Saturday, 07 February 2015 13:28

እየራባቸው የሚማሩ ህፃናትን መታደግ...

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

“ምሳቸውን እያሰቡ እንዲማሩ አንፈልግም”

በቅዱስ ሚካኤል ት/ቤቶች ለሰባት አመታት ያስተማረው ሳሙኤል ተስፋዬ፤ የት/ቤቱ ዳይሬክተር እንደነበረም ይናገራል፡፡ በመምህርነት ዘመኑ በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው ምሳ ሳይመገቡ የትምህርት ገበታ ላይ የሚቀመጡ ህፃናትን ባያስተውልም ተወልዶ ባደገበት  አራት ኪሎ ግን በድህነት የሚማቅቁና ሳይመገቡ ት/ቤት የሚሄዱ ህፃናት ተማሪዎችን መመልከት የዕለት ተዕለት ተግባሩ እንደነበር አይዘነጋውም ፡፡ የወደፊት እጣፋንታቸው እረፍት ይነሳው እንደነበር የሚናገረው ሳሙኤል፤ መምህርነቱን ትቶ እነዚህን ህፃናት በተቻለው ሁሉ የመደገፍ ስራ እንደጀመረ ይገልፃል፡፡ ከጓደኛ፣ ከዘመድ ወዳጅና ከበጐ ፈቃደኞች አምስት እና አስር ብር እየለቀመም ለችግረኛ ተማሪዎች በሳምንት አንድና ሁለት ቀን ዳቦና ወተት ማቅረብ ጀመረ፡፡ ፈቃደኛ የሆኑ መምህራንን በማስተባበርም ቅዳሜ ቅዳሜ ልጆቹን እያስጠና ምሳ ያበላቸዋል፡፡
ይህን በጐ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠልም በ2005 ዓ.ም “Friends Ethio - Students Support (Fess) የተሰኘ የበጐ አድራጐት ድርጅት አቋቋመ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከድርጅቱ መስራች ሳሙኤል ተስፋዬ ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡


እስቲ ፍሬንድስ ኢትዮ ስቱደንትስ ሰፖርት (FESS) የሚያከናውናቸውን ስራዎች ንገረኝ? በዋናነት የምንሰራው የህፃናት ተማሪዎች የነገ ተስፋ ላይ ነው፡፡ ማናችንም ብንሆን ዛሬ ላለንበት ማንነት መሰረታችን ህፃንነታችን ነው፡፡ ዛሬ ኪስ አውላቂ፣ ተሳዳቢ፣ ጋጠወጥ … የሆኑ ሰዎችን የኋላ ህይወት ብንፈትሽ፣ በአብዛኛው የልጅነት ዘመናቸው የተበላሸ ነው፡፡ ከነዚህ ሰዎች ጀርባ በጥሩ ስነ - ምግባር ለማነፅና ለማሳደግ ሃላፊነት የወሰደ ቤተሰብ ወይም ማህበረሰብ አልነበረም ማለት ነው፡፡ እኔም መምህር እንደመሆኔና ከህፃናት ጋር በነበረኝ ቀረቤታ፣ በግል ት/ቤት የሚማሩ የባለፀጋ ልጆችንና በመንግስት ት/ቤት የሚማሩ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን ልዩነት እያየሁ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነበረ፡፡ ስለዚህ በአቅሜ በምችለው መጠን ወላጅ የሌላቸውን ወይም በእናት ብቻ የሚያድጉ ልጆችን የወደፊት ህይወት ብሩህ ለማድረግ፣ ከምግብና ከትምህርት መሳሪያዎች ድጋፍ በተጨማሪ የስነ - ልቦና ድጋፍ ለማድረግ ነው (FESS)ን የመሰረትኩት፡፡
ምን ያህል ተማሪዎች ድጋፍ ያገኛሉ? የድጋፍ ትኩረትህስ?
ህፃናቱ የአንድ ት/ቤት ተማሪዎች ናቸው። ስንጀምር በ10 ተማሪዎች ነበር፤ አሁን ወደ 60 ከፍ ብለዋል፡፡ የምንመርጥበት መስፈርት ያሉበት የኑሮ ደረጃ ነው፡፡ ግማሾቹ ሁለቱም ወላጆች የሏቸውም። ግማሾቹ ምንም የገቢ ምንጭ ከሌላቸው እናቶቻቸው ጋር የሚኖሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የት/ቤት፣ የትምህርት መሳሪያዎች፣ የደንብ ልብስና ምሳ እናቀርብላቸዋለን፡፡  ቅዳሜ ቅዳሜ የግማሽ ቀን ጥናት እያስጠናን ምሳ በልተው እንዲሄዱ እናደርጋለን። ተማሪዎቹ ቢያንስ ምሳቸውን እያሰቡ እንዲማሩ አንፈልግም፡፡ የምሳ ጥያቄያቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ እየጣርን ነው፡፡ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሾላ ገበያ አካባቢ “ተስፋ ብርሃን” በሚባል የመንግስት ት/ቤት ውስጥ ነው እየሰራን ያለነው። እንደ ድርጅት ፈቃድ ሳላወጣ በፊት፣ ኮተቤ አካባቢ ወንድይራድ ት/ቤት ውስጥ ለአንዳንድ ችግር ለባሰባቸው ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ደብተር እና መሰል ቁሳቁሶችን እሰጥ ነበር፡፡ አሁንም ደጋፊ ባገኝና ቢሳካልኝ እዚያ በርካታ በተጐሳቆለ ህይወት ውስጥ የሚኖሩ ተማሪዎች ስላሉ እነሱን መርዳት እፈልጋለሁ፡፡
ስትጀምሩ ለአስሩ ተማሪዎች መርጃ የሚሆን ገንዘብ ነበራችሁ?
ምንም ገንዘብና አቅም አልነበረንም፡፡ ፍላጐት ብቻ ነው የነበረን፤ ነገር ግን እነዚህን አስር ተማሪዎች በት/ቤቱ በጐ አድራጐት ክበብና ቤት ለቤት እየሄድን፣ (በእርግጥ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ካረጋገጥን በኋላ ነው) አምስት አስር ብር እየሰበሰብን፣ ማክሰኞ ማክሰኞ በምሳ ሰዓት ዳቦና ወተት ማቅረብ ጀመርን። ከዚያም ቅዳሜ ከመምህራን ጓደኞቼ ጋር በመሆን ማስጠናቱንና የዳቦና ወተት አቅርቦቱን ቀጠልን፡፡ ይህን ስራችንን ለወዳጅ ዘመድ መንገር ስንጀምር፣ ቦሌ መድኀኒያለም አካባቢ የሚገኝ አንድ መንፈሳዊ ማህበር፣ የኤሌክትሪክ ምጣድና ለስራው መጀመሪያ የሚሆን ጤፍ ለገስን፡፡ እዚያው ት/ቤት ውስጥ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነች ኩሽና ሰርተን፣ እዚያው እያበሰልን ምሳ ማቅረብ ጀመርን፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ነው የምንረዳቸው ተማሪዎች ወደ 60 የደረሱት፡፡ ምሳ በደንብ የምናቀርበው ቅዳሜ ቅዳሜ ነው፡፡ የወደፊት አላማችን ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሙሉ የምሳ አቅርቦት መስጠት ነው፡፡ ከተማሪዎቹ አዕምሮ ውስጥ የምሳ ጥያቄ ወጥቶ ትምህርታቸውን ብቻ እንዲያስቡ ለማድረግ መትጋታችንን ቀጥለናል፡፡
አሁንስ የሚደግፋችሁ አገኛችሁ? የገንዘብ ምንጫችሁ ምንድን ነው?
