Saturday, 24 January 2015 12:44

የአዘቦት ቀን ጀግኖች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የ14 ዓመቱ ኮሊን ስሚዝ በደረሰበት የመኪና አደጋ መላ ሰውነቱ በድን (ፓላራይዝድ) ከሆነ በኋላ ሃኪሞች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የማጠናቀቅ ዕድሉ 20 በመቶ እንደሆነ አርድተውት ነበር፡፡ ኮሌጅ ገብቶ መማርማ እርሳው ነበር ያሉት፡፡ ሆኖም ከ8 ዓመት በኋላ ቢኤ ድግሪውን በኮሙኒኬሽን ከሃይ ፖይንት ዩኒቨርስቲ ለማግኘት ቻለ፡፡ ኮሊን ፈጽሞ የማይታሰበውን ማሳካት የቻለው በዕድሜ 50 ዓመት በሚበልጡትና ጨርሶ በማያቃቸው ደግ አዛውንት እርዳታ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም እንዳጋጣሚ ሆኖ ጡረተኛው ኧርነስት ግሪኒና ባለቤታቸው ካትሪን፣ ኮሊንስና ወላጆቹ በሚያመልኩበት በኖርዝ ካሮሊና በሚገኘው የአሼቦሮ ባፕቲስት ቤ/ክርስቲያን ያመልኩ ነበር፡፡ በእርግጥ እኒህ ቤተሰቦች ትውውቅ አልነበራቸውም፡፡ ምክንያቱም የግሪን ቤተሰብ ወደ አካባቢው ከመጣ ዘጠኝ ወር ያህል ቢሆነው ነው፡፡ ሆኖም ኧርነስት በወሬ ወሬ ኮሊን ስለደረሰበት አደጋና ወላጆቹ የሙሉ ጊዜ እንክብካቤ ሊያደርጉለት አለመቻላቸውን ሰሙ፡፡ ይሄ ለእሳቸው የተላከ ጥሪ መስሎ ታያቸው፡፡
“ፈጣሪ እንድረዳው መራኝ” ይላሉ - ኧርነስት ግሪኒ፡፡ እናም በነበራቸው ትርፍ ጊዜ ኮሊንስን ሊረዱት ቆርጠው ተነሱ፡፡
መጀመሪያ የኮሊንን ቤተሰብ በመቅረብ፣ እነሱ ወደ ሥራ በሚሄዱ ወቅት ልጃቸውን ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ የኮሊን ወላጆች አላቅማሙም፡፡ እርዳታውን በደስታ ተቀበሉ፡፡ አሁን 23ኛ ዓመት እድሜው ላይ የሚገኘው ኮሊን፤ እንዴት ጨርሶ የማላውቀው ሰው እኔን ለመርዳት መላ ህይወቱን እርግፍ አድርጐ እንደተወ ልረዳ አልቻልኩም ነበር ብሏል፡፡
አዛውንቱ ኧርነስት በቀጥታ ወደ እርዳታ አልገቡም፡፡ መጀመሪያ ለኮሊን እንዴት እርዳታ ማድረግ እንደሚችሉ መጠነኛ ስልጠና ወሰዱ፡፡ ከዚያም ወላጆቹ የሥራ ቀናቸውን በሚጀምሩበት አንድ ሰኞ ማለዳ ላይ እነኮሊን ቤት ከተፍ አሉ፡፡ ኮሊንን ከአልጋ ሲነሳ፣ ሲለባብስና ሲተጣጠብ ያግዙትም ጀመር፡፡ ቁርሱንም ሲመገብ እንዲሁ ይረዱታል፡፡ ከዚህም በላይ በራሳቸው መኪና ት/ቤት ያደርሱታል፡፡ በየቀኑ 9 ሰዓት ላይ ደግሞ ወደ ቤት ይመልሱታል፡፡ ወላጆቹ ከስራ እስኪመለሱም ወይ እሳቸው አሊያም ባለቤታቸው እያጫወቱ ይጠብቁታል፡፡
በዚያ ሰዓት ውስጥ ከኮሊን ጋር ብዙ ያወጉ እንደነበር ኧርነስት ያስታውሳሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ በመሃላቸው የነበረው የዕድሜ ልዩነት ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ በሁለት ትውልዶች መካከል የሚከሰት ልዩነት ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዳቸው ራፕ ሲወዱ ሌላኛቸው ምርጫቸው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ተቻችሎ መኖርን ተማሩ፡፡
