Monday, 05 January 2015 07:49

በቆሎ ጤፍን አይታ “አሁን እዚችም ሆድ ውስጥ እህል አለ?” ብትል፤ ጤፍ “ሁለታችንም ስንፈጭ ዱቄት ነን” አለች፡፡

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ወንድማማች ዝንጀሮዎች በአንዲት ዝንጀሮ ወዳጃቸው ይጣላሉ፡፡
አንደኛው ለሁለተኛው፤
“እንግዲህ እዚች ሚስቴ ዝንጀሮዬ ጋ ድርሽ እንዳትል” ይለዋል፡፡
ሁለተኛው፤
“አይ ወዳጄ እኔ ልልህ ያሰብኩትን ነው አንተ አሁን ያልከው፡፡ የሀሳብ መመሳሰል ያስገርማል፡፡ ዞሮ ዞሮ እዚች ሚስቴ ጋ ድርሽ ካልክ በራስህ ፈረድህ”
አንደኛው
“እንዴት?”
ሁለተኛው፤
“ሚስትነትዋ ያለጥርጥር የእኔ ነው፡፡ አርፈህ ተቀመጥ”
አንደኛው፤
“አርፈህ መቀመጥ ከቻልክ አንተው አርፈህ ተቀመጥ! አለዛ እንግዲህ እንዴት በቡጢ እንደማንገጫግጭህ ስታይ ዋጋህን ታውቃለህ!”
ሁለተኛው፤
“አንተ እኔን?”
አንደኛው፤
“አዎ አንተን ምናባክ እንዳትሆን ነው?”
ተጋጋሉ፡፡ ሁለቱም ለቡጢ ተቀራረቡ! ተሰነዛዘሩ፡፡ ሌሎች ች መጡና ከበቡዋቸው፡፡ ጩኸት በረከተ! የሠፈሩ አለቃ የሆነው የሁለቱ ወንድማማች ዝንጀሮዎች አባት መጣና ገላገላቸው፡፡
ሁሉም ፀጥ እርጭ አሉ፡፡
አባት፤
“እሺ የፀቡ መንሥዔ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
አንደኛው፤
“ሚስቴን እየነካ አስቸገረኝ”
ሁለተኛው፤
“እኔንም ሚስቴን እየነካ አስቸገረኝ”
አባት፤
“ሁለታችሁም ስለአንዲት ዝንጀሮ ሴት ነው የምታወሩት?”
አዎን አሉ ሁለቱም፡፡
“እንግዲያው” አለ አባት “ይቺ ዝንጀሮ ትጠራና ትምጣ” አለ፡፡
ዝንጀሮይቱ ተጠርታ መጣች፡፡
አባት፤   
“ይሄኛውም ልጄ የአንቺ ባል ነኝ ይላል፡፡
ይሄኛውም ልጄ የአንቺ ባል ነኝ ይላል…የትኛው ነው ትክክለኛ ባልሽ?”
ዝንጀሮይቱ ራሷን ደልደል አድርጋ ተቀመጠችና፤
“ጌታዬ፤ ከእነዚህ ልጆችዎ አንዱ እንኳ ዕውነተኛ ባሌ ቢሆን ከእኔው ጋር እቤቴ ተቀምጦ ያገኙት አልነበር? አርፎ የተቀመጠ ልጅ ኖሮዎት ያቃል?” ስትል መልሷን በጥያቄ አጠቃለለች፡፡
አባት፤
“እግዜር ይስጥሽ ያቺንም ያቺንም እየነካኩ ባል ነኝ ማለት አቋም የለሽነት ነው፡፡ አሳዳጊ የበደለው ልጅ ማለት የእኔ ልጆች ናቸው!! አንቺ ሂጂ፡፡ እኔም ልጆቼን ልሰብስብ” አሉ ይባላል፡፡
*   *   *
በማናቸውም የህይወት ዘርፍ ውስጥ ምግባረ - ብልሹ መሆን የአስተዳደግን ጉድለት ያሳያል፡፡ የአስተዳደግ ጉድለት ግብረገብነትን፣ ዕምነትን፣ ትምህርትን የሚመለከት በመሆኑ በአብዛኛው ከባህል ጋር ቁርኝት ያለው ነው፡፡ ምግባረ - ሠናይ መሆንም እንደዚሁ እንደ ባህሉ፣ እንደአስተሳሰቡ፣ እንደ አኗኗሩ የሚዳኝ ነው፡፡ በየሥራ መስኩ የምናየው የሰዎች አኳኋንም እንደየአስተዳደሩ የሚመዘን ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡
የሥራ - ዲሲፕሊን፣ የሥራ ፍቅር፣ ለሥራውም ለህሊናም ታማኝ መሆን፣ የኃላፊነት ስሜት ወዘተ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በሀገራችን የመልካም አስተዳደር ጉድለት ከሥራ ባህሉና ከፖለቲካው ተፅዕኖ ጋር በተሠናሠለ መልኩ እግለሰቦች አስተዳደግ ጉድለት ድረስ የተለጠጠ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከተቋማዊ አቅም ይልቅ ግለሰባዊ አቅም አይሎ ይታያል፡፡ አሳዳጊ - የበደለው ሆኗል እንደማለት ነው፡፡ በዚሁ ላይ የሙስና እጀታ ሲሠራለት በደምባራ  በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ሆኗል፡፡ ይህንኑ በውል ለመነጋገርም ሌላ ሙስና ውስጥ መዘፈቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ ሆኗል፡፡
