Saturday, 07 February 2015 13:29

የግዕዝ ፊደልና ቋንቋችን የማንነት ታሪካዊ ቅርሳችን

Written by  ግፍታሔ ገኃተ
Rate this item
(1 Vote)

       ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ስለ ቋንቋ በመጠኑ እንዲሁም የግዕዝ ፊደልና ቋንቋ ለካም የተሰጠ ጥንታዊና መሠረታዊ ሃብታችን እንጂ ሴማውያን ለአፍሪካ ማለትም ለኢትዮጵያ የሰጡት እንዳልሆነ በአጭሩ ለማሳየት  ሞክሬአለሁ፡፡ ይህም ሀሳቤ ምሑራኑ በስፋት ተመራምረውበት ፈር የሚያሲዝና ከዘርፉ ጋር ያለንን ታሪካዊ ቁርኝት የሚያሳይ የጥናት ውጤት እንደሚያቀርቡልን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በዓለማችን ላይ በርካታ ቋንቋዎች አሉ፡፡ በአገራችን እንኳን ከ80 በላይ ናቸው፡፡ ፊደል ደግሞ የጥቂት አገሮች ሀብት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊሠመርበት የሚገባው ጉዳይ እጅግ በርካታ ቋንቋዎች ለጽሑፍ ተግባራቸው ከነዚህ ባለፊደላት አገሮች ፊደልን እንደሚወስዱ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ከላቲን ቋንቋ ፊደሎችን እንደወሰደው ማለት ነው፡፡
ከቋንቋ አኳያ ነገሮች በጥልቀት ከታዩ ለአንድ ቋንቋ ማንኛውንም ተስማሚ ፊደል እንዳለ ወይም መጠነኛ ማሻሻል በማድረግ መውሰድ ነውር አይደለም፡፡ አማርኛም ከግዕዝ የወሰደውን ፊደል በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡ ከዚህ አኳያ የብዙ አፍሪካ አገራት ልሒቃን የግዕዝን ፊደል ባለማወቃቸው  አፍሪካዊውን ትተው የአውሮፓ ፊደል መዋሳቸው ይቆጫቸዋል፡፡ ነገሩን ከቅኝ ግዛት ጋር ሲያዛምዱት ደግሞ የባሰ ይንገበገባሉ፡፡
ግዕዝ የኢትዮጵያ ታላቅ የታሪክ ቅርስ ከመሆኑ ባሻገር የአገሪቱ የማንነት ምስጢራት ተመዝግበው የሚገኙባቸው ጥንታዊ መጻሕፍትና ጽሑፎች በዚሁ ቋንቋ በመሆኑ ታሪክ ለመደምሰስ ሕዝቡን ከመሠረታዊ ቋንቋው የመነጠል ተግባር እንደተከናወነ ማየት አይከብድም፡፡ በመሆኑም የአማርኛ ቋንቋ የተጀመረበትንና ግዕዝ ወደ ገዳማትና አድባራት እንዲመንን የተፈረደበትን ታሪካዊ ወቅት (ጊዜ) በአግባቡ ማጥናት ምስጢሩን ገሐድ ማውጣት ነው፡፡ እንደሚመስለኝ “የዓባይ ወንዝ ምንጭን ለመቆጣጠር” ከፍተኛ ፍላጐት የነበራቸው ወገኖች በተለይ “ሃይማኖትን” ተገን በማድረግ  የፈጸሙት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ከዋናውና ከመሠረታዊ ቋንቋው በመነጠሉ በአገሩ ውስጥ የሚካሄዱ ተግባራትን ለሌሎች (ለአዋቂዎች) አሳልፎ መስጠቱ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በሁሉም የሰው ልጅ የሥራ እንቅስቃሴ ዘርፎች፣ በሥነ - ከዋክብት፣ በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በዓለም ሕዝቦች ፊት በሚቀርብ የማንነት ጉዳይ በግዕዙ ተጽፈው የነበሩ ሀብቶች ቀስ በቀስ ተዘረፉ ማለት ነው፡፡ በግዕዝ መጻሕፍት ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያውያን ባሕረ ዕውቀት፣ ምልአተ ጥበባትና የታሪክ ትውፊቶች ከዐይኑ ሥር ሲመዘበሩ ሕዝቡ “የቄስ ቋንቋ” ከሚለው ግዕዝ ጋር ስለተፋታ እንደዋዛ አለፈው፡፡ እናም የኢትዮጵያን ክብርና ልዕልና ለማኮሰስ የፈለጉ ወገኖች በረጅም ጊዜ ሂደት እንደተሳካላቸው ማየት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያን ጥንታዊ ኃያልነትን /በዕውቀት ላይ የተመሠረተ/ ዝቅ በማድረግ በአካባቢው ኮስሳ እንድትታይና እነርሱ የልባቸውን ያደርሱ ዘንድ በፊደልና በቋንቋችን ዘርፍ (አእምሮአዊና ልባዊ ትውፊቶች) በሦስት ዋና ዋና መንገዶች መጉዳት ችለዋል፡፡ የመጀመሪያው መንገድ አስረስ የኔ ሰው እንደሚገልፁት፤ የተዛባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለአገራችን ማውረስ (መስጠት) ነው፡፡ በካም መታሰቢያ መጽሐፋቸው ላይ (ገጽ 57) “…አይሁድ ይህን የተቀደሰ መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስን) ለዓለም ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሲሰጡ ረቂቅ ምክር ጨምረው ነው፡፡ ምክሩም “ሌላ መጽሐፍ ያገኛችሁ እንደሆን እንዳትቀበሉ” የሚል ነው፡፡ የዓለም ቤ/ክርስቲያናት ይህ ተንኮል መሆኑን ሳያውቁ ተሸክመውት ይኖራሉ፡፡ …አይሁድ ሌላ መጽሐፍ እንዳትቀበሉ ማለታቸው መጽሐፍተ ብሉያት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ስላወቁ ነው፡፡” የሚል ሠፍሯል፡፡ ይህን ቃል የጠቀስኩት ትልቅ እንደሆነ ያመንኩበትን ምስጢር ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡
ሁሉም የግዕዝ ሆሄያት ወይም ፊደላት የራሳቸው የቁጥር ቀመር አላቸው፡፡ በቁጥሩ ቀመር መሠረት ያለፈ፣ የዛሬውና የወደፊቱ በዓለም ላይ በየትኛውም ሥፍራ /ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምሥራቅ/ የሚከወኑ ጉዳዮች በጊዜያት ማለትም ከሰከንድ እስከ ዘመናት ባሉት ተቀንብበው ይታወቃሉ፡፡ ይህ ረቂቅ ምስጢራዊ ጥበብ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ቤ/ክርስቲያን የግዕዝ ሊቃውንት በመጽሐፍ ተዘጋጅቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከሙሴም ጋር ቅርርብና ዝምድና ስለነበራትም ሙሴ በጻፈው ኦሪት ላይ በአግባቡ ተመዝግባለች፡፡ ሥነ - ልሳኗም ጭምር፡፡ በነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የታሪኩን የበላይነት ቀምቶ የራሳቸው ለማድረግ የተጠቀሙበት አንዱ መንገድ እንደ መጽሐፈ ሄኖክ፣ ሙሴ የጻፈው ኩፋሌ፣ መጽሐፈ ሲራክ፣ ጦቢያ፣ መጽሐፈ ዮዲት ወዘተ. ያሉትና ሌሎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳይካተቱና የኢትዮጵያውያን ምልአተ ጥበብ እንዳይገለጥባቸው ማድረግ እንደሆነ አስረስ በማስረጃ ተንትነው ገልፀውታል፡፡ የተከለከሉት መጻሕፍት ደግሞ ታላላቅ ምስጢራትን ያጨቁ ናቸው፡፡
ሁለተኛው ታሪክን የመዘርጠጫና የራሳቸውን ታላቅነት ለማመቻቸት የጠቀማቸው ኢትዮጵያውያን ከመሠረታዊው ከአባታቸው ከካም በመውረስ የማንነታቸውን ታሪክ የገነቡበትን ግዕዝን በአማርኛ መተካት ይመስለኛል፡፡ የዚህን ዋነኛ ጭብጥ ከላይ ገልጨዋለሁ፡፡ ሦስተኛው መንገድ ሃይማኖትን አሳቦ በወዳጅነትና በሥልጣን ትልቁን የሹመትና የቅድስና መድረክ በመረከብ መጽሐፍቱን መዝረፍና ታሪኩንም የራስ ማድረግ ነው፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸው ብሉያት መጻሕፍት ያዘሏቸው ምስጢራትን ለማወቅ ግዕዝን ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ ብዙዎቹ ምስጢራት የያዟቸው አበይት ቀመሮች ጽንፈ ዓለሙን (Universe) በአጠቃላይ ይመለከታሉ፡፡ እዚህ ላይ የግዕዝ ፊደላት እያንዳንዳቸው በቁጥር መለያ (Code) የተሰጣቸውና የጽፈት ዓለሙን ኩነቶች ሁሉ በቀመር እንዲታወቅ ማድረጋቸው