Saturday, 07 February 2015 13:24

የጉዞ ማስታወሻዬ ከውሃ እስከ ውሃ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

     አሁንም አሶሳ ነኝ፡፡ የመጨረሻው ሰዓት ላይ! ስንጓዝ ውለን ደርሰን፤ በግድቡ ዙሪያ ምሣ አለ የተባለበት ቦታ ሰልፍ አለ፡፡ ረሀብ አለብን፤ ግርግር አለ፡፡ ምሬት በሽበሽ ነው፡፡ ምሳ ግን የለም፡፡ ሰው ወዲያ ወዲህ ይላል፡፡ በሚቀጥለው ፕሮግራም ይሄ ይሄ ነው የሚል አንዳችም ሰው አልተገኘም፡፡ (ብሄር ብሄረሰቦች ትናንት ማታ አምሽተን ስለገባን ራት አልበላንም እያሉ ነው፡፡ አይዟችሁ የሚል አላገኙም፡፡) እኔና ኃይሉ ፀጋዬ  ከብዙ መንገላታት በኋላ የግዢ ምግብ ፍለጋ መንገድ ጀመርን፡፡ አንድ የአገሬው ወጣት “ኑ ምግብ ያለበት ላሳያችሁ” ብሎን የጀማውን የሰልፍ ትርምስና ምግብ ቦታ ጥለን ልጁን ተከተልነው፡፡ የግድቡ ሰራተኞች መኖሪያ በሚመስሉ ቤቶች እያቆራረጥን ሄደን አንድ ትልቅ መዝናኛ ክበብ መሰል አዳራሽ ደረስን፡፡ የአዳራሹን ግማሽ የእንግሊዝ ፉትቦል ተመልካቾች ይዘውታል፡፡ ወደ ቲቪው ፊታቸውን መልሰው፣ ጀርባቸውን ለእኛ ሰጥተውናል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ከእናት ክፍላችን ተነጥለናል፡፡ እኛም የት አሉ? አንል፡፡ እነሱም የት ደረሱ አይሉን! ለነገሩ ቀድሞም ቅጥ አልነበረን፣ አሁምን ቅጥ የለንም!
ባለ ክበቦቹ ሽሮና ጥብስ አለን ይላሉ፡፡ መክፈያውና መስተናገጃው የተለያየ ቦታ ነው። ምግቡ እስኪመጣ ቢራ አዘዝን፡፡ በመጨረሻ፤ የተገኘውን፣ ቤት ያፈራውን ቀመስን፡፡ ቀጥሎ የማታ መኝታ ድልድል፤ አልጋ ወደሚሰጥበት ሄድን፡፡ እግዜር ይስጣቸው፡፡ እነዚህ ወዲያው አልጋችንን ሊሰጡን ቃል ገቡ፡፡ አንድ ሰው ተመደበልን። ይዞን ሄደ፡፡ ሳሙና፣ ሶፍት ከአዲስ አንሶላ  ጋር ሰጠን። ለነገሩ የሚነግረን ጠፍቶ ነው እንጂ ስማችንና ክፍላችን በቢሮው ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ነበር አሉ፡፡ አንዳንድ፤ አመራር ውስጥ ጭምር ያሉ ወዳጆቻችንጋ፣ ስንደውል እነሱ ጥሬ ስጋ ጭምር ተመግበው እንደነበርና አሁን እየተዝናኑ መሆኑን አወቅን፡፡
“ዓለም አላፊ ነው - መልክ ረጋፊ ነው - ፎቶግራፍ ቀሪ ነው!” ተባባልን - እኔና ወዳጄ! በየአልጋችን አረፍ አልን፡፡ በኋላ የተባለውን ክለብ አገኘነው፡፡ ይብላኝ ገንዘብ ለሌላቸው ለምስኪኖቹ ባለ ጉዳዮች እንጂ ላለው ምን ጠፍቶ?
ኢትዮጵያ እንደዚህ ናት!
