Saturday, 14 February 2015 15:18

አቶ ልደቱ፤ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” አልበጀንም አሉ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(24 votes)

“ከሃሳብ የዘለለ ህብረት ለተቃዋሚዎች አለርጂክ ነው”  
እኛና ዓለም በቁጥር ጉዳይ ልንስማማ አልቻልንም
“አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይንስ ነው ፍልስፍና?”

   አንዲት ሩሲያዊ ሴት ወይዘሮ፣ ለቀድሞው የሶቭየት ህብረት (አገሪቱ ሺ ቦታ ሳትበታተን ማለት ነው!)  መሪ ለጎርባቾቭ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፤
“ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ኮሙኒዝም ሳይንስ ነው ፍልስፍና?” (ልብ አድርጉ ያኔ ነው!)
ጎርባቾቭም ለአፍታ አሰብ ያደርጉና፤ “ፍልስፍና ነው” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
ሴት ወይዘሮዋ፤ “እኔም እንደዚያ ነው የማስበው፤ ባይሆንማ ኖሮ ሳይንቲስቶች በእንስሳት ላይ ይሞክሩት ነበር”
እስቲ እኔ ደግሞ እናንተን ልጠይቃችሁ፤ “ክቡር አንባቢያን፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይንስ ነው ፍልስፍና?” እርግጠኛ ነኝ መልሳችሁ “ፍልስፍና” ነው፡፡ ሳይንስ ቢሆንማ----ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት በእንስሳት ላይ ይሞከር ነበር፡፡ እናንተ … ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ ምን ያልተሞከረብን ነገር አለ? (የሃበሻን ፅናት  አደነቅሁት!) እስቲ አስቡት----ቢፒአር… ውሃ ማቆር … የዋጋ ተመን--- ወዘተ.. (ትዝ ያላችሁን ሙሉበት!) ከሙከራዎቹ በኋላ የኢህአዴግ ሹማምንት መክሸፉን ሲነግሩን ዘና ብለው መሆኑ ሁሌም ግርም ይለኛል፡፡  
ምናልባት----እንደ አይጥ መሞከሪያ ስንሆን እንዴት ዝም አልን ብለን ላለፈው ልንቆጭ እንችላለን፡፡ (አደራ እንዳንቆጭ!) ለምን መሰላችሁ? “ለልማታችን የተከፈለ መስዋዕትነት ነዋ” (አሪፍ መጽናኛ!) ለነገሩ የየዕለቱ የታክሲ ወረፋ … በሻማ መጨናበስ …ጀሪካን ይዞ መንከራተት … በኔትዎርክ ችግር መከራ መብላት --ሁሉ “ለልማት የተከፈለ መስዋዕትነት ነው” (ኢህአዴግ ግን ዕዳ አይፈራም!)
እኔ የምላችሁ … ባለፈው ሰሞን የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አዲስ አበባ መጥቶ እንደነበረ ሰምታችኋል? (“ቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ኢን ዘ ሃውስ”!) ነገሩ የኮሙኒስት ፓርቲው የመጣው አየር ለመለወጥ ወይም ሊዝናና አይደለም (እዬዬ ሲዳላ ነው አሉ!) በኢህአዴግ ግብዣ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ላይ ሊሳተፍ ነው የመጣው፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል---የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በዚህ ወቅት ጉባኤ ሊቀመጥ አዲስ አበባ ይመጣል ብዬ በህልሜም በእውኔም አላሰብኩም ነበር፡፡ ባይሆን ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ዋናው ክርክር እስኪደርስ የወዳጅነት ክርክር አደረጉ ቢባል እኮ ወግ ነበር፡፡ ለማንኛውም ግን  የአሁኑን “የግምት ስህተት” ብላችሁ እለፉኝ (ለዚህችም ይቅርታ ልጠይቃችሁ?)
በነገራችን ላይ ኮሙኒስት ፓርቲው ከእዚህ በኋላ ቤተኛ መሆኑ አይቀርም - በሰበብ አስባቡ ከች ነው የሚለው!! እናላችሁ ---- ኢህአዴግ አባላቱን በ1 ለ 5 እያደራጀ ቻይንኛ ቢያስተምር ይሻለዋል፡፡ (የቋንቋ barrier ወዳጅነት ያሻክራል!) አያችሁ… ኢህአዴጎች ትንሽ ቋንቋውን ከተማሩ ቢያንስ በቻይንኛ፤ “ዘመኑ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጋር ብሩህ ነው!” ማለት አያቅታቸውም፡፡ (አንዳንዴ አብዮታዊ ዲሞክራሲ  የኮሙኒዝም የእንጀራ ልጅ ይመስለኛል!!)