ብቻ አይደለም ምስጢራቱ፡፡ የፊደላቱ ሆሄያት እያንዳንዳቸው በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ አንድን ነገር እንደሚወክሉ ከትውፊት ወይም ከልቦና መንጭተው እስከ ዘመናችን የዘለቁ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ እጅግ ጥልቅና ምጡቅ የሆነ የፊደላት ሚና እስካሁን ምንም ዓይነት ምርምር የተደረገበት አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩ ግን እንዲህ በቸልታና በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም፡፡
በዚህ በኩል የግዕዙ ልሒቃን ምርምሩን አጠንክረው ቢይዙት የግዕዝ አኃዞችም ደረጃና ምስጢራት በአግባቡ ይታወቁ ዘንድ እግረ መንገዱን ይረዳል የሚል ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡ መዝገበ አኃዝ ዘኢትዮጵያን (ገጽ 73) የጻፉት መሪጌታ በፈቃዱ፤ “ይህ አኃዝ የቤ/ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሀብት ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሀገሩን አኃዝ ማወቅ ይገባዋል፡፡” ሲሉ ያሳሰቡትም ከጠቀስኩት አቢይ ሃሳብ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያላቸው ውክልና መጠናት እንዳለበት ያሳሰብኩት ጉዳዩ ፊደሉ ይቀነስ ወይስ እንዳለ ይቀጥል? የሚለውን የክርክር ሃሳብ ስለሚፈታም ጭምር ነው፡፡ ለመሆኑ ፊደላቱ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ምንን ይወክላሉ? ለሚለው ጥያቄ አጭር ምሳሌያዊ መልስ ይሆን እንደሆነ በማሰብ በጥቂቱ ልዘርዝር። በእኔ ያልታወቀው ጉዳይ የትኛው ሆሄ የምን ውክልና አለው? የሚለው ነው፡፡ በተረፈማ ፊደላቱ ለመዘርዘር የሚያታክቱትን ሁሉ ይወክላሉ ይባላል።
በምድር - ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሕይወት ያላቸውንና የሌላቸውን፣ መናፍስትንም ጭምር። ሰውንና አራቱ የሥጋና ሦስቱን የነፍስ ባሕሪያቱን
በአየር - ነፋሳትን፣ ውሃዎችን፣ ሌሎች ረቂቆችን፣ ብርሃናትን
በሰማያት - ሰባቱ መሳክዎ ሰማያትን፣ 24ቱን ካሕናተ ሰማያትን፣ ከዋክብትን (ሚልክዌ፣ ጋላክሲ ወዘተ) የትየለሌ (Infinitive) የሚባሉትን፤ አምላክን፣ መላዕክታትን…፣ ፕላኔቶችን፣ ጨረቃዎችን፣ ሌሎች ዓለማትን-- ወዘተ፡፡
ለምሳሌ ከሰው የሥጋ ባሕርያት አንዱ እሳት ነው፡፡ እሳት ደግሞ ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ስንጉረ፣ ሰናስለ እና መሐፒለ እሳት የሚባሉት እያንዳንዳቸው 5 ሚሊዮን እሳቶች ሲኖራቸው፣ ሦስቱ 15 ሚሊዮን እሳቶች አሏቸው ማለት ነው፡፡ ውሃዎች፣ ነፋሳት፣ መናፍስት እንደ ከዋክብቱ ሁሉ የትየለሌ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ፊደሎቻችን እነዚህን ሁሉ ወክለው እንደተቀመጡ ይነገራል፡፡ የሆሄያቱ መጀመሪያ ሀ-ለ-ሐ ወዘተ ግዕዝ ይባላሉ፡፡
