Saturday, 24 January 2015 12:40

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሁሉም ሊዋጋው የሚገባ ነቀርሳ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  በመላው አሜሪካ ያሉ ተማሪዎች ባርነት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተወገደ ችግር መሆኑን ይማራሉ፡፡ ይሁንና በሚያሳዝን መልኩ፣ ከ150 ዓመታት በኋላ ዛሬም ችግሩ ሥር እንደሰደደ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በእርግጥ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚል ስሙንና መልኩን የቀየረ ቢሆንም፤ በአሜሪካና በመላው ዓለም አስከፊና የሰው ልጆችን መሠረታዊ ክብር የሚያዋርድ ወንጀል ሆኗል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ጃንዋሪ 2015 ብሔራዊ የባርነትና የህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚወገዝበት ወር እንዲሆን አውጀዋል፡፡ አሜሪካ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን ለህግ የምታቀርብ ሲሆን፤ የችግሩ ሰለባዎችንም ከችግሩ እንዲያገግሙና መልሰው እንዲቋቋሙ ትረዳለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥታችን የጤና ባለሙያዎች፣ የበረራ ሠራተኞችና ሌሎች በግሉ ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎች የህገወጥ ዝውውር ሰለባዎችን በተሻለ መልኩ መለየትና መርዳት የሚችሉበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮችና የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሥራት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስወገድ ዙሪያ የሚደረጉ ጥረቶችን ትደግፋለች፡፡ በዚህ ረገድ የህገ ወጥ ዝውውር ሰለባዎችን ለመጠበቅ፣ ወንጀሉን ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን በመደገፍና ተጎጂዎችን አቋቁሞ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ዙሪያ ከእነዚህ አጋር ድርጅቶች ጋር እንሠራለን፡፡
ዘመናዊ ባርነት በዓለማችን ላይ በየትኛውም ሥፍራ ሊከሰት የሚችል በመሆኑ መንግሥታት፣ የንግድ ድርጅቶችና ደንበኞቻቸው ችግሩን የመከላከል የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማሠማራት፣ ህገወጦች 150 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ህገ ወጥ አሠራር ትርፍ እንደሚያገኙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ መግታት የሸማቾችንም የነቃ ተሳትፎና የግሉን ዘርፍ መሪዎች አጋርነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-“እያንዳንዱ ዜጋ ችግሩን በማጋለጥና የሚለብሰው ልብስ፣ የሚበላው ምግብና ማናቸውም ለሽያጭ የሚቀርቡለት ሸቀጦች ከጉልበት ብዝበዛ በፀዳ መንገድ መመረታቸውን ማረጋገጥ ይችላል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የንግድና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች መሪዎችም የአቅርቦት ሰንሰለቶቻቸው ከጉልበት ብዝበዛ መፅዳታቸውን በማረጋገጥ ባርነትንና ግዞትን መከላከል እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በአሜሪካም ሆነ በዓለም ዙሪያ ከምንጩ ለማድረቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም የአሜሪካ መንግሥት፣ ከወርልድ ቪዥንና ከሜኖናይት የኢኮኖሚ ዕድገት አጋሮች ጋር በመተባበር “የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመዋጋት የተቀናጁ ኢትዮጵያውያን” በተሰኘ ፕሮጀክት በኩል ለጉልበት ብዝበዛና ለህገ ወጥ ዝውውር ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ሰፋ ያለ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማስቻል ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለህገ ወጥ ዝውውር ሊጋለጡ ይችላሉ ለተባሉ ህፃናት ቤተሰቦችም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር አቶ አብዱልፋታህ አብዱላሂ ሐሰን ጋር በመሆን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በተጓዝኩበት ወቅት ፕሮጀክቱ ህገ ወጥ ዝውውርን ከመዋጋት አኳያ እያበረከተ ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ባየሁትም አኩሪ ሥራ የተደነቅሁ ሲሆን፤ኢትዮጵያና አሜሪካ አስከፊ የሆነውን የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን በጋራ በመዋጋት ያሳዩት ቁርጠኝነት በአርአያነት የሚጠቀስ እንደሆነም ተረድቻለሁ፡፡
በሌላም በኩል የአሜሪካ መንግሥት የህገወጥ ዝውውርን ችግር ከምንጩ ለማድረቅ ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(IOM) ጋር በመተባበር “የማህበረሰብ ውይይት” የተሰኘ ፕሮግራም ያዘጋጃል፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ በታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ህገ ወጥ ዝውውርን በመከላከል ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የማህበረሰብ ውይይት ፕሮግራም እያንዳንዱ ማህበረሰብ አባላቱና ነዋሪዎች ለችግሩ እንዳይጋለጡ በማስተማር የህገወጥ ዝውውር ሰለባዎች እንዳይሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ዘመናዊ ባርነት በአሜሪካና ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አጋር ሀገራት የተንሰራፋና ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ያለ ችግር ሆኗል፡፡ ይሁንና ቀጣይነት ባላቸው የተቀናጁ ጥረቶች ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን በመዋጋት ብቻ ሳይሆን ችግሩንም ከምንጩ በማድረቅ ተጨባጭነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንደምንችል እንተማመናለን፡፡

Read 3762 times