Print this page
Monday, 05 January 2015 08:14

ነቢዩ መሐመድና እሥልምና

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(16 votes)

ዛሬ ሠለላ ወአሌ ወሠላም (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁንና) የነቢዩ መሐመድ አንድ ሺህ አራት መቶ አርባ አራተኛው ልደት ወይም መውሊድ ነው፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም በሚገኙ ቢሊዮን ህዝቦች ዘንድ ከፍ ባለ ቅድሥናና ንፅህና በተመላ ክብረ ድምቀት በአምልኮና በደስታ ተከብሮ ይውላል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ዳር እስከ ዳር፡- ሙስሊም ወዳጅ የሌለው ክርስቲያን፤ ክርስቲያን ወዳጅ የሌለው ሙስሊም ስለሌለ እና በታሪካዊና መለኮታዊ ስረ መሰረት መነሾነት ኢትዮጵያና እስልምና የፀና ፍቅር ህልውና አፅንተው የኖሩ የዘለቁ በመሆናቸው ምክንያት ይህ ክብረ በዓል ለመላው ኢትዮጵያውያን የተለየ ትርጉም አለው፡
ኢትዮጵያውያን ካልነኳችሁ … እንዳትነኳቸው … ነው ያሉት ነቢዩ መሀመድ፡፡
I am a hidden Treasure, I like to be discovered, that is why I create creation … ይላሉ ነቢዩ ስለ አላህ ክብርና ታላቅነት የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪና የሁሉም በጎ ነገር መገኛ መሆኑን ሲገልፁ፡- እኔ የተሰወረው ፀጋና በረከት መዝገብ ነኝ፤ እገለጥ ዘንድ እወድዳለሁ፤ ፍጥረታትን ሁሉ መፍጠሬም ስለዚህ ነው….
በዚህች ምድር ላይ ለስልሳ ሁለት ዓመታት በህይወት የኖሩት ነቢዩ መሐመድ፤ ከልጅነት እስከ እውቀት ከነቢይነት እስከ ታላቅ አመራር ባለቤትነት … እጅግ የከበረና የበለፀገ፣ የተቀደሰና በፀጋ ብዛት የታፈረ ታላቅ ሠብዕና ነው የነበራቸው፡፡ በማንም በሌላ ሰው ላይ የማይታይ በሁለንተና ሁሉን ወደሚችል ህያውና ዘላለማዊ ወደሆነ አንድ አምላክ የማንነት ባህሪ ያደገና የበለፀገ፣ ከመወለድ በፊት የሰፈነ ከላይ የተቀዳጁት ታላቅ ሠብዕና፡፡ አምላክ ገና ከመወለዳቸው አስቀድሞ ለቢሊዮን ህዝቦች መንፈሳዊና አእምሮአዊ አርነት፣ አባትነት፣ መሪነትና ነቢይነት ያሰናዳቸው፤ በሚደነቅ ብርሀን፣ በታፈረ ክብር፣ በቅድስናና በግርማ በሞገስ የሞላቸው ታላቅ ሠብዕና፡፡ አርባ ዓመት ሞልቶአቸው የነቢይነት ጥሪ በብርሃን ግልፀት ከመከሰቱ በፊት ጀምሮ በህፃንነታቸው ሳይቀር የታላቅነት ክብር የሚታይባቸው ታላቅ ሠብዕና … ናቸው ነቢዩ መሐመድ፡፡
የዚህች ዓለም በጎነት የታነፀው በሁለት እሴቶች ነው፡፡ በአንድ ታላቅ እሴት፤ እና በአንድ ታናሽ እሴት፡፡ ታላቁ እሴት፡- የሁሉን ቻዩ አምላክ የፀጋ ሥጦታዎች እሽም ነው፡፡ ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች የለውም ይላል መፅሀፍ፡፡ ፍፁምና በጎ ስጦታ ሁሉ ከላይ ከሰማይ ከብርሃናት አባት ነው፤ Every Good and Perfect gift is from the above, from the father, the father of the heavenly light does not change like a shifting shadow. ታናሹ እሴት፡- በየዘመናቱ በህብረተሠብ ውስጥ የሰረፀ ስልጡንና ታላቅ አስተሳሰብ ነው፡፡ በአጭር አቀራረብ አንድ ሰው የተሰራው ከሁለት እሴት ነው፡- ከአምላክና ከህብረተሰብ፡፡ የህብረተሰብ ሁለንተናዊ ዕድገትና ግንዛቤ ደረጃ ደግሞ ከጥንት እስከ ዛሬ በውስጡ ሲሰለጥኑ በኖሩት ታላላቅ አስተሳሰቦች ተስሎና ተመጥኖ እዚህ ደርሷል፡፡