ፓቮ ፒልካነን የተባለ ሐያሲ፤
“ከሰው ልጅ በርካታ ችግሮች ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚይዘው ስለችግሮቹ ለማውራት አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረው የነበረው ደግመ ጥበብ ነው” ይለናል፡፡ ጥበብ የኮሙኒኬሽን ቱባ መሣሪያ ነው እንደማለት ነው፡፡ የአንድ ህብረተሰብ መንፈሣዊ ዕሴት መገለጫ ጥበብ ነው፡፡ ይህ ጥበብ ዕፁብ፣ ክቡርና ንፁህ ዋጋ ያለው ሲሆን ዕውነተኛ ማንነትን ቁልጭ ንጥር አድርጐ ያሳያል፡፡ ያልታየውን ይገልጣል፡፡ ዕሙናዊውን ህይወት ያፀኸያል፡፡ የህብረተሰቡ ማህበራዊ ስነልቡና ሲነክትም ቀና ብሎ ጠቋሚው ጥበብ ነው፡፡ ለህብረተሰብ በጐ በሆነ ገፁ ያፀኸያል፡፡ ይህን ንፁህ ጥበብ ሰውንና ህይወቱን ከመግለፅ አልፎ የፖለቲካ ቅብ ለመቀባት ከተሞከረ ግን ይበረዛል፡፡ ኦርጅናሌነቱን ያጣል፡፡ እንደተቀባው ቅብ ያለ ቀለም እየያዘ የእስስት ጠጨባይ ያመጣል፡፡ ህይወት እንድትፈስ በተፈቀደላት ተፈጥሮአዊ ሂደት መሄዷ ቀርቶ በግድ በፒንሣ ተጠምዝዛ የመሄድ ያህል ጫና ይበዛባታል፡፡ የሀገራችን የጥበብና የጥበብ ባለሙያ ሁኔታ በዚህ መልክ ሊጤን ይገባል፡፡ የጥበብ ባለሙያ መናቅ ጥበብን መግደል ነው፡፡ እርግይ እንደጠባይ ዘርፉ ከጥንተ - ፍጥረቱ ፖለቲካዊ ቃና ያለውም ጥበብ አለ፡፡ ይሄ ለፖለቲካዊ ህይወት መገለጫ ብቻ ነውና በፖለቲካ ሥነ-ውበትና ቃለ-ኃይል ላይ የሚንተራስ ይሆናል፡፡ ከመግባቢያነት አልፎም መቀስቀሻ ዓላማን ማራመጃ ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ጥበብ ችግር ፖለቲካው ትኩሳት ካበቃ ሽባ ሆኖ የመቅረት ዕጣ ፈንታው ነው፡፡ ስለዚህ ቀድመን የገለፅነው ዓይነቱ ንፁህና ኦርጅናሌ ጥበብ የአብዛኛው የጥበብ ማህበረሰብ መናኸሪያና ዘላቂነት ያለው ነው፡፡ የህብረተሰብን ንቁ ተሳትፎ፣ መንፈሳዊ ልሳን የሚከፍትለትም ንፁህ ጥበብ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ጥበብ መንከባከብና ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ጥበብን ማሳደግ የፈጠራ ኃይልን፣ አዲስ የመፍጠርን ባህል ማበልፀግ ነው፡፡ ጥበብ እንደፖለቲካ መፈክር ለጊዜያዊ ግብ ብቻ የምናውለው መሪ ቃል አይደለም፡፡ የፖለቲካ ዲኮሬሽንም፣ ቀለምም አይደለም፡፡ እንደዲፕሎማሲ ነገረ - ስራ የሆድን በሆድ ይዞ አፍአዊ ማማለያ አይደለም፡፡ የጥበብ ሰውን መውደድ፣ ማበረታታትና ማሳደግ መሰረቱ መሆን ያለበት ይሄና ይሄ ዕሳቤ ነው፡፡ ባለፈው ስርዓት “ ኪነት ለመደቧ” ስንል ከርመን አሁን ደግሞ “ ኪነት ለወገኗ” እንዳንል መጠንቀቅ ይገባናል
“የጥበብ ሰው ህሊናውን የተነጠቀ ዕለት አለቀለት” ይላሉ የጥበብ ሊቃውንት! አንድን የጥበብ ሰው ከህሊናው ውጪ እንዲጓዝ ካደረግነው ጥበቡን በንቀት ዐይን ማየታችን ነው፡፡ ፈጠራን ማቀጨጫችን ነው፡፡ በሞቀበት ዝፈን ማለታችን ነው፡፡ ጥበብን ስንንቅ የመወያያ ገመዳችንን መበጠሳችን ነው፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በጥበቡ መስክ መናናቅ ካለ ተያይዞ እረብ ማለት አይቀሬ ነው፡፡ “በቆሎ ጤፍን አይታ አሁን እዚችም ሆድ ውስጥ እህል አለ?” ብትል፣ ጤፍ “ሁለታችንም ስንፈጭ ዱቄት ነን” አለች አሉ የሚለው ይሄንን ሁሉ ያካትታል፡፡

Read 6986 times