Print this page
Saturday, 17 January 2015 11:12

ኢህአዴግ በአንድ ሳምንት ውስጥ ናፍቆቴን አረካልኝ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(14 votes)
  • በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ቦርድ ላይ ቅሬታ አቀረበ
  • የእኛ ምርጫ  ከአሜሪካ ምርጫ መብለጡን በምስጢር እንያዘው  

ባለፈው ሳምንት ምን ብዬአችሁ ነበር? ውዝግብ ከሰማችሁ ምርጫ ደርሷል ማለት ነው አላልኳችሁም፡፡ አሁንም ውዝግቡ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንደውም ያለወትሮው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ “ሆደ ሰፊ” ሆኖ ነው እንጂ ጉዳዩ ከዚህም የባሰ ይሆን ነበር፡፡ እውነት ለመናገር --- የቦርዱ ያልተለመደ “ቅንነት” ለብዙዎች እንግዳ ቢመስላቸው አያስደንቅም፡፡ ሆደ ሰፊነትን የአበሻ ፖለቲካኞች እንኳን በተግባር በምናብም አያውቁትም፡፡  እናም---ለመለማመድ ብዙ ጊዜ ሊፈጅባቸው እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ቦርዱ ሊመሰገን ይገባል፡፡  
በነገራችን ላይ የተሻለ አማራጭ ፖሊሲ በማቅረብ መራጩን ህዝብ መማረክ ባይችሉ እንኳን እንደ እነ መኢአድ ሳይከፋፈሉ በምርጫው ለመሳተፍ የተዘጋጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በይፋ ልናደንቃቸው ይገባል፡፡  ዋናውን የመንግሥት ስልጣን የተቆናጠጠው ኢህአዴግም በዚህ በኩል የበለጠ ይደነቃል፡፡ በአገራዊ ምርጫ ወቅት በረባ ባልረባው ተከፋፍሎ መወዛገብ በእጅጉ ያሳፍራል፡፡ (ከምርጫው በኋላ ያደርሳቸው አልነበር!) እውነት ለመናገር ይሄ እኮ ሌላ ሳይሆን ራስን በራስ ማጥፋት (Sucide) ነው፡፡
እኔ የምለው… ነገሩን በቦርዱ ወይም በኢህአዴግ ላይ ከማላከክ ምናለ እቺን ወቅት እንደ ምንም ታግሰው ቢያልፏት (ህዝብም ይታዘባል እኮ!) እኔማ እልሃቸው ሁሌም በኢህአዴግ ላይ ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ (ለካስ በራሳቸውም ላይ አይመለሱም!)
EBC ሰሞኑን ያነጋገራቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምርጫ ቦርድ፤ ለመኢአድና አንድነት ለሶስተኛ ጊዜ የሰጠው እድል የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋ መሆኑን ጠቅሰው  ፓርቲዎቹ በእድሉ እንዲጠቀሙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የቦርዱን ሆደ ሰፊነትም አድንቀዋል፡፡ (ለምን በሰላማዊ ሰልፍ አድናቆታችንን አንገልጽም?!) አይገርማችሁም… ከEBC አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በሃሳብ የተስማማሁት አሁን ነው፡፡ (ኢቢሲ አንዳንድ “ነዋሪዎቹን” ለወጠ እንዴ?)
ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲዎቹ የውስጥ ችግራቸውን (የቤት ጣጣ መሰለ እኮ!) ፈተው ወደ ምርጫው እንዲገቡ ለሦስተኛ ጊዜ የሰጠውን እድል አንዳንዶች እንደ ሆደ ሰፊነት ሲመለከቱት፣ አንዳንዶች ደግሞ እንደ ልምምጥና እሽሩሩ ባይነት የተመለከቱት ይመስላል፡፡ እኔ ግን ልምምጥም ይሁን እሽሩሩ ባይነት ለዲሞክራሲ እድገትና ከፓርቲዎቹ ጀርባ ላለው ህዝብ ሲባል የተደረገ ነው ባይ ነኝ (ምርጫ ቦርድ ያለውን ሰምቼ እኮ ነው!)
