Monday, 02 March 2015 09:20

የሀገር ባለውለታዎቹ ወዴት አሉ?

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(1 Vote)

“…ለ43 ዓመታት ያህል አስተምሬአለሁ… እንግዲህ ምን ያህል ልጆችን እንዳስተማርኩ እናንተው አስሉት… አሁን በጡረታ የማገኘው 420 ብር ነው… ምንም አይደል ይበቃኛል… ዛሬ ግን እጅግ ተደስቻለሁ… ለካስ የሚያስታውሱኝ አሉ… ይህንን ካየሁ ዛሬ ሞቼ ባድርም ግድ የለኝም…”
አንድ እለት የምፈልገውን ለመፈለግ ኮምፒዩተሬን አብርቼ ወደ Google ጎራ ስል ግድግዳው ላይ የማራቶኑን ጀግና የአበበ ቢቂላን ምስል አየሁ፡፡ Google ብዙውን ጊዜ ታላላቅ ሰዎችን ወይንም አንዳች ክስተትን ለመዘከር ይህን እንደሚያደርግ ባውቅም በእለቱ በGoogle የተዘከረው ግን የእኛው አበበ ቢቂላ በመሆኑ እየተገረምኩ የኮሚዩተሩን የመጠቆሚያ ቀስት ምስሉ ላይ አኖርኩ፡፡ Google አሁንም አልሰሰተም፤ እለቱ የኢትዮጵያዊው የማራቶኑ ጀግና የአበበ ቢቂላ የልደት ቀን መሆኑን ነገረኝ-  ኦገስት 7 1932 ወይም ነሀሴ 1 ቀን 1924 ዓ.ም፡፡ መገረሜን ይዤና “ሁለመናዬን ጆሮ አድርጌ” ዋልኩ፡፡ ማንም ስለ እለቱ ሲያወራ አልሰማሁም፡፡ ለምን? ወይ ጭራሽ ስለማናውቀው (ስላልፈለግን አናውቀውም) ወይንም አውቀነውም ግድ ስላልሰጠነው ይመስለኛል፡፡ ጥሎብን የእኛ የሆነ ነገር ያንስብን የለ! አለመታደል ይሉታል ይሄ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ከራቁ ገጠመኞቼ አንዱ ነው፡፡ ምን ለማለት እንደፈለግሁ እርግጥ ነው፤ገና ቀደም ተረድታችሁታል፡፡ ይህንን ማለት ድፍረት ቢመስልም አይደለም፡፡ “የእኛ ለሆኑ ነገሮች ግድ የለንም! በጣም!” ለዚህች ሀገር እጅግ የደከሙ፣ ለትውልዱ እድሜያቸውን ሙሉ የታተሩ… ታላላቅ ሰዎች አልፈዋል፤ አሁንም አሉ፡፡ የት? እነማን ናቸው? ብዙም ለእነሱ፣ ስለ እነሱ ግድ ስለሌለን አንጠይቅም፡፡ ብናውቅም እውቅና አንሰጥም፡፡ እናም የደከሙልን ቀደምቶቻችን አስተዋሽም ሆነ ተመልካች የላቸውም፡፡ ትናንትም፣ ዛሬም ምናልባትም ነገም፡፡…
እንደ ሀገርና ህዝብ አሁን ያለንበት ቦታ ላይ የደረስነው (የደረስነው የትም ይሁን የት) እንዲሁ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በጋራም ይሁን በግል በደከሙት ድካምና ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይህንን ልብ ማለት፣ ልብም ብለንም የሚገባቸውን ክብር፣ እውቅና እና ምስጋና መስጠት አልቻልንም፡፡ በሰለጠኑት ሀገሮች “seniority” ትልቅ ክብር አለው፡፡ እንኳን የተለየና ተጠቃሽ አገልግሎት ያበረከቱ ሰዎች ቀርቶ ሌሎችም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በተለየ ይከበራሉ፡፡ በመሆኑም በሰዎች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በህግ የተቀመጠ ልዩ አገልግሎትና ቅድሚያ (Priority) ይሰጣቸዋል፡፡ ለምሳሌ ባቡርና አውቶብስ ላይ በነጻ ይሳፈራሉ፡፡ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ቅድሚያ ይስተናገዳሉ፡፡… ሌላም ብዙ! ምክንያቱ ምንም አይደለም፡፡ ሽማግሌዎቹ በአቅማቸው ልክ ያቺ ሀገር የደረሰችበት እንድትደርስ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ስለሚታመን ነው፡፡
