Saturday, 14 January 2012 11:58

ስለማውቀው ፈጣሪ ላውራ!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

“ለምን ለምን ከነስህተታችን ተውከን?”

ኖስቲክ ነኝ፡፡ ኖሲስ (gnosis) እውቀት ማለት ነው፡፡ … ባልተጭበረበረው … እውነተኛ እውቀት ፈጣሪዬ ላይ እደርሳለሁ ብዬ የማምን ነኝ፡፡ …. እውነተኛ ፈጣሪ ዘንድ በእውነተኛ እውቀት መድረስ፡፡ ላለመመለስ … ዳግመኛ ላለመሳሳት … በአንድ እውነት ሁሉም ጥቅል ነገር ላይ መድረስ፡፡ … እናም ሳይንስንም፣ ጥበብ ፍልስፍናንም እንደ  መንገድ እና መሳሪያ ይዤ በጉዞ ዘምቻለሁ፡፡

ጉዞም ያልቃል፤ ዘመቻም በድልም ሆነ በሽንፈት ይጠናቀቃል፡፡ ማሸነፍ የእድሜ ልክ ምኞት ነው እንጂ፤ በእድሜ ዘመን የማይገኝ እውነት አይደለም፡፡ ዘመቻውም ሆነ መንገዱ አሳሳች ነበር፡፡ ተሳስቻለሁ፡፡ መሳሳቴን ያወቅሁት … ትክክለኛውን እውነት በማግኘቴ አይደለም፡፡ መሳሳቴን ያወኩት ግቤን ስለጣሁት እና ስላደከመኝ ነው፡፡ የምፈልገው ነገር ላይ ሳልደርስ ፍለጋዬ ጠፋብኝ፤ እናም በድካም በረሀ ውስጥ ተዳክሜ ቀረሁ፡፡ … ወደኋላ መመለስ አያዋጣም፤ አይሆንም፡፡ ወደፊት መሄድም አያስተማምንም፡፡

እውነተኛው ፈጣሪ ላይ ለመድረስ እውነተኛ ፍጡር መሆን ያሻል፡፡ ሰው በፈጣሪ የተፈጠረ ካልሆነ ፈጣሪውን ትውልድ በትውልድ ላይ እየተተካካ ሲፈልግ ቢኖርም … የፈለገውን ነገር አያገኝም፡፡ እንደማያገኝ እያወቀ የሚፈልግ ሞኝ አይደለም፡፡ ሞኝ የዋህ  ተፍጨርጫሪ ነው፡፡ እንደማያገኝ እያወቀ የሚፈልግ … ስራ ፈት ነው፡፡ ስራ እንዳያልቅ አጭሩን ስራ የማራዘሚያ (ማወሳሰቢያ) … መንገድ እንደሚፈጥር አጉል ብልጥ፡፡ ስራው ካለቀ፤ አ-ል-ቋ-ል፡፡

ስራው ድሮውኑ ካልነበረ … እንደነበረ ወይንም እንዳለ አድርጐ መተወን … ብልጠት መሳይ ድርብ ቂልነት ነው፡፡

… ስለዚህ ስፈልግ የቆየሁት ያልነበረ ነገር ነው፡፡ ብፈልገው የማይገኝ … ባነጋግረው የማይመልስ … ብጨብጠው የማይያዝ ነገርን “እውነት” በሚል ስያሜ ጠርቼ ሳድን ኖርኩ … “ጥንቸል ዘላ ዘላ በስተመጨረሻ ከመሬት”

ከመሬት ጋር ወደሚያገናኝ ጉዳዮች ላይ አርፌ ላተኩር፡፡ ወደሚታየኝ ወደሚመለከተኝ … እኔም በየቀኑ በቴሌቪዥን በሚቀርበው ዲስኩር የምመለከተው የመንደሩ አድራጊ ፈጣሪ ፊቴን ልመልስ፡፡ ፀሎቴን ሳይሆን አቤቱታዬን እያደመጠ የማይመልስልኝ ፈጣሪ፡፡ … እንደኔው ሰው የሆነው፤ ነገር ግን የስልጣን ከፍታው ላይ እንደ ግሪኮቹ አማልክት በመቀመጡ ምክንያት ብቻ ፈጣሪ የሆነብኝ መንግስት፡፡ እኔን መግደልም ሆነ ማኖር የሚችለው መንግስት … ስሰድበው መልሶ የሚሰድበኝ መንግስት፡፡

