ “ጉርጉምበስ የተባለ ወጣት ዝንጀሮ፣ የሰው አተር ሲበላ ባለቤቱ በወጥመድ ይዞ፣ ብዙ ካሰቃየው በኋላ ሊገለው ሲል፣ አንድ መምህር ለገበሬው ካሳ ከፍሎ ዝንጀሮውን እንደወሰደው፣ … በኋላም አምልጦ ወደ ወገኖቹ ሲመለስ ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገለት፣ በ 2 ዓመት ቆይታው ከሰው ልጅ ምን እንደተማረ እንደጠየቁት፣ እሱም “የሰው ልጅ ከዝንጀሮ ነው የመጣው” ከሚለው ውጪ ምንም ነገር እንደማያስታውስ፣ የዝንጀሮ የታሪክ ሊቃውንት ግን የሰው ልጅ ከዝንጀሮ ሳይሆን ዝንጀሮ ከሰው ልጅ የመጣ መሆኑን በመረጃ አስደግፈው እንደተነተኑ … ያብራራል፡፡

በዚህ ተረት፣ “አባዬ ያለው እውነት ነው፡፡ ሰዎች ጥቅም ካላዩ ለደግነት ብቻ …” ማንንም እንደማይረዱ (ገጽ÷ 197)፣ “… ከልጆች ጋር ስጫወት ቆይቼ አብሬያቸው ልበላ ስቀርብ! ተቆጥቶ አንዳንድ ጊዜም መትቶ ያባርረኛል፡፡” (ገጽ ÷201) በማለት ስለሚታየው የዘር መድሎ፣ “ታዲያ አንተ ዝንጀሮዎች ተሻሽለው ተሻሽለው ሰዎች የሆኑበትን መድሃኒት ተማርኸው?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ እንዳነሱ … ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ ሀዲስ በሌሎች የልቦለድ ሥራዎቻቸው በአፅንኦት ያንፀባረቁት እና ብርሃኑም (1992) በጥናቱ ጨምቆ ያወጣው፣ የውጭ ሃገር ትምህርት ጦስ በዚህ ተረት እንደሚከተለው በብልሃት ተወስቷል፡፡

“ኤድያ! እንደ ሰው በሁለት እግር ቁሞ መሄድና እንደ ሰው መናገር ከመማር ይልቅ ከዝንጀሮ ወደ ሰውነት የሚለውጠውን መድሃኒት ተምሮ መምጣት አይሻልም ኖርዋል?” አለ ሌላው አረጋዊ ዝንጀሮ፡፡ (ገጽ 206፤ አጽንኦቱ የራሴ ነው)

የተሰመረበትን ሀሳብ ስንመለከት፣ ገዢዎች እናስተምራችሁ ብለው ወስደው መሰረታዊ የሆነ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ የሚያመጣ ትምህርት ከማስተማር ይልቅ፣ ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ የማይፈጥር ነቢባዊ ብቻ የሆነ እውቀት (ለዛውም ስለ እነሱ ባህል፣ አኗኗር ታሪክ ወዘተ.) ሸምድደን እንደ በቀቀን እንድናነበንብ  ብቻ የሚፈልጉ መሆኑን ያስረዳል - ጠበብ ተደርጐ ሲፈከር እንኳ፡፡

ብርሃኑ በጥናታቸው የሀዲስን “የልምዣት” መጽሐፍ ዋቢ  አድርገው “… ሥርዓቱ ባህልና ታሪክን ከትውልድ ትውልድ የማስተላለፍ ተግባሩን ባለመወጣቱም÷ ተማሪዎቹ የማህበራቸው “መለዮ” የሆኑ እሴቶች÷ የማህበራቸውን ሥርዓት÷ ልማድ÷ እምነትና ወግ ተምረው ማደግ አልቻሉም፡፡” (ብርሃኑ፣ 1992፣ ገጽ 52) በማለት ጨምቀው ያወጡት የርዕዮተዓለም መገለጫ ረቂቅ ሀሳብ፣ ሀዲስ “ዞሮ ዞሮ ለዝንጀሮ” በሚለው ተረታቸው ውስጥ፣ “ጥንታዊያን ዝንጀሮዎች፤ ታሪካቸውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ለተከታያቸው መንገር ይወዱ ነበር፤ ዛሬ ያለነው ዝንጀሮዎች ግን ለታሪካችን ግድ የሌለን ሰነፎች ሆነናል፡፡” (ሀዲስ፣ 1948፣ ገጽ 211) በማለት ተተኪውን ትውልድ ገስፀዋል፡፡