አመሻሹ ላይ፤ ወደ ግድቡ ከነንዋይና ከነአረጋኸኝ ጋር በመኪና ሄድን፡፡ ብዙ ሳንቸገር ለጥበቃዎቹ እነንዋይ እያስረዱ ግድቡ ፕሮግራም ደጃፍ አፍ ድረስ ገባን፡፡
ከአፋፉ ላይ ሆነው ግድቡን ማየት ትንፋሽ ያሳጥራል፡፡ (Breath - takingly - beautiful እንደሚሉት ፈረንጆቹ) የብሔር ብሔረሰብ የባህል ቡድኖች ከእግር ጉዞ በኋላ ደረሱ፡፡ (እኛ በመልካም መኪና ቀድመናቸዋል፤ ታድለናል!) ሲገቡ ይታዩናል፡፡ (ሁሌም ይሄ ትርዒት ያሳዝነኛል፡፡ አሁን እኛ ምን ቤት ነን? ዋናዎቹ?! እነሱ እያሉ የሚል ስሜት አለኝ)
መድረኩ በትልቁ ተገንብቷል (gloriously)፡፡ ከመድረኩ ጀርባ ታላቁን ግድብ የሚሰሩ በክሬንና በተለያዩ መሳሪያዎች ሌት ተቀን የሚታትሩ ትጉህ ባለሙያዎች ይታያሉ፡፡ በጣም ይማርካሉ። የመድረኩን ግርማ ሞገስ ለማድመቅ የበሩት ባውዛዎች አገር ምድሩን አፍክተውታል፡፡ ከአየር ላይ የተጠመደ ካሜራም ይታየኛል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ባህል ቡድኖች ማህሉን ሜዳ በደማቅ ዳንስ ማጀብ የበለጠ ሽብረቃ ሆኖታል፡፡
ከመድረኩ በታች ማዶ የሚታዩት ታዳሚዎች (ክቡሮቹም ጭምር) ከሩቅ ይታዩናል፡፡ በመድረኩና በታዳሚዎቹ መካከል ያለው ሜዳ ላይ ነው ጨዋታው የደራው፡፡ መላ - ነገሩ፤ ንዋይና አረጋኸኝን ጨምሮ የተለያዩ ድምፃውያን፣ “የ8100-ኤ” ኮሜዲያንና፤ ገጣሚያን የተካፈሉበት ፕሮግራም ነበር፡፡ ሁለት የመድረክ አስተዋዋቂዎች አሉ፡፡ እኔ ከብዙ አርቲስቶች ጋር ከመድረኩ ጀርባ ነኝ፡፡ ከእኛ ጀርባ ደግሞ ሌት ተቀን ስራቸውን የሚያቀርቡት የግድብ ስራ ባለሙያዎች በሰማይ በክሬን ላይ፤ በመሬት በትናንሽ የሥራ መኪናዎች ወዲህ ወዲያ ሲሉ ነው የሚታየው፡፡
የግድቡ ጉድጓድ ዟ ብሎ አፉን ከፍቶ ተኝቷል። ያለጥርጥር ግዙፍ ግድብ ነው፡፡ በማታ እጅግ ደማቅ እጅግ ውብ ነው፡፡ ዐባይ ባንድኛው ወገን ሲንፎለፎል ይታያል! ለተወሰነ ደቂቃ መንፈሴን ሰቅዞ ይዞታል፡፡ ወዳጆቼን ሁሉ ኑ እዩት! አልኩ፡፡ ዐባይን ማሰብና፣ ቀርቦ ማየትና መንካት፣ ፈሊጡ ለየቅል ነው! ስለግድቡ ያለንን መንዲስ ምኞትና ሰፊ ምናብ ከጨመርንበት ልዩ ስሜት ይሰማናል! ከአፎቱ ተርፎ ሲፈስ 262 ኪ.ሜ ግድም (ከአዲስ አበባ እስከ ዝዋይ) እንደሚንሰራፋ ለሚያውቅ፤ ግዙፍነቱ ይህ ወሰንህ ይህ ዲካህ የማይሰኝ፣ እጅግ ሰፊ መሆኑን ለማየት አያዳግትም፡፡ እኛማ ገና ስንመጣ አውቀነዋል፡፡ ገና መንገድ ላይ ሳለን፤ ለምን ዛፉ ይመነጠራል? ስንል፤ “ዐባይ የት ይተኛ?” አሉን፡፡ “እንኳን መተኛ ማንኮራፊያም አለው!” ብለን ተሳሳቅን! አያ - አዎ ነው ነገሩ - paradox፡፡ ድህነትን ለማጥፋት ምንም ከማድረግ አንመለስም!