ከማላውቀው የሩቅ ፈጣሪ ጋር ከምጣላ … ከሚገባኝ፣ ቅርቤ ካለው ተራው ፈጣሪ እና መንግስታዊ ሰራዊቶቹ ጋር ላውራ፡፡ በጊዜ፣ በኮታ፣ በርዝመት እና ቁመት … በልኬት እና ስፍር ቁጥር ልመጥነው ስለማልችለው እውነተኛ ፈጣሪ እንደማውቅ አድርጌ ሳወራ ኖሬአለሁ፡፡ እምነቴ ፈተናዬን አበረታብኝ እንጂ ማስተማመኛ አልሆነኝም፡፡ ስለዚህ የማላውቀውን ልተውና ስለማውቀው እርግጠኛ ስለሆንኩበት ብቻ ላውራ፡፡…  ምስጋናዬንም ሆነ እንቅስቃሴዬን በፊልም አቀናብሮ ወደሚቀርፀኝ እና በፍርድ ቤት “አሸባሪ” ብሎ ሊከሰኝ ወደሚችለው መንግስት፡፡ መንግስት ተራው የመንደር እግዜር ነው፡፡ ምህረቱም ሆነ ቅጣቱ ምድራዊ የሆነው መንግስት፡፡ … ለስጋዬ ምቾት ወይንም መከራ ማምጣት የሚችለው እግዜር፡፡ እንደኔው ቢቆረጥ የሚደማ፣ ቢፈራ የሚደነብር ወይንም የሚጨፈጭፍ የመንደሩ እግዜር፡፡

ከዋናው የምኞቴ እና የእምነቴ እግዜር ጋር የመንደሩን አድራጊ ፈጣሪ አንድ የሚያደርገው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ … ያ አንድ ነገርም ሁለቱንም አናግሬአቸው መልስ ያለመስጠት አባዜያቸው ነው፡፡ የጠየቅሁት ሳይሆን ያልጠየኩት ነው ምላሽ የሚሰጠኝ፡፡ ተራው ካድሬ … ወይንም ተራው የሀይማኖት ተወካይ ቄስ ነው ከድሮውም መልስ የሚሰጠኝ መልስ የምሻው ከመንደሩ ሳይሆን ከሙሉኤኩሉው እግዜር ነበር፡፡

መልስ የሚቀርብልኝ ግን ድሮም እንደ ዘንድሮ ከቄስ እና ከካድሬ ነው፡፡ ቋንቋ ያልገባው አስተርጓሚ … እና ትርጉም አዛቢ ብቻ ነው የሞላው፡፡

የሚገርመው፤ የመንደሩ እግዜር መንደራዊ አስተሳሰቦች አሉት፡፡ … ትልቁን ፈጣሪ ሊመስል የማይችለው ለዚህ ነው፡፡ ጠባብ ነው፤ ጐጠኛ፤ ዘረኛ እና በሙሉ በ”ኛ” ፊደል የሚቋጩ “አድጀክቲቮችን” በሙሉ የተላበሰ ነው፡፡ ሁሉ ነገሩ መንደርኛ ነው፡፡

በሀገሬ ላይ መንደር እንዴት ይነግሳል? የሚል ጥያቄ ይፈጠርብኛል፤ ግን ማንን ጠይቄ መልስ እንደማገኝ አላውቅም፡፡ በህዝብ ማመን ከቆየሁ ውዬ አድሬአለሁ፡፡

ለምን ዙሪያ ጥምጥም እሄዳለሁ? … ፊለፊት ስለሚታይ ነገር ፊለፊት ለምን መናገር አቃተኝ? ፊለፊት የተቀመጠ ነገር በፊለፊት አደጋ ያደርስብኛል በሚል ፍርሀት ሳይሆን አይቀርም፡ በአሉ ግርማ ራሱ ፊለፊት ይታይ ስለነበረ ነገር በዙሪያ ጥምጥም በመናገሩ በፊለፊት ከመገደል አላተረፈውም፡፡ መሞት እንደሆነ አይቀርም፡፡ … የተስፋ ስግብግብነት ፈሪ ያደርጋል፡፡ … መሸሽም የሚያዋጣው መሸሸጊያ እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡

አይ ተስፋ፡፡ ግልፁን ማወቁ  አይሻልም? ለሁሉም ሰው የሚበቃ ተስፋ በምድረ ገፅ ላይ የለም፡፡ ተስፋ ያላቸው የተወሰኑት ናቸው እነሱም … ለተወሰነ ጊዜ ብቻ፡፡ ስለዚህ ተስፋ ማድረግ ራሱ ስራ በሌለበት አላስፈላጊ ስራ ፈጥሮ ጊዜ ለመግደል እንደመሞከር ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥን ነው ለካ እስካሁን ተስፋ አድርገን ስንጠብቅ የኖርነው፡፡ “And hope was hope for the wrong thing”

