Saturday, 31 January 2015 12:47

የግዕዝ ፊደልና ቋንቋችን የማንነት ታሪካዊ ቅርሳችን

Written by  ግፍታሔ ገኃተ.
Rate this item
(12 votes)

   ሰሞኑን ጌታቸው አበበ የሚባሉ ጸሐፊ የአማርኛ ቋንቋን አስመልክቶ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በአራት ተከታታይ ክፍሎች ውይይት ሊከፍቱ የሚችሉና ቀላል የማይባሉ ጭብጦችን ለመፈንጠቅ ጥረዋል፡፡ በፊደል ላይ ዘመቻ ይቁም፣ አማርኛ የራሱ ፊደል አለውን?፣ የአማርኛ ፊደል ይሻሻል ማለት ተገቢ ነውን? እና ሌሎችንም ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት በራሳቸው መንገድ የሚሰማቸውን ሀሳብ አጋርተውናል። ምንም እንኳን በአማርኛ ቋንቋና ፊደል ዙሪያ ያሉት አጠቃላይ አመለካከቶች በጋዜጣ፣ በመጽሔቶችና በመጻሕፍት በተለያዩ ሰዎች እየቀረቡ እንደነበር ቢታወቅም፣ እልባት ያላገኙ ጉዳዮች በመኖራቸው አሁንም ሆነ ወደፊት ልዩ ልዩ ሀሳቦች መቅረባቸው ተገቢ ይሆናል። በመሆኑም የጌታቸው አበበን ትጋትና ተቆርቋሪነት በማድነቅ ለጥረታቸው የምሥጋና ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው፡፡
በዚህ ዐቢይ በሚባል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ እኔም የበኩሌን እንደሚከተለው ሰንዝሬአለሁ፡፡ ለማንም አንባቢ ግልጽ የሆነው ጉዳይ “ቋንቋ” እጅግ የተወሳሰበ ትርጉም የሚሰጠው ሳይሆን በሁሉም ዘንድ ግልጽና ቀላል ግንዛቤ እንደሆነ ማስረገጥ ተገቢ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም “ሰዎች እርስ በርሳቸው ለመግባቢያነት የሚገለገሉበት፤ ሃሳባቸውን፣ ስሜታቸውን የሚገልፁበት፤ ሥርዓት ያለው የድምፆች፣ የቃላት…ጥንቅር፤” የሚለው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ ሁሉንም ያስማማል። የቋንቋ ትርጉም ይህን ያህል ቀላልና በዓለም ሕዝብ በሙሉ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑ ከታወቀ በእኔ ሀገር ጓዳና ጐድጓዳ “የችግር መንስዔ” ሆኖ ለምን ይታያል? የሚለው ጥያቄ አስደማሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንኑ ዓለም አቀፍ የትርጉም ተቀባይነት አለማመንም አዋቂነትን የሚያላብስ አይመስለኝም። ለማንኛውም የቋንቋ ትርጉም የአገልግሎቱንም መሠረታዊ ድርሻ ከመመልከቱም በላይ ቋንቋ የፍልስፍና አንድ ይዘርፍ አለመሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ይልቁን የሕብረተሰብ የተለያዩ ፍልስፍናዎች በቋንቋ መሣሪያነት ይቀመራሉ፡፡ ስለ ቋንቋ በአጭሩ ይህችን ካሰፈርኩ ወደ ዋናው የጽሑፌ ሀሳብ ልሸጋገር፡፡
መቼም ሁላችንም እንደምንገነዘበው አማርኛ ቋንቋችን እንዴት ዘመናትን ተሸጋግሮ ለዚህ ዘመንና አሁን ላለበት ደረጃ እንደበቃ ለማወቅ ካልተፈለገ በስተቀር በድንቁርና አተያይ ጉዳዩ የትናንትና እንደሆነ መቁጠር ቀላል ነው፡፡ ነገሮች ከማንነት ታሪክ ጋር ሲገናዘቡ ደግሞ በዘመናት ሂደት የተጠራቀሙትን ኩነቶች መካድ “እራስን ከመካድና ከማዝቀጥ” ሌላ ምንም ትርፍ የለውም፡፡ በዚህ ረገድ ማንም ሰው መረዳት ያለበት መሠረታዊና ቁልፍ ጉዳይ የአንድ ሀገር ታሪክ፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ትውፊቶች፤ የአንድን ሰው ወይም ሕዝብ ማንነት የሚያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ የክብርና የልዕልናውንም ደረጃ የሚወስኑ መሆናቸውን ነው፡፡ የአማርኛ ቋንቋን ሥረ - መሠረት በአግባቡ መመርመርና ግልብ ያልሆነ፣ ነገር ግን ዘመንና ትውልድን ተሻጋሪ የሆነ ሀሳብ መሠንዘር መቻል ከጠቀስኩት ሃሳብ ጋር የሚያቆራኝ ይሆናል፡፡