በአያሌ ሺህ ዘመናት የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የተከሰቱ ታላላቅ አስተሳሰቦች የፈለቁት ከሁለት የልቀት ማህፀኖች ነው፡፡ ከሃይማኖትና ከሣይንስ የልቀት ማህፀኖች፡፡ ሃይማኖት የፍልስፍና ከፍተኛው ደረጃ ብቻ ሳይሆን መለኮታዊና መንፈሳዊ የብርሃን እመርታ እና ከፍታ ጭምር ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ልክ፡- Human Philosophy and Devine Philosophy (Devining) እንደሚሉት ነው በሰብአዊ ፍልስፍና እና በመለኮታዊ ፍልስፍና እመርታ መሃከል ያለው የከፍታ ልዩነት፡፡ በአጭሩ በዚህ ዘመን የሚኖረው ህብረተሰብ ግንዛቤና ስልጣኔ፣ አኗኗሩና ሁለንተናዊ ዕድገቱ የበለፀገው በሃይማኖትና በሳይንስ አላባዎች ወይም (Elements) ነው፡፡
ዋነኞቹ ሥልጡን፣ ቅዱስና ክቡር የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮዎች፤ በሶስት ያህል ዓበይት ቅዱሳን መፃህፍት ውስጥ ታሽመዋል፡፡ ቅዱስ ቁርዓን (The Holly Quran) ከአምላክ የወረደው ወይም በብርሃን ግልፀት የበራው ዋናውና ታላቁ የእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ መፅሀፍ ነው፡፡ ሀድስ ወይም ሱናህ (Hadith or Sunah) በነቢዩ መሐመድ ቅዱሥና ክቡር ታላላቅ አባባሎች የተመላ ነው፡፡ ሸሪያህ ወይም የካነን ድንጋጌ (Shariah or Cannon Law) በጎና ሥልጡን፤ ቅዱስና ክቡር ፍትሀዊና ትክክለኛ … ከፍ ያለ የሞራል ደረጃና በጎ ምግባር ያለው ኢስላማዊ አኗኗርን ጭምር የሚገልፅ የእስልምና ሃይማኖት ቅዱሥ መፅሐፍ ነው፡፡ በቅድስና የታፈረ በሥልጡን ምግባር የከበረ … የሙስሊም ግለሰብና ህብረተሰብ አኗኗር እንዴት መሆን እንደሚገባው በዚህ ቅዱሥ መፅሐፍ ውስጥ ሠፍሮ ይገኛል፡፡
የሂንዱዎች ብሀቫጋድ ጊታ፣ የአይሁድ ታልሙድ ወይም ቶራህ የዞራስቴሪያን አቬዳስ፣ የቡድሂስቶች ፒታካሥ፣ የክርስቲያኖች መፅሀፍ ቅዱስ የሙስሊሞች ቅዱሥ ቁርዓን፣ የባሃኢዎች ኪታብ አል አቅዳሥ፣ የባቢዎች ባያን፤ የማናቸውም ሃይማኖት ዓቢይ ቅዱሳን መፃህፍት በሁለት መንገዶች የመመሳሰል ወይም የመቀራረብ ባህሪ አላቸው፡፡ አንደኛው መመሳሰል፡- ቃል በቃል ነው፡፡ ሌላኛው መመሳሰል ወይም መቀራረብ ደግሞ፡- የፍሬ ሃሳብ ወይም የፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት መፍለቂያና መገኛ ማህፀናቸው አንድ ስለሆነ ነው፡፡ ታላላቅ ቅዱሳን መፃህፍት ሁሉ የተፃፉት በመነካትና በመገለጥ ነው፤ በኢንስፓይሬሽንና በሪቨሌሽን፡፡ እውን የሆኑበት ሥፍራ እና ዘመን፣ መልዕክተኛቸውና ነቢያቸው የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ ምንጫቸው አንድ የቅድሥና ማህፀን ነው፡፡ እርሱም፡- ህያውና ዘላለማዊ ሁሉን የፈጠረ ሁሉን የሚችል አንዳች የማይሳነው … አንድ አምላክ ነው፡፡