ሀገሮቹ ይህንን በማድረጋቸው የበለጠ ያተርፋሉ እንጂ ቅንጣት አይከስሩም፡፡ አንደኛ ሀገሪቱንና ትውልዱን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ያገለገሉትን ሰዎች መልሰው በማገልገላቸው የሽማግሌዎቻቸውን ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ በዚህም ሽማግሌዎቹ የሚያገኙት እርካታ አለ፡፡ በመሆኑም ለሀገራቸው በሰጡት አገልግሎት አይቆጩም፡፡ (“ይህቺ ሀገር ብዙ ብደክምላትም አሁን የት ወደቅህ አላለችኝም” የሚለውን የአረጋውያኖቻችንን ምሬት እዚህ ጋ ልብ በሉ)
ሁለተኛ የአሁኑ ትውልድም ታላላቆቹ ለሀገራቸው በመድከማቸው የሚሰጣቸውን ክብርና እውቅና ስለሚያይ እሱም ሳያመነታ የድርሻውን ለሀገሩ ያበረክታል፡፡ ምክንያቱም ሀገሩና ቀጣዩ ትውልድ ለእሱም ነገ ክፍያውን እንደማይነፍጉት ያውቃል፡፡ እንግዲህ ይህ የሚሆነው ቀደምት ባለውለታዎቻቸውን በሚያከብሩ ሀገራት ነው፡፡ ወደ እኛዋ ሀገር ስንመጣ ግን መልኩና ሁኔታው ሌላ ነው፡፡ ምናልባትም የተገላቢጦሽ፡፡ ይህቺን ሀገር በብዙ ያገለገሉትና ለትውልዱ የደከሙት ሰዎች ወዴት አሉ? ይህንን በቅጡ ጠይቀን ማወቃችንንም እንጃ፡፡
ይህቺን ሀገር በነጻነት አስከብረው ያኖሩ ጀግኖች፣ በአለም ፊት ስሟን ያስጠሩና ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ስፖርተኞች፣ በረሀ ሳይሉ ጫካ ድሀ ህዝቧን ያገለገሉ ሐኪሞች፣ ለረጅም ዘመናት ጠመኔን አንቀው ትውልድን በእውቀት ያነጹ መምህራን፣ የሀገሪቱን ባህልና እሴቶች ሲያስተዋውቁ፣ ህዝቡን ሲያስተምሩና ሲያዝናናኑ እድሜያቸውን የሰዉ የኪነ ጥበብ ሰዎች… በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለዚች ሀገርና ህዝቦቿ የደከሙ ባለውለታዎቻችን ወዴት አሉ? ማንስ ያስታውሳቸዋል? በምንስ ተዘክረዋል? አጋጣሚ ፈቅዶ በየሚዲያው የሚቀርቡትን ጥቂት ሰዎች በማየት ብቻ ውለታ ቢስነታችን ምን ያህል ልክ አልባ እንደሆነ ልብ ማለት እንችላለን፡፡
እርግጥ ነው ሁሉንም ማገዝና መዘከር ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ፍላጎቱና ቀናነቱ እሳካለ ድረስ ቢያንስ ለሀገራችን እጅጉን አስተዋጽኦ ያደረጉትን ታላላቆቻችንን ማመስገን ከባድ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ገንዘብ አይደለም፡፡ ቢያንስ እውቅናን መስጠትና ማመስገን ነው፡፡
