Saturday, 17 January 2015 11:02

በልጅነት ድህነት ላይ ያተኮረው የ“ያንግ ላይቭስ” ጥናት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

* ጥናቱ ለ15 ዓመታት በአራት አገራት ላይ የተካሄደ ነው
*  ያለ ዕድሜ ጋብቻ ላይ ያልተጠበቀ ውጤት ተገኝቷል
* በህፃንነት የተጎዱ ልጆች ላይ የመሻሻል ሁኔታ ታይቷል
* የትምህርት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል

   በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በአራት የተለያዩ አገራት ለ15 ዓመታት የተካሄደው ልጆች ላይ ያተኮረ የ“ያንግ ላይቭስ” ጥናት ኢትዮጵያንም ያካትታል፡፡ በጥናቱ ላይ የተሳተፈው የፓንክረስት የምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሰጡንን ማብራሪያ እንደሚከተለው ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡
የ“ያንግ ላይቭስ” ፕሮጀክት
“ያንግ ላይቭስ” የተሰኘው የጥናት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ፣ ፔሩ፣ ቬትናምና ህንድ ላይ ለ15 ዓመታት የተካሄደ ሲሆን በልጆች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በየአገሩ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተወለዱና በአሁኑ ወቅት 14 አመት የሞላቸው ልጆች ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ አገር ሶስት ሺህ ልጆች ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ሁለት ሺዎቹ በ2000 ዓ.ም የተወለዱ፣ አንድ ሺዎቹ ደግሞ ለማነፃፀሪያ እድሜያቸው ከፍ ያለ አሁን አስራ ዘጠኝ አመታቸው ላይ የሚገኙ ልጆች ናቸው፡፡  ሁለት ሺዎቹን ከተወለዱ ጀምሮ እየተከታተልናቸው ሲሆን እስከ አሁን ድረስ  በልጆቹና በወላጆቻቸው ላይ አራት ዙር ጥናቶች  ተካሂደዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጥናት የተካተቱት ክልሎች አዲስ አበባ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ሲሆኑ ከተማ ገጠር፣ ሀብታም ቤተሰብ ድሀ ቤተሰብ፣ ሴት ወንድ የሚሉ ስብጥሮችን ባካተተ መልኩ የተካሄደ ነው፡፡  ጥናቱ ድሀ ተኮር በመሆኑ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው  በሀያ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተሰራ ነው ፡፡
የጥናቱ ትኩረት
ጥናቱ አመጋገብና ጤና ፣ ትምህርት፣ የልጆች እድገትና የወደፊት አላማቸው ላይ ያተኩራል፡፡ ጥናቱን  የሚያሰራው የኢትዮጵያ የልማት ጥናት ድርጅት ሲሆን  የኮሙኒኬሽን ስራችን ደግሞ ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር ነው፡፡ አሁን  በአራተኛው ዙር ጥናት ውጤትና ከአንድ እስከ አራት ዙር በተካሄዱት ጥናቶች ለውጦቹ ምንድን ናቸው የሚለው ላይ አተኩረን እየሰራን ነው፡፡    
ለጥናቱ የተመረጡ አገራት መመዘኛ
ጥናቱ የሚካሄደው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በተለያየ የአለም ክፍልና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት በሚል መመዘኛ ነው የተመረጡት፡፡ ኢትዮጵያ ድሀ አገር እንዲሁም  ለጠንካራ እድገትና ለልማት ጥሩ የመንግስት አቋም ያለበት በሚሉ መስፈርቶች ነው የተመረጠችው፡፡ ክልሎቹ የተመረጡበት መስፈርት ደግሞ ጥናቱ የረጅም አመታት ጥናት እንደመሆኑ መጠን ትልቁ ስጋታችን የምንከታተላቸው ልጆች ከአካባቢው እንዳይጠፉ የሚል ነበር፡፡ አርብቶ አደር አካባቢዎች ምናልባት ልጆችን ለመከታተል ያስቸግራል ከሚል አንፃር ነው በጥናቱ ያልተከታተሉት፡፡ ነገር ግን  ተጨማሪ ጥናቶችም ይኖሩናል፡፡ በህፃናት አድን ድርጅት ድጋፍ ለማነፃፀር እንዲያግዘን ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት በሶማሌና አፋር ክልል ላይ አድርገናል፡፡
