Saturday, 21 February 2015 13:05

ኳስና ዴሞክራሲያ!

Written by  ኢዮብ ምህረተአብ
Rate this item
(15 votes)

“ኳስ ነጻ ጋዜጠኝነት ምን እንደሚመስል አሳይቶናል”

    Football ብዙም አልወድም፡፡ በልጅነቴ ኳስ ተራግጬ ስላላደግሁኝ ይሆናል፡፡ “ከ’ዱርዬ’ ልጆች ጋር እንዳትገጥም!” ተብሎ ያደገ ልጅ አታውቁም--።  ለመውደድ ሞክሬም አልተሳካልኝም….. የዋንጫ ጨዋታ ከጓደኞቼ ጋር እያየሁ ሰልችቶኝ አቋርጬ ወጥቻለሁ፣ ብዙ ጊዜ። ( I couldn’t help it)
ቢሆንም ቢሆንም ባየነው፣ በሰማነውና ባስተዋልነው ላይ ተመስርተን ኳስን በዚህ መልኩ ብንተነትነው  ምን ይለናል?
ሳስበው ሳስበው፡
የዲሞክራሲን  እሴቶች ለማስተማር ኳስ አንዱ Tool ነው፡፡
ብዙ ገጠር ዞሬያለሁ፣ በጣም ሩቅ፣ የተለያዩ ቦታዎች፣ እጅግ ልዩ ልዩ ባህል፣ ቋንቋ፣ አኗኗር…ያለው ህብረተሰብ ገጥሞኛል፡፡ ውሃና መብራት በሌሉባቸው መዓት ከተሞች ውስጥ ከርሜ አውቃለሁ፡፡ ዲሽ የሌለው ከተማ ግን almost አላጋጠመኝም፡፡ የከተማው ባለ ሆቴል ቤት፣ ዲሽና DSTV ያስገጥማል፤ ከዚያ  ፊልምና ኳስ ያሳያል፣ በጀኔሬተር፡፡ የሚገርመው የገጠር ልጅና የገጠር መምህር --- የሌለ ኳስ አዋቂ ሆነዋል። አንዳንዴ እርስ በራሳቸው ይከራከሩና ወደኔ ዞረው፤ “እስቲ አንተ ፍረድ” ይሉኛል፤ ‘ከትልቅ ከተማ ስለመጣህ መቼም ከኛ ትሻላለህ’ ነገር ነው። “ኳስ አልወድም” ስላቸው አያምኑኝም፣ ወይም ይደነግጣሉ፡፡
የዲሞክራሲን  እሴቶች ለማስተማር ኳስ አንዱ Tool ነው፡፡
ከምሬ ነው፡፡ ባህላችን፣ ታሪካችን፣ አስተሳሰባችን ---- ብዙው ነገራችን በሁለት ጽንፍ የተከፈለ ነው:: ቅልቅል፣ ማሻሻል ወይንም መቀየር ብሎ ነገር የለም። አንዱ የሰይጣን አንዱ የፈጣሪ፣ አንዱ ነጭ ሌላው ጥቁር የሚል ጥልቅ ፍልስፍና ብዙውን እሳቤ ይመራዋል፣ (ይመስለኛል)፡፡ ይሄ ነገር የሀይማኖት፣ የኑሮ፣ የባህል ድጋፍ አለው፡- እገሌ ወይ ክፉ ነው ወይ ጥሩ ነው፤ መንግስት ወይ መጥፎ ነው ወይ መልአክ ነው፤ የእኛ ትክክል፤ የእነእገሌ ግን-- ፣ የድሮ ቺክህ ጋኔን ነች፣ ያሁኗ ግን መልአክ፡፡ Neo liberalism የሸረኞች ideology ነው፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግን ገነት ነው …….. በምንም ጉዳይ ጽንፈኝነት ብቻ!
ይሄ ጽንፈኝነት ወደ ገጠር ስትሄድ ይጨምራል፡
ለምን?
ቀላል ነው፡፡
የዕውቀት እጥረት ስላለ፣ ችግርና ኋላቀርነት ስለተጣመሩ፤ ሌላ አለም እንዴት function እንደሚያደርግ ለማየት እና ለማስተዋል አጋጣሚው ጠባብ ስለሆነ፡፡ የባልዲ ውስጥ እንቁራሪት ይመስል ከተቀረው አለም ተለያይተን ጠቃሚ እውቀት፣ Structure እና አሰራር ሳንኮርጅ፤ ምንም ነገር ሳናሻሽል፣ ሳንሞክር፣ የሞከረውንም መሪ ጥለን (Remember ቴዎድሮስ!)  እርስ በርስ ስንፋጅ ስለኖርን፡፡
አሁንም በቅጡ አለቀቀንም፡፡
…..ብቻ አሁን አሁን ትንሽ መንገድ እና ትራንስፖርት ስለተስፋፋ የተወሰነ መዟዟር ተፈጠረ እንጂ ብዙው ሰው ከጎጡ ሳይወጣ እዚያው ተወልዶ አድጎ፣ አግብቶ፣ ወልዶ፣ ሞቶ፣ ይቀበር ነበር፡፡ ጎጥ ማለት ባልዲ ማለት ነው፤ ትልቅ ከኒኬል የተሰራ የዱሮ ባልዲ፣ የቤት ሰራተኛችን ወደ ግራ ተንጋዳ በቀኝ በኩል ውሃ የምታመላልስበት ባሊ፣ ዘመዱ ቧንቧ ብቻ የሆነ ባሊ፤ ከምር!
