Saturday, 24 January 2015 12:50

አንድነት ጉባኤ ረግጦ በመውጣቱ ይቅርታ ጠይቅ መባሉ አይቀርም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)

*  ፋና “ድምጽ ለተነፈጉ ተቃዋሚዎች ድምጻቸው ነኝ” ብሏል  
*  “ፈንድ” አፈላልጌ  የፓርቲዎች ክርክር ለማዘጋጀት አስቤአለሁ   
*  “ሳይማሩ ያስተማሩኝን መምህሮቼን አመሰግናለሁ” ከማለት ያድነን!  

    በአንድ የአገራችን ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን መፅሄት ላይ አንዱ ተመራቂ ከፎቶው ስር ምን ብሎ እንደጻፈ ታውቃላችሁ? “ሳይማሩ ያስተማሩኝን መምህራኖቼን አመሰግናለሁ” (ምኑን ተማረው ታዲያ!) የሚገርምም፣ የሚያሳዝንም፣ የሚያስቆጭም መልዕክት ነው፡፡ በደጉ ጊዜ “ሳይማር ያስተማረኝን ወገኔን…” ሲባል ነበር የምናውቀው፡፡ (ሳይማሩ የሚያስተምሩ መምህራን ግን ይደንቃሉ?!)
አሁን በቀጥታ ወደ ምርጫ ወጐች እንግባ፡፡  ባይገርማችሁ… ከምርጫ ጋር በርቀትና በቅርበት የተያያዙ ውዝግቦች አሁንም ቀጥለዋል፡፡ (የአውጉቾ ተረፈን “እያስመዘገብኩ ነው” የሚል አጭር ልብወለድ አንብባችኋል?)
እኔ የምላችሁ---ባለፈው ሳምንት ምሽት ሬዲዮ ፋና፤ የአንድነትን ሁለት የተለያዩ አመራሮች ያወያየበትን መንገድ ታዝባችሁልኛል? እኔማ ጋዜጠኛው የቱ ጋ መቆም እንደፈለገ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ (መሃል አልነበረማ!) ባለፈው ሳምንት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በምርጫ ዙሪያው በሸራተን ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ግን አንድ ነገር ፍንትው አለልኝ - በአስማት እንዳይመስላችሁ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ተወካዮች በአንደበታቸው ከተናገሩት ነው፡፡ አዎ --- ድምፅ ላጡ ድምፅ እንሆናለን ነው ያለው፡፡ (በሬዲዮ ክርክሩ ጋዜጠኛው የቱ ጋ እንደቆመ የገባኝ ይሄኔ ነው!)
 ትንሽ ግልጽ ያልሆነልኝ ምን መሰላችሁ? ፋና፤ ድምፅ ላጡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ድምፅ መሆን የጀመረው በዘንድሮ ምርጫ ነው ወይስ ጥንትም ባህሉ ነበር? (እንዴት ሳንሰማ ቀረን ብዬ እኮ ነው!)  ለነገሩ ጥንት ባህሉ ሆነም አልሆነም ለውጥ የለውም፡፡ የሚመዘነው በዛሬ ሥራው ነው፡፡ እናም  ድምጽ አጥቷል (መድረክ ልትሉትም ትችላላችሁ!) ላለው የአንድነት ክፋይ ፓርቲ አመራር፣ ከመቅጽበት ደርሶላቸዋል፤ በብርሃን ፍጥነት እኮ ነው!  ቡድኑ በጥር 3 ላይ በዲአፍሪክ ሆቴል ጉባኤ ጠርቶ፣የፓርቲው ህጋዊ ፕሬዚዳንት መሆኑን አሳወቀ፤ ፋናም ታዲያ በዚሁ ወር ነው ቡድኑ ድምጽ አልባ መሆኑን ተረድቶ “ድምጽ እሆነዋለሁ” ያለው (ተሳሳትኩ እንዴ?) እናንተ ግርም እኮ ነው የሚለው? (ግጥጥሞሹን ማለቴ ነው!) ከመቼው የአመራር ቡድኑ ተፈጥሮ፣ ከዚያ ድምጽ ተነፍጎት፣ ከመቼው ፋና ድምጽ እንደሆነው---ትንግርት ነው!