እናላችሁ … ኢህአዴግ ከቻይና ጋር በጀመረው “ያገረሸ ፍቅር” የተነሳ አንዳንድ ያልተጠበቁ ነገሮች ቢከሰቱ እንዳይገርማችሁ፡፡ ለምሳሌ አንድ ምሽት ላይ ሁለት ሃዲዱን የሚሰሩ ቻይናዎች በEBC መስኮት ብቅ ብለው በአማርኛ፤ “የምርጫ ካርድ ወስዳችሁ … ልማቱን ያስቀጥላል የምትሉትን ፓርቲ ምረጡ!” የሚል ቅስቀሳ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ (ጠርጥር አለ!) ኢቢሲ ከ“አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ጋር ቀላቅሎ ቢያመጣቸውም እንዳይደንቃችሁ፡፡ (“ያገረሸ ፍቅር” የአፍላ ያህል ነው!) እኔ የምለው ግን … የግንቦቱን ምርጫ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ እንኳን አይታዘበውም እንዴ? (የምርጫው ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑ አልጠፋኝም!)
እስቲ ለአፍታ ደግሞ ወደ አራት ኪሎ ጎራ እንበል (ፓርላማ ማለቴ ነው!) ከሁለት ሳምንት በፊት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በፓርላማ ተገኝተው ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በም/ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ (አሁን የወከሉት ባይታወቅም) የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ የሰነዘሩት በአስተያየት የተጠቀለለ ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩን ኃይለ ቃል አናግሮአቸዋል (“ከተናግሮ አናጋሪ ሰውረኝ” ነው እኮ!) እናላችሁ … አቶ ግርማ በፓርቲያቸው የተከሰተውን ድንገተኛ ክፍፍል ተከትሎ በምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም እንዲህ አሉ፤ “ከመቼ ወዲህ ነው ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን መሪ የመሾምና የመሻር ሥልጣን የተሰጠው?” ለነገሩ ጠ/ሚኒስትሩም የዋዛ መልስ አልሰጡም፡፡ ቦርዱ የፓርቲዎችን መሪ እንዳልሾመና እንዳልሻረ ጠቁመው፤ የተከፈሉትን የአንድነት አመራሮች “የአገር ውስጥና የውጭ” በሚል ሁለት ቦታ መደቧቸው፡፡ እኔ ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም… ወዲያው ወደ አዕምሮዬ የመጣው  “የአገር ውስጥና የውጭ ምርት” የሚል ነገር ነው፡፡ (ቅዠት ይሆን እንዴ!)
እናም ምርጫ ቦርድ፤ ለአገር ውስጡ አመራር “አንድነት” ፓርቲን ያፀደቀለት፣ ለቦርዱ ህግና ደንብ የተገዛ በመሆኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ ይሄን ብቻ ብለው ግን አላባቁም፡፡ (“መች ተነካና” አለ  ጀግና!) “በግሌ” በሚል ጠንከር ያለ የምርጫ ሰሞን ማስጠንቀቂያ ሠጡ፡፡ እኔን ያሰጋኝ ታዲያ ምን መሰላችሁ? የግል አስተያየታቸው ከመንግስት አስተያየት ጋር እንዳይደባለቅ ነው (በሥራ ብዛት ማለቴ ነው!) እናም… ቦርዱ እየተሰደበና ስሙ እየጠፋ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንደሌለና ጉዳዩን ወደ ህግ እንደሚወስደው ጠ/ሚኒስትሩ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
ለነገሩ እኮ ቦርዱም ቢሆን አልዘለቀበትም እንጂ “በህግ የተሰጠኝን ሥልጣንና ኃላፊነት” አክብሩልኝ ማለት ጀምሮ ነበር፡፡ ቦርዱ ከመንግስት በሚመደበው የገንዘብ ድልድል ቀመር ላይ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ያዘጋጀውን መድረክ “ሰማያዊ ፓርቲ” ረግጦ በመውጣቱ (በስልት ይሆን በስሌት!) ፓርቲው ይቅርታ ይጠይቀኝ ብሎ ነበር፡፡ ክፋቱ ግን ፓርቲው “ይቅርታ የሚያስጠይቅ ጥፋት አልፈፀምኩም” በማለት እምቢተኝነቱን ገለፀ፡፡ ይሄኔ ታዲያ ቦርዱ ለዲሞክራሲያዊ ግንባታ መጐልበት ሲል ነገሩን በ“ሆደሰፊነት” እንዳለፈው ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ (“ሆደ ሰፊነት” በክትባት መልክ ቢሰጥ ሸጋ ነው!) በነገራችን ላይ…  ህገመንግስታዊ መብታችንን በሙሉ አቅምና ቁርጠኝነት ለመጠቀም ስንፍጨረጨር በህገወጥነት እንዳንጠየቅ እያስተዋልን መራመድ ይኖርብናል (ከተቃዋሚዎች ባላውቅም!)
ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያ የሰጡበት ሌላው ጉዳይ --- ምን መሰላችሁ? የአንድነት ፓርቲ አባላት (የቀድሞዎቹን ማለቴ ነው!) ዕውቅና ያልተሰጠው ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርጉ ሲሞክሩ፣ በፀጥታ ኃይሎች የደረሰባቸውን ድብደባ የተመለከተ ሲሆን ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የፓርቲው አባላት እንደሆነ አስረግጠው  ተናግረዋል - ፖሊስ የታዘዘውን መፈፀም እንጂ ፖለቲካ እንደማያውቅ በመግለፅ፡፡ (ታዛዦቹስ እሺ … አዛዦቹሽ?)
እኔ የምለው ግን .. የዘንድሮ ምርጫችንን ለመታዘብ የገንዘብ አቅም የለንም አሉ የተባሉት የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ መንግስታት፤ አስለቃሽ ጭስ ለመስጠትም አቅም አጡ ማለት ነው? (ከቆመጥ ጭስ ይሻላል ብዬ እኮ ነው!) የዱላ ነገር ሲነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? በአዲስ አበባ የግል ት/ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች ምን ቢያጠፉ፣ ከምክርና ተግሳፅ በቀር ዝንባቸውን እሽ ማለት አይፈቀድም፡፡ (“የሰብዓዊ መብት ጥሰት” ነው ይባላል!) ወላጅ በብርሃን ፍጥነት ከተፍ ይልና “አስተምሩልኝ እንጂ ቅጡልኝ አላልኩም” በማለት ይደነፋሉ፡፡ (ዱላ በት/ቤትም እየቀረ ነው ለማለት ነው!) እናላችሁ … እኔም የገንዘብ ድጋፍ (fund) አፈላልጌ፣ የፀረ-ዱላ አገር አቀፍ ዘመቻ ልጀምር አስቤአለሁ፡፡ (ዘመቻም ፈቃድ ያስፈልገዋል እንዳትሉኝ!?)
በነገራችን ላይ --- በዘንድሮ የግንቦቱ ምርጫ “ይሆነኛል .. ይበጀኛል … ልማቱን ያስቀጥልልኛል …” የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ የተመዘገበው ህዝብ ብዛት … በከፍተኛነቱ ሪከርድ ሳይሰብር አይቀርም፡፡ የሌላ አገርን ባይሆን እንኳን የራሳችንን! (“ራስን ነው ማሸነፍ” አሉ!!) ትንሽ የሚያሰጋኝ ግን ምን መሰላችሁ? እኛና ዓለም በቁጥር ጉዳይ ተግባብተን ስለማናውቅ፣ እኛ 37 ሚሊዮን መራጭ ተመዝግቧል ስንል፣ እነሱ ቁጥሩን በግማሽ ጎምደውት ሪከርድ የመስበር ህልማችንን እንዳያሰናክሉብን ነው (አሁንም ዋናው የምርጫው ባለቤት ህዝቡ መሆኑ አልጠፋኝም!)