በነገራችን ላይ--- በዚህ ምርጫ በርካታ “ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰቱ” ነገሮች እየገጠሙን ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቃዋሚዎች አድናቆት ቀርቦለታል፡፡ ቦርዱ በፓርቲዎች  የገንዘብ ድጋፍ ቀመር ላይ ማሻሻያ በማድረጉ ነው የተደነቀው (ተቃዋሚዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል!) ለካስ---አንዳንድ ወገኖች በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚዎች እንደ ኢህአዴግ “ጥገኛ” እንጂ እንደ ትክክለኛ ተቃዋሚዎች አይመለከቷቸውም፡፡ (“ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” አሉ!)
በሌላ በኩል---በገንዘብ ድልድል ቀመሩ የፓርላማ መቀመጫ ድርሻ ከ55 በመቶ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ማለቱ ከዓለም አቀፍ መመዘኛ ውጭ ነው ሲል ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ቅሬታውን የሰነዘረ ሲሆን እንዲያም ሆኖ ግን የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡ በነገራችን ላይ… ኢህአዴግ በቦርዱ ላይ የሰነዘረው ቅሬታ በ20 ምናምን ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ እኔን ከሁሉ የገረመኝ ደግሞ ---- ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት የምርጫ ውዝግብ ወግ ላይ ኢህአዴግ ለለውጥ ያህል እንኳን በምርጫ ቦርዱ ላይ ቅሬታ ሲሰነዝር መስማት እንደናፈቀኝ ገልጬ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ በሳምንት ጊዜ ውስጥ በቦርዱ ላይ ቅሬታውን በመሰንዘር ናፍቆቴን አረካልኝ፡፡ በአዲሱ የምርጫ ቦርድ የገንዘብ ድጋፍ ቀመር ማሻሻያ፣ የፓርላማ መቀመጫ ድርሻ መቀነሱ ግን የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋዋል የሚል ነገር አልወጣኝም! የኢራፓ ሊ/መንበር በበኩላቸው፤ የድጋፍ ቀመሩ መሻሻል የአቻነት ስሜት ይፈጥራል (ከኢህአዴግ ጋር መሆኑ ነው!) ብለዋል፡፡
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም… ኢህአዴግ መንግስት በመሆኑ ከተቃዋሚዎች የተለየ Privilege (ልዩ መብት) እንዳለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እሳቸው ያሉት ፕሪቪሌጅ በምርጫውም ይሰራ እንደሆነ ከአሁኑ እንዲነገረን እንፈልጋለን (እንዳለፈው ዱብእዳ እንዲሆንብን አንፈልግማ!)
ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ ቃለምልልስ ያደረጉት የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ፤ በምርጫው የሚፎካከራቸው (የሚገዳደራቸው) ተቃዋሚ ፓርቲ ይኖር እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በዚህ ሰዓት አሸንፋለሁ ብሎ መናገር እንደ ምርጫ ቅስቀሳ ስለሚቆጠር ተገቢ አይደለም ብለው ሲያበቁ፣ መልሰው እንዴት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የማሸነፍ ተስፋ እንደሌላቸው በዝርዝር ማስረዳት ጀመሩ፡፡ የቻሉትን ያህል ከተናገሩ በኋላም መልሰው፣በዚህ ሰዓት አሸንፋለሁ ማለት የምርጫ ቅስቀሳ ስለሚሆን ከዚህ በላይ ባልናገር እመርጣለሁ አሉ (ግን እኮ ተናግረው ጨርሰዋል!) አንዳንድ የEBC የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “ልማቱን ያስቀጥልልኛል የምለውን ፓርቲ ነው የምመርጠው” እንደሚሉት አይነት ሆነብኝ (ዝም ብለው ኢህአዴግን እመርጣለሁ ቢሉ እኮ ነው የሚሻለው!)
