Saturday, 31 January 2015 12:52

በ21ኛው ክ/ዘመን ተቃዋሚዎችን መደብደብ አይመከርም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)
  • የሰለጠነ ተቃዋሚ በላቀ ብስለት እንጂ በእልህ አይመራም
  • የአስለቃሽ ጭስ ችግራችንን ኒዮሊበራል መንግስታት ይታደጉን  
  • እነ “አንድነት” እርስ በርስ ከሚወነጃጀሉ ቢናዘዙ ይሻላቸው ነበር

     እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ የዛሬውም ጉዳያችን ትንሽ ጠነን የሚል ስለሆነ፣ ወጋችንን ዘና ብለን እንጀምረው - በቀልድ፡፡ መጀመሪያ “ቀልድታትን አሽሙራትን ምህረይ ወሊሃንስ” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ ከወጣ የትግርኛ መጽሐፍ ውስጥ እኔና ጓደኞቼን በሳቅ ካፈረሱን ቀልዶች (ስላቆች) መካከል አንዱን ላቅምሳችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የመፅሐፉ ዳሰሳ (Review) በጥበብ አምድ ላይ ስለወጣ አብዛኛውን ጉዳይ ከዚያ ልታነቡ ትችላላችሁ፡፡
የመፅሐፉ ባለታሪክ ምህረይ ወልደዮሐንስ፤ በአክሱም “እብድ” እየተባሉ የኖሩና እሳቸውም ማበዳቸውን ተቀብለው እስከ ዕለተ ሞታቸው የኖሩ ታላቅ ሰው እንደነበሩ አዘጋጁ ጠቁሟል፡፡ እናላችሁ…ምህረይ አንዱን ታጋይ እንዲህ ይሉታል፤ “ደርግ ስኳር ይሰጠን ነበር፤ ጡረታም ይከፍለናል፤ እናንተ ይሄን ሁሉ ጊዜ ታግላችሁ…ለህዝቡ ምን ይዛችሁ ነው የመጣችሁት?”
ታጋዩም፤ “ዲሞክራሲ” ሲል ይመልሳቸዋል፡፡
“ዲሞክራሲ ደሞ ምንድነው?” ይጠይቁታል
“ሰው ሃሳቡን እንደፈለገ ያለገደብ በነፃነት የሚናገርበት መብት ነው” ሲል ያስረዳቸዋል፡፡
ምህረይም፤ “እህ… እንዲህ እንደኛ” ይሉታል (እንደ አበድነው ማለታቸው ነው)
አንድ ሌላ ቀልድ ደግሞ ልመርቅላችሁ - ከባህርማዶ፡  
አንድ ራሽያዊ ከአገሩ ይሰደድና ሰተት ብሎ አሜሪካ ኒውዮርክ ሲቲ ይገባል፡፡ በከተማዋ ጐዳና ላይ ሲዟዟር ይቆይና ፊትለፊት ያገኘውን የመጀመሪያ ሰው በማስቆም፤ “ሚ/ር አሜሪካ፤ ወደ አገራችሁ እንድገባ ስለፈቀዳችሁልኝ አመሰግናለሁ፡፡ ምግብ፣ መኖሪያ ቤት፣ ህክምና፣ ትምህርት…በነፃ ስለሰጣችሁኝ ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ!” ይለዋል - ከልቡ፡፡
ስደተኛውን ሲያዳምጥ የቆየው መንገደኛም፤ “ተሳስተሃል የእኔ ወንድም፤ እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም፤ የሜክሲኮ ተወላጅ ነኝ” በማለት ይመልስለታል፡፡
ስደተኛው ትንሽ እንደተጓዘ ሌላ ሰው ያገኝና፤ “እንዲህ ያለች ውብ አገር ስለፈጠራችሁ አመሰግናለሁ”  
ሰውየውም፤ “እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም፤ ቬትናም ነኝ” ሲል ይመልስለታል፡፡
ራሽያዊ ስደተኛው ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ መንገድ ላይ የገጠመውን አንድ ሰው ያስቆምና ከጨበጠው በኋላ፤ “ድንቅ አድርጋችሁ ለፈጠራችኋት አሜሪካ አመሰግናለሁ” በማለት ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ሰውየው ግን፤ “እኔ የመካከለኛው ምስራቅ ሰው እንጂ አሜሪካዊ አይደለሁም” ብሎት ጥሎት ይሄዳል፡፡ ግራ የተጋባው ስደተኛ በመጨረሻ አንዲት ሴት ያገኛል፡፡ “አሜሪካዊት ነሽ የእኔ እመቤት?” ይጠይቃታል፡፡
ሴትየዋም፤ “አይደለሁም፤ አፍሪካዊት ነኝ” ትለዋለች።
ስደተኛው ሴትየዋን አፍጥጦ እየተመለከታት፤ “ታዲያ አሜሪካኖቹ የት ነው ያሉት?” ብሎ ይጠይቃታል፡፡
አፍሪካዊቷ ሴት ሰዓቷን አየት ታደርግና፤ “ሥራ ላይ ሳይሆኑ አይቀሩም” ትለዋለች፡፡
በእርግጥም ሥራ ላይ መሆን አለባቸው፡፡ ያለዚያማ ከመላው ዓለም ለሚጐርፍ ስደተኛ የሚበቃ አገር መፍጠር አይችሉም ነበር፡፡ ያውም የታተረ ሁሉ የሚበለፅግባት፤ ሞልቶ የተረፋት ዕፁብ ድንቅ የዲሞክራሲ አገር!! አያችሁ ልዩነታችንን?! እኛ እኮ በፖለቲካው በሉት በኢኮኖሚው አገራችን ለራሳችን እንኳን ስላልበቃችን (አንሳ ሳይሆን በመልካም አስተዳደር ችግር!) ዓይንና ልባችን ስደትን እያማተረ ነው፡፡ (“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” አሉ!)