በ1951 ዓ.ም አሥመራ ኮከበ ጽባሕ ማተሚያ ቤት የታተመ፣ የአስረስ የኔሰው መጽሐፍ “የካም መታሰቢያ” ቋንቋና ፊደልን ከታሪክና ከቅርስ በላይም ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ “ፊደል መልክ ነው። መልክም ፊደል ነው፡፡ ፊደል ልጅ ነው። ልጅም ፊደል ነው ወዘተ” በዚህ ትርጓሜና አስተሳሰብ ፊደል እራስን መሆኑን ያመለክታል። በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የፊደልን ሃብትነትና ቅርስነት ከታደሉ ጥቂት (ከአሥር እስከ 12 የሚደርሱ) ሀገራት አንዷ መሆኗን የዚህ ታሪክ ተጋሪ የሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኩራትና በክብር ምልአት እራሱን መግለጽና ማላቅ ሲገባው ለውርደት ዝቅታን ይመርጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ፊደሉንና ቋንቋውንም እንደ ራሱ ማየት ያለበት ከዚሁ ዐቢይ ቁምነገር በሚመነጭ ምክንያት ነው፡፡
በዓለማችን ላይ ታሪክ በቋንቋ መገለጽ ወይም መዘከር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በእያንዳንዱ አህጉርና አገር ቀጥ ያለና ያለውጣ ውረድ የተቀረፀ ታሪክ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ በየአህጉራቱና በየሀገራቱ የሚኖረው ሕዝብ በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ ችግሮች ሲመሰቃቀልና ከወዲያ ወዲህ ሲዛክር የኖረ መሆኑ በበርካታ የታሪክ ድርሳናት ተዘግቧል፡፡ በዚህም መሀል የሕዝብ ሀብት፣ ቅርስና ታሪኮቹ ጠፍተዋል፣ ተቀብረዋል ወይም ተዳቅለዋል። የአንዱ ሀገርና ሕዝብ ቅርስና ታሪክ ሲጠፋ የሌላው ወገን እየገነነ፣ እንደገናም ገናናው በተራው እየጠፋ ሂደቱ በቀጠለበት ዓለም በማንኛውም ዘርፍ ታሪክ አይዛባም ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ ጉዳዩ ከግዕዝ ፊደልና ከአማርኛ ቋንቋ አኳያም ሲታይ ሀቁ ከዚህ የሚርቅ አይመስለኝም፡፡ ይህንኑ ለማስረገጥ ይመስለኛል አስረስ የኔሰው ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው ላይ “እስከዛሬ በካም ቤት ከወረደው መንግሥትና ፊደል የንጉሠ ነገሥቱ ስምና ግዕዝ ሳይደመሰሱ በመቆየታቸው የማይቀና የለም፡፡ ከካም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ዛሬ 4600 ዘመን የቆየውን ታሪክ ሁሉ ለመደምሰስ ታስቦ “በኢትዮጵያ ፊደልን ያመጡ የደቡብ ዓረቦች ግዕዝን አመጡ ያንንም አባ ሰላማ ከካዕብ እስከ ሳብዕ ያሉትን የፊደል ደረጃዎች አሰናዳ፡፡ መጽሐፍተ ብሉያትም በአባ ሰላማ ከጽርዕ ወደ ግዕዝ ተገላበጡ” ይላሉ። መጽሐፍተ ብሉያት ከልደተ ክርስቶስ በፊት በኢትዮጵያ መኖራቸውን ይክዳሉ፡፡” በማለት አብራርተውታል፡፡
