Saturday, 17 January 2015 10:58

ራስን እንደ ማጣት ነው!- “ጣይቱ ሆቴል” እና ትዝታዎቹ

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(181 votes)

እሑድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ማለዳ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቤተኛና ወዳጆች ለሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎችም ጭምር መልካም ረፋድ አልነበረም፡፡ አሳዛኙ ዜና የብዙዎችን ጆሮ ለማዳረስና ለማሳዘን ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ “ቀደምቱና ታሪካዊው የጣይቱ ሆቴል በእሳት ተቃጠለ!” ይህንን ዜና በርካታ ድረ ገጾችና መገናኛ ብዙሀን ተቀባበሉት፡፡ ክስተቱ እጅጉን አሳዛኝ ነበርና የምር ኢትዮጵያዊነት ለሚሰማውና እሴቶቹን ለሚያከብር ዜጋ ሁሉ ሀዘኑ መሪር ነበር፡፡
                 “የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ
                 ተቃጥሎአል መሰለኝ ሸተተኝ ሀገሬ”  (ዮፍታሄ ንጉሴ)
እንዳለመታደል ሆኖ እንደ ህዝብ የራሳችን ለሆኑ ነገሮች ያለን ግምት እጅጉን ያነሰ ነው፡፡ እናም የእኛ ከሆኑ ነገሮች ይልቅ የሌሎችን እናከብራለን፡፡ በዚህም ታሪካችንን፣ እውነታችንን… በአጠቃላይ ማንነታችንን ቀርሰው የያዙ በርካታ እሴቶቻችንን ቸል እንላለን፡፡ ብለናልም! አስገራሚው ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህን ችላ ብለናቸው የኖርነውን እሴቶቻችንን የምናከብረው ባዕዳን ሲመሰክሩላቸው ስንሰማ ወይንም እሴቶቹን በአንዳች ያልተጠበቀ አደጋ ስናጣቸው ነው፡፡ ያኔ ወጋችን ሁሉ እነሱን ይሆናል፡፡ ሲያልፍ ልንዘነጋቸው፡፡ ወረተኞች ነን ልበል?!
“(እቴጌ) ጣይቱ ሆቴል” በሀገራችን ቀዳሚው ሆቴል መሆኑን በርካታ ድርሳናት መዝግበዋል፡፡ ሆቴሉ በ1898 ዓ.ም በነሀሴ ወር ግንባታው ተጀምሮ በ1900 ዓ.ም ጥቅምት 25 ቀን ተመርቆ መከፈቱን ታላቁ ብዕረኛ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለውና የአጼ ምኒልክን ታሪክና ተግባራት በከተበበት መጽሐፉ ይገልጻል፡፡
በዘመኑ በነበረው ባህልና ማህበረሰባዊ አስተሳሰቦች ምክንያት በወቅቱ ሆቴል ከፍቶ “ምግብ ከፍላችሁ ተመገቡ፤ መጠጥም እንዲሁ” ማለት፣ እንዲሁም ሆቴሉ እንኳን ቢገኝ ከፍሎ መመገብ እንደነውር የሚታይ በመሆኑ፣ ህዝቡም ሆነ መኳንንቱ ስለማይፈጽሙት ጉዳዩ ንጉሡን አጼ ምኒልክንም ሆነ እቴጌ ጣይቱን እጅጉን አሳስቧቸው ነበር፡፡ እናም ምኒልክና ጣይቱ ይህንን መፈጸም ነውር እንዳልሆነ በቅርባቸው ላሉ መኳንንት ከማስረዳት ባለፈ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነባሩን ባህልና ልማድ ባጠበቀ ማህበረሰብ ውስጥ አዲስ ባህልን መትከል ቀላል አይደለምና፡፡ የጳውሎስ ትረካ ይህን ይላል፡-
 “እንደ አገር አባባል ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እያሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ:: እንኳን ምግብ መብላት ከግሪኮች ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ መጠጣት ነውር ነበረና ጣይቱ ጠዋት የሚያሠሩት ወጥ ለሠራተኞቹ የማታ ራት ይሆን ጀመር፡፡ የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኩዋንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዱዋቸው፡፡ መኳንንት በላ ጠጣና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ፡፡
በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ ቀጥሎም ጠፋ፤ ቀጥሎም ጠፋ፡፡ እንደገና ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለ መሆኑን ለመኳንንቱ ገልፀው እንደገና ምሣ ጋበዙ፡፡ በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ አጤ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙሪያቸው ላሉ መኳንንት “ሰማችሁ ወዳጆቼ” አሉ:: “በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል፡፡” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ “እርስዎን ፈርተንና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከሆነ የምኒልክን ብድር ለመመለስ እኔ አለሁ” እያለ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዝ ጀመረ፡፡ ገበያ እየደራ ሄደ፡፡ ምሳችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ የሚለው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ፡፡”
ይህንን ታሪክ መዝግቦ ላቆየልን ለደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ “እረፍት ይስጥልን!” ብለን እንቀጥል፡፡ እንግዲህ ጣይቱ ሆቴል ተመርቆ ሥራ የጀመረበትን ጊዜ ይዘን ስናሰላ እነሆ ሆቴሉ የ107 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ነው ማለት ነው፡፡ ሊያውም አምስት ዘመነ መንግስታትን ያሳለፈ ትልቅ ቅርስ! በሆቴሉ ነገሥታቱንና ቤተሰቦቻቸውን ወዳጆቻቸውን ጋብዘዋል፤ እርስበርስም ተገባብዘዋል፡፡ መኳንንቱ የሚወዱትን ጨብጠው ብዙ አውግተዋል፡፡ የበርካታ የውጪ ሀገር መሪዎችም አርፈውበታል፡፡  ጣይቱ ሆቴል በሀገራችን የሆቴልና ቱሪዝም መስክ ቀዳሚው በመሆኑና አንድ ለእናቱ ሆኖ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱም ጭምር በውስጡ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ተወስተውበታል፤ ተወስነውበታልም፡፡ ሆቴሉ ለዘመናት የሰጠው አገልግሎትና ያቀፋቸው ትዝታዎች፣ በዚህም የተሸከመው ታሪክ የትየለሌ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጣይቱ ሆቴል ከተለመደው የሆቴል አገልግሎት ባለፈ የብዙ ጥበባት ቤትና ልዩ ልዩ ድርጊቶች መከወኛም ነበር፡፡ የማይሰለቸውና የማይታጎለው የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ መገኛና ማቀንቀኛ፣ የበርካታ ፊልሞችና መጻሕፍት መመረቂያ፣ የበርካታ ጥበባዊ ክንውኖች “ማሄጃ” ነበር፡፡ እጅጉን ለፒያሳ ቅርብ በመሆኔ በሳምንት ውስጥ ጣይቱ ሆቴልን የማላይባቸው ቀናት ጥቂት ናቸው፡፡ በሆቴሉ ውብ አዳራሽ በተካሄዱ ልዩ ልዩ ጥበባዊና ሌሎች ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ ታድሜአለሁ፡፡ ትዝታዬ ብዙ ነው! መቃጠሉን ስሰማ ያ ግርማ ሞገሱ የሚጣራው ህንፃና በውስጡ ያቀፋቸው የማይተኩ ቅርሶች፣ እንዲሁም ውብ አዳራሹና የታደምኩባቸው ፕሮግራሞች በአይኔ ሞሉ፡፡ ራሱ ህንፃውና አቅፎአቸው የኖሩት ቅርሶች የማንነታችን አንድ ምስክር፣ የታሪካችን መዛግብት ናቸው፡፡ እንዴት እንተካቸው ይሆን? እውነት ለመናገር በሆቴሉ ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ፎቶ ግራፎች፣ መገልገያ ቁሶች፣ ህንፃውን ቀጥ አድርገው የተሸከሙት ዋልታዎች… ዙሪያ ገባውን ሁሉ ደጋግሜ ያየሁት ቢሆንም ወደ ሆቴሉ በገባው ቁጥር ይህ ውበት እንደ አዲስ ትኩረቴን ይስባል፡፡ ዙሪያ ገባው ኢትዮጵያዊነትን ይናገራል!