ከወራት በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር (ወዳጄ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም መምህር ነው) በጉዳዩ ላይ ስናወራ የነገረኝን ላንሳ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የትምህርት ተቋሙ ዓመታዊ የምስረታ በዓሉን ያከብር ነበር፡፡ የበዓሉ ኮሚቴ “የክብር እንግዳ ማን ይሁን?” በሚለው ላይ ሲወያይ ከኮሚቴው አባላት አንዱ የበዓሉ የክብር እንግዳ ለረጅም ዓመታት ያስተማሩና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙ አንጋፋ መምህር እንዲሆኑ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ይህ ሀሳብ በወቅቱ ጥቂቶችን ባያሳምንም በብዙዎቹ ተቀባይነት በማግኘቱ ሀሳቡ እውን ሆነ፡፡ እናም ተጋባዡ አንጋፋ መምህር በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኙ፡፡
መምህሩ በእለቱ የተሰማቸውን ስሜትና ያደረጉትም ንግግር ካለ እንዲነግረኝ ወዳጄን በጉጉት ጠየቅሁት፡፡ ነገረኝ፡፡ መምህሩ እጅግ ተደስተው ነበር፡፡ ምን አሉ መሰላችሁ? “…ለ43 ዓመታት ያህል አስተምሬአለሁ… እንግዲህ ምን ያህል ልጆችን እንዳስተማርኩ እናንተው አስሉት… አሁን በጡረታ የማገኘው 420 ብር ነው… ምንም አይደል ይበቃኛል… ዛሬ ግን እጅግ ተደስቻለሁ… ለካስ የሚያስታውሱኝ አሉ… ይህንን ካየሁ ዛሬ ሞቼ ባድርም ግድ የለኝም…”
ተመልከቱ የጉዳዩ አስኳል ገንዘብ አይደለም፡፡ እውቅና እና ምስጋና ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ያገለገሉንን በሀገር ደረጃ ማመስገን ቢከብደን እንኳን በየመስካችን እንችላለን፡፡ ምን በዚህ ብቻ “ከአንጀት ካለቀሱ…” እንዲሉ አበው፣ ሌሎችም ብዙ አማራጮች ሞልተዋል፡፡ እስከፈለግን ድረስ ከባድ አይደለም፡፡
ታዲያ ጉዳዩ ይህንን ያህል ቀላል ከሆነ ለምን መፈጸሙ አቃተን? ምክንያቶቹ በርካታ ይመስሉኛል፡፡ አንድ ሁለቱን ልጥቀስ፡፡ ቀዳሚው ነገር ታላላቆቻችንን ማድነቅ ባህላችን ስላልሆነ ነው፡፡ እንደ ህዝብ እጅጉን ከምንቸገርባቸው ነገሮች አንዱ ከልብ ማድነቅ አለመቻላችን ነው፡፡ ለምን እንደሆነ በቅጡ ባይገባኝም (ምናልባት ሌሎችን ስናደንቅ እኛ ዝቅ የምንል ስለሚመስለን ይሆን?) አለማድነቅ ችግራችን ነው፡፡ የምር ከማድነቅ ይልቅ ከአንገት በላይ ማንቆለጳጰሱ ይቀናናል፡፡ ከልቡ ማድነቅ የማይችል ደግሞ ታላላቆቹን ሊያከብር፣ ለዋሉለት ውለታም ሊያመሰግን አይችልም፡፡
ሌላው ምክንያታችን ደግሞ ሰዎቹ ካበረከቱት አስተዋጽኦ ይልቅ ለነበራቸው (ላላቸው) አስተሳሰብ፣ ለተወለዱበት ብሔር ወዘተ… ትኩረት ስለምንሰጥ ነው፡፡ “እሱ እኮ እንዲህ ነበር” ወይም “እንዲህ ነው” ማለት ይቀናናል፡፡ አስተሳሰባቸውንና ማንነታቸውን ከአስተዋጽኦዋቸው መለየት አንችልም፡፡ እናም ብዙዎችን በማንነታቸው ብቻ እንገፋለን፤ ገፍተናልም፡፡ የዘከርናቸውን ጥቂቶችንም የዘከርነው ካበረከቱት አስተዋጽኦ ይልቅ የነበራቸውን ማንነትና አስተሳሰብ እንዲሁም አባል የነበሩበትን ቡድን መለኪያ አድርገን ነው፡፡