ቋሚ ለጋሽ አላገኘንም፤ ሆኖም አሁን አሁን ጓደኞቻችንም እያገዙን እኛም ፕሮፖዛል በአንዳንድ ድርጅቶች በማስገባት፣ ጥቂት ድጋፎችን በማግኘታችን የተማሪዎቹን ቁጥር ወደ 60 ማሳደግ ችለናል፡፡ ከዚህ የበለጠ መስራት እንፈልጋለን፡፡ በአዲስ አበባ የመንግስት ት/ቤቶች ውስጥ በርካታ ምሳ ሳይበሉ የሚውሉ፣ ነገር ግን በትምህርት ገበታ ላይ በየቀኑ የሚቀመጡ በርካታ ተማሪዎች እንዳሉ በጥናትም ተረጋግጧል፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎችም ተዘግቧል፡፡ እኛም ድጋፍ ባገኘን ቁጥር አሁን ከምንሰራበት ት/ቤት በተጨማሪ በሌሎች ት/ቤቶች ያሉትን ለመድረስ እቅድ አለን፤ አሁን አቅም ገድቦን ነው፡፡
ዕቅዳችሁን ለመተግበር ምን አሰባችሁ? በገንዘብ በኩል ማለቴ ነው …
በአሁኑ ሰዓት ከፅዳት ሰራተኛ እስከ ዶክተሮች እንዲሁም የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ድረስ አባላት ማፍራት ችለናል። አምስት ሺህ አስር ሺህ ብር የሰጡን አንዳንድ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ለጊዮርጊስ ቢራ ፕሮፖዛል አስገብተን 10ሺህ ብር ለግሶናል፡፡ በጣም እናመሰግነዋለን፡፡ እነዚህ አባላት ያልኩሽ በወር ከአምስት ብር ጀምሮ እስከ አምስት መቶ ብር ይሰጡናል፡፡ ከውጭም ጓደኞቻችን ብር እያሰባሰቡ መላክ ጀምረዋል፡፡ ይህን በማሰባሰብ ነው የልጆቹን የነገ ተስፋ ለማለምለም የምንሮጠው፡፡
እነዚህ ተማሪዎች ክረምት ላይ ት/ቤት ሲዘጋ ምሳቸው ይቆማል ማለት ነው?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ይሄንንም በጣም አስበንበታል፡፡ እኛ ምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ከማቅረብ ባሻገር በጣም ትኩረት የምንሰጠው ለስነ - ልቦናቸውና ነጋቸውን የመቅረፅ ጉዳይ ላይ እንደሆነ ቀደም ሲል ገልጨዋለሁ፡፡ አንድ እናት ያለምንም ቋሚ ገቢ ሶስትና አራት ልጆች ለማሳደግ ያገኘችውን ሁሉ ስትሰራ፣ ስለምትውል ልጆቹን ለመቆጣጠር አትችልም፤ ስለዚህ እነዚህ ልጆች ባህሪያቸውም ወጣ ያለ ነው፡፡ እኛም ያንን ባህርይ ለማራቅ እንሰራለን። እነዚህ 60 ልጆች አሁን ፍቅርና እንክብካቤ ስንሰጣቸው፣ ባህሪያቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ አይተናል፡፡ ስለሆነም ክረምት ላይ ሁለት ወርና ከዚያ በላይ ዝም ብለን ከለቀቅናቸው፣ ወደ ቀደመ ባህሪያቸው ይመለሳሉ የሚል ስጋት ስላለን ባለፈው ክረምት ከሰኔ እስከ ነሐሴ መጨረሻ በሳምንት ሶስት ቀን ሐሙስ፣ አርብና ቅዳሜ አስጠንተን፤ ምሳ እያበላን ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በአሁኑም ክረምት ይሄው አሰራር ይቀጥላል፡፡
አንተ ታስተምርበት የነበረው ቅ/ሚካኤል ትምህርት ቤት ደህና ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች የሚማሩበት ነው፡፡ አንተ በህይወትህ በዚህ አይነት ችግር ውስጥ አልፈህ ነበር? እንዴት ስራህን ትተህ እዚህ ውስጥ ገባህ?
በእርግጥ እኔ የተማርኩት የመንግስት ት/ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ምሳ ያለመብላት ችግር አልነበረብኝም። ወላጆቼ በጥሩ ሁኔታ ነው ያሳደጉኝ፡፡ ተወልጄ ያደግሁት ግን አራት ኪሎ ነው። አራት ኪሎ የድህነት ጥግ የሚታይበት አካባቢ እንደነበር ማንም አይክደውም፡፡ ስለዚህ አካባቢዬ ላይ የነበረውን የኑሮ ሁኔታ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ብዙ ነገሩን ከአካባቢዬ አይቼዋለሁ፡፡ ለዚህ ነው ይሄንን ስራ ለመስራት በጥሩ ደሞዝ የምሰራበትን የዳይሬክተርነት ስራ ትቼ የወጣሁት፡፡
በመጨረሻ ...
ህፃናት የመመገብ፣ በጤናና በህይወት የመኖር፣ የመማርና ፍቅር እንዲሁም እንክብካቤ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ምሳና ቁርስ ማግኘት የእነሱ የቤት ስራ መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም ለአቅመ ስራ አልደረሱም፤ ፈልገውም ወደዚች ምድር አልመጡም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በምንችለው አቅም ከዚህ ጭንቀት እናውጣቸው ባይ ነኝ፡፡ አንዳንዶቻችን ተርፎን ከምንጥለው እናጉርሳቸው። እኛ የአቅማችንን ያህል ህፃናቱን ለመርዳት ስንነሳ፣ በኢትዮጵያዊያን የመደጋገፍ ባህል ተማምነን ነው። ስለዚህ በገንዘብም፣ በጉልበትም፣ በእውቀትም፣ በምክርም ድጋፍ እንሻለን፡፡ ግለሰቦችም ድርጅቶችም እንዲያግዙን ጥሪ እናቀርባለን፡፡ አሁን ስንተባበር ነው ኃላፊነት የሚሰማው መልካም ዜጋ የምንፈጥረው፡፡

Read 2200 times