Saturday, 21 February 2015 13:05

ከትዝታ ማኅደር እንዴት አስታወስኩት?

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(2 votes)

     በኛ ጥር 1984  መሆን አለበት። በፈረንጅ 1992  መሆኑ ነው። አሜሪካ ገና እንደመጣሁ  ኒው ዮርክ፤ኒው ዮርክ (New York,New York) ሦስት ሳምንት የሰነበትኩት አለአዛር ደሴ ቤት፤ማንሀተን Manhatten ነበር። አሁን እንዳወቅሁት ማንሃተን ከኒው ዮርክ በጣም ውዱ አካባቢ ነው። እንደገናም ሳንገናኝ አለአዛር ወርደ ኢትዮጵያ ሔደ። ከዚያም ታሰረ የሚል ሰምቼ አዘንኩ። ባለውለታዬ፤ከብዙዎቹ አንዱ ነው።
በኋላ ወደ ዋሽንግተን  ዲ.ሲ (Washington, D.C) መጣሁ። እዚህም እዚያም ና ከሚሉኝ ውስጥ የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር Friends of Ethiopia Association አንዱ ነበር። የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር በየምክንያቱ ኢትዮጵያን የሚያውቁ፤ እናውቃለን የሚሉትንም የሚያሰባስብ ነው። በመንግስት ስራ፤ አስተማሪነት ፤ ፒስ ኮር ፤ዲፕሎማቲክ አገልግሎት ይጨምራል። (ስለላ ዲፕሎማቲክ አገልግሎት ውስጥ የሚጨመር ይመስለኛል።)
ለመጋበዜ  ዋና ምክንያት የሆኑት  ዲን ፖል Dean James Paul ይመስሉኛል። ዲን ፖል የዩኒቨርሲቲውን የህግ ትምህርት ቤት ያቋቋሙ፤ የመጀመሪያው ዲን የነበሩ፤ Constitutional Development in Ethiopia  የሚል መጽሐፍ ከክልፈም  Clapham ጋር ያዘጋጁ ናቸው፡፡ በኋላም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንትም ነበሩ። በነሐሴ 1983 ሌላ የህግ ትምህርት ቤት መምሀር ከነበረ፤ አሁን ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከሚያስተርም  Fisher  ጋር አዲስ አበባ መጥተው ነበር። ዘገየ አስፋውን ጨምሮ ሌሎችም ባሉበት  አንድ የጋሞ ሰው ምግብ ቤት ድል ያለ ግብዣም አድርገንላቸው ነበር። ብቻ አዲስ መንግስት ሲመጣ “ ምነው በደህና?”፣ “ምን አመጣችሁ?”፣ ”እንዴት አወቃችሁ/ተዋወቃችሁ/ መምጣት ቻለችሁ?”፣ “የመግቢያውንስ ፈቃድ ማን ስጠችሁ?” “በማን በኩል?” የሚለውንና የመሳሰለውን ጥያቄ፣ ያኔም ከዚያ መልስም አልጠየቅሁም። ምን ፋይዳ አለው! በዚህም ላይ 2+2 ሲደመር 4 መሆኑ የታወቀ ነው። Self Evident Truth - የአደባባይ ሚስጥር የሚባለዉ አይነት መሆኑ ነዉ። ይልቁንም አንድ ለንጉሱም ለደርግ ዘመንም የሚስጢር ጉዳይ የሚያዉቅ ወዳጄ ይህንን ነገር ጫወታ ላይ አንስቼበት፤ “ይኸ ያንተ ዲን በፊትም የሚሰራው የትርፍ ጊዜ ስራ ነበረው” ብሎ አንዳንድ ነገሮች ጣል ጣል አደረገልኝ። ሰው ለእናት አገሩ ለአባት አገሩ መሰለል/ ማነፍነፍ ያለ ነው። ነገሩ አነፍናፊውን ማወቁ ጥሩ ነው ለማለት ነው።