ወላጅ ያጡ ልጆች የጉልበት ብዝበዛ፣ በከተማ እድገት ምክንያት ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ እንዲሁም ከኮንዶሚኒየም ቤት አሰራር ጋር የተገናኘ ጥናት አካሂደናል፡፡ በቅርቡም አንድ የጀመርነው ወደ አዋቂነት ሽግግርና ቤተሰብ እንዴት እንደሚመሰርቱ፣ እንዴት እንደሚያገቡ፣ እድሜ፣ ወሊድ እና የመሳሰሉት ላይ ያተኮረ ጥናት አለ፡፡
ሌላ የምንጀምረው ጥናት ደግሞ የመዋዕለ ህፃናትና ቅድመ ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ይሆናል፡፡ በጥናቱ ያገኘነው አንድ ነገር ምንድን ነው… የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከመጀመራቸው በፊት በቄስ ትምህርትም ይሁን በመዋዕለ ህፃናት ተምረው ያለፉ ልጆች፣ ሲያድጉ ያንን እድል ካገኙት ጋር ሲነፃፀሩ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ነው፡፡ በማንበብ፣ በሂሳብና በማሰላሰል ችሎታቸው የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ የመዋዕለ ህፃናት ደግሞ በመንግስት ብዙ ትኩረት ስላልተሰጠውና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ ይበልጥ ልናጠናው ሀሳብ አለን፡፡ ሌላው የጥናት ትኩረታችን ልጆች ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው፡፡
የጥናቱ ውጤቶች
ጥናቱ ከሚያተኩርባቸው አንዱ አመጋገብ ላይ ነው፡፡ ሌላው ትምህርት፣ ሶስተኛው የልጆች እድገት ላይ ነው፡፡ አመጋገብን ስናይ ብዙ ለውጦች ያሉ ቢሆንም አሁንም የአመጋገብ እጥረት ችግር ላይ የወደቁ ልጆች እንዳሉ የጥናት ውጤቱ ያሳያል፡፡ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮችም አሉ፡፡  እስከ አሁን አንድ ህፃን ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ያሉት አንድ ሺህ ቀናት ለህፃኑ እድገት ወሳኝ እንደሆኑ ይታመን ነበር፡፡ በነዚህ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ ህፃናት ጥሩ ምግብ ካላገኙ በዕድገት ሂደታቸው የአእምሮና አካላዊ ጉዳት እንደሚያጋጥማቸውና ተስፋ አይኖራቸውም የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ በጥናት ውጤቱ ግን እኛም ያልጠበቅነው ነገር ነው ያገኘነው፡፡ በልጅነታቸው ከተጎዱት ውስጥ የተወሰኑት በጣም ደህና ሆነው ነው ያደጉት፡፡ ቁመታቸው፣ የትምህርት ደረጃቸው ጨምሮ በብዙ ነገር ጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም በመነሳት አንዳንዶቹ በህፃንነታቸው ተጎድተው ለምን ደህና ሆኑ? አንዳንዶቹ ለምን መጥፎ ሁኔታ ላይ ሆኑ? ለውጡን ያመጣው ምንድነው? በሚሉት ላይ አተኩረን ማጥናት እንፈልጋለን፡፡ የምግብ ዋስትና ችግር ትንሽ ተሻሽሎ ነው ያገኘነው፡፡ ልጆቹ የሚመገቧቸው ምግቦች  ስብጥርም ተሻሽሏል፡፡ የንፅህና ጉዳይም ላይ መሻሻሎች አሉ፡፡ ስጋት ሆኖ ያገኘነው የመጠጥ ውሀ ላይ ነው፡፡ የመጠጥ ውሀ ሁኔታ የባሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ትምህርት