Saturday, 14 January 2012 11:54

ንግግር ሲያንቀላፋ በምን ይቀሰቀሳል?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(4 votes)

ንግግር ሲያንቀላፋ በምን ይቀሰቀሳል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ታልሞ የተዘጋጀውን መፅሃፍ ነው ለዛሬ የማስቃኛችሁ፡፡ “አሻንቲ” ተብሎ የሚጠራ ነገደ ሕዝብ የዕድሜ ባለፀጎችና ምሁራን በበኩላቸው ለዚህ ጥያቄ ሲመልሱ “ንግግር ሲያንቀላፋ ታሪክና ምሳሌዎች ሞተር ሆነው ቀስቅሰው ያስነሱታል” ይላሉ፡፡ በርካታ አዝናኝ ቁምነገሮችን ያካተተውና “አምስተኛው ጉባዔ” በሚል ርዕስ በመጋቢ አእላፍ መክብብ አጥናው ተዘጋጅቶ ዘንድሮ ለአንባቢያን ከቀረበው መጽሐፍ ውስጥ አለፍ አለፍ እያልኩ አንባቢያንን ዘና ያደርጋሉ ያልኳቸውን እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

የነገሥታት ነገር አዋቂነት

በኢፌዴሪ የፓርላማ ስብሰባ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሚገኙባቸው ስብሰባዎች በሚያደርጉት ንግግርና በሚሰጡት ምላሸ መሐል በድንገት በሚያቀርቡት ቁም ነገር አዘል ቀልድ ተሰብሳቢዎቹንና በቀጥታ የሚዲያ ስርጭት የሚከታተሉትን ሁሉ ፈገግ እያሰኙ አግራሞት እንደሚፈጥሩት ሁሉ የቀድሞ ዘመን የአገራችን ነገሥታትም በነገር አዋቂነታቸው ዝነኛ እንደነበሩ ከአፄ ፋሲል፣ ከአፄ ቴዎድሮስ፣ ከአፄ ምኒልክ፣ ከፈታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ጋር በተያያዘ ማሳያ ሆነው የቀረቡ ታሪኮችን ይዟል መጽሐፉ፡፡

በአፄ ፋሲል ዘመን በጎንደር ከነበሩት ነጋዴዎች በአንዱ አረብ ሱቅ ውስጥ አንድ ሀበሻ ተቀጥሮ ሲሰራ፣ በአንዱ ሌሊት ሙሉ ዘረፋ ያደርግና ጠዋት ሱቅ ደጅ ላይ ተቀምጦ ሌባ ዘረፈኝ ይላል፡፡ አረቡ የሰማውን ስላላመነ ክሱን ለአፄ ፋሲል ያቀርባል፡፡ ንጉሡም ሁለቱንም የተለያየ ክፍል ያስገቡና እንደየሃይማኖታችሁ ከችግሩ ነፃ ለሚያወጣ አምላካችሁ ፀሎት አቅርቡ ይሏቸዋል፡፡

አደራ በላተኛው ቅጥር ሠራተኛ በመጀመሪያም ያልለፋበትን ንብረት የራሱ እንዲሆን ስለተመኘ ለአምላኩ ሲፀልይ ከዚህ ጉድ ካወጣኸኝ ከዘረፍኩት ግማሹን ላንተ እሰጣለሁ ሲል ዋናው ባለሀብት በተቃራኒ “አምላኬ ሆይ ንብረቱ የደከምኩበት መሆኑን ታውቃለህና ተመልሶ እጄ እንዲገባ ብታደርግልኝ ከመቶ ሃያውን ለድሆች እሰጣለሁ” በማለት ፀሎቱን አቀረበ፡፡ አፄ ፋሲል ሰዎች በፀሎት ቤት የሚያዳምጥ ሰው መድበው ስለነበር የማታ ማታ ሀብቱ ለዋናው ባለንብረት እንዲመለስ አደረጉ፡፡

ለድንግልና ክብር የተከፈለ 130 ሚሊዮን ዶላር

ባለታሪኮቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ልጅቱ በዋሽንግተን ዲሲ በአንድ ምግብ ቤት ተቀጥራ ስትሰራ ሚሊየነሩ ኢትዮጵያዊ በሬስቶራንቱ እየገቡ ሲገለገሉ ዕውቂያቸው ይጠነክራል፡፡ የልጅቱ በድንግልና መቆየት ያስገረማቸው ባለሀብት በክብር ሊያገቧት ይወስናሉ፡፡ ወደ ፈረንሳይ ሄደው በአንድ ደሴት ላይ ታላቅ ድግስ ተዘጋጅቶ ጋብቻው ተፈፀመ፡፡ ባለሀብቱ ድንግልናዋን ጠብቃ ለቆየችው ወጣት 40 ሚሊዮን ዶላር አበረከቱላት፡፡ ወንድ ልጅ ስትወልድላቸው 60 ሚሊዮን ዶላር አከሉላት፡፡ በተጨማሪ 30 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ዘመናዊ ቪላ ቤት በአሜሪካ ቨርጂኒያ ስቴት አሰርተው በምቾት እንድትኖር አደረጉ፡፡