ሰሞኑን ምሽት ላይ ብቸኛ የማታ መተከዢያዬ (መዝናኛዬ ብላችሁ ዋሾ እሆንባችኋለሁ!) የሆነውን EBCን ስመለከት፤ፕሮግራሙ የአፋርና የሶማሊያ አርብቶአደሮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ እናም ከጉዳዩ ባለቤት (From the horse’s mouth!) እንዲህ የሚል አስተያየት ሰማሁ፤ “የሶማሊያ አርብቶ አደር ችግር:- አንደኛ - ውሃ። ሁለተኛ - ውሃ፡፡ ሦስተኛ - ውሃ፡፡” (ትልቁ ችግራቸው የውሃ እጦት እንደሆነ አስረግጦ መናገሩ ነው!) “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንደሚባለው…እኔ ደግሞ ወዲያው በፖለቲካ መነዘርኩት፡፡ እናም የጦቢያ ፖለቲካ ችግር “አንደኛ - አለመደማመጥ፡፡ ሁለተኛ - አለመደማመጥ። ሦስተኛ - አለመደማመጥ፡፡” ስል አሰብኩ፡፡ ከምሬ እኮ ነው…ዋና ችግራችን እኮ ሌላ ሳይሆን አለመደማመጥ ነው፡፡ በቃ ፈርዶብን አንደማመጥም፡፡ ተቃዋሚዎች እርስ በርስ አይደማመጡም፡፡ ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ፈጽሞ አይደማመጡም፡፡(“አንዱ ሲናገር ሌላው ጆሮውን ይደፍናል!”) ተቃዋሚዎችና ምርጫ ቦርድ አይደማመጡም፡፡ ኢህአዴግና ህዝቡ (ህዝብ እኛ ነን!) አንደማመጥም፡፡(መሰረቱ ህዝብ መሆኑን ብናውቅም!) ተቃዋሚዎችና የመንግስት ተቋማት አይደማመጡም፡፡
ያለመደማመጥ --- ውጤቱ ደግሞ ያለመግባባት፣ ባስ ሲልም ቀውስ ነው፡፡ ያውም ዘርፈ ብዙ ቀውስ… የፖለቲካ ቀውስ -- የኢኮኖሚ ቀውስ… ማህበራዊ ቀውስ -- አገራዊ ቀውስ!!! እኔ የምላችሁ ግን … በአንድ ቋንቋ እያወራን ለምንድነው የማንደማመጠው? አደራ! መልሱን ከእኔ እንዳትጠብቁ! (ለሀገር ሙሉ ችግር እንዴት መልስ አገኛለሁ!) ላለመደማመጣችን ማስረጃ ትፈልጋላችሁ እንዴ? (ሞልቶ ተርፎናል!) አሁን ለምሳሌ ኢህአዴግ የምርጫ ስነምግባር ኮዱን ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር ጠበል ፃዲቅ አልጠጣም ብሎ ምሎ ከተገዘተ ስንት ዓመቱ ነው? ተቃዋሚዎችም ከድርድር በፊት አንፈርማትም ብለው እልህ ከገቡ ስንት በጋ ጠባ? ሆኖም ግን ዘንድሮም እንደ አዲስ ተነስቷል፡፡ ለምን? አይደማመጡማ! ቢደማመጡማ… ሌላ የመግባቢያ ሃሳብ ያፈልቁ ነበር - ቢያንስ ከሁለት አንዳቸው፡፡(ግን እኮ ለመደማመጥም ሌላውን ማክበር  ይጠይቃል !) እኛ ደግሞ ከራሳችን ውጭ ሌላውን ማክበር ውርደት ይመስለናል፡፡ (ነቄ አይደለንማ!)
