Saturday, 24 January 2015 12:43

ባህልና ብዝሃ ህይወት ምንና ምን ናቸው?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

“መልካ ኢትዮጵያ” ሥራ ከጀመረ ወደ 10 ዓመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ በአካባቢ ተቆርቋሪዎች፣ በህግ ባለሙያዎችና ሌሎች  የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በብዝሃ ህይወት ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዝሃ ህይወት የተጋረጠበትን የመመናመን አደጋ ለአዲሱ ትውልድ ለማስገንዘብ በትጋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም የድርጅቱ መስራች፣ አባልና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚሊዮን በላይ ይናገራሉ፡፡ ብዝሃ ህይወትና ባህል ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ለአርሶ አደሮችና ተማሪዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወንን ነው ይላሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በ “መልካ ኢትዮጵያ” አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ዓላማና ስኬቶች ዙሪያ ከዶ/ር ሚሊዮን በላይ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

“መልካ ኢትዮጵያ” ዋና ትኩረቱ አድርጎ የሚሰራው ምንድን ነው?
“መልካ ኢትዮጵያ” በዋናነት በሶስት ጉዳዮች ላይ ይንቀሳቀሳል፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ባህላችን እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ አዲሱ ትውልድ መቶ በመቶ ባህሉን አያውቅም ባይባልም የቀድሞውን ትውልድ ያህል ግንዛቤ አለው ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ ደግሞ ለአገሪቱ አደጋ ነው፡፡
ብዝሃ ህይወትና ባህል ምንድነው የሚያገናኛቸው?
ቀላል ምሳሌ ልስጥሽ፡፡ ወደ ጉራጌ አካባቢዎች ብትሄጂ፣ ከመቶ በላይ የኮባ ዝርያዎች ታገኛለሽ፡፡ ወደ ሰሜን ብታመሪ፣ ወረኢሉ አካባቢ ከመቶ በላይ የስንዴ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ይህ በምርምር የተገኘው ነው፡፡ የአማራው ሰው ከመቶ በላይ የኮባ ዝርያ መኖሩን አያውቅም፤ ምክንያቱም ከዚያ ባህል አልወጣምና፡፡ የጉራጌው ተወላጅም እንዲሁ በአማራ አካባቢ ከመቶ በላይ የስንዴ ዝርያ መኖሩን አይገነዘብም፡፡ ለምን? ከአማራ አካባቢና ባህል ስላልወጣ ነው፡፡ የከተማ ልጅ አማራም ጉራጌም አካባቢ ቢሄድ፣ እነዚህን የኮባና ስንዴ ዝርያዎች አያውቃቸውም፡፡ ለምን ያልሽ እንደሆነ፣ ባህሉን ስለማያውቀው… በቃ!
ወደ ሼካ ሄደሽ ከአንድ የአካባቢው ሽማግሌ ጋር ወደ ጫካ ብትዘልቂ፣ እያንዳንዱ ዛፍና ቅጠል ለምን ለምን እንደሚያገለግል፣ ስሩ ነው ቅጠሉ መድኀኒት የሚሆነው፣ የትኛው ቅጠል የትኛውን ህመም ያድናል…? የሚለውን ተንትነው ያብራሩልሻል፡፡ ከአካባቢው ባህልና አገር በቀል  ዕውቀት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ዘፈኖች፣ ተረቶችና ስነ-ቃሎች ሰብስበሽ ብትመረምሪያቸው፣ በውስጣቸው በርካታ ብዝሃ ህይወት ታገኛለሽ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፣ ስለ ስራስር መድሃኒትነት፣ ስለ አየሩ፣ ስለ ጋራ ሸንተረሩ፣ ስለ እርሻ፣ ስለ ግብርና፣ ስለ እንስሳት፣ በአጠቃላይ ስለ ብዝሃ ህይወት ብዙ ነገር ይዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሸረሸረና እየጠፋ ያለው ደግሞ ይህ ባህልና እውቀት ነው፡፡ እኛም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች የምንሰራው ይህን እየተሸረሸረ የመጣ የብዝሃ ህይወትና የባህል ጉዳይ ለመታደግ ነው፡፡
ለብዝሃ ህይወትና ለባህሉ መሸርሸር ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?