እነዚህ በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምናልባትም የውክልና መነሻ ይሆን? ስለዚህ ጉዳይ መሪጌታ ፈቃዱ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው (ገጽ 73)፤ የግዕዝ ፊደላትን ትርጉም “ሀ” ማለት “የአብ አኗኗር ከዓለም በፊት ነው” የሚል ሠፍሮ የሁሉም ትርጉም እስከ “ፐ” ቀጥሏል። እዚህ ነጥብ ላይ አንድ የቅርብ ጓደኛዬ የፊደላቱን የተናጠል ውክልና በተመለከተ ሁለት ነገሮችን ነግሮኛል፡፡ አንደኛው የፊደላት ውክልና ሲሆን  ሌላው ደግሞ የኩነቶች የጊዜ ቀመርን ይመለከታል። በዚህ ጽንፈ ዓለም ውስጥ “ጸ” የሚባለው ሆሄ ጸሎቱ በሚል ይታወቃል፡፡ ጸሎቱ “ጸ” ከሰባቱ ዘሮቹ ጋር ለመላዕክታትና ለመለኮት ውክልና የተሰጣቸው መሆኑን በአንድ ሊቅ እንደተነገረው ጓደኛዬ አስረዳኝ፡፡ ለምሳሌም ግዕዙ “ጸ” በምድር ላይ ሰዎችን ለማጥቃት ሰይጣን የሚያሰማራቸውን ርኩስ መናፍስትን ለሚዋጉ የመላዕክት ተዋጊዎች በአርማነት ማገለገል አንዱ ውክልናው እንደሆነ፤ በአሁኑ ወቅትም በዓለማችን ሕዝብ ዘንድ በስጋትነት የተንሰራፋውን ኤችአይቪ ቫይረስን ለመከላከል የወጣው ምልክት ቅርፁ “ጸ” መሆኑ ትክክለኛ የፊደላችን ውክልና እንደሆነ ሊቁ እንዳስረዱት ነግሮኛል፡፡ ይህን ምልክት ያመጡ ሰዎች በመላዕክቱ መንፈሳዊ ወይም ልባዊ ምክር እንደሆነም ጨምሮ ገልፆልኛል፡፡ በዚህም  እጅጉን ተገርሜያለሁ፡፡
 እኚሁ ሊቅ ለጓደኛዬ እንደነገሩት ከሆነ፣ በዓለማችን ላይ በሥልጣኔ የገዘፈች ሀገር ሁለት መንትያ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች በክፉ ሰዎች ተነሳሽነት የሚፈርሱበት ጊዜ በግዕዝ የፊደልና የአኃዝ ጥምረት ተቀምሮ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 1 ቀን 1992 መሆኑ ይታወቅ እንደነበር ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉትንና ሌሎችንም ዘበት የሚመስሉ ትውፊቶች ንቆ ለማለፍ ይቻል እንደሆነ በእውነቱ መናገር ይከብደኛል፡፡ ለማንኛውም የግዕዝ ፊደላት ከነሙሉ ክብራቸው ግዕዝንና አማርኛን ማገልገል እንደሚኖርባቸው በጠቃቀስኳቸው ሃሳቦች መሠረት ማመን ይቻላል፡፡ ፊደላቱ እንዳይሸራረፉ ሌላው አሳማኝ ጉዳይ በሞክሼ ፊደላቱ የተጻፉ ጥንታውያን መጻሕፍት ያሰፈሯቸው ቃላት እንደየአገባባቸው ትርጉማቸው ስለሚለያዩ፣ የተመዘገበውን ታሪክ መጭው ትውልድ እንዲያውቀውና እንዲመራመርበት ሙሉውን ፊደላት ማወቅ ግድ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም ላለማንዛዛት ስም ተቆጥቤአለሁ፡፡ ሆኖም ይትባረክ ገሠሠ የሚባሉ ጸሐፊ፤ “ኪነጥበብ ሥነጥበብ ዘጠነኛ” በሚል ካዘጋጁት መጽሐፍ (ገጽ ሠ) ላይ ያሠፈሩትን በአጭሩ እጠቅሳለሁ፡፡ “በግዕዝ እግዚአብሔርን ለማመስገን የተለያዩ የክብር ቃላት አሉ፡፡ ባረከ፣ ቀደሰ፣ አእኰተ፣ ወደሰ፣ ሰብሐ…የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሁሉም አመሰገነ ማለት ነው፡፡…በዘፈቀደ የፈለግነውና የቀናንን ቃል ጐትተን አንጽፍም፡፡ ቦታ ቦታ አላቸው፡፡ የሚለዩትም በትምሕርት ብቻ ሳይሆን በልብ ስብራት ጭምር ነው፡፡” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ እነዚህን ቃላት አማርኛም ይጠቀምባቸዋል፡፡ ስለሆነም ከፊደላቱ ውስጥ “ሰ፣ አ፣ ሐ” ቢቀነሱ ቀሪው ቃል “ባረከ” የሚለው ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ ደግሞ መንፈሳዊ ግንኙነታችንን በሙሉ ይወጣል ማለት አይቻልም፡፡ በተለዋጩ ፊደላት ደግሞ “ቀደሠ፣ ዐዕኰተ፣ ወደሠ፣ ሠብሀ ወይመ ሠብኃ” ብለን ብንጽፍ፣ ቃላቱ የሆሄ ጥርቅም እንጂ የሚታወቁ አይደሉም። በዚህና በቅንነት ታሪካችንን ጠብቆ ለመሄድ የሚያስችሉ ምክንያቶችን በመቀበል ፊደሉ ሳይሸራረፍ በእንክብካቤና በጥበቃ እንዲቀጥል ማድረግ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሆነ ማመን ይቻላል፡፡ መልካም ጊዜ፡፡  

Read 3597 times