ላይ ጥሩ ተብሎ የሚጠቀሰው ሽፋን ነው፡፡ የገጠርና የከተማ ልዩነት እንዳለ ቢሆንም  የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ቁጥር በጣም ከፍ ብሏል፡፡ ከዚያም ሌላ የሴቶች ተማሪዎች ቁጥር ይበዛል፡፡ በትምህርት ላይ ያገኘነው አሳሳቢ ነገር የጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ የሁለት እድሜ ክልል ነው የምናነፃፅረው፡፡ ይህን ስናደርግ የማንበብና የሂሳብ ችሎታ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፤ በተለይ በገጠር፡፡ ይህ አሳስቦናል፡፡ በተለይ የሂሳቡ ውጤት መቀነሱ ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ችግሩ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመምህራን ችሎታና ፍላጎት ፣ ከተማሪዎች መብዛት፣ ከልጆች የስራ ጫና… የመሳሰሉት አንፃር መታየት ይኖርበታል፡፡  እዚህ ላይ መጠናት ያለበት ነገር የተማሩ እናቶች ያሏቸው ህፃናት የተሻሉ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ሌላው ያለ እድሜ ጋብቻ ላይ ያገኘነው ውጤት ያልጠበቅነው ነው፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ ሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ ዝቅ ያለ ነው፡፡
የአገራቱ ንፅፅር
አራቱን አገራት ስናነፃፅር፣ እኛ የጠበቅነው ያለ እድሜ ጋብቻ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር ትይዛለች ብለን ነበር፡፡ ውጤቱ ግን በተቃራኒ ነው የሆነው፡፡ ህንድ ከፍተኛውን ቁጥር ይዛለች፡፡
በህንድ አስራ ዘጠኝ አመት ከደረሱ ሴቶች 34 በመቶው አግብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አስራ ሶስት በመቶ ብቻ ናቸው ያገቡት፡፡ ከአራቱ አገራት የቀነሰ ቁጥር ነው የተገኘው፡፡ልጆች በመውለድ ደግሞ አንደኛ ፔሩ ናት፤ ምክንያቱም ሳያገቡም ይወልዳሉ፡፡ ውጤቱ በደረጃ ሲቀመጥ፤ ፔሩ፣ ህንድ ፣ ቬትናምና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ይህ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ግኝት ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ላይ ኢትዮጵያና ህንድ የሚያሳስባቸው አገሮች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የፔሩ ልጆች በተለይ በሂሳብ በጣም የላቁ ናቸው፡፡ የጥራት ችግሩ በህንድና ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሲሆን በሌሎቹ አገራት ሲሻሻል ሁለቱ ላይ ለምን ዝቅ አለ የሚለው ገና ጥናት የሚፈልግ ነው፡፡ ግን አገሮቹ የጀመሩበት ሁኔታ ግምት ውስጥ ሲገባ ኢትዮጵያ ማዳረስ ላይ ጥሩ ውጤት አምጥታለች፡፡
ለዚህ ደግሞ ብዙ ስራ መሰራቱ ይታወቃል፡፡ ትምህርት ቤት መገንባት፣ መምህራንን ማሰልጠን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር፣ የመፃፊያ ፊደሎች ለውጥ… ግምት ውስጥ ሲገባ ጥራትን እንደሚነካ የሚጠበቅ ነው፡፡ በአመጋገብና በጤና ረገድ ኢትዮጵያ ችግር የነበረባትና ያለባት አገር ናት፡፡ ግን ሌሎቹም አገሮች ውስጥ ደሀው አካባቢ ችግሮች አሉ፡፡ በጣም የሚገርመው በአራቱም አገሮች በህፃንነት የተጎዱ ልጆች ላይ የመሻሻል ሁኔታ ታይቷል፡፡ ይህ አለምአቀፍ ክስተት ሲሆን ኢትዮጵያም ላይ ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቷል፡፡

Read 2264 times