እኔ የምላችሁ…በምርጫ መዳረሻ ላይ ዕጣፈንታቸው መከፋፈልና መሰነጣጠቅ የሆኑት መኢአድና አንድነት እንዴት እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ እንደሰነበቱ አያችሁልኝ አይደል?! (“ትዝብት ነው ትርፉ” አለ ሀበሻ!) አሁንማ ቦርዱ ገላገለን! በነገራችን ላይ…የተከፈሉት የሁለቱ ፓርቲዎች ቡድኖች ሲሰነዝሩት ለነበረው ውንጀላ ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያጡት አይመስለኝም። (ፓርቲው ውስጥ ነበሩ ብዬ እኮ ነው!) እናላችሁ…ቢያንስ እነ እገሌ ፈፀሙት ብለው ከሚካሰሱ፣እንደ ኑዛዜ ቢያቀርቡልን የተሻለ ነበር፡፡ (እግረመንገዳቸውንም ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃሉ ብዬ እኮ ነው!) እርግጠኛ ነኝ… በመሰንጠቃቸው ወይም በመከፈላቸው ብቻ አንዱ ወገን ከደሙ ንፁህ እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም (እንዴት ይሆናል? በ11ኛው ሰዓት!)
እኔ የምለው ግን … ከዳያስፖራ የሚመጣ ገንዘብ በግል አካውንት ሲገባ፣ አመራሮች ሲበለፅጉበት፣ ፓርቲዎቹ ሲመዘበሩ፣ ሥርዓተ አልበኝነት ሲሰፍን፣ አምባገነንነት ሲንሰራፋ፣ ዳያስፖራው ያልተገባ ተፅዕኖ ሲያሳድር፣ ግለሰቦች ፓርቲዎቹን የግል ኩባንያ ሲያደርጉ፣ ወዘተ… (በኢቢሲ የሰማሁትን ነው!) በማለት ሲወነጅሉ የሰነበቱት ቡድኖች የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ ነበር? (ከሆነ አይቀር ሃቅ ሃቁን ነዋ!) አብረው ሲያፀድቁ፣ አብረው ሲመርጡ፣ አብረው ሲጥሉ፣ አብረው ሲክቡ፣ አብረው ሲያፈርሱ፣ አብረው ሲመክሩ…አልነበረም? (መቼም ትግላቸው ህቡእ አልነበረም!)
 በነገራችን ላይ ይሄ የፓርቲዎች ክፍፍል በአንዳንድ ፓርቲዎቹን ለማዳከም ባለሙ ኃይሎች ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው ቢባልም ለእኔ ግን ተጠያቂዎቹ ባለቤቶቹ ናቸው - ራሳቸው ፓርቲዎቹ!! የውስጥ ችግራቸውን ወይም ክፍተታቸውን ቀድመው ቢፈቱ ወይም ቢደፍኑ ኖሮ ይሄ ሁሉ ምስቅልቅል ባልተፈጠረ ነበር፡፡ (ያውም ለህዝብ በሚያጋልጥ ሰዓት!) እሺ ችግሩስ ይፈጠር…(ፓርቲዎች የመላዕክት ስብስብ አይደሉምና!) ግና በሆነ መንገድ ተማክረው እንዴት መግባባት ላይ መድረስ አቃታቸው? (የዜሮ ፖለቲካል ጌም ጣጣ እኮ  ነው!) ምርጫ ቦርድ እንዳለው፤ ቢያንስ ለሚደግፋቸው ህዝብ ብለው ሊስማሙ ይገባ ነበር፡፡ (መደማመጥ ከየት ይምጣ!)
