Saturday, 14 January 2012 10:52

በኦሎምፒክ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ያነሰ ግምት ተሰጥቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለንደን ከምታስተናግደው 30ኛው ኦሎምፒያድ መጀመር 6 ወራት ቀደም ብሎ ለታላላቆቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ሃይሌ ገብረስላሴ፤ ቀነኒሳ በቀለና እና ጥሩነሽ ዲባባ የዓለም መገናኛ ብዙሃናት ኦሎምፒኩ ከሚናፍቃቸው ኦሎምፒያኖች ተርታ በመጥቀስ እየዘገቡ ቢሆንም ለኢትዮጵያ የሜዳልያ ዕድል የተሰጠው ግምት ማነሱ እንደሆኑ ታወቀ፡፡ ከ2 ወር በፊት የዓለም የማራቶን ክብረወሰንን የተነጠቀው ኃይሌ ገብረስላሴ ለንደን ላይ በማራቶን ለመወዳዳር ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረውም ሚኒማውን ባለማሟላቱ ከሳምንት በኋላ በሚደረገው የዱባይ ማራቶን ውጤታማነት ላይ ማተኮሩ እየተገለፀ ነው፡፡ በውድድር ደረጃ የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎውን ያለረጋገጠው ሃይሌ ከስፖርት መድረኩ ውጪ ባሉ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ግንየኦሎምፒክ ተሳትፎውን አሟሙቆታል፡፡