ይህ አመለካከት የብዙዎችን ክብርና ምስጋና ነፍጎአል፡፡ አንድ ግለሰብ መመስገንና እውቅና ማግኘት ያለበት በስራው ሊሆን ሲገባ ማንነቱና አስተሳሰቡ ተመዝግቦ ውለታው አፈር ይለብሳል፡፡ የዚህ አመለካከት ጉዳቱ ከዚህም ያልፋል፡፡ በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ከሀገር አሰድዷል፤ ከዚህ የተረፉትንም እንጀራ አሳጥቶአል፡፡
የሀገርና የህዝብ ባለውለታዎችን አለማመስገንና እውቅና አለመስጠት ሞራላዊ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሀገራዊ ጉዳቶችን የሚያስከትል በመሆኑ ግዴታም ነው፡፡ አንዱ ጉዳቱ ትውልድን አለማነሳሳቱ ነው፡፡ ባለውለታዎችን የማታከብርና የማታመሰግን ሀገር ቀጣይ  ባለውለታዎችን አትፈጥርም፡፡ በፍጹም! “ደግሞ ለዚች ሀገር…” የሚል ቃልን በምሬት የሚናገሩ ሰዎች አጋጥመዋችሁ አያውቁም? እነዚህ ሰዎች እንዲህ ማሰባቸው ልክ ነው ባልልም መነሻ ግን አላቸው፡፡ ሀገሪቱ የደከሙላትን ዞር ብላም እንደማታይ ያውቃሉ፡፡ ይህ ተስፋ አስቆርጦአቸዋል፡፡ እኔስ ነገ አሰኝቶአቸዋል፡፡ ጉዳቱ ሀገርን ትጉህ ተረካቢ እስካማሳጣት ይደርሳል፡፡
ሌላው ጉዳት አዲሱ ትውልድ ሊከተላቸውና ሊማርባቸው የሚገቡ ሀገራዊ አርአያዎችን ያሳጣል፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙዎቹ የዘመናችን ህጻናት የሚያደንቋቸው ታላላቅ ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡
ምክንያቱም ሊከበርና ሊመሰገን የሚገባውን አክብረንና አመስግነን አላስተዋወቅናቸውም፡፡ እናም በቅርቡ ያገኙትን አርአያ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ እጅጉን ትጉህ የሆኑት የውጪ ሚዲያዎች በሚያከብሩአቸውና በሚያደንቋቸው ግለሰቦች የእኛን ልጆች ልብ ቅኝ ይገዛሉ፡፡
የእኛን ቀደምቶች ለማስታወስ ዳገት የሆነባቸው የሀገራችን አብዛኞቹ ሚዲያዎችም ለዚህ ትጉህ ናቸው፡፡ የውጪውን ዓለም ስፖርተኛ በሉ ተዋናይ፣ ሙዚቀኛ በሉ ቢሊየነር… የህይወት ታሪኩን ብቻ ሳይሆን እስከሚወደው ምግብና አለባበስ ሳይቀር አብጠርጥረው ይነግሩታል፡፡ በዚህም ህጻናቱ ሀገራዊ አርአያዎችን በማጣታቸው ከሀገራቸው ታላላቅ ሰዎች ሊማሩአቸው የሚገቡ የሀገር ፍቅር፣ ስነምግባር፣ ታሪክና በርካታ እሴቶችን ያጣሉ፡፡
ሀገርና ትውልድ የሚገነቡት በቅብብሎሽ ነው፡፡ በዚህ ቅብብሎሽ ውስጥ ደግሞ ታላላቅ አስተዋጽኦዎችን የሚያደርጉ የሀገርና የትውልድ ባለውለታዎች አሉ፡፡ እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች የራሳቸውን ግላዊ ጥቅም ለሀገርና ለትውልድ እስከመስጠት ድረስ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እነሱን ማመስገንና ለአስተዋጽኦዋቸው እውቅና መስጠት ሀገራዊም ህዝባዊም ግዴታችን ነው፡፡ ይህን አለማድረግ ጉዳቱ ያህላል የለውምና፡፡
መልካም ሰንበት!!

Read 1625 times