በዚህ የታሪክ ግንዛቤ መሠረት በዓለማችን ላይ የካምና የኩሽ ዘመናት በአፍሪካ ልዕለ ኃይል እንደነበሩና በኢኮኖሚና በባሕል እድገትም ቀደምት እንደነበሩ ሲታወስ፣ በዚህም ውስጥ የኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበር ሲታወቅ፣ የኋላ ኋላ በእምነት ጥግ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን አባዎች በዚህ የቋንቋና የፊደል ዘርፍ ባለቤት አድርጐ ማሰብ እንዴት ተቀባይነት እንዳገኘ በእጅጉ መመራመርን ይሻል። “የኢትዮጵያን ታላቅነትና ገናናነት” የማይሹት እነማን ነበሩ? ለምን? በመሪጌታ ፈቃዱ መንገሻ የተዘጋጀው “መዝገበ አኃዝ ዘ ኢትዮጵያ” የተሰኘ መጽሐፍ ስለዚሁ ዐቢይ ጉዳይ ፈንጥቋል። “የአንድ አገር ሕዝብ ታላቅነቱና ቀደምትነቱ የሚለካው፤ የሚመዘነው በራሱ ፊደል፣ ቋንቋና በራሱ አኃዝ የተመዘገቡ በዓለም የታወቁ አስደናቂ ቅርሶች ሲኖሩት ብቻ ነው፡፡” በእርግጥ እንዲያ መሆኑ አይጠረጠርም። ይሁንና በሌላ በኩል ደግሞ ለአንድ አገርና ሕዝብ ታላቅነት ወይም ጥንታዊነት የተፃፈ ብቻ ምንጭ ይሆናል ሊባል አይችልም፡፡ የታሪክ ምንጮች በሌላም ማዕዘን ሊገኙ ይችላሉና፡፡
ዶ/ር ዲበኩሉ ዘውዴ የተባሉ ተመራማሪ፤ “ፍትሐ ነገሥት፣ ብሔረ ሕግ ወቀኖና” የተሰኘ የምርምር መጽሐፍ በሚያዘጋጁበት ጊዜ ለሥራቸው በምንጭነት የተጠቀሙባቸው ዘርፎች መልካም ስለመሰሉኝ እኔም አልፎ አልፎ ልፈነጥቃቸው ስላሰብኳቸው መነሻ ሀሳቦቼ በምንጭነት ዋቢ ባደርጋቸው ብዬ አሰብኩ፡፡ የምንጮቹ ዓይነቶች:-
ሰነዳውያን (በሠነድ ወይም በጽሑፍ)
ትውፊታውያን (ከልማድና ከልብ የመነጩ)
አምሳላውያን (በተመሳሳይነት የሚታዩ)
ሥነ - አእምሮአውያን (ልቦና ያስገኛቸው) ናቸው፡፡
እነዚህ ምንጮች ከሞላ ጐደል ለፊደልና ቋንቋችን ጥንታዊነትና የአፍሪካ በተለይም የኢትዮጵያ ስለመሆኑ ለማጣቀስ ይጠቀሙ ይመስለኛል፡፡ በዚህም መሸጋገሪያ ለጽሑፌ ዋነኛ ጉዳይ ወደሆነው ወደፊደላችን አመራለሁ፡
ስለ ፊደላችን አመጣጥና መሠረት ጠንቅቆ ለማወቅ የሰውን አፈጣጠር፣ ዝግመተ ለውጥና በየጊዜው ወደተሻለ የሥልጣኔ ደረጃ የተሸጋገረባቸውን የታሪክ ሂደት አምዶች ለይቶ ማወቅ ይጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ታሪክ ሠሪው ሕዝብ እንደመሆኑ በየትኛው አሕጉርና ሕዝብ ምን ዓይነት የእድገት ዝግመተ ለውጥ ተካሄደ? ብሎ መጠየቅም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በእኔ ግንዛቤ ፊደልም ሆነ ቋንቋ የመገኛ ምንጩ አፍሪካ ነው፡፡ እስካሁንም ባሉ መረጃዎች መሠረት የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ ስለሆነች የፊደልና ቋንቋም የመጀመሪያ ውልደት እዚሁ ነው፡፡ ከዚያም ከሰው አስተሳሰብ እድገት ጋር በረጅም ዘመናት የዝግመተ ለውጥ ሂደት ለዚህ ደረጃ መድረስ መቻሉን ማመን ይቻላል። ይህን አስተሳሰብ ምናልባትም እንደ እብደት የሚቆጥሩ ወገኖች እንደሚበረክቱ ይገባኛል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ስለ ፊደል አፈጣጠር መጠነኛ ምርምር ያደረጉ ምሑራን የፊደል ፈጣሪነትን ለሴማውያን ሰጥተዋል። የአገራችንም ፊደል የተወረሰው ከነዚሁ ባሕር ተሻግረው በመጡ ስደተኛ ሴማውያን እንደመሆነ ያስረዳሉ፡፡ ማስረጃ ሲያቀርቡ ደግሞ ፈረንጆቹ የጻፏቸውን ሐተታዎች ነው፡፡
ዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ ባዘጋጁት፤ “ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል” በሚል መጽሐፋቸው (ገጽ 15) “ፊደል ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ላይ የፈለሰፉት ሰመራዊያን የሚባሉ፣ ከአምስት እና ስድስት ሺህ ዓመታት በፊት በዛሬዋ ኢራን አገርና አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች መሆናቸው በፈረንሳይኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተብራርቶ ይገኛል፣ ወቅቱም በ4ኛው በርኩሜ (ሚሊኒየም) መጨረሻ አካባቢ…” በማለት ይገልፃሉ፡፡
እንደተለመደው ፈረንጆች የፃፉት እንደ ትክክለኛ መረጃ መወሰዱ ላይደንቅ ይችላል። በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 16 ደግሞ “ፊደል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈለሰፈው የግብፅን ሒሮግሊፍ (ሥዕላዊ ጽሑፍ) መሠረት በማድረግ ከ1800-1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሴማውያን እንደሆነ ይነገራል፡፡” በማለት ተጽፏል፡፡
የላቀና የሰከነ ምርምር ቢደረግ ምናልባትም በግብፅ አካባቢ ፊደል ተፈለሰፈ የሚለው ሃሳብ ሚዛን የሚያነሳ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከአባይ ወንዝ መነሻ እስከ መድረሻው ባለው ረጅም ሸለቆ፣ የካምና የኩሽ ሥልጣኔ ከዓለም ማንኛውም ሥልጣኔ በፊት የተንሠራፋና ገናና እንደነበር ስለሚታወቅ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ደግሞ በግብጽ የበላይ ገዥዎች ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡
የሰውን ዝግመተ ዕድገት በመከተልና ዘመናትን ዋቢ በማድረግ የረጅም ሥልጣኔ ባለቤት አፍሪካ እንደሆነች የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ በሰው ዘር መገኛነትም ሆነ በሥነ - ልሳን አጀማመር ወደፊት የሚገኙ ማስረጃዎች የአፍሪካን በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን ክብርና ልዕልና ወደነበረበት ትክክለኛ ቦታው ይመልሱታል፡፡ የአፍሪካም ልሒቃን የፈረንጅን ተረት ተረት እያጣቀሱ ከሚቆዝሙበት ድብርት የሚላቀቁበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል ትፊታዊውንንና ሥነ - አእምሮአውያኑን የማስረጃ ፈለግ መከተል የሚቻል ከሆነም የቋንቋም ሆነ የፊደል የልደት ቦታ አፍሪካ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ የአስረስ የኔሰውን “የካም መታሰቢያ” መጽሐፍ (ገጽ 2) መጥቀስ ይቻላል፡፡
“መልአኩ ለሙሴ እየነገረው እንደጻፈው ሲመረመር፣ አንድ የነበረው ቋንቋ እስከ ባቢሎን ግምብ እስከ 2827 ዓ.ዓ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በ72 አለቆች ልክ 72 ቋንቋ ተለይቷል፡፡ የኢትዮጵያን ፊደል እናስተካክላለን የሚሉ ከ72ቱ ቋንቋዎች ጀምረው እስካሁን ሳይለወጥ የቆየ ቋንቋ አምጡ ተብለው ቢጠየቁ በቂ መልስ የላቸውም፡፡” ይላል፡