መድረኩ፤ ከታዳሚው መካከል ያሉ አርቲስቶች ጓደኞቻችን ደማቅ እይታ እንደነበር አጫውተውናል። በጭፈራው አቧራው ሲጨስ እኛም ከመድረክ ኋላ ሆነን ይታየናል፡፡ ለአርቲስት ጓደኞቻችን፤ እኛ ስለቀኑ የምሳ ረሃብ ስናወራላቸው ግን፤
“እናንተ ሰፊውን ህዝብ ትላላችሁ፡፡ እዚያ ከታደምነው መካከል፤ ካሉን ጥቂት ሴት ሚኒስትሮች ውስጥ አንዷ፤ እራት ፈልጉልኝ ብለው ብንፈልግ አጥተናል!” አሉኝ፡፡ “ገደደ!” አልን፤ የባሰ አታምጣ እንደማለት!
እኔ እስካየሁት ድረስ የብሔር ብሔረሰቦች ምግብ አለማግኘት አንጀቴ ውስጥ ገብቶ ስለነበር፤ የሚኒስትሮቹ አለማግኘት አላስገረመኝም፡፡ አላስጨነቀኝም፡፡ እንደፌዝ “የሚኒስትሮች ቀን ቢኖርና ዛሬ ቢሆንስ? ምን ሊሉ ነው!?” ብዬ ከጓደኞቼ ጋር ተሳስቀናል፡፡  
በተለያዩ ባለስልጣናት ተገቢ ናቸው የተባሉ ንግግሮች ተካሄዱ፡፡ የመድረክ ምስቅልቅል መጠነኛ ችግር እዚህም ታይቷል፡፡ የዘፋኞች ዓይነተኛ ምሬትም አልጠፋም፡፡ እኔም ግጥሜን አላነበብኩም። በኋላ እንደተነገረኝ ከሱዳን የመጡ ሙዚቀኞች Last Minute ላይ መጥተው አጨናንቀውን ፕሮግራሞች ተዛብቶብን ነው ያሉት፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው የ Disorganization አካል ነው፡፡ ፕሮግራሙን በአንክሮ አለማቀናጀት! ከዚህ ብዙም ተለይተን ስለማናውቅ ብዙ አልገረመኝም፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ሥራዎቻቸውን አልቀረቡም፡፡
ወደ መኝታችን አምሽተን ነው የሄድነው፡፡ የምሽቱን ፕሮግራም ለመወያየትም ጊዜም አቅምም አልነበረም፡፡ እንደተለመደው ነገ በጠዋት እንነሳለን ስለተባለ በጊዜ እንተኛ ብለን ወደ ማረፊያችን ሄድን!
*           *           *
በነጋታው አሶሳ ደርሰን ልዩ ልዩ ሲምፖዚየሞች ሲካሄዱ ውለዋል፡፡ እኔ ከዘነበ ዎላና ከጓደኛው ጋር በ1959 ዓ.ም ብርሃነ መስቀል ረዳ (ከኢህአፓ መሪዎች አንዱ) በአሶሳ ከተማ አቋቁሞታል ወደተባለው መጽሐፍት ቤት ለጉብኝት ልሄድ ጓጉቻለሁ፡፡ በስዩም ወልዴ ራምሴም የግለ - ታሪክ መጽሐፍ “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ አንብቤያለሁ፡-
“በ1959 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ባህር ዳር በኋላም ወደ አሰብ ተጉዣለሁ፡፡ የባህርዳሩን የፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ጉብኝት አዘጋጅቶ “ጋዜጠኞችን” የጋበዘው አዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ነው። ቡድኑ በብዙ አንቱ በተባሉ አንጋፋ “ጋዜጠኞች” የተሞላ ነበር፡፡ ከብስራተ - ወንጌል የሄድኩት እኔ ስሆን በዕድሜና በስራ ጀማሪነቴ ታናሽ እኔው ነበርኩ፡፡ ለዕድሜዬ ቀረብ የሚለኝ ያገኘሁት አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡     እርሱንም ዘጠነኛ ተማሪ  በነበርኩበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተዘጋጀ “ካፒቴን ትስዊት” በተሰኘ ቴአትር ውስጥ ሲካፈል ያየሁት የዩኒቨርሲቲው አንደኛ ዓመት ተማሪ ነበር። ባንተዋወቅም በተዋናይነት ስላየሁት በቅርብ እንደማውቀው ሰው ተጠጋሁት። በጉዞአችን ወቅት በነበረው እንቅስቃሴ ሁሉ አንድ ላይ ስለታየን ባህር ዳርም እንደደረስን