Saturday, 14 January 2012 12:05

የግርግም ባለቤቱ ወግ

Written by  ብርሃኑ አበጋዝ ከኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል (አ.አ.ዩ.) Natanem2003@yahoo.com
Rate this item
(0 votes)

ጊዜው ወደ አመሻሽ ላይ ነው፤ የቤቴልሔም ከተማ በእንግዶች ጫጫታ ተሞልታለች፡፡ እንግዶቹ በየሰው ቤት ስፍራ ስፍራቸውን ይዘዋል፡፡ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይዘፍናሉ፡፡ አንዳንዶቹ በቡድን በቡድን ሆነው ስለህዝቡ ቆጠራ፣ ስለወቅቱ ፖለቲካ ያወጋሉ፡፡ የቤተልሔም ከተማ እንደዛሬው ሆና አታውቅም፡፡ የከተማው ሕዝብ እንግዶቹን ለመቀበል ተፍ ተፍ ይላል፡፡ ዘግይተው ወደ ከተማይቱ የገቡት እንግዶች ደግሞ ማረፊያ ሥፍራ ፍለጋ በከተማይቱ ውስጥ እየተዘዋወሩ ይጠይቃሉ፡፡ የእኔም ቤት በእንግዶች ሞልቷል፡፡ መፈናፈኛ እንኳ የለም፡፡ በእንግዶቹ መስተንግዶ እኔም ገረዶቼም ደክመናል፡፡ መቼም የሚገኘው ገንዘብ ጠቅም ያለ በመሆኑ እንጂ ሁኔታው ሁሉ አሰልቺ ነበር፡፡ በሬ እየተንኳኳ ነው፡፡

በዕለቱ አንዱ አድካሚ የነበረው ደግሞ በር እየከፈቱ ማረፊያ ቦታ ለሚጠይቁት መልስ መስጠት ነው፡፡ ብቻ እንደማጉረምረም እያልኩ ሄጄ ከፈትኩት፡፡ አንድ በእድሜው ገፋ ያለ (አረጋዊ) ከአንዲት ውብ ሴት ጋር በደጃፌ ቆሟል፡፡ የሴቲቱ እና የሽማግሌው እድሜ በፍጹም አይገናኝም፡፡ ግራ የሚገባው ግን ሴቲቷ እርጉዝ መሆኗ ነበር፡፡

ሀሳቤን ያቋረጠኝ ጐርነን ያለው የሽማግሌው ድምጽ ነበር፡፡ “ለእንግዶች ማረፊያ ስፍራ ፈልገን ነበር” አለኝ፤ በጣም አሳዘኑኝ፡፡ በቤት ፍለጋም ብዙ እንደደከሙ ያስታውቃል፡፡ ምናልባትም የሴቲቷን እርጉዝ መሆን እያዩ ሰዎች ስፍራ ሊሰጧቸው እንዳልፈለጉ ገመትኩ፡፡ ግን ምን ያደርጋል… የእኔም ቤት በእንግዶች ተይዟል፡፡ በሀዘን ልቤ እየተነካ “ይቅርታ ቦታው በሙሉ በእንግዶች ተይዟል፡፡ ለእናንተ የሚሆን አንድም ሥፍራ የለኝም” አልኳቸው፤ አረጋዊው ሰው ተስፋ በቆረጠ ስሜት “በከተማው በሙሉ ተዘዋውረናል፤ ቤቶቹ በሙሉ በእንግዶች ተይዘዋል፡፡ እንደምታይው እኔም ደካማ ሽማግሌ ነኝ፤ እርሷም መውለጃዋ ወቅት ስለደረሰ እንደሌሎቹ መንገዱን በጊዜ ማቋረጥ ስላልቻልን ሌሎቹ ቀድመውን ሥፍራውን ያዙት፡፡ ከዚህ በኋላ ወዲህና ወዲያ የምንልበት አቅም የለንም፡፡ እንደው ትንሽም ሥፍራ ብትሆን ፈልጊልን” አለኝ፡፡ እኔም “ኧረ ጌታው ቢኖርማ ምን አሻኝ… ቤቴን ለእንግዶች ሁሉ ክፍት አድርጌዋለሁ፡፡ ነገር ግን አንድም ስፍራ የለም፤ በግቢዬ ውስጥ ነጻ ስፍራ ቢኖር የከብቶቹ በረት ብቻ ነው፡፡ መፈናፈኛ እንኳ የለም” በማለት አዘኔታዬን ነገርኳቸው፡፡ ሰውዬው ግን ቶሎ ብሎ ፊቱ በደስታ ተሞልቶ “ታዲያ የከብቶቹ በረት ውስጥ እናርፋለና! ምንም አትሳቀቂ ለአንድ ሌሊት ብቻ ብንቸገር ነው” አለኝ “በዛ ውስጥ ማረፍ አትችሉም አይመችም ይሸታል” ብዬ ብሟገትም በጄ አላሉኝም፡፡ እንዲያውም “ትክክለኛ ስፍራ ነው ያለነው” ብለው ድርቅ ስላሉብኝ ሳልወድ በግዴ አስገባኋቸው፡፡ በበረቱ አንድ ጥግም የከብቶች ግርግም ስላገኙ ሴቲቷን በዛ አረፍ አደረግናት፡፡