በዚህ ተረት፣ “ዝንጀሮ ከሰው ዘር የመጣ መሆኑን ለመግለጽ የቀረበው ማስረጃ፣ የወቅቱን የዓለም ሁኔታ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ የሰው ልጅ ስግብግብ ባህሪው አሸንፎት የራሱ ያልሆነውን ሁሉ ማጋፈፍ በፈለገ ጊዜ ይሄን ከልክ ያለፈ እራስ ወዳድ ባህሪውን ለማርካት የሚያስችለውን እርምጃ ሁሉ በጭካኔ መውሰድ እንደጀመረ፣ ተረቱ ያስረዳል፡፡

“ከዚያ … ሁሉም ያልሰሩት የመሳሪያ ዓይነት የለ፤ በዚህ እርስ በርሳቸው ይተራረዱ÷ እርስ በርሳቸው ይፋጁ ጀመር እንጂ! አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሰሩት መሣሪያ ምኑ ቅጡ! የሚገድል ብቻ መሰላችሁ? መግደልማ ያባት ነው … የሚቆማምጠው ሰውን ወደ ሌላ ነገር የሚለውጠው÷ … እርጉዞችን ጉድ የሚያስወልደው÷… ሰዎችን ሁሉ ከማጥፋቱ አልፎ የኖሩበትን አገር ሁሉ መልኩን ለወጠው! ተክሉም ምድሩም ሁሉ ተመርዞ ስለነበር … ከኒያ ከተረፉት በሽተኞች ሰዎች የተወለደው ሁሉ በሰው ፋንታ ዝንጀሮና ጦጣ÷ ጉሬዛ ሆነ … ይህ ነው ታሪኩ …” (ገጽ÷ 217)

ከዚህ በላይ የቀረበውን ማብራሪያ ከወቅቱ ጋር እያመሳከርን ስናነበው፣ በ2ኛው የዓለም ጦርነት፣ እ.ኤ.አ ነሀሴ 6 እና 9፣ 1945 ዓ.ም አሜሪካ ሄሮሺማና ናጋሳኪ ከሚባሉ የጃፓን ግዛቶች ላይ የጣለችውን አቶሚክ ቦንብና መዘዙን ሀዲስ በብልሃት እንደዘከሩት እንረዳለን፡፡     በሁለተኛነት የምንመለከተው “ጥጋብ ስስትን ያገባ እንደሆነ÷ ረሃብን ይወልዳል” (ገጽ 31) የሚለውን ተረት ነው (ሀዲስ አለማየሁ፣ “ተረት ተረት የመሰረት” በሚለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ “… መጀመሪያ ስለ ኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ ስለ ቅኝ አገር አስተዳደር እንድናገር ስለጠየቀኝ … ይህን በድመትና በአይጥ የተሳለ ተረት ተናገርሁ፡፡” በማለት በወቅቱ “የድመት ስህተት” በሚል ርዕስ ከሥዕል ጋር መታተሙን ገልፀዋል፡፡)፡፡ ይህም ተረት ቀደም ሲል እንደተተነተነው፣ በዘር ልዩነት ላይ ያጠነጥናል፡፡ የድመት መንግስትና የአይጥ መንግስት ሰፊ ባህር በመሃከላቸው ለያይቷቸው እራሳቸውን ችለው እየኖሩ እያለ፣ የድመት መንግስት “… በስልጣኔና በኃይልም ከፍ እያለ በመሄዱ መጠን፤ ለህዝቡም፣ ለፋብሪካውም የሚሆን ምግብ ማምጣት ስለጀመረ …” ባህር ተሻግሮ የአይጥ መንግስትን ግዛት በዘዴ እንደወረረ እና “ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ ወዘተ. እየከፈትንላችሁ እንደኛ ስልጡን እናድርጋችሁ” በማለት እያታለሉ ብዙ ጉዳት እንዳደረሱባቸው፣ በመጨረሻም የአይጥ መንግስት ነቅቶ እራሱን መጠበቅ እንደ ጀመረ ያትታል፡፡

ይህም ተረት የወቅቱን የቅኝ ግዛት ሁኔታ ለማሳየት ብለው ሀዲስ እንደፈጠሩት ቀደም ሲል ተወስቷል፡፡ በዚህ ተረትም ደራሲው ርዕዮተዓለማቸውን ለመግለጽ ተገልግለውበታል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ተረት ገጽ 39 ላይ “ባዲሱ ተማሪ ቤት የገቡትም የአይጥ ህፃናት የድመትን አገረ ጂኦግራፊ፤ የታላቁን የድመትን ህዝብ ታሪክና … የጦር ሜዳዎችና ያገኙዋቸውን ድሎች ይማሩ ጀመር፡፡”