አንደኛ የከተማ መስፋፋት ነው፡፡ ከተሞች በተስፋፉ ቁጥር ከተማ ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገው እውቀት ብዙ ከባህል ጋር የተቆራኘ ሳይሆን ከመዘመን ጋር የተያያዘና ይበልጥ ከቴክኖሎጂው ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ከተሞች ሲስፋፉ የእርሻና የገጠር መሬቶችን እየወሰዱና እያጣበቡ ነው፡፡ መሬቱ በጠበበ ቁጥር ደግሞ የሚዘራውና የሚተከለው ብዝሃ ህይወት እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ከተሞች በተስፋፉ ቁጥር የገጠር ወጣቶችና ታዳጊዎች ወደ ከተማ ስለሚፈልሱ ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ይቋረጥና የተበረዘና የተከለሰ የከተማ ባህል ውስጥ በማደግ፣ ከወላጆቻቸው የሚያገኙትን ባህልና እውቀት ያጣሉ፡፡ ይህ አንዱ ነው፡፡ ሌላው የእርሻ ስርአታችን ነው፡፡ በፊት ስትዘሪና ስታመርቺ የነበረውን ትተሽ ወደ ሌላ ነገር ስትገቢ የብዝሃ ህይወት ሃብት ይጠፋል፤ ስለ ብዝሃ ህይወት የነበረሽም እውቀት አብሮ ይጠፋል፡፡ ሚዲያውም ለብዝሃ ህይወትና ለባህል መሸርሸር በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ሚዲያው … እንዴት?
በአሁኑ ወቅት በየገጠሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን… ዲሽን ጨምሮ ተስፋፍቷል፡፡ ይሄ ልጆች ከሽማግሌ አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ጋር ያላቸውን የውይይት፣ የምክር፣ የተረት መስሚያና የባህል ጉዳይን መወያያ ጊዜ በእጅጉ ይሻማል፡፡ የወላጅና የልጆች የግንኙነት ጊዜ ይቀራል ወይም ይጣበባል፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው ተረትና ምክር ይልቅ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ላይ ያተኩራሉ፡፡ በዚህም ስለ ብዝሃ ህይወትና ባህል ያላቸው እውቀት ይጠፋል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ አንድ ተማሪ አዲስ አበባ፣ ሆለታ ወይም ሆሳዕና… ብቻ የፈለገበት ቦታ ይማር (ጋናም ይሂድ) ቋንቋው ይገናኛል ወይም ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው፡፡ ስርዓተ ትምህርቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ ልጆች ት/ቤት ውስጥ ፊዚክሱን፣ ሳይንሱን፣ ሂሳቡን እንጂ የራሳቸውን ባህል አይማሩም፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ትምህርት ላይ ነው፡፡ ሲመለሱም በጥናት ላይ ይጠመዳሉ፡፡ ስርዓተ ትምህርቱም ሲቀረፅ አካባቢን ያማከለ አይደለም፡፡ በእንግሊዝኛው “De contextualized” ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት የአካባቢው እውቀት እና ባህል ይሸረሸራል፡፡ ከዚያ በኋላ ልጆች፤ ወላጆቻቸው እውቀት ያላቸው አይመስላቸውም፡፡ የእነሱን ምክር እንደ ኋላቀር መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ለብዝሃ ህይወትና ለባህል መሸርሸር አስተዋፅዋቸው የጐላ ነው፡፡
እነዚህ በችግርነት የተነሱት ጉዳዮች በአኗኗራችን፣ በስነ ምህዳር ስርዓት ወይም በምግብ ዋስትናችን ላይ በተጨባጭ ያመጡት ጉዳት ምንድን ነው?