ወደ ቤቴ ስመለስ የእንግዶቹ መስተንግዶ ሌሊቱን በሙሉ ፋታ አልሰጥ አለኝ፡፡ በከብቶቹ በረት ውስጥ ያሉት እንግዶች ትዝ ያሉኝ ወደ መኝታዬ ገብቼ ጐኔን ሳሳርፍ ነበር፡፡ ደነገጥኩ፡፡ የሚበሉት እንኳን አለመስጠቴ፣ መኝታውም እንደተመቻቸውና እንዳልተመቻቸው አለመጠየቄ አናደደኝ፡፡ እስቲ ለማንኛውም አየት አድርጌአቸው ብተኛ ይሻላል በማለት የቤቱን ደጃፍ ከፍቼ ወደ ከብቶቹ በረት ላመራ ስል ደንግጬ ባለሁበት ክው ብዬ ቀረሁ፡፡ ግቢዬ በታላቅ ብርሃን ደምቋል፡፡ የብርሃኑ ፀዳል ደግሞ የሚያበራው በከብቶቹ በረት ላይ ነበር፡፡ ምን አይነት ትዕይንት ነው ስል ተገረምኩ፡፡ ነገር ግን መገረሜን ሳልጨርስ ደጃፉ በኃይል ተንኳኳ፡፡ ልቤ ምቱን ጨመረ፡፡ በፍርሃት እየራድኩ ሄጄ ስከፍት የበግ ጠባቂ እረኞች ናቸው፡፡ “የተወለደው የዓለም መድኃኒት እዚህ ነው” አለኝ አንዱ ከመካከላቸው፡፡ የ”ዓለም መድኃኒት” የሚለውን ቃል አሰላስዬ ሳልጨርስ እረኞቹ እየተግተለተሉ ወደ ከብቶች በረት ገቡ፡፡ ግራ በመጋባት ተከተልኳቸው፡፡ እረኞቹም ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ፡፡ ምን እያደረጉ ነው? ለማንስ ነው የሚሰግዱት? በማለት ቀና ብዬ ሳይ ለካ ሴቲቱ ወልዳ ኖሯል፡፡ ደስ የሚል ወንድ ልጅ ታቅፋለች፡፡ በበረቱ ውስጥ ያሉትም ላሞች በትንፋሻቸው ሲያሟሙቋቸው ነበር፡፡ አረጋዊው ሰውዬ እንደኔ በሁኔታዎቹ የተገረመ ይመስላል፡፡ እረኞቹም ሰግደው ሲያበቁ “ምስጋና ለእግዚብሔር በሰማያት ሰላምም ለሰዎች በምድር እያሉ በማዜም” በደስታ እየዘለሉ እኔን ከቁብም ሳይቆጥሩኝ ከግቢዬ ተፈትልከው ወጡ፡፡