ቆየት ብሎ በዚህ በኢትዮጵያና  ኤርትራ መካከል በነበረው ጦርነት ለተፈጠረው ለአስታርቂ ይሆን አካካሽ ኮሚቴ፣ ዲን ፖል አባልም ነበሩ። የትኛው ወገን/መንግስት ነው የመረጣቸው? ሁለቱም በርሳቸው ላይ ተቃዉሞ አልነበራቸውም ማለት ነው?  አንዳንዱ ነገር መልሱ በሙሉ ላይታወቅ፣ የሚቀጥለውንም ጥያቄ ጠይቅ የሚል መገፋፋት አለው።
የዚያን ለት እኔን ለመቀበል የተገኙት ወደ 10 ይጠጋሉ። የአሜሪካን መኳንንትና ምሁራን ናቸው። ይመስላሉ። ከዲን ፖል ሌላ አንድ ቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ፤ሌላ፤ብዙዎቻችን የምናውቀው የሚመስለኝ ፖል ሔንዜ Paul Hanze፤ የEmpress Taytu and Menilek II of Ethiopia, 1883-1918 የጻፉት ክሪስ ፕርውቲ Chris Prouty ከነባለቤታቸውና አንድ ሁሉም ሰው አንቱ አንቱ  ሊሏቸው የሚፈልጉ፣ ስራቸው ምን እንደሆነ የረሳሁት፣ ያደባባይ በሚሆን መልክ የለበሱ ይገኙበታል።
አምባሳደር የነበረው ሰውየና ሔንዜ ስለ ኢትዮጵያ ያለቀለት አስተያየት ይሰጡና የኔን አስተያየት ይጠይቃሉ። የኔ አስተያየት የሚገባበት ቀዳዳ ፈልጌ አላገኝምና በትህትና አልፈዋለሁ። ኢትዮጵያን ማወቃቸውን ሊነግሩኝ ፈልገው ሊሆን ይችላል። ወይም የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያውቃት መንገራቸው ይሆናል። ድሮ ሁለተኛ ደረጃ እያለሁ ያነበብኩትን  The Ugly Americanን አስታወሰኝ።
እኝህ አንቱ የተባሉት ሰው ፤ከብዙ ዝምታ በኋላ በመገረምና  “እኔ አላምንም!” በሚል ቃና፤ “You are different”(አንተ ለየት ትላለህ!) አሉኝ። ያሉት ነገር መድረኩ ላይ ካለው ጫወታ ጋር የሚሔድም አልነበረም። ሰምቼ እንዳልሰማ ሆኜ ወደተጀመረው ተመለስኩ። አንድ 10 ደቂቃ ይሆን እንዲያ ቆይተው ያንኑ ደገሙት።
“አንተ ለየት ትላለህ!” አሉ።
አሁን ፊቴን ወደሳቸው ሙሉ ለሙሉ መልሼ፤  “እንዴት ነው  የምለየው? ከምን/ ከማን ነው የምለየው?” አልኩኝ፤ አቶ ሐዲስ አለማየሁ “ፍርጥም ብሎ!” በሚሉት መልክ። አስረዱኝ! ወይም ሊያስረዱኝ ሞከሩ።
“የምትናገረውን በድፍረት በሙሉ ልብ ስትናገር!” አሉ።
   “እና ከማን ጋር አወዳድረውኝ ነው የተለየሁት?” አልኳቸው።
“Generally spkeaing” (እንደሁ ጠቅለል ባለ አነጋገር ማለቴ ነው!) አሉ።
“አልገባኝም!” ያንኑ ቃላት ለዋውጠው ደገሙልኝ።
 “አልገባኝም!”
“ምኑ ነው ያልገባህ?”