በአኗኗራችን ላይ ያመጣው አንዱና ተጨባጩ ችግር አዲሱ ትውልድ ነባራዊውን ምግብ መመገብ እየተወ ነው፡፡ ታዲያ ነባራዊ ምግቡን መተው ምን ጉዳት አለው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ መልስ ለማግኘት በየገጠሩ አካባቢ ያሉ ክሊኒኮችን መጐብኘት በቂ ነው፡፡ ነባር የአመጋገብ ስርዓታችን ስለተቀየረ፣ በአገራችን በፊት ላልነበሩ አዳዲስ በሽታዎች እየተጋለጥን እንገኛለን፡፡ ወደፊት ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን እያጣን እንሄዳለን፡፡ ለምሳሌ ጤፍ ከዛሬ 20 እና 30 አመት በፊት ከውጭ የመጡ ተመራማሪዎች፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጤፍ የሚባለው ምግብ ጥሩ ስላልሆነ መቀየር አለበት ብለው ነበር፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ የማያድገው ተጫዎቾቹ ጤፍ ስለሚበሉ ነው እስከመባል ደርሶ ነበር፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ግን ጤፍ “ኪኒዋ” የሚባል ከላቲን አሜሪካ የሚመጣ የእህል ዘር አለ፡፡ እሱ ዘር አንደኛ የጤና ዘር ተብሎ ነበር የሚጠራው፡፡ አሁን ጤፍ ኪኒዋን እየተገዳደረና “The best seed” እየተባለ መጥቷል፤ በምግብ ዘይቱ ማለት ነው፡፡ በመሰረቱ “ግሎቲን” የሚባለው አለርጂ አምጪ ንጥረ ነገር በጤፍ ውስጥ የለም፡፡ ብዙ ልጆች ለግሎቲን አለርጂ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ጤፍ በምግብ ዘይቱ ከስንዴ፣ ከገብስ፣ ከሩዝ እና ከሌሎችም እንደሚበልጥ ተረጋግጧል፡፡ እንደ ጤፍ ጥናት ቢደረግባቸው የምግብ ጥራታቸው የላቀና ለጤና ተስማሚ የሆኑ በእጃችን ላይ ያሉ በርካታ ነባር ዘሮች አሉን፡፡ ወጣቱ ይህን ምግብ ትቶ በኬሚካል የታሸገ፣ አዳዲስ የተዳቀለ ምግብ በሚመገብበት ጊዜ ለጤና ችግር ይጋለጥና አምራች ዜጋ መሆኑ ይቀራል፡፡ ይሄ ሁሉ በአኗኗር፣ በምግብ ዋስትናም ሆነ በስነ ምህዳር ስርዓት ላይ መዛባትን መፍጠሩ ግልፅ ነው፡፡
“መልካ” በአራቱ ክልሎች እየሰራ ያለው የአድቮኬሲ ስራ ነው --- የትኛው ዘርፍ ላይ ነው ትኩረቱ?
“መልካ” --አንደኛ፤ አገሪቱን ሁሉ ማዳረስ ባንችልም በተመረጡ ነገር ግን በርካታ የነባር ዘር ዝርያ ባላቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት እነዚህ ያሉት ዝርያዎች ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ይሰራል፡፡ ሁለተኛ፤ የጠፉና ለመጥፋት የተቃረቡ ነባር ዝርያዎች ካሉ፣ ከአርሶ አደሮች በማፈላለግ እንዲያወጡና እንዲያባዙ ድጋፍና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ያከናውናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ገበሬዎች ዝም ብሎ ጉዳዩ ስለሚገባቸውና ስለሚያሳስባቸው ዘሩን ቋጥረው ያስቀምጡታል፡፡ ሶስተኛ፤ በእነዚህ ነባር ዝርያዎች ዙሪያ አዲሱ ትውልድ እውቀቱ እንዲሰርፅና ስለ ብዝሃ ህይወትና ስለ ባህል አውቆ እንዲያድግ እንዲሁም ለነባር ዝርያዎቹ ጥበቃ እንዲያደርግ የሚያስችላቸውን የእውቀት ስንቅ ማስታጠቅ ነው፡፡ አራተኛው እነዚህ ነባርና ውድ ዝርያዎች የሚቀመጡበት የዘር ባንክ መስራት አንዱ የመልካ ኢትዮጵያ ስራ ነው፡፡
አምስተኛው፤ ገበሬዎችን ያማከለ ምርምር እየተካሄደ ነው፡፡ ገበሬው ዘሩን ከዘራ በኋላ አገር በቀል እውቀቱን እና ሳይንሱን እንዴት አዋህዶ ምርታማ ይሁን በሚለው ላይ ምርምር ያካሂዳል፡፡ ምክንያቱም ሳይንሱንም መተው አይቻልም፡፡ አሁን ችግሩ አገር በቀል እውቀቱን ጥሎ ሳይንሱን ብቻ በተጋነነ ሁኔታ መከተሉ ነው፡፡ አርሶ አደሩ የለመድከውን ትተህ በሳይንስ ተመራ ስትይው፣ ችግር ውስጥ ይገባል፤ አለመደውማ! አሁን የህብረተሰቡ ሳይንቲስቶች ይመጣሉ፣ አርሶ አደሩን ያገኛሉ፤ አብረው ዘር ይዘሩና በዚያው ላይ ስልጠና ይሰጧቸዋል፡፡ ገበሬው በእውቀት እንዲበለጽግ የተለያዩ ስልጠናዎችን እናዘጋጃለን፡፡ ሌላው እርሻ ሲባል ሰው የሚገባው ዘር የሚዘራበት ቦታ ብቻ ነው፤ ነገር ግን በዙሪያው ያለው ሳር፣ ዛፍ እና ሌሎች አይታዩም፡፡ አፈር እንዳይሸረሸር ለመጠበቅ በእርሻው ዙሪያ ያሉ ዛፎች፣ ሳሮች… ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአበባ ዘሮችን የሚያራቡት እነ ቢራቢሮ እንዳይጠፉ ግንዛቤ እንሰጣለን፡፡ ይህን ሁሉ ነው መልካ የሚያከናውነው፡፡
መልካ ባለፉት 10 ዓመታት ምን ውጤት አስመዘገበ?