ድንገት ያ ባሊ ውሃ ሳይሆን ነዳጅ አለው ብንባል፣ አለቀልን!....ራስን የማስተዳደር የመብት ጥያቄ ትዝ ይለናል፡፡ ‘ተጨቆንን’ የሚሉ አዳዲስ narratives ከች ይላሉ፡፡ ሌሎች የቂል ዜማዎችም ይፈጠራሉ፡፡
ወደ ኳስ እንመለስ….
….እና ገጠር ዲሽ በመግባቱ ገጠሬው ቁጭ ብሎ የሌላን አለም activty ማየት ጀመረ፡፡ አንደኛው ኳስ ነው፡፡ ኳስ ደሞ ላይ ላዩን ስሜትና  መዝናናት መስሎ  Dynamism ይዞልህ መጣ፣ ያልታሰበ፡፡ ከምሬ ነው፣ ዲሞክራሲ እና ነጻነት ምን እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ኳስ አሪፍ Tool ነው። የትኛውንም ክለብ ብትደግፍ ችግር የለውም። የዘር፣ የሀይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኑሮና የሙያ ልዩነት ተጽዕኖ አያመጣም::
በኳስ አንተ የምትደግፈው ክለብ ተጫዋች ወደ ተቃራኒ ክለብ ይቀላቀላል፡፡ የ’እንትን ክለብ እንበል ተሸንፎ፣ ‘እውነት ነው፣ ደካሞች ነበርን፣ ተበልጠናል’ ይላል፡፡ የ’እንትን ክለብ አሰልጣኝ ደሞ  ደጋፊዎቹን በይፋ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡
የትም ሂድ፣ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ያለ ወጣት፤ ‘Balatoli ስንት ያወጣል?’ ብሎ ይከራከራል (ብቃቱን ገምግሞ ማለት ነው) ”የኔ ቡድን ትልቁ ድክመት defense ላይ ሰው የለም፣ ስስ ነው” ይልሃል፡፡ “ቬንገር ለምን ደህና ተጫዋች አይገዙም?” ይሞግታል፡፡ የእንትና Performance የጨመረው በእድል ወይም በጸሎት ሳይሆን በራሱ ጥረት ራሱን እያሻሻለ፣ እየበሰለ ስለመጣ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ … ‘Messy በዘንድሮ ብቃቱ የዓመቱ ምርጥ ተብሎ መሸለሙ አይገርምም’ ይልሃል፤ በእድል ወይንም በዘመድ ሳይሆን በችሎታው እንደሆነ አይጠፋውም። ዋንጫ ካላመጣ፣ ሞሪንሆ ሊባረር እንደሚችል ካሁኑ ይተነብይልሃል፡የፈለገ ያገሩን ቡድን ቢደግፍም፣ ስለት ቢሳልም፣ በአፍሪካ ዋንጫ የቡድናችንን መሸነፍ ከእድለ-ቢስነት ወይንም ከእርግማን ጋር የሚያገናኝ በትምሮ ያልገፋ የገጠር ኳስ አፍቃሪ እንኳ ያለ አይመስለኝም… በችሎታ መበለጣችንን (ተስፋ ቢኖረንም) ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ምንም በኛ ቡድን መሸነፍ ቢቃጠልም ለአፍሪቃ ዋንጫ መድረሳቸው በራሱ ለውጥ እንደሆነ ያስረዳሃል፡፡
ቡድናችን አንዴ በሱማሌ የተሸነፍነው፣ የሶማሌ ደጋፊ መርቅኖ ዱአ አድርጎ ሳይሆን ብቃት ስላልነበረን እንደሆነ ያውቃል፡፡ ለብዙ ዘመናት ግብጽ ኳስ የምታሸንፈን ተመቅኝታን ሳይሆን ነባራዊ ብቃታቸው ከኛ የተሻለ ስለሆነ ነው ብሎ ይሞግትሃል፡፡
እና፣ ከዚህ በላይ ምን ማስተማሪያ አለ?
ዲሞክራሲም በግርድፉ ካየነው ተመሳሳይ ነው።