በሙስሊሞች አላህ፣ በክርስቲያኖች እግዚአብሔር፣ በሂንዱዎች ብራህማ፣ በየይሆዋ ምሥክሮች ያህዌይ ወይም ጆሆቫ… ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ የከበሩ መጠሪያ ሥሞች ቢሆኑም፤ አምላክ ግን ለሁሉም የሁሉም አንድ አምላክ ነው፡፡ በእስልምና ብቻ እንኳን ዘጠና ዘጠኝ ያህል የአምላክ መጠሪያ ሥሞች አሉ፡፡ በክርስትናም በርካታ የአምላክ መጠሪያ ሥሞች አሉ፡- ኤልሻዳይ፣ አዶናይ፣ ያህዌይ፣ ዮሆዋ፣ ጆሆቫ … የሚሰኙትን የመሳሰሉ፡፡ በሌሎች ሃይማኖቶችም እንዲሁ አያሌ የአምላክ መጠሪያ ስሞች አሉ፡፡ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያሉ እነዚህ ሁሉ የአምላክ ስሞች የሚገልፁት ባህሪውን ነው፡፡ ይሁንና የእነዚህ ሁሉ የከበሩ መጠሪያ ሥሞችና ባህሪ ባለቤት የሆነው፡- እርሱ አንዱና ብቸኛው አንድ አምላክ ነው፡፡ አንድን ታላቅና የሚደነቅ የብርሃን አካል ከተለያየ አቅጣጫ ማየት፤ ወይንም አንድን ታላቅና የሚደነቅ የብርሃን አካል በተለያየ አኳኋን ማየት … እንደማለት ነው፡፡
ሙስሊሞች፡- አላህ ወአክበር! አሸሀዷና ላ ኢላህ ኢለላህ ወአነ መሀመድ ረሡለላህ፤ ሢሉ፡- አላህ ታላቅ አምላክ ነው፤ እርሡ አንዱ እና ብቸኛው አምላክ ነው፤ መሐመድም የእርሱ መልእክተኛ፤ ማለታቸው ነው፡፡ እንዲሁም ከቅዱሥ ቁርዓን አልፋቲኻኽ ወይም The Opening [መክፈቻ (መግቢያ)…] ከሚለው ሱራህ ወይም ምዕራፍ፤ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ፊታቸውን ወደ ቂልባ (መካ ቅዱስ ካዕባን) አዙረው በቀን አምሥት ጊዜ ዕለታዊ ፀሎት ሲያደርሱ፡- … Thee (Alone) we worship; Thee (Alone) we ask for help. Show us the straight path; The path of those whom thou hast favoured … እርሱን ብቻውን ያለውን አንድ አምላክ እናመልካለን፤ ልበ ቅኖች ሁሉ ሄደውበት የተጠቀሙበትን ቅንና ቀና የሆነውን (ቀጥተኛ) መንገድ ያሳየን ዘንድ ከእርሱ ብቻውን ካለውና ብቸኛ አንድ አምላክ ከሆነው እርዳታን እንጠይቃለን… ይላሉ፡፡ ክርስቲያኖች፡- ጎዶሊያስ ሲሉ፤ እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነው! ማለታቸው ነው፡፡ አላህ ወአክበር! በክርስቲያናዊ አገባብ ሲታሰብ ጎዶሊያስ ማለት ነው፡፡ አላህ ታላቅ አምላክ ነው! እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነው! ሁለቱም ለአንድ ከፍተኛ መለኮታዊ አካል የተሰጡ ክብሮች ናቸው፡፡ ባሃኢዎች ሰላምታ ሲለዋወጡ፡- He is the most Glorious፤ እርሱ ከተከበሩት ሁሉ በላይ እጅግ የከበረው ነው፡፡
የጥበቡና የዕውቀቱ አድናቂዎች The beloved master (ተወዳጁ መምህር) የሚሉት ሊባኖሳዊው ሊቀ ጠቢብ ካህሊል ጂብራን፤ ሃይማኖቶች የእግዚአብሄር አንድ እጅ ብዙ ጣቶች ናቸው… የሚል ዝንባሌ አለው፡፡ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ፡- Different direction, But the same target ብሎ ያምናል፤ የተለያየ አቅጣጫ ነገር ግን አንድ ግብ… ለማለት፡፡ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በጥንታዊቱ ፋርሥ ወይ ፐርሺያ በአሁኒቱ ኢራን የኖረው የሱፊው ቅዱስ ሊቀ ትጉኋን ጀላሉዲን ሩሚ፡- እግዚአብሔርን በተራሮች ከፍታ፣ በሸለቆዎች ጥልቀት፣ በአይሁዶች ምኩራብ፣ በሙስሊሞች መስጊድ በመካ ቅዱስ ካዕባን፣ በክርስቲያኖች ቤተ መቅደስ፣ በጥንታዊው የሂንዱዎች ፓጎዳስ … ፈልጎ በመጨረሻ የሚያገኘው በገዛ ራሱ ልብ ውስጥ ነው፡፡ በገዛ ራሴ ልብ በማደሪያው በፀባኦቱ … አገኘሁት ይለናል፡፡