 ይኸውላችሁ ባለፈው ሳምንት እንዳወጋነው…እርስ በእርስ መጠላለፍ፤ መወነጃጀልና መናቆር የኋላቀር ፖለቲካ ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡ (መደማመጥም እንደ ዲሞክራሲ ሂደት ነው እንዳትሉኝና እንዳልስቅ!) እንግዲህ የኋላቀር ፖለቲካችን ማሳያዎች የትየለሌ---አይደሉ?! የሰሞኑን የሰላማዊ ሰልፍ ጉዳይና ያስከተለውን ቀውስ እንመልከት፡፡ በነገራችን ላይ በጦቢያችን ብዙ አገራዊ መግባባት (Consensus) ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ቆይ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃድ ነው ዕውቅና የሚያስፈልገው? ይሄን ጉዳይ የሚመለከተው መንግስታዊ አካል ሥልጣኑ እምን ድረስ ነው? ሰላማዊ ሰልፍ ወንጀል የሚሆነው መቼ ነው? ወንጀል ሲሆንስ…ቅጣቱ ምንድነው? እዚህ ጋ ህግና ህገመንግስቱን አልጠቅስም፡፡ (ሁለቱም ወገኖች ህገመንግስቱ መጣሱን እየተናገሩ ነዋ!) በሱ ብንመራማ (ብንደማመጥ እንደማለት ነው!) የእሁዱ ቀውስና በየጊዜው የሚነሳው ውዝግብ ባልተከሰተ ነበር፡፡ በማንም ላይ እየፈረድኩ እንዳልሆነ ዕወቁልኝ! (መፍረዴማ አይቀርም!)
አያችሁ … ለመፍረድ እየቸኮልን እኮ ነው መደማመጥ ያቃተን፡፡ ባለፈው እሁድ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዕውቅና ሳያገኙ ሰልፍ ወጡ የተባሉ የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት በጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው የቆሰለ ገላቸውን እያሳዩ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡ እኔ የምለው--- በ21ኛው ክ/ዘመን የምን ዱላ ነው? የምንስ ድብደባ? በሰለጠነ መንገድ ቁጭ ብሎ መወያየቱ ባይሆንልን እንኳን… እንዴት ራሳችንን ከዱላ ማቀብ ያቅተናል? ህግ የጣሱትን በህጋዊ አሰራር ለፍርድ ማቅረብ አይቻልም ነበር? (ኧረ እንደማመጥ!)
እኔ የምለው ግን … ፖሊስ የመደብደብ ፈቃዱ እምን ድረስ ነው? (ለመረጃና ለጠቅላላ ዕውቀት ብዬ ነው!) በነገራችን ላይ ፈቃድ አለው ከተባለም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዎርክሾፕ ቢጤ መካሄድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ (ለፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ለዜጐችም ጭምር!) መብትና ግዴታችንን እንድናውቅ እኮ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በዕለቱ የአንድነት ሰልፈኞች በፀጥታ ሃይሎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸውን ጠቁሞ፤ “የወሰድኩት ራስን የመከላከል ተመጣጣኝ እርምጃ ነው” ብሏል፡፡ አሁንም ለመፍረድ አትቸኩሉ፡፡ ግራ ቀኙን ሳይመዝኑ መፍረድ ነው እቺን ምስኪን አገራችንን ለጥላቻና ለፅንፈኛ ፖለቲካ የዳረጋት። (“ተመጣጣኝ እርምጃ” ሌላ አገራዊ መግባባት ያልተደረሰበት ጉዳይ ይመስለኛል!)
አንድ ሁነኛ ጥያቄ አለን - ለልማታዊ መንግስታችን፡፡ በ97 የነበረው የአስለቃሽ ጭስ ችግር አሁንም አልተፈታም እንዴ? ቀላል እኮ ነው… እነ እንግሊዝን እንዲታደጉን መጠየቅ ነው (ኒዮሊበራል ቢሆኑም የአስለቃሽ ጭስ ድጋፍ ቢያደርጉልን ችግር የለውም!) ከምሬ እኮ ነው… በምዕራብ አገራት የሚገኙ ቀንደኛ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ እያሉ በየዓመቱ ሪፖርት ለማውጣት ከሚጣደፉ ቢያንስ በቂ የአስለቃሽ ጭስ ድጋፍ ሊያደርጉልን ይገባል፡፡ አስለቃስ ጭሽ እኮ የ21ኛው ክ/ዘመን የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አክሰሰሪ ነው፡፡ (“Prevention is better than cure” የጤና ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብትም መርህ ነው!)
ይሄን ሁሉ የተንደረደርነው ወደ አንድ መቋጫ ለማምራት ነው፡፡ አዎ---ህግ መጣስም ሆነ የ“ድብደባ” እርምጃ የሥልጣኔ ምልክት አይደለም፡፡ (ዓላማችን ዲሞክራሲን ማጐልበትና የሰለጠነ ህዝብ መፍጠር ከሆነ ማለቴ ነው!) መቼም ኢህአዴግም ቢሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ “ተቃዋሚዎችን የሚደበድብ መንግስት” የሚል ስም እንዲወጣለት የሚፈልግ አይመስለኝም (አስለቃሽ ጭስ አልቆበት እንጂ!) ይሄ ነገር እኮ የአገርንም መልካም ገጽታ ክፉኛ ይጎዳል (ቶሎ የማይለቅ ጥላሸት ነው የሚቀባው!) እናላችሁ…በ21ኛው ክ/ዘመን ተቃዋሚን መደብደብ አይመከርም። (ከእነ አምነስቲ ግን ይሄን ትሁትነት እንዳትጠብቁ!)