ይህንን እጅጉን የማንነታችንና የታሪካችን ምስክር የሆነን ህንፃና ጓዞቹን በአደጋ አጣን፡፡ (“መንግስት አደጋው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡” ቢልም፡፡ ለነገሩ ሌላስ ምን ሊል ይችላል?!) ጉዳቱ በቀደምት አበው የተሰሩ ታሪካዊ ቅርሶችን በማሳጣት ብቻ እንዳላበቃና በዛሬው ትውልድ የተበጁ ልዩ ልዩ እሴቶችንም እንደነጠቀን እየተነገረ ነው፡፡ የምር ታሪካችንን ለምናከብርና የኢትዮጵያ አክባሪ ለሆኑ የውጪ ወዳጆችን ሁሉ ሀዘኑ ታላቅ ነው! መጽናናቱን ይስጠን ከማለት ሌላ  እንግዲህ ምን እንላለን? አላውቅም!
በመጨረሻም አንድ እጅጉን ያስገረመኝንና እሱን ተከትሎ በውስጤ የተነሳውን ጥያቄ አንስቼ ላብቃ፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካን መንግስት አምባሳደር የሆኑት ፓትሪሺያ ሃስላክ በጣይቱ ሆቴል ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን በራሳቸውና በአሜሪካ ህዝብ ስም የገለጹበትን የሀዘን መልዕክት አነበብኩ፡፡ ከአምባሳደሯ መልዕክት ጀርባ ያለውን የዲፕሎማሲ ጣጣ ትተን እናስብ፡፡ መገረማችን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ተከትለው የሚመጡ በርካታ ጥያቄዎች አሉና፡፡
ለምንም ይሁን፣ ሌላ መንግስት ስለደረሰብን ጉዳት ሀዘኑን ሲገልጽ የቅርሱና የታሪኩ ባለቤት የሆነው መንግስት በጠፋው ጉዳት የምር ምን ተሰምቶት ይሆን? ፕሮግራሞችን በመደጋገም የአየር ሰዓታቸውን የሚሸፍኑት የመንግስት መገናኛ ብዙሀንስ (ከዜና ሽፋን ባለፈ) ለክስተቱ የሰጡት ሽፋን ምን ይመስል ነበር?... “ባለቤቱ ያቃለለውን አሞሌ…!” ይመስላል፡፡  
ሌላም ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በጣይቱ ሆቴል የተነሳውን የእሳት አደጋ በቁጥጥር ሥር በማዋል ታላቁን ቅርስ ለማዳንስ ምን ያህል ጥረት ተደርጎ ይሆን? “የእሳት አደጋ በደረሰ ቁጥር በፍጥነት ደርሶ የሚጠበቅበትን አገልግሎት አልሰጠም” እየተባለ ሠርክ ወቀሳ የሚደርስበትና እዚያው መሀል ፒያሳ ላይ የሚገኘው ተቋምስ አደጋውን ለመቆጣጠር የሚጠበቅበትን ያህል ደክሞ ይሆን? ሌላም ብዙ!
በአደጋው የደከሙባቸውን ንብረቶቻቸውን ላጡ ተቋማትና ግለሰቦች፣ ለሆቴሉ ቤተኞች፣  በተለይም የማንነቱ ምስክርና ታሪክ የሆነውን ቅርስ ላጣው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መጽናናትን ተመኘሁ!!
መልካም ሰንበት!!


Read 13038 times