Saturday, 21 February 2015 13:00

የካይሮ የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

ከውሃ ወደ ውሃ

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑካን ፕሮግራም የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ምን ያህሉን በሥራ ላይ እናውለዋለን? እያልን ነው ካይሮ የገባነው። እኔ ካይሮ ስሄድ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፡፡
ብዙዎቻችን እንደዚያው ነን ብዬ ገምቻለሁ፡፡ ከፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ጋር ቦሌ ኤርፖርት አብረን ነበርንና እሱ የጐልድ ሜምበር ስለሆነ ባለው መብት ላውንጁ ውስጥ ቢራ ጋብዞኝ ጠጥቼ ነው ከሌሎቹ ተጓዦች የተደባለቅሁትና ብርድ አልተሰማኝም፡፡
 (ካይሮ ከ16-20 ዲሴምበር 2014)
ማክሰኞ ዲሴምበር 16/2014
(ከተከበሩት የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የሚደረገው ውይይት ቀኑ አልተቆረጠም)
ካይሮ ይደረሳል
ወደፈርሞንት ናይል ሲቲ ሆቴል ይኬዳል
የ15ኛው ዓመት የግብፅ የውጪ ጉዳይ ምክር ቤት  ግብዣ በኮንራድ ሆቴል
ባረፉበት ሆቴል - እራት
ዕሮብ ዲሴምበር 17/2014
ታላቁን የአል አዝሃር ሼክ ዶ/ር አህመድ አልታይብን ማግኘት
ምሣ ባረፉበት ሆቴል
የተከበሩ ጳጳስ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ጋር መገናኘትና የካቴድራል ጉብኝት
የቱሪዝም ሚኒስቴር የራት ግብዣ በናይል ማክሲም
ሀሙስ ዲሴምበር 18/ 2014
ከአረብ ሪፑብሊካዊት ግብፅ ፕሬዚዳንት ጋር ስብሰባ በባህል ሚኒስቴር በተዘጋጀው የዘመናዊ ጥበብ ሙዚየምና ኦፔራ ሃውስ ጉብኝትና ከግብፅ ምሁራንና ፀሐፍት ጋር የሪሴፕሽን ግብዣ
በአልአህራም ጥናት ማዕከል  የስብሰባ ግብዣ ከምሳ ጋር
ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት  
የባህል ትርዒትና የእራት ግብዣ
ዓርብ ዲሴምበር 19/2014
የቱሪስት ፕሮግራም ወደ ፒራሚድና ስፊኒክስ ጉዞ
በአላዝሃ ፓርክ የምሣ ግብዣ በቱሪዝም ሚኒስቴር
ከግብፅ የዲፕሎማሲ ልዑክ ጋር ስብሰባ
በማረፊያ ሆቴል የቴሌቪዥን ኢንተርቪው
የራት ግብዣ በሚስተር አይማን ኢሳ የኢትዮ - ግብፅ ቢዝነስ ምክር ቤት
ቅዳሜ ዲሴምበር 20/2014
መልስ ወደ አዲስ አበባ
“ግብፅ’ኮ ነው የተሠራው!”
(የካይሮ ባለሱቅ)
ካይሮ እንደፈራሁት ቆንጆ ናት ከፊት ለፊት። የሚገርም ግርማ - ሞገስ ካለው ሆቴላችን ሆኜ ቁልቁል ስመለከት ዐባይ (ልክ እንደቸርቸር ጐዳና በሉት) ሽንጡን ዘርግቶ ማህል ለማህል ተንሰራፍቷል፡፡ ላዩ ላይ ጀልባዎችና መርከቦች ዐባይ የእኛ ነው በሚል ስሜት ይንሳፈፋሉ፡፡ ዕውነት ያው የእኛው ዐባይ ነው? የሚል የአበሻ ጥያቄያዊ ስሜት መፍጠሩ አይታበሌ ነው! ዐባይ ላይ በወርዱ ሁለት ሶስት መሻገሪያ ድልድይ ተዘርግቶበት ይታያል፡፡ ግብፆች እንደኛ፤
“ዐባይን ቢሞላ
ዞረሽ ነይ በሌላ!”
የሚለውን ዘፈን የሚያውቁት አልመሰለኝም። እኛ ካለንበት ዐባይን አሻግሮ ሲያዩ፣ እኛ ስሙን በኳስ ቡድኑ ብቻ የምናውቀው የዛማሌክ ከተማ አለ፡፡ ዐባይን በድልድዩ ሠንጥቀን አልፈን ከ10-15 ደቂቃ በእግር ተጉዘን ያገኘነው በኋላ ያየነው ከተማ ነው። ሞቅ ያለ ከተማ ነው፡፡ ሱቆቹ የደመቁ ዘመናዊነት ዘመናዊነት የሚሸት ከተማ ነው፡፡ አንድ ትልቅ ትምህርት ያገኘሁበት ቦታ ነው፡፡ ይህንኑ ትምህርት ውዬ አድሬ የእነሱ መርካቶ ዘንድ ሄጄ ሰምቼዋለሁ፡፡ ትምህርቱ ምን መሰላችሁ?