10 ዓመት የሞላቸውም ያልሞላቸውም ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ 10 ዓመት ከሞላቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ወጣቶች ላይ የምንሰራው ነው፡፡ ወጣቶችን ጫካ እንወስዳለን፤ ጫካ ውስጥ ለአምስት ቀናት ከሽማግሌዎች ጋር እንዲቀመጡ እናደርጋለን፡፡ በነዚህ ቀናት ውስጥ የተለያዩ ዕውቀቶችን ከሽማግሌዎች እንዲቀስሙ ይደረጋሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ ተረት ይነግሯቸዋል፤ ስለ እያንዳንዱ ዛፍና ጠቀሜታው ስለሚያወሯቸው ከባህል ጋር ይገናኛሉ፤ ከደኑ ጋርም እንዲሁ፡፡ ወጣቶቹ “ዛፍ አትቁረጡ፤ በረሃማነት ይመጣል” ከሚለው ባሻገር በአምስቱ ቀናት ጫካ ውስጥ ሲኖሩ ስለ አካባቢ የሚገነዘቡት ነገር አለ፡፡ እነዚህ ልጆች አሁን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡
 በ10 ዓመታት ውስጥ ብዙ መጥፎ ባህሪ የነበራቸው ልጆች ተለውጠው ጥሩ አመለካከት ይዘዋል፡፡ አካባቢያቸውን በራሳቸው ተነሳሽነት የመጠበቅና የመንከባከብ ልምድ አዳብረዋል፤ ይህ ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች የባህል መነቃቃቶች ታይተዋል፡፡ አሁን ባሌ አካባቢ በሰራነው ስራ ከፍተኛ የባህል መነቃቃት አለ፡፡ ስለ ህብረተሰባቸውና ስለ አካባቢያቸው እንዲሁም ስለ ነባር የዘር ዝርያዎቻቸው ያላቸው እውቀት በመጨመሩ፣ ለነዚህ ዝርያዎች ያላቸው ክብርና የሚያደርጉት ጥበቃ የውጤታችን ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) Education for Sustainable Development የሚባል ፕሮግራም አለ፡፡ ይህ ፕሮጀክታችን በዚህ ፕሮግራም እንደ ምርጥ ተምሳሌትነት ተወስዷል፡፡ ይሄም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ “teach a man to fish” በሚል ፕሮግራም ተወዳድረን አሸንፈናል፡፡ (አሳ አትስጠው፤ አሳ እንዴት እንደሚያጠምድ አስተምረው እንደማለት ነው፡፡)
እርስዎ እንዴት በአካባቢና በብዝሃ ህይወት ላይ ሊያተኩሩ ቻሉ? አስተዳደግና የትምህርት ዝግጅትዎ ከዚህ ጉዳይ ጋር ይያያዛል?
ተወልጄ ያደግሁት መርካቶ ነው፡፡ ነገር ግን ት/ቤት ሲዘጋ ክረምቱን አያቶቼን ጥየቃ ወደ ክፍለ ሀገር እወጣ ነበር፡፡ መርካቶ ካሮትና የተለያዩ የአትክልት አይነቶች እንድገዛ እላክ ስለነበር፣ ያም ተፅዕኖ ይኑረው አላውቅም፤ የተማርኩት ግን ባዮሎጂ ነው፤ የባዮሎጂ መምህርም ነበርኩኝ፡፡ አስተማሪ ሆኜ ግንደበረት ስሄድ የሚያምር ገጠር ነበር፡፡ ከዚያ ወሊሶ ስመደብ የአካባቢ ጥበቃ ክበብ አቋቋምኩኝ፡፡ ይህ ክበብ በአገሪቱ ከነበሩ ክበቦች ትልቁና ብዙ ስራ የሰራ ነው፡፡ “ኢንስቲትዩት ኦፍ ሰስቴይኔብል ዴቨሎፕመንት” የሚባል ድርጅት ውስጥ መስራቴም ወደዚህ ጉዳይ እንድገባና እንድቆረቆር ያደረገኝ ይመስለኛል፡፡ አሁን በምሰራው ስራም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡       


Read 4733 times