መቼም የኢኮኖሚ ዕድገቱን በተመለከተ በመንግስታችንንና በዓለም ባንክ መካከል የነበረውን የአሃዝ ልዩነት የምታውቁት ነው፡፡ በህዝብ ብዛትም እኮ አልተግባባንም (ልዩነታችን የትየለሌ ነው!) የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ የህዝቡ ቁጥር ከ90 ሚ. አይበልጥም ሲል፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት በበኩላቸው፤ 100 ሚ. ይደርሳል ብለው ቁጭ አሉ (ለዕድገት ሲሆን የሚያንሳቸው ቁጥር ለህዝብ ብዛት ከየት ተገኘ?!)፡፡ ሌላው የሚገርመው ምን መሰላችሁ? በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከፖሊስ ጋር በተነሳ ግጭት፣ በሞቱ ሰዎች ቁጥር እንኳን ተስማምተን አናውቅም፡፡ ለሰልፍ የወጣ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊና አባላትን ቁጥር በተመለከተማ … ጉድ ነው! (ቁጥር ለምን ተፈጠረ ነው? የሚያሰኛችሁ!) ፓርቲው 50ሺ ሲል፣ የአገር ውስጥ ሚዲያ 10ሺ ይላል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ደግሞ 25ሺ ገደማ ብለው መሃል ላይ ያርፋሉ፡፡ እናላችሁ .. እኛና ዓለም በቁጥር ጉዳይ ፈፅሞ መግባባት ተስኖናል እያልኳችሁ ነው፡፡ እርግጥ ነው መረጃ ሳይዙ መደምደም ከስነ ምግባር ውጭ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አንድ ነገር እጠረጥራለሁ፡፡ ከሁለት አንዳችን ቁጥር አናውቅም - ወይ እኛ አሊያም ዓለም አቀፍ ተቋማቱ! (ዝም ብሎማ ልዩነት አይመጣም!!)
እኔ የምላችሁ…የቀድሞው የኢዴፓ ሊ/መንበር አቶ ልደቱ አያሌው፣ ሰሞኑን ለንባብ ያበቁትን አዲስ መፅሃፍ አያችሁት? “ቴአትረ ቦለቲካ፤ አሉባልታና የአገራችን የፖለቲካ ገመና” የሚል ነው፡፡
በዚህ መፅሃፋቸው አቶ ልደቴ፤ ሁለት ለየት ያሉና ትኩረት የሚስቡ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡ አንደኛው በተለይ፣ ነባር ሃሳብንና እምነትን (ተረትን ጭምር) የሚያፈራርስ ነው (አፈር ድሜ የሚያስግጥ!) ምን ይላሉ መሰላችሁ? “የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያፈራረሳቸው መተባበራቸው ነው” (“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ተረትም እኮ ነው ያፈረሱት!) ተረቱ ቢፈርስም ግን ነገራቸውን በማስረጃ እያስደገፉ ነው የሚሞግቱት፡፡ ኢዴፓ ከቅንጅት ጋር ህብረት መፍጠሩ ፓርቲውን አጠፋው እንጂ አላለማውም የሚሉት ፖለቲከኛው፤ ህብረት የሚባል ነገር ባይኖር ኖሮ እስካሁን ሁለት ወይም ሦስት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጥረው ይወጡ ነበር ባይ ናቸው፡፡ እንግዳ ሃሳብ ቢመስልም ከአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ይመስላል፡፡ (ህብረት የፈጠረ ሲፈርስ ነዋ የምናየው)!
ሌላው ተቃዋሚዎችን ክፉኛ የጐዳው የአሉባልታ ባህል ነው ሲሉ አቶ ልደቱ ያብራራሉ፡፡ በነገራችሁ ላይ መላ መጽሃፉ በአሉባልታ ዙሪያ ነው፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ በእሳቸውና በፓርቲያቸው ላይ ምን ዓይነት አሉባልታዎች ይነዛባቸው እንደነበር በዝርዝር እየጠቀሱ ይተቻሉ፡፡ (ምን ያልተባሉት አለ?!) በቦታ ጥበት የተነሳ ከዚህ በላይ ማውጋት ስላልቻልኩ፣ እናንተ ደሞ መፅሃፉን ገዝታችሁ አንብቡና ሃሳባችሁን ሰንዝሩ፡፡ (እንደ 21ኛው ክ/ዘመን ሰው!!)

Read 9220 times