በነገራችን ላይ የውስጥ ችግራቸውን ለመፍታት ተስኗቸዋል የተባሉት አንጋፋዎቹ አንድነትና መኢአድ (አሁንም በዝና አንጋፋ ናቸው ብዬ እኮ ነው?!) የምርጫውን አጀንዳ ጠለፉት አይደል? አያችሁልኝ--- ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይዞ ቶሎ ቶሎ መራመድ እንደማይቻል? ራሳቸውን ችለው ሳይሆን እኛንም ይዘውን እኮ ነው የተጎተቱት? በእነሱ የውስጥ ችግር የተነሳ፣ ሁላችንም እኮ ስለ ምርጫው ሳይሆን የፓርቲው ህጋዊና ፎርጂድ  አመራር የቱ ይሆን በሚል ምናባዊ ደመና ላይ መንሳፈፍ ይዘናል፡
 በጣሙን የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የስልጣን ጥማት ያለበት ሰው፤ በአንዲት ጀንበር አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መስርቶ ፕሬዚዳንት መሆን እየቻለ፣ (እንደ ግል ኩባንያ መቁጠር ችግር አምጥቷል!) ምንድነው አንድ ፓርቲ ላይ ሙዝዝ ማለት፡፡ የአንድነት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው፤ በ“ዳያስፖራ ጫና” ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የተመረጠው አመራር ህገወጥ ነው በሚል የሚከስሰው ድምፅ አልባ የተባለው የአቶ አወል ቡድን፤ ራሱን የፓርቲው አመራር አድርጐ ለመሰየም እኮ አፍታ አልወሰደበትም፡፡ (አመቺ ጊዜ ሲጠባበቅ የነበረ አይመስልም!)
እኔ የምለው ግን ድምፅ ተነፍጓል የተባለው ይሄ ቡድንስ፣ ህጋዊነቱን የሚያረጋግጥልን ማነው? (ወይ እች አገር አሉ አቦይ!) ለካስ የመንግስት ብቻ ሳይሆን  የፓርቲ ስልጣንም እንዲህ ያናክሳል? (በአንድ ስሙ የመንግስት ስልጣን ቢሆን እኮ ይሻል ነበር?!)
በነገራችን ላይ የአቶ አወል ቡድን፤ ኢንጂነሩ የዳያስፖራ ተፅእኖ አላሰራኝም ብለው በለቀቁበት ሁኔታ ብሄራዊ ም/ቤቱ አዲስ ፕሬዚዳንት መምረጡ ትክክል አይደለም በሚል ሲሟገት በEBC ተመልክተናል፡፡(የኢንጂነሩን ወደ ስልጣን መመለስ የሚፈልግ ይመስላል አይደል?) ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ አሁን በሆነ ተአምር (ለምሳሌ ውዝግቡን ለመፍታት በሚል!) ኢንጂነር ግዛቸው ወደ ቀድሞ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኔ እመለሳለሁ ቢሉ፣ እሺ የሚላቸው አያገኙም፡፡ እንደውም ያን ጊዜ ሁለቱ የፓርቲውን መዘውር የጨበጡ ተፃራሪ ቡድኖች ግንባር ፈጥረው፣ ኢንጂነሩን የሚታገሏቸው ይመስለኛል (የፓርቲ ስልጣን ብርቅ ሆኗል ስላችሁ!)
የዘንድሮ ምርጫን አስመልክቶ ለተቃዋሚዎች የወጣላቸውን አዲስ ስም ሰምታችሁልኛል? - “ጐምዢው” ፓርቲዎች ተብለዋል፡፡ (ኮፒራይቱ የማን እንደሆነ አልተረጋገጠም!) አዎ ገዢው ፓርቲና “ጐምዢው ፓርቲ” ናቸው እንግዲህ በ2007 አገራዊ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩት፡፡ በእስካሁኑ አካሄድ ግን መኢአድና አንድነት ጐምዢው ፓርቲዎች ለመባል እንኳን የሚበቁ አይመስሉም፡፡ በምርጫው መሳተፍ ካልቻሉ እንዴት ሊጐመዡ ይችላሉ? ጐምዢ እኮ የተባሉት የመንግስት ስልጣን ፍለጋ ለምርጫ ተወዳድረው፣ ድሉን ገዢው ፓርቲ ስለሚጠቀልለው ነው (የማሸነፍ ምስጢሩ ገና አልገባቸውም!)
ሰሞኑን አንዳንድ የEBC “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች”፤ እነመኢአድን በተመለከተ የሚሰጡትን አስተያየት እየሰማችሁ ነው፡፡ “ቤታቸውን ሳያፀዱ…” እያሉ ቆዩና አንድ ቀን ድንገት “በእነሱ የተነሳ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት…” ምናምን የሚል “አሸባሪ አስተያየት” መሰንዘር ጀመሩ፡፡ የኢቢሲ ኤዲተር ዘገነነው መሰለኝ  አልተደገመም፡፡ እንዴ --- የኢቢሲ “አንዳንድ ነዋሪዎች” አበዱ እንዴ?  በሰላም አገር--- የምን ደም መፋሰስ ነው የሚያወሩት?