“አንድ ነገር ለመለየት፤ለመብለጥ ፤ለማነስ ከሌላ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ነገር ጋር መነጣጠር አለበትና ከምንና ከማን ጋር እንዳወዳደሩኝ ለማወቅ ፈልጌ ነው”  አልኩኝ ፤ያው ፍርጥም ብዬ!  ከዚያ ነገሩ መንገድ የሚለቅ መስሏቸው ዲን ፖል ሲገቡበት፣ እስቲ  እኔ የገባኝን ላስረዳ ብዬ በጥሞና ወደ ሰውየው ዞርኩ።
“እናንተ ቅድስት አገር ስትሉ እስራኤልን፤ እየሩሳሌምን ነው። ኢትዮጵያዊ ቅድስት አገር ሲል ኢትዮጵያ ማለቱ ነው። ገነትን ከከበቡት አራት ወንዞች አንደኛው ግዮን መሆኑን ታውቃለህ አይደለም? ምዕራፉንና ቁጥሩን ጠቀስኩለት። “ግዮን ያለው ኢትዮጵያ ነው። አባይም እንለዋለን። ከዚያ ከኢትዮጵያ ሲወጣ ናይል አላችሁት። እዚያ ውስጥ አሁን አልገባም። የሶስት ሚሊዮን ዓመት የሰው አፅም ሉሲ የተገኘችው ከኢትዮጵያ መሆኑን ሰምተህ የለ ? ያች ሔዋን ልትሆን ትችላለች። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መጠንሰሻም መሆኑ ነው። ክርስቲያን ነህ አይደለም? በሩን የከፈተች ኢትዮጵያ ነች። የሐዋሪያት ስራ ምዕራፍ 8ን አንብበው።  ከዚህ ታሪካዊ ነጭ፤ ፈረንጅ የበላይ ነኝ ብሎ ነው አይደል የሚያምነውና የሚያስበው? ያ የትላንት የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው። ያ ትእቢት ነዉ። ታሪክና ትእቢት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የግብፅን ፒራሚድ ትዉቃለህ አይደል? ያ ብቻ አይደለም:: ወረድ ብለህ ሱዳን -- ኢትዮጵያ ያሉትን ፒራሚዶች ጎብኝ። አክሱም፣ ላሊበላና ሌላም ብዙ ብዙ አለ።
ከዚህ ከኦሪትና  ክርስትና፣ መሬትም ላይ በቆመው የታሪክ ምስክርነት የተነሳ ኢትዮጵያዊው ኢትዮጵያንና ራሱን ለየት ያለ መሆኑን አምኖ ተቀብሎ የሚኖር ህዝብ ነው። ይህንን ሌሎች አወቁለት አላወቁለት የሚል ሃሳብም የለበትም። እንዴት ላያውቁ ይችላሉ? የሚል እምነት ያለን ይመስለኛል:: ኢትዮጵያዊ ሌላውን አይንቅም። ከኢትዮጵያዊ የሚበልጥ ነገድ ይኖራል ብሎ ደግሞ ጭራሽ ሊያስብም አይችልም። ኢትዮጵያዊ ከሁሉም ይልቃል!፣ትበልጣለችም! ብሎ  አፉን ሞልቶ ሲናገር ባይሰማም በውስጡ እንዲያ የሚያምን ይመስለኛል። አሁን አንተ የተለየህ ነህ ያልከኝ የተለየሁ አይደለሁም። ኢትዮጵያዊ ነኝ። ያንን ትንሽም ቢሆን የታዘብክ ይመስለኛል::
ስታነጣጥረኝ የነበረው እዚሁ ከምታውቀው ከእናንተው ጥቁር አሜሪካዊ ይመስለኛል። እሱማ ተሽጦ፤ተለውጦ፤ሰብእናው ተዳሽቆ፤ የቀረው ሰው ሳይሆን የሰው ጥላ ነው። አሁን አሁን በዚህ በትምህርትና በመሳሰለው ከኔ በፊት አንድ ሁለት ትውልድ  ፈረንጅን የተቀበለው ይመስላል እንጅ ከዚያ በፊት የነበረው ፈረንጅን እንደጉድ! ለምጥ እንደወረረው ፍጡር! ነበር የሚያየው። በዚህ ላይ ቅኝ ግዛት አለመሆን ብቻ ሳይሆን ፈረንጅን አፈር ድሜ ያስጋጠ ህዝብ ነው” አልኩት። ብቻ ሌላም ሌላም ብየዋለሁ:: ለአሁኑ እንለፈው።