የ”የአምስተኛ ጉባዔ” መጽሐፍ ደራሲ መጋቢ አእላፍ መክብብ አጥናው፤ ስለ አስገራሚው የድንግልና ታሪክ ካስነበቡ በኋላ በመቀጠል እንዲህ የሚል ጥቆማ አቅርበዋል:- “ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ታሪክ ባለቤት አሁን በኢትዮጵያ ብዙ የልማት አውታር ዘርግተው የታላላቅ አንዱስትሪ ተቋማትን በመገንባት በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን/ኢትዮጵያዊት የሥራ አጥነትን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ወደፊት ቃል በቃል አነጋግረናቸው ሲፈቅዱ በሁለተኛው እትም ሙሉ ስማቸው ይጠቀሳል፡፡”

የቀራትን ተጋፍታ ትግባ

ገበሬው ሚስቱ ትሞትበታለች፡፡ የንስሐ አባቱ ለሙታን መታሰቢያ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ገልፀውለት አርባዋን አስቆርብ ሲሉት ከሁለት በሬዎቹ አንዱን አርዶ ትዕዛዛቸውን ፈፀመ፡፡ በመቀጠል “አርባዋን ስላስቆረብህላት ወደ ነነት ለመግባት ተቃርባ በበሩ ላይ ቆማ ትገኛለች፤ ሰማኒያዋን ካላስቆረብህላት ግን እዚያው እንደቆመች መቅረትዋ ነው” ሲሉት የቀረው አንዱን በሬ ማረድ ልጆቹን ጦም ሊያሳድርበት መሆኑን የተረዳው ገበሬ “እንግዲህ እርስዎ እንዳሉት ከሆነ እኔ አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን አርባዋን አስቆርቤ ከበር አድርሻታለሁ፡፡ ካሁን በኋላስ ተጋፍታ ትግባ” የሚል ምላሽ ሰጣቸው፡፡

የባል ክሳት ሚስጥር

ሰውነታቸው ግዙፍ የሆነ ሸምገል ያሉ አንድ ሼህ በጣም ቀጭን የነበረች ሚስት አገቡ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ እርሳቸው እየከሱ እርስዋ ግን እየወፈረች መምጣቷን ያዩት ሼህ “አጀብ! አምና ይህን ጊዜ ይህ ሁሉ ሰውነት የእኛ ነበር እኮ” አሉ፡፡

የሔዋን አፈጣጠር

ሔዋን የተፈጠረችበት አጥንት ከአዳም የራስ ቅል ተወስዶ ለምን አልተሰራም? እግሩ ስር ካሉ አጥንቶች ያልተወሰደበት ምክንያትስ ምንድነው? መልሱ “እግዚአብሔር አምላክ ከባልዋ ጋር እኩል እንድትሆን ፈቅዶ (To be equal with him) ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጎን አጥንት አንሥቶ ፈጥሯታል፡፡ ባልዋ በክብር እንዲጠብቃት አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት (under His arm to be protected by her husband) በክርኑ ሥር ከምትገኝ አጥንት የፈጠራት ሲሆን ባልዋ ከልብ እንዲወዳትም ፈቅዶ (Near his heart) ከልቡ አጠገብ ፈጥሯታል፡፡”

ሴትና እውነት

የፋርስ ንጉሥ በዓለም ላይ አሸናፊ ሆኖ መቀጠል የሚችል ነገር ምን እንደሆነ ለባለሟሎች ባቀረበው ጥያቄ ያገኘው ቀዳሚ መልስ “ከንጉሥ በላይ ታላቅ ነገር የለም” የሚል ሆነ፡፡ ሌላኛው ይህንን በመቃወም ብዙ ታላላቅ ሰዎችን ማንበርከክ የቻለው አስካሪ መጠጥ (አልኮል) ነው ሲል መልስ ሰጠ፡፡ የፋርሱን ንጉሥ የሚያረካ መልስ ማቅረብ የቻለው ባለሟል ግን በመላው ዓለም ግንባር ቀደም አሸናፊዎች ሴቶችና እውነት ናቸው፡፡ ሴት ንጉሥን በፍቅር ትማርከዋለች፡፡ ሲጫወቱ ፊቱን በጥፊ ልትመታው ትችላለች - ይህን ማድረግ ከሷ ውጭ ማንም አይችልም፡፡ የስልጣናት ባለቤት የሆነው እውነትም እንደ ሴት ሁሌም የበላይና ቀጣይ ነው፡፡

በ160 ገፆች የተቀነበበው “አምስተኛው ጉባዔ” መፅሐፍ እነዚህን መሰል ታሪኮች፣ መዝናኛዎችና አስተማሪ ቁም ነገሮች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ አቅርቧል፡፡ በአባቶች የሚቀርብን ጨዋታ “አምስተኛ ጉባኤ” ብለው የሰየሙት አለቃ ገብረሃና ናቸው የሚሉት ደራሲው፤ መጽሐፋቸውን በአለቃ ገብረሐና በሰየሙት “በኩረ አርእስት” አሰናድተው ማቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡

 

 

 

Read 5659 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 11:58