ከምሬ ነው የምላችሁ --- አንዳንድ “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ባይሆኑ ኖሮ፣ “የሌለ ሽብር በመፍጠር የህዝብን ሰላም ለማወክ ተንቀሳቅሰዋል” ተብለው ፍርድ ቤት ይገተሩ ነበር፡፡ በደህና ጊዜ ወደ “አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች” ጎራ መግባታቸው ጠቀማቸው፡፡ የእነሱን “አሸባሪ አስተያየት” ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ለ90ሚ. ህዝብ ያሰራጨውም EBC ሆነ እንጂ ጣቢያው ተዘግቶ ክስ ይመሰረትበት ነበር፡፡ እሱ እንኳን ቢቀር ጉደኛ ዶክመንተሪ ይጠናቀርበት ነበር - “ጨለምተኛና ብጥብጥ ናፋቂ” በሚል፡፡ (EBC የቤት ልጅ መሆኑ አተረፈው!) በነገራችን ላይ ይሄ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲቀጥል----እኔም የዜግነቴን ለማበርከት ስለምፈልግ፣ ፈንድ ወይም ስፖንሰር በማፈላለግ ላይ እገኛለሁ፡፡ ሃሳቤ ምን መሰላችሁ? (አይዲያዋን ለመመንተፍ እንዳትሞክሩ!)  ወዳጆቼ፤ሪስኪ ፕሮጀክት እኮ ነው፡፡ ይሄውላችሁ ---- ደህና ፈንድ ሰብሰብ አደርግና፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ጉደኛ ዲቤት አዘጋጃለሁ፡፡ (እስክጨርስ ካልተከፋፈሉ ነው እንግዲህ!) በዚህ ዘርፍ በቂ ልምድ ስለሌለኝ፣ በቀደም በሸራተን ተመሳሳይ ጉባኤ ያዘጋጀው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከልምዱ እንዲያካፍለኝ ደጅ እጠናና ወደ ሥራው መግባት ነው፡፡ እኔ ግን እንደምታውቁት መስዋዕትነት---በጎ ፈቃደኝነት ወዘተ-- ምናምን አላውቅም፡፡ ትርፍና ኪሳራውን አስልቼ ነው የምገባበት፡፡ አገር የተጎዳችው፣ ፓርቲዎች ስልጡን የፖለቲካ ባህል ያልፈጠሩት -- ትርፍና ኪሳራውን ሳያሰሉ በጭፍን እየገቡበት እኮ ነው፡፡ እናላችሁ---የምርጫ ክርክር ማዘጋጀትም ቢሆን ለእኔ ቢዝነስ ነው፡፡ ዋናው ነገር ፓርቲዎቹ እኔ ከማሰናደው ነገር መጠቀማቸው ነው፡፡ እነሱ ከተጠቀሙ ደግሞ እኔም መጠቀም አለብኝ፡፡ ይሄን ሁሉ የምዘባርቀው እኮ ወደጄ አይደለም፡፡ ፋና የሸራተኑን ጉባኤ ቤሳ ቤስቲን ሳያገኝ፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት በሚል በነጻ አዘጋጅቶት ይሆናል በሚል ሰግቼ ነው፡፡ (እሱ ኮርፖሬሽን፤ እኔ ግለሰብ!)   በነገራችን ላይ ፕሮጀክቱ ከተሳካልኝ፣ የክርክሩ ጊዜያዊ ርዕስ “ምርጫ 2007ና ስልጡን ፖለቲካ--” የሚል ነው፡፡ መቼም ለፋና ተፈቅዶ ለእኛ ሲሆን አይቻልም ቢባል “ፌር” አይሆንም፡፡
 ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ… የበቀደሙን የፋና ጉባኤ ረግጠው የወጡት የአንድነቱ አቶ አስራት ጣሴ ኮርፖሬሽኑን ይቅርታ ጠይቁ ሊባሉ እንደሚችሉ ጠርጥሬአለሁ፡፡ “ዎክ አውት አድርገዋላ!” ቆይ ግን ባላመንኩበት ጉባኤ የመሰብሰብ ግዴታ አለብኝ እንዴ? አንቀጽ 39 በጸደቀበት አገር ባትፈልግም መቀመጥ አለብህ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን አምባገነንነትም ጭምር ነው፡፡ ይልቅስ አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ የፓርቲ አመራር ውይይት ረግጦ በወጣ ቁጥርና ጥፋት በፈጸመ ጊዜ ሁሉ ይቅርታ ጠይቅ፣ አልጠይቅም የሚል ውዝግብ ውስጥ ከመግባት፣ ለምን የይቅርታ ሥነምግባር ደንብ ተረቅቆ ፓርቲዎች አይፈራሩም? (አደራ! ዋናውንም ያልፈረሙ አሉ ብላችሁ ሃሳቤን ውድቅ እንዳታደርጉብኝ!) ከተሳካ እኮ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለምም ጥሩ ተመክሮ ይሆናል፡፡
ይሄ እንዳለ ሆኖም  ከየአቅጣጫው የ2007 ምርጫን  ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ--ለማድረግ --- ሁሉም ሲረባረብ ማየት በጣም ያስደስታል፡፡ (“የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ” እንዳይሆን ግን ጠንቀቅ ነው!) ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ?  እንደ 97 ምርጫ “እንከን የለሽ” ምናምን አለማለት ነው፡፡ እሱ እኮ ነው ጉድ የሰራን፡፡ እንከን የለሽ ምርጫ እንኳንስ በዲሞክራሲ ዳዴ ላይ ላለነው ለእኛ ቀርቶ ዲሞክራሲን ከእናት ጡት ጋር ለሚጋቱትም አልተሳካም፡፡ እንከን የለሽ ምርጫ በዓለም ላይ እውን የሚሆነው መቼ መሰላችሁ? የሮቦት ዘመን ሲመጣ ነው፡፡ (የሰው ልጅማ ፍጹም አይደለም!)  