በመሰረታዊ አስተምህሮ (Doctrine) ከሌሎች ሃይማኖቶች ይልቅ፡- እስልምና ከክርስትና፣ ሂንዱኢዝም ከቡድሂዝም … ይቀራረባሉ፡፡ ለምሳሌ ሙስሊሞችም ክርስቲያኖችም በገነትና በሲኦል ያምናሉ፡፡ ልዩነቱ የቃል ነው እንጂ የመሰረተ ሀሳብ አይደለም፡፡ ሂንዱዎችና ቡድሂስቶች ደግሞ፡- ካርማ ሪንካርኔሽን እና ኒርቫና የተሰኙ ዓበይት የአስተምህሮ ንድፈ ሃሳቦች አሏቸው፤ እንጂ በገነትና በሲኦል አያምኑም፡፡ እነዚህ ሶስት ያህል መሰረታዊ የአስተምህሮ ንድፈ ሀሳቦች ቤት ሙሉ መፅሀፍ ሊያፅፉ ይችላሉ፡፡ በአጭሩ ግን ሪንካርኔሽን፤ በሰው፣ በእንስሳ፣ በተክል አካላት አማካይነት የአንዲት ነፍሥ ተደጋግሞ መወለድ ነው፡፡ የዚህች ነፍስ ተደጋግሞ መወለድ የሚያበቃው ኒርቫና ዕድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ ነው፡፡ ኒርቫና ጥንቅቅ ያለ ብቃትና የሀሴት ጫፍ ነው፡፡ ካርማ ይህቺ ተደጋግማ የምትወለድ ነፍስ ለሰራችው በጎ ነገር ተደጋግማ በተወለደችባቸው ጊዜያት ሁሉ የምታገኘው ወሮታ፤ ወይንም (እና) ለሰራችው መጥፎ ነገር የምትከፍለው ዋጋ ነው፡፡ ከአንድ ሺህ ሃምሳ ዓመታት በፊት በፋርስ (ኢራን) የኖሩት ፐርሺያዊው አስትሮኖመር፣ ባለቅኔና ሊቅ ዑመር ኻያም በቴህራን ዩኒቨርሲቲ አጠገብ ሲያልፉ፣ ዩኒቨርሲቲው እየታደሰ፣ አህያ ድንጋይ ተጭኖ ወደ የትምህርት ተቋሙ ግቢ እንዲገባ ሲደበደብ ያያሉ፡፡ አህያው ወይ ፍንክች፡፡ ዑመር ኻያም ቆይ አሉና፣ ለአህያው በጆሮው አንዳች ነገር አንሾካሾኩለት፡፡ በዚህን ጊዜ አህያው እየሾረ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ገባ፡፡ አህያ ነጂው ዑመር ኻያምን፡- “ምን ብለው ቢነግሩት ነው እንደዚህ እየሾረ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ መግባቱ …” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የሰባ አራት አመቱ አዛውንት ዑመር ኻያም ለአህያ ነጂው፡- “አየህ …” አሉት፡፡ “አየህ ይሄ አህያ፤ አህያ ሆኖ ከመወለዱ በፊት በቀድሞ የህይወት ዘመኑ የዚህ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ሆኜ ወደ ኖርኩበት ዩኒቨርሲቲ እንዴት ድንጋይ ተጭኜ እገባለሁ … ብሎ ነው በጅ አልል ያለህ፡፡ እኔ፡- ዛሬ አህያ ሆነህ ብትወለድም ነገ አገረ ገዢ ሆነህ ትወለዳለህ ስለው እንደምታየው እየሾረ ገባልህ …” አሉት፡፡
በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች ዋነኛ (ዓበይት) ቅዱሳን መፃህፍት፣ በመፅሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን መሃከል ብዙ መመሳሰሎች ወይንም መቀራረቦች መኖራቸውን የሚገልፁ ጥናቶች አሉ፡፡
በቅዱስ ቁርዓን ሱራሀ (ምዕራፍ) ሶስት፤ ሁለት (NJD) ላይ፡- “በጎና ክፉ የሆነውን ትለይበት ዘንድ የክርስቲያኖችን መፅሀፍ ቅዱስ፣ የአይሁዶችን ቶራህ የሰው ልጆች የመርሆ መመሪያ አድርጎ በብርሃን የገለጸው አምላክ፤ በእውነት የተመላውን መፅሀፍ (ቅዱስ ቁርዓንን) በብርሃን ገልፆልሃል ..” ተብሎ ተፅፎአል፡፡ He has revealed to you the Book with the Truth confirming the scriptures which preceded it for he has already revealed the torah and the Gospel for the guidance of men, and the distinction between right and wrong (Surah 3:2) NJD