የሆቴል ድልድል ሲደረግ ከእርሱ ጋር አንድ ክፍል ተሰጠን፡፡ ለእኔ ከእርሱ ጋር መሆኑ አስደስቶኛል። ሌሎቹ ጋዜጠኞች ግን እርሱ አጠገብ መቆምም፣ መታየትም አይፈልጉም ነበር፡፡ “እናንተ ጎረምሶች ታዲያስ?” ይሉናል፡፡ በአውሮፕላን ደርሶ መልስ ውሎ አዳር በነበረው ጉዞ ሙሉ የሁለታችን ውይይት ከጉብኝቱ ጋር እምብዛም የተያያዘ አልነበረም፡፡ በሁለታችንም ዘንድ በጎ የመንፈስ መቀራረብ ይሰማ ነበር፡፡ ወጣቱ ጋዜጠኛ የሔራልድ ጋዜጣ ዘጋቢ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነቱ ለተወሰነ ጊዜ በቅጣት ተገልሏል፡፡ ጋዜጠኞቹ የሚሸሹት በአደገኛነት የሚታይ ሰው ስለነበር ነው፡፡ ይህን ሚሥጥር በውይይታችን ወቅት እሱ ራሱ ባይነግረኝ ኖሮ አላውቅም ነበር፡፡ ሁኔታውን ከተገነዘብኩ በኋላም ቁም ነገሬም ብዬም አልተጨነኩበትም፡፡ ጉዞውን በመግባባት ጀምረን በመግባባት ጨረስነው፡፡ በመጨረሻ ግን አንዱ በቅርብ የሚያውቀኝ ጋዜጠኛ “ከዚህ አደገኛ ሰው ጋር ምን አጣበቀህ?!” ብሎ ነገር ጣል እንዳደረገብኝ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሶ መደበኛ ተማሪ ሆነ፡፡ በ1960 ዓ.ም በብሔራዊ አገልግሎት ተልዕኮ አሶሳ ያስተምር ነበር። እዚያም ቤተመጻሕፍት አሰርቶ በዓመቱ አጋማሽ ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ መፅሐፍትንና የመሳሰሉ ነገሮች ለመለመን አዲስ አበባ መጣ፡፡ በሬዲዮም በጋዜጣም ሀሳቡን ካሳወቀ በኋላ በግል ለሚያውቃቸው ሰዎች ስልክ እየደወለ እርዳታ ይጠይቅ ስለነበረ እኔን በዚህ እንድሳተፍ በጠየቀኝ መሰረት አንድ ቀን ወደ ሬዲዮ ጣቢያው ይዤው መጣሁ፡፡ በየቢሮው እየገባን መፅሐፍትና የመጽሐፍት መግዣም ገንዘብ ከየግለሰቦች ስንሰበስብ ቆየንና በመጨረሻ ከጣቢያው ኢትዮጵያዊ አማካሪ ቢሮ ገባን፡፡ አስተዋወኩት፡፡ አማካሪውም ስለእርሱ ተግባር በጋዜጣ ማንበባቸውንና ብዙ የወንጌል ማስተማሪያ ኃይማኖታዊ መፅሐፍት ሊሰጡት እንደሚችሉ ቃል ከገቡለት በኋላ ለዚያ አካባቢ ህዝብ እንዲህ ያለውን ተግባር ለማከናወን ከመጨነቅ ይልቅ ወደ አባቱ አገር ሄዶ ቢሰራ የተሻለ ይሆን እንደነበር ነገሩት፡፡ ራሱን ለመቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ ተቆጥቶ ምክራቸውን እንደማይቀበል ሲገልጥላቸው፡- “እኔኮ አሁን በስምም በመልክም አውቄሃለሁ፤ የአቶ ረዳ ልጅ አይደለህም? ብርሃነ መስቀል ረዳ፡፡ ለዚህ ብዬ ነው እንዲህ የመከርኩህ” አሉት፡፡ ቃል የገቡለትንም መፅሐፍ እንደማይቀበል ነግሮአቸው ተከታትለን ወጣን፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አውሮፕላን በጠለፋ አስገድደው ከወጡት ሶስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ሆነ፡፡ በኋላም ከኢ.ሕ.አፓ መሥራቾችና መሪዎች አንዱ ነበር ይባላል”፡፡
ይህን የማውቀውን ታሪክ በአዕምሮዬ ይዤ ነበር ወደ ጉብኝቱ ያመራነው፡፡ ጓጉቻለሁ፡፡ ብርሃነ የእኔ ትውልድ ሰው ስለሆነ ነው መሰለኝ ስስ (sensational) ሆኛለሁ፡፡ በዚያን ዘመን የብርሃነ መስቀል ተማሪ የነበሩ አቶ ስንታየሁ ቀልቤሳን በስልክ አግኝቻቸው ደግሞ እንዲህ ብለውኛል፡-
“ያኔ ተማሪው ነበርኩኝ፡፡ ሂሳብ ተማሪ ነበርኩ” አሉ፡፡
“አቶ ስንታየሁ ማን ልበል?” አልኳቸው፡፡
“ቀልቤሳ” አሉኝ፡፡
“የት ት/ቤት ነው?”