እዚህ ላይ ግዕዝ ቋንቋና የእርሱም ፊደል የመጀመሪያና ሳይለወጥ የቆየ መሆኑን እኚሁ ሊቅ አብራርተዋል፡፡ ግዕዝ የተሰጠው አለቃ ደግሞ ካማዊ እንጂ ሴማዊ አልነበረም፡፡ በዚህ እሳቤ መሠረትም በተለይ በኢትዮጵያ ባጠቃላይም በአፍሪካ የካም ሥረ-ቋንቋዎች ተጠናክረው ወደ ሌሎች አገሮች ተዛምተዋል በሚል አመክኖአዊ ሃሳብ መከራከር ይቻላል፡፡  በእርግጥም ካምና ሴም ወንድማማቾች መሆናቸው እየታወቀና ሊገለገሉበትም የሚገባው ቋንቋ ዝምድና ሊያጠራጥር እንደማይችል እንደማብራራት “ግዕዝ ከሴም ቋንቋዎች አንዱ እንደሆነ” ቀንጭቦ ታሪክን ማዛባት ጠቃሚ አይሆንም፡፡ ይልቁንስ ሴም ከአፍሪካ ወደ ሌላ አህጉር ሲሰደድ የቤተሰቡን ትውፊቶች ይዞ እንደሄደና በሂደትም ዘሮቹ ታሪክና ትውፊቶቹን እንዳሻሻሏቸው መገመት የሚቀል ይመስለኛል። ስለሆነም አሁን አማርኛ የሚጠቀምበት የግዕዝ ፊደል አፈጣጠሩም ሆነ እድገቱ አፍሪካዊ በተለይም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማስረገጥ ይገባል፡፡
በዓለም ላይ በርካታ ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ የራሳቸው ፊደልና ቋንቋ የታደሉት ግን የጥቂቱ አገራት ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ እንዲያውም ለሌሎቹ የፊደል ባለቤት አገሮች ፊደል እንዲቀዱ ምንጭ መሆኗን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
የራስ ፊደልና ቋንቋ ባለቤት መሆን ማለት በአንደኛው የታሪክና የትውፊት ዘርፍ ልዕለ ሃያል መሆን ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ስለ ፊደልም ሆነ ስለ ቋንቋ ሲነሳ “ሀገሬ ኢትዮጵያ በታሪክ የከበረ፣ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤትና የሰው ዘር መገኛ፣ መራቢያና የጥንታዊ ሥልጣኔ ማዕከል ነች፡፡ እኔም የዚህች ሃያልና ታላቅ አገር ዜጋ ወይም ልጅ በመሆኔ በዓለማት ፊት ግዙፍ ስብዕና አለኝ፡፡” ብሎ መነሳት ታላቅነት ነው፡፡ በፊደልና በቋንቋ ሳቢያ እዚህና እዚያ የሚነሱ የጓዳ አሉባልታዎች ላይ ከማተኮር አድማስ ተሻጋሪ አስተሳሰቦች ላይ ተከራክሮ አገርንና ሕዝብን ወደነበሩበት ክብርና ልዕልና መልሶ ማስቀመጥ ራስንም ማግዘፍና ማላቅ የተሻለ ነው፡፡
በዓለማችን ዙሪያ ያሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች፤ በሀብት፣ በመሳሪያ ጥንካሬና ሌሎችን በመዝረፍ የሚታዩ ታላቅነቶችና ክብሮች በሕዝብ ፊት ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ ሕዝብ ራሱ ካልጠፋ የማይጠፋ፣ ዘላቂ የታላቅነትና የማንነት ታሪካዊ ቅርስ ፊደልና ቋንቋ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፣ ራስንም በማወቅ ወደ ላቀ ምርምርና እሳቤ ለመግባት ያስችላል፡፡ በሚቀጥለው ጽሑፌ የግዕዝ ፊደል በአፍሪካ ብቸኛ መሆን አለመሆኑን፣ የፊደል ቅነሳ ወይም እንዳለ መቀጠሉ ስለሚኖረው ፋይዳ፣ ለፊደላችን ስለሚገባው ክብርና ጥበቃ ከአንዳንድ ታሪካዊ ኩነቶች ጋር በመጠኑ በማዛመድ ያለኝን ሃሳብ ለመፈንጠቅ እሞክራለሁ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡  

Read 11005 times