ሱቅ ገባሁና፤
“ይሄ ሸሚዝ ስንት ነው?” አልኩት ባለ ሱቁን፡፡
ዋጋውን ነገረኝ፡፡
ግብፅ እንደኢትዮጵያ “እርግጡን በል!” ማለት ይቻላል፡፡
“ቀንስልኝ” አልኩት፡፡
“አሃ! ይሄ የቻይና መሰለህ እንዴ? Made in Egypt! እኮ ነው” አለኝ፡፡ ግብፅ እኮ ነው የተሠራው እንደማለት፡፡
ይሄንን ስሰማ አዕምሮዬ ወደ ዳርማር፣ አስኮ፣ ካንጋሮ ….ጫማ ሄደ፡፡ መቼ ይሆን እኛ፤ “ይሄኮ ኢትዮጵያ ነው የተሠራው!” ብለን ለመኩራት የምንችለው? አልኩኝ በሆዴ! በጣም ቀናሁ!
የዘማሌክን ከተማ ሱቆች እንደ ካይሮ ፒያሳ ቆጥሬ ባስብ፤ የካይሮን መርካቶ ደግሞ እንደራጉዔል አካባቢ ብቆጥረው አያስገርምም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዱ የካይሮ ክፍለ - ከተማ በወፍ-በረር ሳየው ተጀምሮ ያላለቀ ከተማ ይመስላል፡፡ እንደውም     “የካይሮ ኪቤአድ እንደ አዲሳባው ኪቤአድ ሁሉ ቤት አያድስም” ተባብለናል፡፡ አንድ ወዳጄ ደግሞ “ኪቤአድ በየትም አፍሪካ አገር እናቱ አንድ ናት!” ብሎ አስቆናል፡፡
መርካቷቸው ውስጥ “ከእኔ ግዙ፣ ከእኔ ግዙ” እያሉ ልብሳችንን የሚጐትቱ ብዙ አይተናል። ከእንዲህ ያሉት ነጋዴዎች አንድ እንግሊዝኛ የሚችል፣ በእኛ አገር ሚዛን ነጋዴ ነው ሊባል ፈጽሞ የማንጠረጥረው ቦጀቦጅ ልጅ አጋጥሞናል። ውፍረቱ (Obesed እንደሚሉት) የሚያስደነግጥ፣ ፍጥነቱ ደግሞ በጣም የሚያስደንቅ ልጅ ነው፡፡ የድብቅ ዕቃ የሚሸጥልን ይመስል ሁለት ደረጃ አስወርዶን ምድር ቤት ከተተን፡፡ በባህል ዕቃ ግጥም ያለ፣ ለዐይን የሚያደክም ቅርሳቅርስ ተጠቅጥቆበታል፡፡ ዐይን አዋጅ ሆነብን፡፡ እንግሊዝኛ ሲናገር አፉ - ጤፍ ይቆላል የሚባል ነው - በካይሮ እንግሊዝ ውድነት፡፡ የሚገርመው ካይሮ እንግሊዝኛ በጣም ውድ ነው፡፡ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስለነበሩ ያንበለብሉታል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ሆኖም፤ ቢያንስ እኛ ያገኘናቸው ግብፆች በብዛት እንግሊዝኛ ደጃቸው ያልደረሰና እኛ መናገራችን ጭምር የሚያናድዳቸው ናቸው! “ዐረቢኛ እያለላችሁ?!” ያለኝ ግብፅ አጋጥሞኛል፤ በእንግሊዝ ጉዳይ ታክሲ ላይ ብዙ ችግር ገጥሞናል። ሌላው በታክሲም፣ በሆቴሉ ሰርቪስም ስንሄድ ግራ ያጋባን ነገር፣ የካይሮ መኪናዎች ጥሩምባ ብዛት/ክላስክ በክላስክ የሆነ ከተማ መሆኑ ነው። እንደሞተር ብስክሌት ነው እያንዳንዱ መኪና በፍጥነት የሚሹለከለከው! ይምዘገዘጋሉ ማለት ይቀለኛል፡፡ እኔ ነብሴ ልትወጣ ደርሳለች፡፡ ሹፌሬ ከጓደኛው ጋር ጠብ የሚገጥም በሚመስል ጩኸት ያንባርቃል፡፡ እኔ ካሁን አሁን ተጣሉ እያልኩ እጠብቃለሁ፡፡ እኔ በሄድኩበት ትራፊክ ፖሊስ አላየሁም፡፡ በቆየሁባቸው ቀናትም የመኪና ግጭት አላየሁም፡፡ ወደ ፌርሞንት ናይል ሲቲ ሆቴል ይወስደኝ የነበረውን ያን የሚጮህ የታክሲ ሹፌር፤ “ከየት ነህ?” አልኩት፡፡
“ከአስዋን ግድብ አካባቢ” አለኝ፡፡ ቀጥሎ “አንተስ?” አለኝ፡፡
“ከኢትዮጵያ” አልኩት፡፡
“ኢትዮጵያ የት?” አለኝ፡፡ ድምፀቱ ውስጥ የጣሊያን ክልስ ይመስላል፡፡ ጣልያንኛ ቃና አለው፡፡
ገርሞኝ፤ “አዲስ አበባ” አልኩ፡፡ “ታውቀዋለህ?”
“አልሄድኩም፡፡ ስለአዲስ አበባ ግን እሰማለሁ። አውቃለሁ”
“ግድብ እየሠራን መሆኑንስ ሰምተሃል ወይ?” አልኩት፡፡
“ድምፅህን ዝቅ አድርግ” አለኝ፡፡
ቸኩዬ “ለምን?” አልኩት፡፡
እየሳቀ፤ ወደ ሽንጣሙ ዐባይ እያየ “ይሄ ጐናችን ያለው የእኛ ዐባይ እንዳይሰማህ ብዬ ነው!” አለኝ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 1694 times