የኢህአዴጉ ተወካይ፤ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን በምርጫው ሊፎካከሯቸው እንደማይችሉ ሲያስረዱ፤ የትኛው ተቃዋሚ ነው ህዝቡን በልማት አግዞ የሚያውቀው ወዘተ… ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ እንኳን በልማት ለማገዝ በአግባቡ ለመቃወምም መፈናፈኛ አጥተናል ባይ ናቸው፡፡ እንዴት ሲባሉ… ኢህአዴግ እንኳን የልማቱን የፖለቲካ ምህዳሩንም አጥቦታል በማለት ይከሳሉ (ኢህአዴግ አመላቸው ነው እንደሚል አልጠፋኝም!)
አንዳንዴ ምን አስባለሁ መሰላችሁ? ከቻይና፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ--ወዘተ የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት “እውነት አጣሪ ኮሚሽን” ለምን አይቋቋምም እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ካለበት ነፃና ገለልተኛነቱ ላይ ጥያቄ ይነሳል ብዬ እኮ ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ እሱን የሚያጣራ ሌላ ኮሚሽን ያስፈልጋል፡፡ እናም ኮሚሽኑ አንዳንድ መተማመን ላይ ያልተደረሰባቸውን አገራዊ ጉዳዮች በገለልተኝነት እየመረመረ እውነቱን ለህዝቡ ያሳውቃል፡፡ ተጠሪነቱ ታዲያ ለጠ/ሚኒስትሩ ሳይሆን ለህዝቡ ነው የሚሆነው! (ሥራ ይበዛባቸዋል ብዬ  እኮ ነው!)
ከዚሁ ከምርጫ ጉዳይ ሳንወጣ ባለፈው ረቡዕ ምሽት፣ በEBC የሚዲያ ዳሰሳ ላይ የቀረበውን አስገራሚ የምርጫ ትንተና  ዳሰስ አድርገን ወጋችንን እንቋጨው፡፡ መቼም ይሄ --- በሁሉ ነገር ከዓለም አንደኛ ነን የሚል ክፉ አባዜ አለቀን ብሏል አይደል?! እናላችሁ… የሚዲያ ዳሰሳ አቅራቢው ጋዜጠኛ ታደሰ ሚዛንና በእንግድነት የተጋበዘው የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ በምርጫው ዙሪያ ባደረጉት አስገራሚ ትንተና፣ ገና ሁለት አስርት ዓመታት ያስቆጠረው የአገራችን ምርጫ፣ 200 ዓመት ገደማ ከሆነው የትልቋ አገር አማሪካ ምርጫ በብዙ ነገሮች እንደሚበልጥ አስረዱን፡፡ (ደፋር አይጥፋ እኮ ነው!) አሜሪካኖቹ ቢሰሙ ምን ይሉን ይሆን?
አይገርማችሁም… በምርጫ እኩያ የሚሆነን የአፍሪካ አገር እንኳ ጠፍቶ ከአሜሪካ ጋር ተወዳደርን፡፡ መወዳደር ብቻም ሳይሆን እንደምንልቅም ተነገረን፡፡ በሁለቱ ጋዜጠኞች አባባል እኮ አሜሪካ በ200 አመታት ያልደረሰችበትን የምርጫ እድገት፣ ጦቢያ በሁለት አስርት ዓመታት አልፋ ሄዳለች፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደሞ ዲሞክራሲ ሂደት ሳይሆን የአንድ ጀምበር ክስተት ሆነ  ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ግን የእኛ ምርጫ ከአሜሪካ ምርጫ ይበልጣል የሚለውን ትንታኔ በምስጢር ብንይዘው ይሻላል፡፡ (“እዩኝ እዩኝ ያለች--” የሚለውን ተረት አልወደውም!)

Read 3642 times