በመፅሀፍ ቅዱስ የተለያዩ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ የተወሳው፡- አዳም፣ ኖህ፣ አብርሃም በቅዱስ ቁርዓን ሃያ አምስት የተለያዩ ምዕራፎች (ሱራህ) ሰባ ጊዜ ተደጋግመው ተወስተዋል፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የምናውቃቸው ይስሃቅ፣ ሎጥ፣ ዮሴፍ፣ ሙሴ በቅዱስ ቁርዓን ሰላሳ አራት ምዕራፎች (ሱራህ) ውስጥ ተፅፈዋል፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ብዙ ስፍራዎች ላይ ተደጋግመው ሲወሱ የምናያቸው ሳኦል፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስ፣ ኢዮብ፣ ዮናሥ በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ በተለያዩ ምዕራፎችና በተለያዩ ቦታዎች ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ ተፅፎ የሚገኘው የፍጥረታት አፈጣጠር ታሪክ፤ የመጀመሪያው ሰው አዳም ዝርያዎች አፈላለስና አሰፋፈር … በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ በአምስት ያህል ስፍራዎች ተፅፎ እናገኘዋለን፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ በስፋት የተወሳው የውኃ ጥፋት፤ እና የሰዶምና ጎሞራ ታሪክ፣ በቅዱስ ቁርዓን ስምንት ቦታዎች ውስጥ ተፅፎአል፡፡ እንዲሁም በመፅሀፍ ቅዱስ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ በስፋት የሚታወቁት ኢየሱስ (ኢሣ)፣ ቅድስት ድንግል ማርያም (መሪየም)፣ መጥምቁ ዮሐንስ እንደዚሁ በቅዱስ ቁርዓን ላይ ተፅፈው ይገኛሉ፡፡
“History of the Arabs” የተሰኘውን የመረጃ ምንጭ ዋቢ ያደረገው፡- Man Kind’s search for God የተሰኘው መፅሀፍ ነው፤ በክርስቲያኖች መፅሀፍ ቅዱስና በሙስሊሞች ቅዱስ ቁርዓን መካከል ያለውን መመሳሰልና መቀራረብ እንዲህ እንዳነበብነው በተጨባጭ መረጃ ቁልጭ ቅልብጭ አድርጎ ያስቀመጠው፡፡
በሂንዱኢዝም፡- ጃይኒ እና ሢኪ፤ በክርስትና፡- ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ ጆሆቫ ዊትነስ፤ የተሰኙ ሃይማኖታዊ ክፍሎች (sects) እንዳሉ ሁሉ፤ በእስልምናም ሱና እና ሻይት የሚባሉ ሃይማኖታዊ ክፍሎች (sects) አሉ፡፡ የሡና እና የሻይት ዋና ልዩነታቸው፡- የሰው ልጅ በተፈጥሮው በአድራጎቶቹ ሁሉ ያሻውን ለመምረጥ የምርጫ ነፃነት አለው የሚለው ነጥብ ነው፡፡
ይሄ ፅሁፍ ዛሬ የምናከብረውን የነቢዩ መሐመድ ልደት (መውሊድን) መነሻ በማድረግ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የአምላክና የብርሃን የልብ ወዳጅ እና የእስልምና ሃይማኖት አባትና ከሳች ለሆኑት ነቢያችን ክብር በልዩ ፍቅር የተሰጠ ነው፡፡ … ኢትዮጵያውያን ጥርሳቸው ነጫጭ፣ የትንፋሻቸው ጠረን ደስ የሚል፣ ቁጥቦች፣ ጨዋዎችና ጀግኖች .. ንጉሡ ፍትህ እማያጓድል፣ ህዝቡ እንግዳ የሚቀበል …፤ በማለት ላወደሱን ለወደዱን ላከበሩን ነቢዩ መሐመድ ክብር በልዩ ፍቅር የተሰጠ፡፡
ሰላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli. Deo. Gloria!

Read 12359 times