የዲሞክራሲ ጽንሰ-ሀሳብ ውስጥ ነጻነት የሚባል ትልቅ እሳቤ አለ፡፡ አንደ መንጋው ሳይሆን እንደ ራስህ የማሰብ ነጻነት፣ ሃሳብህን ሳትፈራ የመግለጽ ነጻነት፤ ብቃት ያለውንና በስነ-ስርአት አስተዳድሮ የተሻለ ዕድል ያመጣልኛል ብለህ ‘ምታምንበትን ፓርቲ/ስርአት የመምረጥ፣ ያልፈለከውን የመቃወም ነጻነት፣ ወዘተ…፡፡ አንድ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች እርስ በርስ በሃሳብም ይሁን በምንም ሊለያዩ ይችላሉ፣ አብረው ግን ይቀጥላሉ (ሒላሪና ኦባማ)፣ የእንትና ፓርቲ ደጋፊዎች ላ’ገር አሳቢዎች፣ የእንትና ግን ምቀኞች አይደሉም፡፡
ልደቱን ማንዴላ ብሎ ሰቅሎ፣ ከዚያ ይሁዳ ብሎ መርገም፣ ስዬ አብርሃን ጀግናችን ብሎ አሞግሶ፣ ሲለያዩ እንደ ከሃዲ መቁጠር፣ እንትና የተባለው ባለስልጣን ሊመታ ሲል ካርድ መምዘዝ……የሚባል ነገር በዲሞክራሲ አለም አይሰራም፤ በኳስም አለም የለም፡፡
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም ያልሰሩ ጋኔን አድርጎ መሳል፣ ወይንም በተቃራኒው የማይሳሳቱ፣ አጥፍተው የማያ’ቁ ጻድቅ  አድርጎ መፎጋገር በኳስ አለም የለም፡፡ በዲሞክራሲ አለምም እንደዚያ ነው፡፡ የመናገር ነጻነት አለ፤ ‘ፓርቲዬ በዚህ ደካማ ነው፣ በዚህ ደሞ ጥሩ ነው’ ማለት ትችላለህ፤ አትገመገምም። የፈለገ ሮናልዶን ባትወደው የማይረባ ተጫዋች እንዳልሆነ ታውቃለህ፣ የባርሴሎና ደጋፊዎችም ይህንን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ  ታውቃለህ፡፡ ጽንፍ ብሎ ነገር የለም፡፡ በኳስና በዲሞክራሲ!
አዎ! የዲሞክራሲን  እሴቶች ለማስተማር ኳስ አንዱ Tool ነው፡፡የሰው ልጅ የሚለካው ልፋትን እና ሳይንስን መርህ ባደረገ ብቃቱ እንጂ፣ በዘሩ፣ በምላሱ ወይንም በኮኔክሽኑ አይደለም፤ ድክመትን ጣጣ ሳያበዙ መቀበል ፋርነት አይደለም፡፡ ዲሞክራሲም ኳስም ይሄንን እውነታ ይጋሩታል፡፡
ከትላንት ወዲያ የአዳም ዘር ጃህን፣ “ስዩመ-እግዚአብሄር፣ የሰለሞን ዘር” ብሎ ሰገደ፣ ትላንት ሲጠመዝዙት “ኢምፔርያሊዝም፣ የነብሰ-በላዎች አገዛዝ፣ በቅርቡ ይጠፋል” ብሎ ፎከረ፡፡ ዛሬ ‘ያለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አለቀልን፣ እንበታተናለን’ ይልሃል፣ ፍሬሽ ካድሬ፤ ጽንፈኛው ተቃዋሚ ደግሞ “ስርአቱን ካልናድነው አገሪቷ ገደል ገባች፣ ምን ትጠብቃለህ?”  ትባላለህ፡፡
…ይሄ የተበላ እቁብ ነው..ይሄ  ጆካ ነው…ዴሞክራሲም ኳስም በዚህ እሳቤ አይመሩም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ጋዜጠኞች (የግልም በለው የመንግስት) የስፖርት ጋዜጠኞችን ያህል በነጻነት critical እና ጥልቅ ትንታኔ የመስጠት፣ እንዲሁም እንደፈለገ የመተቸት እድል ያለው የሌላ ዘርፍ ጋዜጠኛ ያለን አይመስለኝም፡፡ ’ስለማያነካካ’ ነው (ግልጽ ነው)፡፡
‘ኦ! ያ! ያ! ያ!’ እያለ ቢያሰለችህም፣ ወይንም አራት ነጥብ የሌለው ረጅም ቶክ ቢቀድም፣ ሁሉም ነጻነታቸውን እንደ ልብ ሲያጣጥሙት ታያለህ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲሻሻሉም ትታዘባለህ (በ’ውቀትም፣ በSponsorም፣ በኑሮም) ሁሉም የየራሳቸው አድናቂና አድማጭ አላቸው፡፡
ስለዚህ ኳስ ነጻ ጋዜጠኝነት ምን እንደሚመስል አሳይቶናል ማለት ነው፡፡
…ህምም--
ቪቫ ኳስ!!

Read 6181 times