Saturday, 14 January 2012 10:47

በፊፋ ኮከቦች ምርጫ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ፊፋ በሚያዘጋጀው የ2011 የዓለም እግር ኳስ ኮከቦች ምርጫ ላይ ባለፈው ዓመት ምንም ተሳትፎ ያልነበራት ኢትዮጵያ ዘንድሮ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓ ታወቀ፡፡ የዓለም እግር ኳስ ኮከቦችን ለመምረጥ ከዓለም ዙሪያ ከተሰበሰበው ድምጽ የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋናአሰልጣኞችና አምበሎች እንዲሁም ሁለት የግል የስፖርት ጋዜጣዎችን የወከሉ የስፖርት ጋዜጠኞችን ተሳትፈዋል፡፡ አርጀንቲናዊው የባርሴሎና ክለብ ተጨዋች ሊዮኔል ሜሲ የ2011 የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የወርቅ ኳስ ለመሸለም የበቃው ከተሰበሰበው ድምፅ  47.88% ድጋፍ በማግኘት ነው፡፡ ፖርቱጋላዊው የሪያል ማድሪድ ተጨዋች ክርስትያኖ ሮናልዶ 21.60% እንዲሁም ስፔናዊው የባርሴሎና ተጨዋች ዣቪ ኧርናንዴዝ 9.23% ድርሻ በመውሰድ ተከታታዮቹን ደረጃ ወስደዋል፡፡