“አሶሳ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው የሚባለው፡፡ ብርሃነ መስቀል ረዳ እዛ አስተማሪ ነበር፡፡ ይወደኝ ነበር፡፡ መጽሐፍት ቤቱን ከማቋቋሙ በፊት ብዙ ዓይነት ውጣ ውረዶች ነበሩበት! ከሰራው በኋላ መጽሐፍ አጠረው፡፡ ወደ ክልል አካባቢ፤ ወደ ለቀምት … አምቦ ሄዶ መጽሐፍ ይለምን ነበር፡፡ አጠራቅሞ ነው ተማሪዎቹ ዕውቀት እንዲቀስሙ ያደረገው፡፡ …ዘወትር አፍሮ ፀጉር የነበረው ብርሃነ መስቀል ጎበዝ ነው፤ ታታሪ ነው … ቤተ መጻሕፍቱ ዛሬ ደህና ብቅ ብሏል!”
“ማን ያስተዳድረዋል?” አልኳቸው
“ራሱ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቱ ነዋ!”
በብሔር ብሔረሰብ በዓል ምክንያት ይመስለኛል እንደ ብዙ መ/ቤቶች ሁሉ የብርሃነ መስቀል መጽሐፍት ቤትም ተዘግቶ ደረስን፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ የለንም፡፡ አዘንኩኝ፡፡ ከብሔር ብሔረሰቦች በዓል ጋር በተያያዘ አንድ በአዕምሮዬ ያልጠፋ ነገር አለ፡፡ አንድ ዕለቱን በቅርብ የተከታተለ ወዳጄ ያጫወተኝ ትርዒት ነው፡፡ ከዘጠነኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኅዳር 29 2007 ዓ.ም አከባበር አንዱ አካል የሆነው ዋንጫ የመረካከብ ሥርዓት ነው፡፡ ለሃያ ስድስት ቀናት በመኪና የተጓዘው ዋንጫ ወደ አሶሳ ሲመጣ፤ ምን የገጠማችሁ ነገር ነበር? ያልኩት ከሁለቱ ዋንጫ አምጪ አርቲስቶችና ማስታወቂያዎች አንደኛው “ህዝቡ በየወረዳው ዋንጫውን ካላሳደርነው ማለቱ ነበር ችግራችን!” ብሎኛል፡፡ ዋንጫው በመኪና ከመጣ በኋላ አሶሳ በዓሉ የሚከበርበት ግቢ ግን የገባው በተለየ መንገድ ነበር፡-
ዋንጫው የመጣው በሄሊኮፕተር ነበር፡፡ (ይሄ ፈጠራ ነው ያሉኝ አሉ) ዋንጫው የተንጠለጠለበት ገመድ አጠረ፡፡ ስለዚህ ዋንጫው መሬት አልደርስ አለ፡፡ ያለ ጥርጥር ሄሊኮፕተሩ ዝቅ ካላለ ዋንጫውን የሚቀበለው ሰው እጅ ውስጥ አይገባም፡፡ ስለሆኑም ሄሊኮፕተሩ ዝቅ ማለት ጀመረ፡፡ ጉዱ እዚህ ላይ ነው! (ገደደ! የሚሉት ነው የሰሜን ወንድሞቼ! ) ሄሊኮፕተሩ ዝቅ ሲል የተኛ አውሎ ንፋስ ቀሰቀሰ! ግቢው በንፋስ ታመሰ፡፡ ከየቦታው ለበዓሉ ድምቀት የመጡት ቆነጃጅት የት ይግቡ? በየወንበሩ ሥር!! የኦርኬስትራው ኖታ ከስቴጁ አየር ላይ በረረ! ታዳሚዎች አንዱ አንዱን መሸፈን፣ ፊትና ፊት መከናነብ ግድ ሆነ! ዋንጫውን ተረካቢው ገመዱን ከዋንጫው ለማላቀቅ ከአቧራው እሽክርክሪት መታገል ነበረበት! ኋላም ሲያወራ “ጉድ ሆነናል ኧረ!” ነው ያለው!!