እናም ዙሪያ ጥምጥም አልሄድም፡- ፊለፊት እናገራለሁ፡፡ የመንደሩ እግዜር ሰው ነው፡፡ … አስተሳሰቡ መንደርኛ፣ ርዕዮተ አለሙ ብሔርተኛ ነው፡፡ ሰው የዋናው ፈጣሪ ሳይሆን የመንደርኛው ፈጣሪ “ባሪያ” ነው፡፡ መንግስት እና ሀይማኖት ሰውን ከእውነተኛ ፈጣሪው ጋር እንዳይገናኝ፣ ፅድቅን እንዳይፈልግ፣ በመንደር ጥበት ውስጥ መከራን ፈትለውና ሸምነው የሚያለብሱት “ኢምንት ሀይል” ያላቸው የእኩይ አይነቶች ናቸው፡፡ ገሀነም እንዳንገባ እንፈራለን እንጂ እንዳንገባ የምንፈራው ውስጥ መሆናችንን አንቀበልም፡፡

እኔም በሀሳቤ እርቄ ዋናውን ፈጣሪ ለማግኘት ወጣሁ እንጂ … እግሬ ሀገሬ ውስጥ በመንደርኛ እግረ ሙቅ ታስሮ እንዳይላወስ … እንዳይንከላወስ ተጠፍሯል፡፡ ፈጥሮ አያገባኝም ብሎ ከረሳኝ የሩቅ እግዜር ይልቅ … ሳይፈጥረኝ እገልሀለሁ ብሎ የሚያስፈራራኝ … ተሸብሬ መግቢያ ባጣሁበት ወቅት ማፅናናትን ካዘገየብኝ የሩቁ አምላክ ይልቅ፣ ተሸብሬ አሸባሪ ብሎ የሚያቀውሰኝ ይቀርበኛል፡፡ የሚቀርበኝ ግን ይሻለኛል ማለት አይደለም፡፡ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሠይጣን የበለጠ ይበድላል፡፡ ከመንደር ፈጣሪ ጋር አብረህ አትሰደድ ሳይሆን አብረህ አትኑር፡፡ እውነትን ወደ ሰማይ ቤት አድርሶ ማስገባት ካልተቻለ ወደ ቤት ወይንም መንደር መልሶ መቀርቀር ግን ይቻላል፡፡  ምናልባት ፈረንጆቹ “Home truth” ብለው የሚጠሩት ይህንን ሊሆን ይችላል፡፡ …”የሀገር ቤት እውነት” ብዬ እኔ ሰይሜዋለሁ፡፡ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ፍትሕ የለም፡፡   … ተስፋን እና እውነትን ማስተዋወቅ እንጂ ማቀዳጀት የቻለ ማንም የለም፡፡ … ሁሉም ገንዘብ ፈላጊ ነው፡፡ እውነትን፣ ፍትሕን እና ነፃነቱን የሚቀዳጀው በገንዘብ መስሎታል፡፡

ሁሉም በየአቅጣጫው ይሮጣል፤ ተደፍቶ እስኪወድቅ የተሻለ ገንዘብ አግኝቶ አንድ ሰሞን ተመችቶት ከታየ በኋላ የገዛው ሱፍ ሳያረጅ ተስፋ ቆርጦ በመንገድ እየለፈለፈ ሲሄድ ይታያል፡፡ … አንዱ ከሌላው ብዙም ለውጥ የለውም፡፡ ሁሉም ግንባር ላይ “ገንዘብ አይታችኋል ወይ?” የሚል የከረረ፣ የተወጠረ ጅማት ተገትሮ ይታያል፡፡ ጅማቱ ወደ ቀንድ ይቀየራል … ተቀይሯል፡፡ በቀንዱ እንደ ኮርማ ሲዋጋ ይውላል፡፡ ብዙ የማስታወቂያ ፖስተሮች በማስተዋወቅ እና በመተናነቅ ላይ ናቸው፡፡ ሁሉም ባለቀንድ የሚሸጠው ነገር አለው፡፡ ትንሽ ገንዘብ የቀመሰ የበለጠ ይራባል፡፡ ትንሽ የቀመሰ በበለጠ ፍጥነት ቀንዱ ያድጋል፡፡ … እውነት ተስፋ አለን? … ተስፋስ እኛ አለነው?

ከሰው መልስ አልሻም፡፡ ሙሉ ሰው በእድሜ ዘመኔ አይቼ አላውቅም፡፡ በሰው ስም ስንሰማ የኖርኩት ሁሉ ለኔ የአውሬ ግዛት ፍካሬ ነው፡፡ ከብረት ዝገትን መከላከል እንደሚቀለው አይደለም፡፡ የሰው ስህተት መከላከያ የለውም፡፡

… በቅርብ የማውቀው እግዜር መንግስት ነው፡፡ የእኔን ቋንቋ ይናገራል፤ እኔ የሱን ግን አልናገርም፡፡ … ከሰው ሳይሆን ከፈጠረኝ አምላክ ብቻ ነው ከእንግዲህ መልስ የምጠብቀው፡፡ … ለምን ለምን ከነስህተታችን ተውከን? …. Lamma sabactani

 

 

 

 

 

 

 

Read 2706 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 12:04