በማለት ፈረንጆች ስለ ራሳቸው ሃገር ህዝብ ባህልና ታሪክ በየመድረኩ የምንለፍፍ ካድሬ አድረገው በስውር እንደሚያሰለጥኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሄንኑ ሃሳብ ሀዲስ፣ በየልምዣት (1980÷ 373) “ፈረንጆች÷ በእውቀት ይሁን በስህተት በየትኛው መሆኑን እግዜር ይወቀው የሚጽፉት ሆነ የሚያስተምሩት÷ ፈረንጅ እና የፈረንጅ የሆነውን የሚያስወድድ÷ የሌሎች የሆነውን ሁሉ … የሚያስጸይፍ ነው፡፡” በማለት እንደገለፁት መመስከር ይቻላል፡፡  በመጨረሻም የምንመለከተው ክቡር ሀዲስ አለማየሁ “አይጥ ከጠፋ ድመት አይኖርም” በሚል ርዕስ ከፍተኛ የሆነ የምናብ ምጥቀት፣ ሰዋሰዋዊ ከሆነ ሕያው ፍልስፍና ጋር አዋደው ያቀረቡት ተረት ነው፡፡ ይህ ተረት አነርና ዛጐል የሚባሉ ባልና ሚስት ድመቶች ከአሳዳሪያቸው ጋር የተቆራኙበትን የኑሮ ፍልስፍና ያስቃኛል፡፡ “አባወራው ድመት፣ ሚስቱና ልጆቹ አይጦችን ለማጥፋት ከልብ መስራታቸው ለነገ ህልውናቸው አደጋ እንዳለው፣ አይጥ ይዘው እያሳዩ ወተትና ሥጋ ለመቀበልና ለማታለል አይጦችን ጨርሶ ማጥፋት እንደማይገባ፣ አይጦች ከተወገዱ አሳዳሪዎቻቸው  እነሱንም እንደማያኖሯቸው … ይተርካል፡፡ የዚህም ተረት ማእከላዊ ጭብጥ ቀደም ሲል ከቀረቡት ተረቶች ጋር ይዋደዳል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ለመኖር ግዛት ማስፋት፣ ጉልበተኛ መሆን ካልሆነ አጭበርብሮ፣ ሰይጣናዊ ተግባር ፈጽሞ መኖር ግድ እንደሚል ያሳያል፡፡ የድመት መንግስት ያደረገውም ይሄንኑ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ የቀረቡትን ተረቶች በጥልቅ ሳይሆን ላይ ላዩን ለማስረጃ ያህል እየተነተንን ስንፈክር ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ጨምቀን እናወጣለን፡፡

የመጀመሪያው፣ የሀዲስ አለማየሁ ተረቶች፣ ልክ እንደ ሌሎቹ የልቦለድ ሥራዎች የወጡበትን ዘመን አሻራ እንደያዙ፣ አንዳች የሆነ ፍልስፍናና ተሞክሮ ማሳየት እንደሚችሉ ግንዛቤ ይፈጥራል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ ሁለተኛ ብርሃኑ በጥናቱ ሀዲስ “ልቦለድን እንደ ርዕዮተዓለም መገለጫ” መገልገላቸውን ሲያስተነትን እነዚህን ተረቶችም ሊያካትት እንደሚገባ ወይም ቢያንስ እንኳ በእረጅም ልቦለዶቻቸው ያነሷቸው ፍልስፍናዎች በቀዳሚነት በተረቶቻቸውም እንዳነሷቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ብርሃኑ ሀዲስ “ልቦለድን እንደ ርዕዮተ ዓለም መገለጫ” መጠቀማቸውን ለማንፀር የተጠቀሙበት የደራሲው ኢ-ልቦለድ መጽሐፍ፣ የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም (1948) ውስጥ ደራሲ ሀዲስ አንዳንድ ያነሷቸው የስነ-ምግባርና ሌሎች ፅንሰ ሃሳቦችን ለማብራራት የራሳቸው በርከት ያሉ የፈጠራ ተረቶችን መጠቀማቸውን እንዴት አላስተዋሉ ይሆን? የሀዲስ አለማየሁ ጽሁፎች በቅርጽም ሆነ በይዘት ተረታዊ ባህሪ የሚታዩባቸው መሆኑን ብርሃኑ በጥናታቸው እንደ ደራሲው ድክመት አድርገው አንስተዋል (ብርሃኑ፣ 1992÷ 69)፡፡ እዚህ ላይ፣ ተረት፣ በሀዲስ የጽሁፍና የፍልሰፍና የትባህል ውስጥ የዚህን ያህል ቦታ እንዳለው እየታወቀ፣ በርካታ አመራማሪ ጽንሰ ሀሳቦች የታጨቁባቸው ተረቶችን የያዘው መጽሐፋቸው፣ በብርሃኑ ጥናት በተወሰነ ደረጃ እንኳ ቦታ አለማግኘቱ ጥያቄ ሊያስነሳ ቢችልም የብልሁን መምህር ጥናት ብዙም የሚያጎልበት አይመስለኝም፡፡

 

Read 3470 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 12:12