በ2011 ኮከብ ሴት ተጨዋች ምርጫው ደግሞ የወርቅ ኳሱን የጃፓኗ ሳዋ ሆማሬ ከጠቅላላው ድምጽ 28.51 በመቶውን በመሰብሰብ ስታሸንፍ የብራዚሏ ማርታ በ17.28% 2ኛ እንዲሁም የአሜካው ዋምባች አባይ በ13.26% 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በ2011 የዓለም ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ ላይ ያሸነፈው ደግሞ  የባርሴሎና ክለብ አሰልጣኝ ፔፔ ጋርዲዮላ 41.92% ድምጽ በመውሰድ ሲሆን ፈርጉሠን በ15.0% እንዲሁም ሞውሪንሆ በ12.43% ተከታታይ ደረጃዎችን አግኝተዋል፡፡ ሰሞኑን ፊፋ በዙሪክ ባካሄደው ስነሰርዓት የጃፓን እግር ኳስ በሴቶች ምድብ ኮከብ ተጨዋች እና ኮከብ አሰልጣኝ ከማስመረጡም በላይ  የዓመቱ ምርጥ ስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማትን በመጠቅለል ጭምር የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ተሳክቶለታል፡፡ከ50ሺ በላይ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች ማህበር አባላት የሆኑ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በተሳተፉበት ምርጫ የ2011 የዓለም እግር ኳስ ምርጥ ቡድን ተለይቷል፡፡ ግብ ጠባቂው ስፔናዊው ኤከር ካስያስ፤ ተከላካዮች የብራዚሉ ዳንኤል አልቬዝ፣ ስፓንያርዶቹ ጄራርድ ፒኬና ሰርጂዮ ራሞስ እንዲሁም የሰርቢያው ኔማንዳ ቪደች፤ አማካዮች ስፓንያርዶቹ አንድሬይስ ኢኒዬስታ፣ ዣቪ ኧርናንዴዝና ዣቢ አሎንዞ፤ አጥቂዎች የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ፣ የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ እና የእንግሊዙ ዋይኔ ሩኒ ናቸው፡፡ በ2011 የዓመቱ ምርጥ ጐል ምርጫ የቀረበውን የፑስካሽ አዋርድ ተሸላሚ ለመምረጥ 1.5 ሚሊዮን ስፖርት አፍቃሪዎች የሰጡትን ድምጽ ያሸነፈው ደግሞ ለብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ  የሚጫወተው ኔደማር ነው፡፡  በ2011 መጨረሻ 70ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩት  የማን ዩናይትዱ ሰር አሌክስ ፈርጉሠን ለስፖርቱ ዕድገት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው እውቅና አግኝቶ የፊፋ የክብር ፕሬዝዳንት ሽልማትን ተጐናጽፈውበታል፡፡ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በ2011 በማን ዩናይትድ አሰልጣኝነት 25ኛ ዓመታቸውን ያከበሩ ሲሆን ከ30 በላይ ዋንጫዎችን በክለቡ የክብር መደርደርያ አስገብተዋል፡፡በ2011  የእግር ኳስ ኮከብ  ምርጫ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት የወንድና የሴት ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኞች፣ ዋና አምበሎች እና የሚዲያ ተወካዮች ባስመዘገቡት  ድምጽ ሙሉ ለሙሉ አልተሳካላቸውም፡፡በኮከብአሰልጣኝምርጫውየቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የሆነው ደጉ ደበበ  ሞውሪንሆ፣ ቬንገርና ጋርዲዮላ  በማለት ድምፅ ሲሰጥ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ጋርዲዮላ፣ ፈርጉሠን ና ዴልቦስኬ በማለት ምርጫቸውን አስመዝግበዋል፡፡ በኮከብ ተጨዋች ምርጫ ላይ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሜሲ፣ ሮናልዶና ኢንዬስታ  ብለው ድምፅ ሲሰጡ ደጉ ደበበ  ዣቪ፣ ሮናልዶና አኒዬስታ በቅደምተከተላቸው አስመዝግቧል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከሰጡት ድምጽ ኢትዮጵያን በመወከል በኮከብ አሰልጣኞችና ተጨዋቾች ምርጫ የተሳተፈው የኢትዮ ስፖርቱ መንሱር አብዱልቀኒ ሲሆን ከአሰልጣኞች ጋርዲዮላ፣ ቦአስና፣ ፈርጉሠን በማለት ከ1-3  ሲያስመዘግብ፤ በኮከብ ተጨዋች ምርጫው ለሊዬኔል ሚሴ 1ኛ ደረጃ ከሰጠ በሃላ ዣቪና ክርስትያኖ ሮናልዶን በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ አስቀምጧቸዋል፡፡ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነችው ብዙሐን እንዳለ በሰጠችው ድምፅ ማያሚ አያ፣ ማርታና ሳዋ ሆማሬ ከ1-3 ደረጃ ሲያገኙ የሉሲ ዋና አሰልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት ደግሞ ማርታ፣ ማያሚ አያና ሞርጋን አሌክስ የተባሉ ተጨዋቾችን መርጧል፡፡ የኢትዮጵያን ሚዲያን በመወከል በኮከብ ሴት ተጨዋች ምርጫ ድምጽ የሰጠው የሃትሪኩ ይስሃቅ በላይ ሲሆን 1ኛ ደረጃን ለጃፓኗ ሳዋ ሆማሬ ሰጥቶ ዋምባች አባይና ሴቺሊን ሎታን በ2ኛና 3ኛ ደረጃ መርጧቸዋል፡፡ በ2011 የዓለምን እግር ኳስ በክለብ ደረጃ ከፍተኛ የበላይነት ያስመዘገቡት የባርሴሎናዎቹ ዋና አሰልጣኝ ፔፔ ጋርዴዬላ እና አርጀንቲዊው ሊዮኔል ሜሲ ምርጫ የዓለም መገናኛ ብዙሀናት ይገባቸዋል በሚል ተቀብለውታል፡፡ ሜሲ እና ጋርዲዮላ በ2011 የፊፋ የዓለም ክለብ ዋንጫን ጨምሮ በስፔን ላሊጋና ሱፕር ካፕን እንዲሁም በአውሮፓ ደረጃ የሻምፒዮንስ ሊግና የሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን ከባርሴሎና ጋር ተቀዳጅተዋል፡፡ ጋርዲዮላና ሜሲ በፊፋ የ2011 ኮከብ አሰልጣኝና ኮከብ ተጨዋች ሆነው ሲሸለሙ ለስኬታቸው የቡድን አጋሮቻቸውን ያመሰገኑ አመስግነዋል፡፡ ከሽልማቱ ስነስርዓት በሃላ በዓለም ሚዲያዎች የፔፔ ጋርዲዮላ የባርሴሎና ቆይታ በአጠያያቂነት ያነጋገረ ሲሆን በሜሲ ዙርያ የተነሱት ጉዳዮች ደግሞ በቀጣይ የውድድር ዘመናት በባርሴሎና በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ብዙ ሪኮርዶች መቆጣጠሩ እንደማይቀር በይበልጥ ተወስቷል፡፡ፔ ጋርዲዮላ በባርሴሎና አሰልጣኝነት በሰራባቸው 3 የውድድር ዘመናት 13 ዋንጫዎችን መሰብሰብ ችሏል፡ ጋርዲዮላ በካታላኑ ክለብ ስራውን ከጀመረበት የውድድር ዘመን አንስቶ ኮንትራቱን በ1 ዓመት ቅጥር ብቻ እየወሰነ የቆየ ሲሆን ይሄው የውል አፈፃፀም ቀጣይነቱን አጠያያቂ የሚያደርገው ሆኗል፡፡ ጋርዲዮላ ከባርሴላ ጋር በክለቡ ታሪክ ከፍተኛው ውጤታማ ሊያደርገው የሚችል ታሪክ በመስራቱ ከ2012 በሃላ ከክለቡ ጋር ለመቆየት ያለውን እድል እንደሚያጠበው እየተነገረ ሲሆን እሱ ከካታላኑ ክለብ ሲለቅ ማን ሊተካው ይችላል  በሚልና ከባርሴሎና በኋላ ሃላፊነቱን በየትኛው ክለብ ይቀጥላል በሚለው ሁኔታ እርግጠኛ ግምት ለመሰንዘርም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ከአውሮፓ ክለቦች ጋርዲዮላን ለመቅጠር ፍላጎት ካላቸው ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ማን ዩናይትድና እና ቼልሲ ዋና ተጠቃሾች ይሆናሉ፡፡ በተለይ በኦልትራፎርድ የ70 ዓመቱን ፈርጉሰን ለመተካት የፔፔ ጋርዲዮላ ተመራጭነት እነደሚያመዝን የተለያዩ ዘገባዎች በየአጋጣሚው አውስተዋል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ በዓለም ኮከብ ተጨዋችነት በሶስት ተከታታይ ዓመታት የወርቅ ኳስ ለመሸለም በመብቃቱ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት የቀድሞ ምርጥ ተጨዋች ሚሸል ፕላቲኒ ክብረወሰን ጋር ለመስተካከል በቅቷል፡፡ በቀጣይ የውድድር ዘመናት ደግሞ በባርሴሎና ክለብ ታሪክ እና በአውሮፓ እግር ኳስ የግብ አግቢ ሪኮርዶችን እንደሚያሳድድ ይጠበቃል፡፡ዘንድሮ የሚያገኘው ገቢ ግምት 49 ሚሊዮን ዶላር  የተተመነለት ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና ዋና ቡድን ያገባቸው ጐሎች ብዛት በዘንድሮ የውድድር ዘመን መጨረሻ  237 እንደሚደርስ የተገመተ ሲሆን ከተሳካለት በክለቡ ታሪክ በከፍተኛ ግቢ አግቢነት በ236 ጐሎች በሴዛር ሮድሪጌዝ የተያዘውን ክብረወሰን ይረከባል፡፡በአንድ የውድድር ዘመን በአማካይ ከ50 በላይ ጐሎችን የሚያስመዘግበው ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና የተጫዋችነት ታሪኩ የሚያገባቸውን ጐሎች ብዛት 537 ያደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ የግብ ብዛት ደግሞ ከዚህ ቀደም በየትኛው የክለብ ታሪክ

 

 

ተመዝግቦ አያውቅም፡፡

 

 

Read 2922 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 10:52