ሰውየው የተናገርኩትን አጣጥመው አንዳች ሳይናገሩ ዲን ፖል ጠረጴዛ እየመቱ በሳቅ ሞቱ። “አሰፋ! አሰፋ! ለአመታት ያስቸገረኝን እንቆቅልሽ Enigma ዛሬ ፈታህልኝ!” አሉ። እንዴት? ሲባሉ፣ ኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ የታዘቡትን ግን ትርጉም ሳይገኝላቸው የኖረውን አስረዱን። “የልጅ ካሳ ወልደ ማርያም፤የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት፤አቶ ዉብሸት ድልነሳሁ፤ምክትል ፕሬዚዳንት ሌሎች ብዙ የቅርብ ባለስልጣንም ሆነ ያልሆነ፤ቤታቸው የምሔድ፤ቤት የሚመጡ፤ለአመት በአልም ሆነ ዘወትር የምንገባበዝ ጓደኞች ነበሩኝ። እኔ ከልቤ ጓደኞቼ ናቸው እላለሁ። እነሱ ያንን ያክል አልተቀበሉኝም:: ይልቁንም የመቻል “ይሁን እንጅ” Condiscending አይነት፤በደንብ ያልተገለጠ፤እኔ የሚሰማኝ የውስጥ ቅሬታ የሚመስል ነገር ነበርኝ። አሁን ስለ ኢትዮጵያና  ኢትዮጵያውያን ስትናገር ያንን እንቆቅልሽ Enigma  ፈታህልኝ። እንደገባኝ ከሆነ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ሲቀበል በር በርግዶ ውስጥ ጓዳ ድረስ አያስገባም ማለት ነው” አሉ።
ከዚያ ሌሎችም የመሰላቸውን፤ የገባቸውን፤ያ ልገባቸውንም ጨማምረዉበት በዚሁ ታለፈ።
ከዚያ ጋብ ሲል፤ ተነስቼ የEpressTaytu and Menilik the II of Ethiopia ደራሲ የሆኑትን ክርሲ ፕሮውቲን አመሰገንኩ። “ጣይቱን ከተረዱ፤ተረድተውም ለሌላው ገልጠው ማሳየት የቻሉ ይመስለኛልና ኢትዮጵያን ለማወቅ ጥረት ያደረጉ ሰው ነዎት። ለዚህም ባለውለታችን ሆነው ለዘለአለም ይኖራሉ!” ብዬ መቀመጫቸው ሔጄ፣ አቅፌ ጉንጫቸው ላይ ሳምኳቸዉ። ሔኔዜም አምባሳደሩም መጽሐፍ ጽፈናል ባዮች ናቸውና ሳይቀየሙኝ የቀሩ አይመስለኝም።
ከዚያ የኢትዮጵያ ወዳጆች ማሕበር የወቅቱ ሊቀ መንበር ሔንዜ ነበርና ውይይቱን ሲዘጋ ጎንተር አደረገኝ። “በዲን ፖል በኩል ሁለቴ ቀጥሮ ተይዞለት ሁለቱንም አፈረሰው” አለ። ዲን ፖልም አረጋገጡ። በነሐሴ 83 አዲስባ መጥቶ ኖሮ፣ አንድ ሁለት ሰው ፖል ሔንዜ የሚባል ሰው በጥብቅ ይፈልግሀል ብለውኝ ነበር። እኔ ደግሞ በጥብቅም በልልም የምፈልገው ሰው ስለአልነበር ፍለጋው ቦታ ጊዮን ሆቴል አልሔድኩም። በዚህ በሶስተኛው ቀጠሮ  ዋሺንግቶን ዲ.ሲ አንድ ሆቴል ተቀጣጥረን፣  ገና ቡና እንኳን በደንብ ፉት ሳልል የጠየቀኝ ጥያቄ ወደ “ፈግጠው !ፈግጠው!” አመራና በዚሁ ተለያየን። አንድ ቀን በዚህ ጉዳይ መመለሴ አይቀርም።
ዲን ጀምስ ፖል በዚህ ሁሉ ውስጥ ”እዩት የኛን ልጅ!” የሚል አይነት የኩራት መንፈስ አይባቸው ነበር። ስንወጣም ይህንኑ ነገሩኝ።
Emperess Tayitu and Menilik  II ,1883-1910 ን  ከፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት  Memoir ጋር ማንበብ፤ያነበበም ቢሆን  ደጋግሞ ማንበቡ ጥሩ ይመስለኛል። የንግስቲቱንም የአድዋንም ጦርነት ታሪክ እንደገና በአዲስ ዐይን እንድናይ የሚጋብዘን ይመስለኛል።

Read 3512 times