እናላችሁ-- መራጩ - ሮቦት፣ ምርጫ ቦርዱ - ሮቦት፣ የድምጽ ታዛቢው- ሮቦት፣ ድምጽ ቆጣሪው- ሮቦት፣ አሸናፊው- ሮቦት፣ ተሸናፊውም- ሮቦት ሲሆኑ ብቻ ነው እንከን የለሽ ምርጫ የሚሳካው፡፡ እኛ ደግሞ  የሮቦት ዘመንን አንሻም፡፡ (እንከን የለሽ ምርጫ ይቅርብን እንጂ!)
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ --- የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!) መንግስት የመላዕክት ስብስብ አይደለም ብለው ነበር፡፡ ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለህዝብም፣ ለፓርቲዎችም---የሚሰራ አባባል ነው፡፡ እንከን የለሽነት ወይም ፍጹምነት ከመላዕክት ወገን እንጂ ከሰው ልጅ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ግን እንችላለን - ከፈለግንና ከጣርን፡፡ ሌላ እኮ አይደለም የሚያስፈልገን - ትንሽ ሰልጠን ማለት ብቻ ነው፡፡ ሥልጣኔም እንደ ዲሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚመጣ ግን አይደለም፤ ሂደት ነው፡፡ የሚያስፈልገንም በየ5 ዓመቱ  ምርጫ ሲመጣ ብቻ አይደለም፡፡ በአዘቦት ቀን ህይወታችንም ከስልጣኔ ጋር መተዋወቅ ይኖርብናል፡፡ በ11ኛው ሰዓት የተከሰተው የመኢአድና የአንድነት ፓርቲዎች ክፍፍል እኮ ሌላ ሳይሆን የዚህ ስልጣኔ አለመዳበር ነው፡፡ የስልጡን ፖለቲካ ባህል ድህነት! በሰላሙ ጊዜ ልዩነትን በስልጡን መንገድ ተከባብሮ በመወያየት፣ ችግርን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመፍታት እየተለማመዱ ቢቆዩ እኮ ይሄ ሁሉ ግርግር ባልተፈጠረ ነበር፡፡
የጦቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ስልጡንነት ብዙ እንደሚቀራቸው ትንሽ ማሳያ ላቅርብና ልጨርስ፡፡ ገዢውንም “ጎምዢውንም” ፓርቲዎች ይመለከታል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በየአጋጣሚው የሚያወጡትን መግለጫ አይታችሁልኛል? (ውበትም ይዘትም የላቸውም እኮ!) ገዢው ፓርቲ በአብዛኛው የሚያወጣው መግለጫ፣ የሰላም ጊዜ ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው የሚመስለው፡፡ የሌለ ጠላት ፈጥሮ ሲያወግዝ ይገኛል፡፡ የ“ጎምዢዎቹ” ፓርቲዎች ግን ይብሳል፡፡ ሁሌም መግለጫቸው በስድብና በውግዘት የታጀበ ነው፡፡ ሰነፍ የጻፈው መግለጫ ነው የሚመስለው፡፡ የቋንቋ ውበት ቢኖረው ደግሞ ለሥነጽሁፍ ዋጋው ተብሎ ሊነበብ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳልኳችሁ---  ውበትም ይዘትም የለውም፡፡ ይሄም የኋላቀርነት መገለጫ እንጂ የሥልጣኔ አይደለም፡፡ እናም ሥልጣኔው ይሄን ሁሉ ስለሚጨምር ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ የማይቻል ግን አይደለም፡፡
 በመጨረሻ፤ ምርጫው በልምዳችንም ሆነ ከሌላው ዓለም በቀመርነው ተመክሮ ወይም በጸሎትም ይሁን በአስማት ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዓለም የሚተርፍ ተመክሮ ባይገኝበት እንኳን ለራሳችን የምንማርበት እናድርገው፡፡
“ሳይማሩ ያስተማሩኝን መምህራኖቼን አመሰግናለሁ” ከማለት ይሰውረን!!  


Read 3011 times