“አዛውንቶች ዕድሜያቸው የገፋ እኛ ማለት ናቸው” የሚለው ኮሊን፤ “ድንቅ ታሪክ ያላቸው የእኛው ዓይነት ሰዎች” ሲል ይገልፃቸዋል፡፡
አንዳንድ ቀናት ከሌሎቹ የተሻሉ ነበሩ፡፡ “ምንም ነገር ራሱን ችሎ ማከናወን ስለማይችል ብዙ ሊያደክም ይችላል” ይላሉ ኧርነስት፡፡ ነገር ግን ፈታኝ ጊዜያትን ለማለፍ ያስቻለው የራሱ የኮሊን ጠንካራ ቁርጠኝነት መሆኑን ኧርነስት ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ኮሊን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከቀሩት የክፍል ጓደኞቹ ጋር በአጥጋቢ ውጤት አጠናቆ በአቅራቢያቸው በሚገኘው ሃይ ፓይንት ዩኒቨርስቲ ለመግባት ቻለ፡፡ በእያንዳንዱ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ኧርነስት ከአጠገቡ አይለዩም ነበር፡፡ “የመጀመሪያው ዓመት አስደሳች ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ - ኧርነስት፡፡ “ኮሊን ከሌላው ጐልቶ መታየት አይፈልግም ነበር” ግን ደግሞ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ ይጠቀም ነበር - አስተማሪ ሲያስተምር ማስታወሻ ይይዛል፤ ብዙ ጊዜም ክፍል ውስጥ አስተያየት ይሰጥ ነበር፡፡
በምረቃ ቀን ታዲያ ኮሊን ብቻ አልነበረም ዲግሪውን የተቀበለው፡፡ አዛውንቱ ኧርነስትም ላከናወኑት ሰብዓዊ ተግባር ዩኒቨርሲቲው የክብር ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡ ያልጠበቁት ስለነበር ትንግርት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ኮሊን ግን ጨርሶ አልተገረመም፡፡ “ኧርነስት ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት መለኮታዊ ምሳሌ የሚሆኑ ሰው ናቸው - ዝምተኛና ትሁት” በማለት ይገልፃቸዋል፡፡
ኮሊን ዛሬ በዚያው ሃይ ፖይንት ዩኒቨርሲቲ፣ የቅርጫት ኳስ ረዳት አሰልጣኝ ሲሆን ዕውቅና በተሰጠው ልዩ የእንክብካቤ ባለሙያ በየቀኑ ድጋፍ ያገኛል፡፡ አዛውንቱ ኧርነስትም አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከቤተሰባቸው ጋር ያሳልፋሉ፡፡
አሁን ሁለቱ የተለያየ ትውልድ ጓደኛሞች እምብዛም አይገናኙም፡፡ “ነገር ግን ኮሊንና እኔ ሁልጊዜም ግንኙነታችን ይቀጥላል” ይላሉ - ኧርነስት፡፡ ኮሊንም በዚህ ይስማማል፡፡ “በቀን ከ14-16 ሰዓታት አንድ ላይ ነበር የምናሳልፈው” ሲል ያስታውሳል፡፡ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን አስቸጋሪ ፈተናን በጋራ ተወጥተዋል፡፡ ለዚያም ነው የአዘቦት ቀን ጀግኖች የሚባሉት፡፡
(ሪደር ዳይጀስት - የፌብሯሪ 2015 እትም)

Read 3007 times