ትልቅ ዝግጅት ተደርጎ በትንሽ አለማስተዋል “ዕዳ ከሜዳ!” ሲያጋጥመው ማየት አሳዛኝ፣ አንዳዴም አስደንጋጭ ነው! ዋንጫውን በሄሊኮፕተር ማምጣት በእርግጥ ፈጠራ ነውን? አንዳንዶች እንደቀለዱት “በየብስም በአየርም” የተጓዘው ዋንጫችን!” ለማለት ነውን? ከሆነስ በቂ ዝግጅት ነበረውን? ምን ያህል ዋጋ አስከፍሎ ይሆን? “ለነገ ያብቃን ለማተቱ
ፍሬ ነገሩ ተውኔቱ!”
በሚለው በሐምሌት መራር ቋንቋ ልደምድመው! የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በደማመቀ ባህላዊና ዘመናዊ ዝግጅት አበቃ፡፡ የመለያያ ግብዣ ተደረገ፡፡ ያቺን አሶሳ፤ ከነቀርከሃዋ፣ ከነ አሾተሬ የሚባል ባቄላዋ፣ ከሚያገለግለው ክማ፣ ከነቄንቄስዋ (Lady’s finger)፣ ከነከድከዴዋ፤ ከነሞቀ አየርዋ … ተሰናብተን ወደ አዲስ አበባ ልናመራ፤ በአካልም፣ በመንፈስም ተዘገጃጀንና ፊታችንን ወደ አዲስ አበባ አዙረን ተኛን!  
የካይሮ ጉዞዬ
ከአሶሳ ተመልሼ ብዙም ሳልቆይ ዓርብ እለት ስብሰባ አለ የሚል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ ፖስታ አየሁ፡፡ ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ደውሎ ጉዳዩ ወደ ካይሮ ጉዞ ሊደረግ መሆኑንና ፓስፖርትና ፎቶግራፍ ማዘጋጀት እንዳለብኝና፤ ከ60ዎቹ ልዑካን አንዱ እንደሆንኩ አበክሮ ነገረኝ፡፡ በዛው ቀን ስለጉዳዩ የምታውቅ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ደወለችና “ነቢይ ብትሄድ ጥሩ ነው!” ብላ  አፅንኦት ሰጠችው። “ከውሃ ወደ ውሃ ጉዞ መጣብኝ/መጣልኝ!!” አልኩ፡፡ ፓስፖርቴ አልታደሰም፡፡ ደሞም የት እንዳረኩት እንጃ! ለመዘገጃጀት አሰብኩ፡፡ አንድ ወዳጄን ስለጥንታዊቷ ግብፅ መፅሐፍ ስጠኝ አልኩት፡፡ አንባቢ ሰው ጥሩ ነው Ancient Egypt ጥንታዊቷ ግብፅ የሚል ቆንጆ መፅሐፍ አመጣልኝ! የግብፅን ነገሥታት ታሪክ ከዱሮ ትምርታችን እስካሁን ለማገናኘት መንገድ ጀመርኩ - የንባብ!
እንግዲህ ዋና ዋናዎቹ ጥያቄዎች በአዕምሮዬ መጡ፡-
የኢትዮጵ የፐብሊክ ዲፕሊማሲ ልዑካን ዓላማ ምንድነው?
የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑካን እነማናቸው? እንዴት ተመረጡ? ዕውነት ኢትዮጵያን ይወክላሉ ወይ?
ዓርብ ታሕሳስ 3 2007 በ8 ሰዓት የተጠራው ስብሰባ ፍሬ - ነገረ ምንድነው?
የሰኞ ጠዋት ታህሳስ 6 2007 ስብሰባስ ምን ፍሬ አፈራ?
የአጠቃላይ የካይሮ ጉዞ ፕሮግራም ዝርዝር ምን ነበር?
እኔና ተጓዦቹ እንዴት አየነው?
(ይቀጥላል)

Read 1742 times