በሁኔታው በውስጤ ግራ መጋባት ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም የግቢዬን በር ዘግቼ የሆነውን ሁሉ ለእንግዶቼ መንገር አለብኝ በማለት ወደ በሩ ዞር ስል ባየሁት ነገር ደንግጬ “እንዴ?” ብዬ በመደነቅ ጮህኩ፡፡ ከፊት ለፊቴ በራሳቸው ላይ የንጉሥ ዘውድ የደፉ ሦስት ሰዎች በእጃቸው ስጦታ ይዘው ወደበረቱ እያመሩ ነበር፡፡ ከግቢው  ውጭ የመጡበት ግመሎቻቸው ቆመዋል፡፡ የሩቅ ምስራቅ ሰውም ይመስላሉ፡፡ ከድንጋጤዬና ከሃሳቤ የባነንኩት ከመሃላቸው አንዱ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው” ሲለኝ ነበር፡፡ መልስ ግን አልነበረኝም? ከመሃላቸው አንዱ ወደ ሰማይ ሲያንጋጥጥ እኔም ተከትዬ አንጋጠጥሁ፡፡ አንዲት ኮከብ በከብቶቹ በረት ላይ ታበራ ነበር፡፡ ሲገቡ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር አገኙ፡፡ ዘውዳቸውን አውልቀው በምድር ተደፍተው ሰገዱ፡፡ ከያዙት የስጦታ እቃ ውስጥ በየተራ እጣን፣ ከርቤና፣ ወርቅ አውጥተው ሰጡ፡፡ ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመገኑ ወደመጡበት በግመሎቻቸው ሆነው ነጐዱ፡፡ ለካ ሳላውቀው በቤቴ ውስጥ ስፍራ አጥቼለት ከብቶቼ በረት ያስተኛሁት ሲጠበቅ የነበረው መሲህ፣ የዓለም መድሃኒት ንጉሥ ኢየሱስ ነው - አልኩ በልቤ፡፡ በዚህ ሃሳብ እንደደነዘዝሁ ሌሊቱ ነግቶ ኖሯል፡፡ አረጋዊው ሰውዬ ሴቲቷንና ህፃኑን ይዞ ለመሄድ ተነሳ፡፡ “እመቤቴ ለዚህ ምሽት መስተንግዶሽ ፈጣሪ ዋጋሽን ይክፈልሽ” አለኝ፡፡ እኔም እግራቸው ስር ወድቄ ለመንኳቸው፡፡ “ዛሬን ብቻ በቤቴ አሳልፉ” በማለት፡፡ አረጋዊው ሰው “የለም ቤትሽ በእንግዶች ተሞልቷል፡፡ ደግሞም መሄድ አለብን” አለኝ፡፡ እኔም በሲቃና በእልህ “የለም በቤት ያሉትን እንግዶች በሙሉ አስወጣለሁ፤ ዛሬን ብቻ እንዳስተናግዳችሁ ፍቀዱልኝ” ስል ተማፀንኩ፡፡ “እሺ ብንልሽ በወደድን ነበር፡፡ ነገር ግን ለቆጠራው እንግዶቹ ወጥተው ሰልፍ ሳይዙብን መፍጠን ስላለብን ነው፡፡” ብሎኝ ተሰናብተውኝ ወጡ፡፡ እኔም ተከትያቸው ሄድኩ፡፡ የተወሰነ መንገድ ከሸኘኋቸው በኂላ ህፃኑ በእናቱ እቅፍ እንዳለ እግሮቹን ሳምኩት፡፡ እነርሱም በፍቅር ዓይን እያዩኝ አረጋዊው ሰውዬ “እኔ ዮሴፍ እባላለሁ የእርሷ ጠባቂዋ ነኝ፤ እርሷ ማርያም ስትባል ህፃኑም ኢየሱስ ነው” በማለት አስተዋውቆኝ ተሰናብተውኝ ሄዱ፡፡ እንባ ከዓይኔ ላይ ኩልል ብሎ ወረደ፡፡ በማንነቴም አዘንኩ፡፡ የማይረቡና የማይጠቅሙኝን የአይሁድ ሕዝብ፣ የመቅደሱ ካህናቶችና ፈሪሳውያንን በቤቴ በእንግድነት ሳስተናግድ፣ በሳሎንና መኝታ ቤቴ እግራቸውን አጥቤ ሳስተኛ፣ የሚበሉትን ምግብና የሚጠጡትን ወይን ሳቀርብ ሳስደስት፣ ለአይሁድ ንጉሥና ለዓለም መድኃኒት በዘመናት ስንጠብቀው ለነበረው መሲህ ስፍራ ልጣለት፡፡ ወይኔ አልኩ በመቆጨት፡፡ ለእኔ ቤት ብቻ ሳይሆን ለመላው የቤቴልሄም ነዋሪ አዘንኩ፡፡ ሁሉም ለንጉሥ ኢየሱስ የሚሆን ስፍራ አልነበራቸውም፡

በቆምኩበት ቦታ ሳለሁ ለካ የቤቴ እንግዶች ጓዛቸውን ጠቅልለው በግቢው ሲያጡኝ መንገድ ጀምረው ኖሮ የቆምኩበት ስፍራ ደረሱ፡፡ ሁሉም በፍቅር የምስጋና መአት አዥጐደጐዱልኝ፡፡ ግማሹ ጉንጬን፣ ግማሹ እጄን ለቀም እያደረጉ ስመውኝ ተሰናበቱ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ልቤ ከእነርሱ ጋር የለም፡፡ በቤቴ ስፍራ ካጣሁት ንጉሥ ጋር ነጉዷል፡፡ ወደቤቴም ስመለስ እያስጠላኝ ነበር፡፡ በተለይ ግቢው ወስጥ ስገባ ያን ሁሉ እንግዳ ያስተናገደው ትልቁን ቤቴ ማየት እንኳ አስጠላኝ፡፡ ሰተት ብዬ የሄድኩት ወደ ከብቶቹ በረት ነበር፡፡ በዛም ቁጭ ብዬ አሰላሰልኩ፡፡ ለጌታዬ የከበረ ስፍራ ለእኔ ደግሞ የተዋረደ ቦታ የሆነው የከብቶች በረት፡፡ በልቤም ሰው ምን ያህል ሞኝ ነው፡፡ በተለያዩ እንግዶች ልቡን (ቤቱን) ሞልቶ ጌታውን ደጅ የሚያሳድር፡፡

ቤቱን በእንግዶች አስይዞ የህይወቱን አዳኝ ለማስተናገድ ስፍራ የሚያጣ፡፡ መድሃኒቱንና ንጉሡን ማስተናገድን ያልቻለ ከንቱ ፍጥረት - የሰው ልጅ! በበረቱ ውስጥ ያሉት እንስሶች በደስታ ይፍነከነካሉ፡፡

በበረታቸው ባደረው እንግዳ የተደሰቱ ይመስላል፡፡ ለነገሩ የነቢዩ ትንቢት “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፡፡ ሕዝቤም አላስተዋለም” ብሎ የለ፡፡ /ትን.ኢሳ.1፡3/ ለጌታ ሥፍራ የጣው ልቤ እንደቆዘመ ነው፡፡…

 

 

Read 2125 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 12:08