በሌላ በኩል በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የውጤት ነገስታት የሚባሉት ሁለቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ለረጅም ወራት ከውድድር ካረቃቸው ጉዳታቸው በማገገም ወደውድድር መመለሳቸው ተፎካካሪዎቻቸውን አሸብሯል፡፡ በሌላ በኩል በለንደን ኦሎምፒክ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ለኢትዮጵያውያን ተፎካካሪነት እና የሜዳልያ ዕድል የተሰጠው ግምት ከባለፉት ጊዜያት ያነሰ መሆኑ በተለያዩ ግምታዊ ትንበያዎችና ትንተናዎች ተረጋግጧል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን ኢትዮጵያን በመወከል ለመሮጥ የሚችልበትን  ሚኒማ ያላገኘው ኃይሌ ገ/ስላሴ ኦሎምፒክ ለዓለም ወጣቶች መነቃቃት በሚል መርህ በሚንቀሳቀስ ፕሮግራም እና በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር መካሄጃ ሰዓት ላይ ተፅእኖዎችን እየፈጠረ ነው፡፡  በለንደን ከተማ የሚከናወነወን 30ኛው ኦሎምፒያድ እና የፓራ ኦሎምፒክ ውድድርን በበላይነት የሚያዘጋጀው የለንደን የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ የኦሎምፒኩን መርህ ዓለምአቀፍ መነቃቃት እንዲፈጥር በማድረግ በጀመረው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ 19ኛው አገር ሆና ገብታለች፡፡ ይሄው ፕሮግራም ከሳምንታት በፊት ይፋ ሲሆን በስነስርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ፉአድ ኢብራሂም የሴቶችና የህፃናት ጉዳይ ሚኒስትሩ አልማው መንግስቱ የእንግሊዝ ዲ ፓርድ ኦፊርስ ተወካይ፣ የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በተገኙት የህብረት ስምምነት ተደርጓል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ይህን ስምምነት ለመደገፍ 4ሺ ህፃናት የተሳተፉበትን የሩጫ ውድድር አድርጓል፡፡ በብሪትሽ ካውንስል፤ በዩናይትድ ኪንግደም በሚሰራው ዩኒሴፍና በዩኬ ስፖርት ትብብር የሚከናወነው ፕሮግራሙ ከዓለም ዙርያ ወጣቶችንበማሰባሰብበኦሎምፒክ መነቃቃትን መፍጠርን ያልማል፡፡ሃይሌ በጂ4ኤስ አምባሳደርነቱ በዓለም ዙርያ ከ14 በላይ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞችን ለለንደን ፓራኦሎምፒክ ለማብቃት እየሰራ ነው፡፡ በሌላ በኩል አትሌት ሃይሌ በለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን መካሄጃ ሰዓት ላይ ለዴይሊ ቴሌግራፍ ሲናገር አትሌቶች በማለዳ ተነስተው ልምምድ ይሰራሉ እንጅ ለውድድር አይገቡም ብሎ ሩጫው የሚካሄድበት ጎዳና ሳይሆን የመወዳደርያው ሰዓት ምቹ አይደለም ብሏል፡፡ የኦሎምፒኩ አዘጋጆች የማራቶን ውድድሩን ለማካሄድ የመረጡት ሰዓት ለቴሌቭዥን ስርጭት እንጂ ለአትሌቶች በሚመች ሁኔታ ለማከናወን አላሰቡም በሚል  ተቃውሞው ኃይሌ የማራቶን ውድድር በለንደን አቆጣጠር ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ እንዲደረግ ግፊት እየፈጠረ ነው፡፡  ኃይሌ ገ/ስላሴ በለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን ለመሳተፍ የሚያበቃውን ሚኒማ ለማምጣት ከሳምንት በኋላ በሚደረገው የዱባይ ማራቶን በሚኖረው ተሳትፎ ካልሆነም ከወራት በሃላ  በሚከናወነው የቶኪዮ ማራቶን ላይ ለማሳካት እቅድ እንዳለው እየተነገረ ነው፡፡ አትሌቱ በተሟላ ብቃት ከሁለቱ ውድድሮች  በአንዱ ላይ  ከ2 ሰዓት 04 ደቂቃ በታች በመግባት ሚኒማ ሊያሟላ እንደሚችል ተገምቷል፡፡  በነበረበት ጉዳት ላለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ከሃያልነቱ ርቆ የቆየው በ2012 በሙሉ ጤንነት ወደ ውድድሮች ተመልሶ ለኦሎምፒክ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩ የቅርብ ተፎካካሪዎቹን አሸብሯል፡፡  የረዥም ርቀት ንጉስ ተብሎ በዓለም ሚዲያዎች የሚደነቀው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ6 ወራት በኋላ በለንደን በሚካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር በድርብ ወርቅ ሜዳልያዎች ክብሩን ለማስጠበቅ ትኩረት ማድረጉን ተናግሯል፡፡  ቀነኒሣ በቀለ በለንደን ኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን የማግኘት እድሉን ሊያሳካ እንደሚችል  ያወሱ ዘገባዎች በኦሎምፒክ ውጤታማነቱ ላይ ማተኮሩ ታላላቆቹ የኬንያ አትሌቶች፤ እንግሊዝን በመወከል ውጤታማ እየሆነ የመላው ሶማሊያዊውን ሞ ፋራህና አሜሪካዊው በርናንድ ላጋትን ሽብር ውስጥ የከተተ ርምጃ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዴይሊ ሚሊ ባሰራጨው መረጃ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በ1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ዘመናዊ የትራክ መለማመጃ ማሰራቱን የገለፀ ሲሆን በዚሁ ትራክ ላይ ከ2 ወራት ባነሰ ጊዜ ከጉዳት የነፃ ልምምድ ለመስራት እቅድ መያዙን ጨምሮ አመልክቷል፡፡የ38 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀጣዩ ከለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ ማሸነፍ ከቻለ በሶስት ከታታይ ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት የበቃ ብቸኛው ኦሎምፒያን ይሆናል፡፡ ቀነኒሳ ከሳምንት በፊት ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ የመጀመርያ የአገር አቋራጭ ሩጫ ውድድርን ተሳትፎ አድርጎ ባይሳካለትም ለለንደን ኦሎምፒክ በሙሉ ተስፋና ብቃት ዝግጅቱን እንደጀመረ ይገልፃል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ለመሳተፍ ከወዲሁ ለመወሰን ይቸግረኛል ያለው ቀነኒሳ ሪኮርዶችን በያዘባቸው ሁለቱም ርቀቶች እኩል ፍላጎት እንዳለው ሲገልፅ እስከ ኦሎምፒኩ በሚያደርጋቸው ውድድሮች ያለውን ብቃት በማረጋገጥ ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ማሰቡን ተናግሯል፡፡ ከሳምንት በፊት ለንባብ የበቃው ዴይሊኔሽን ጋዜጣ‹ ኬንያውያን ተጠንቀቁ፡፡ ጥሩ ተመልሳለች› በሚል በሰራው ዘገባ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ታላቅነት አረጋግጧል፡፡ ለረጅም ጊዜ በነበረባት ጉዳት ከውድድር ርቃ የነበረችው ጥሩነሽ በ2012 ወደውድድርመመለሷኬንያዎቹን ምርጥ አትሌቶች ቪቪያን ቼሮይትና ሲልቪያ ኪቤትን ያሸብራል ያለው ዴይሊኔሽን በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትርኬንያ አትሌቶች ያሳዩት የበላይነት በወርቅ ሜዳልያ እንዳይደምቅ ምክንያት ትሆናለች ብሏል ፡፡ ከ4ዓመታት በፊት በቤጂንግ  ኦሎምፒክ በ10ሺ እና በ5ሺ ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ ብቸኛ ታሪክ የሰራችው ጥሩነሽ ወደ ውድድር የተመለሰችው በጉዳት ለ14 ወራት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ተገልላ ከቆየች በሃላ ነው፡፡ ጥሩነሽ በ2012 ዋዜማ የመጀመርያውን ውድድሯን ባደረገችበት ወቅት ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቷ በማገገሟ መደሰቷን ገልፃ ቀጣይ ትኩረቷ ለለንደን ኦሎምፒክ በተሟላ ብቃት በመድረክ ድርብ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ክብሯን ማስጠበቅንደምትፈልግ ተናግራለች፡የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በለንደን ኦሎምፒክ 12 ሜዳልያዎች (4 የወርቅ፣ 4 የብር፣ 4 የነሐስ) ለማግኘት ማነጣጠሩ ሲታወስ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተገኙ ትንበያዎች ይህን እቅድ በግማሽ እንኳን ለማሳካት የሚከብድ መሆኑን እያመለከቱ ናቸው፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በለንደን በሚካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ በተሳትፎ ታሪኩ ትልቁን ቡድን ለመላክ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን ከ4 ዓመታት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ በአጠቃላይ 14 ሜዳልያዎች 6 የወርቅ የተመዘገበበትን ታሪክ ለማሻሻል አትሌቶቹ በከፍተኛ ማባረታቻ ለመደገፍ አቅዷል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡና ሜዳልያዎችን ለሚያመጡ አትሌቶች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንደሚኖር በማሳወቅ እየቀሰቀሰ ያለው የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለባለሜዳልያ አትሌቶች ልዩ ልዩ ስጦታዎች መኪና መሬትና ሌሎችን ለማጎናፀፍ እየሰራን ነው ብሏል፡፡በለንደን ኦሎምፒክ የሜዳልያ ሰንጠረዡን ቻይና በበላይነት እንደምታጠናቅቅ ብዙ ግምታዊ ትንተናዎች እየቀረቡ ሲሆን አሜሪካ በቅርብ ተፎካካሪነት መጠቀሷም አልቀረም፡ ከ4ዓመታት በፊት ቤጂንግ ላይ ቻይና በ110 ሜዳልያዎች 56 የወርቅ ስብሰባ መሪ ሆና ስትጨርስ አሜሪካ በ100 ሜዳልያዎች 36 የወርቅ ሆነው 2ኛ ነበረች፡፡ ተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተገኙ የሜዳልያ አሸናፊነት ትንበያዎችን በማማከል በተሰራ ግምታዊ የደረጃ ሰንጠረዝ በለንደን ኦሎምፒክ ቻይና በአጠቃላይ 90 ሜዳልያዎች 38 የወርቅ በማግኘት አንደኛ ትሆናለች፡፡ አሜሪካ በ89 ሜዳልያዎች 37 የወርቅ፤ ሩስያ በ81 ሜዳልያዎች 20 የወርቅ እንዲሁም ብሪታንያ 59 ሜዳልያዎች 15 የወርቅ በማስመዝገብ እሰከ 4 ያለውን ደረጃ እንደሚያገኙ ተገምቷል፡ስፖርትሚራድ የተባለ ድረገጽ በሰራው ትንበያ በአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ለቀረቡ ሜዳልያዎች እድል ያላቸውን አገራት ዘርዝሯል፡፡ ለግምቶቹ ማስረጃም ዋና መነሻውን በኮርያ ዳጉ ተደርጐ የነበረውን 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤትን አገናዝቧል፡፡ በትንበያው  መሰረት በለንደን ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ በሚኖራት ተሳትፎ 1 የወርቅ 2 የብርና፣ 2 ነሐስ ሜዳልያዎችን ብቻ እንደምታገኝ ተገምቷል፡፡ ለኬንያ ደግሞ 7 የወርቅ፤4 የብርና 8 የነሐስ ሜዳልያዎችን እንደምትሰበስብ ተንብየዋል፡፡

 

 

 

Read 2766 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 10:56