እግረ መንገዴን (ከዋናው ጉዳይ የወጣ ቢሆንም!) ለኢህአዴግ አንድ ምክር ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡  (ቢያዳምጠኝም ባያዳምጠኝም!) እርግጠኛ ነኝ ዛሬም ባይሆን ሌላ ጊዜ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ (ቆይቶ ነው የሚባንነው ሲባል ሰምቻለሁ!) ምክሩ ምን መሰላችሁ? የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ የሆኑትን እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ)፣ ፍሪደም ሃውስ ወዘተ… የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን የሚመለከት ነው። ኢህአዴግ እነዚህንና አጋሮቻቸውን የቱን ያህል እንደሚጠላቸው በየጊዜው ከሚያወጣቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ (ስሙን “ጥላሸት እየቀቡበት”  እንዴት አይጠላቸው?!) ነገር ግን ተቋማቱን መጥላትና ማጥላላት ብቻውን ያመጣው ለውጥ እንደሌለ ለዓመታት አይተነዋል። (በየዓመቱ አሉታዊ ሪፖርት ከማውጣት አልተገቱማ!) እናም… መፍትሄው ማጥላላትና መጥላት ሳይሆን ተመሳሳይ አገር በቀል ተቋማትን ማብዛትና ማጠናከር ብቻ ነው፡፡ (“የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” እንዲሉ!) አንዳንዶች እንደሚሉት ወይም እንደሚሰጉት፣ የይምሰልና ተለጣፊ ከሆኑ ግን  ምንም ፋይዳ የለውም። አገር በቀል ተቋማቱ ሙሉ በሙሉ ነፃና ገለልተኛ ሆነው በአገሪቱ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሃቅና በድፍረት የሚያጋልጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ኢህአዴግ ጥርሱን ነክሶ መጨከን ያለበት፡፡ (ፈታኝ ቢሆንም የማይቻል ግን አይደለም!) በዚያ ላይ እነ አምነስቲ .. ስሙን ከሚያጠፉት ገለልተኛ አገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲፈጠሩ ዕድል መስጠት የተሻለ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ለፕሬስና ለጋዜጠኛ መብትና ነፃነት የሚቆሙ ገለልተኛ ማህበራትና ተቋማትም እንዲሁ እንዲመሰረቱና እንዲጎለብቱ እድል መስጠት ከኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ተፅዕኖ ነፃ መውጫ ብቸኛ መንገድ ይመስለኛል፡፡ (አሁን “ያሉትስ?” እንዳትሉኝና እንዳልስቅ!)
ከምሬ ነው የምላችሁ … ይሄን ምክሬን ኢህአዴግ ዘግይቶም ቢሆን ከተገበረው ከማንም በላይ የሚጠቀመው ራሱ ነው! “ዲሞክራሲ ለእኛ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” ለሚል ፓርቲም ሆነ መንግስት ይሄን እውን ማድረግ ሊያስቸግረው አይገባም፡፡ እርግጥ ነው በአንድ ቀን ጀንበር የሚሆን አይደለም - ሂደት ነው፡፡ ግን ደግሞ ሂደቱ ዛሬ መጀመር አለበት፡፡ ከሁሉም የሚቀድመው ታዲያ መደማመጥ መሆኑን ሳንረሳ ነው! በተረፈ ምርጫውን ከልባችን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እናድርገው፡፡ (በነቢብም ሆነ በገቢር!)
የፖለቲካ ወጌን የምቋጨው ከሰሞኑ የኢቢሲ “አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች” መካከል ቆፍጠን ያሉ ባልቴት ሴትዮ የሰጡትን አስተያየት በመጥቀስ ነው። “ሰማያዊ ምናምን ትላላችሁ--- እኔ ግን በደንብ አውቃቸዋለሁ---ሁሉንም ፓርቲዎች እወዳቸዋለሁ---ካርዴን ወስጃለሁ---ጊዜው ሲደርስ የምፈልገውን ፓርቲ እመርጣለሁ” ነው ያሉት ባልቴቷ፡፡ (የ2007 ምርጫ ምርጥ አባባል!!)       


Read 3988 times