Monday, 29 December 2014 07:52

የደርግ ዘመን የፈጠራቸው ቃል ግጥሞች

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(14 votes)

    ስነቃል (Oral literature) የሰው ልጅ ራሱን ከሚገልጥባቸው፣ ስሜቱን ከሚነግርባቸውና ማንነቱን ከሚቀርስባቸው ባህላዊ እሴቶች አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ማህበረሰብና ስነቃል ያላቸው ቁርኝት እጅጉን ጥብቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአንድን ማህበረሰብ ባህላዊ እሴቶች ማጥናትና መረዳት ማህበረሰቡን ማወቅ ነው የሚባለው፡፡  አይነቱና መጠኑ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ቢለያይም ስነቃል የሌለው ማህበረሰብ የለም፡፡
የጽሑፌ ማጠንጠኛ ስነቃል፣ ከስነቃልም (በቅርጽ ግጥማዊ የሆነው) ቃል ግጥም (Oral poetry) ነው፡፡ ትኩረቴም በደርግ ዘመን በስርዓቱ ላይ በተቃውሞ የተነገሩት (በድጋፍ ከተነገሩት ይበዛሉና) ቃል ግጥሞች ናቸው፡፡ በዚህም በሰፊው የተነገሩ ጥቂት ቃል ግጥሞችን “የዘመኑን እውነት” (ግጥሞቹ የተነገሩባቸው ግፊቶች ዘመኑ ውስጥ አሉና) እማኝ አድርጌ እቃኛለሁ፡፡ ምክንያቴም በአንድ የአገዛዝ ዘመን የተነገሩ ስነቃሎች የአገዛዙን መንፈስ፣ የወቅቱን ማህበረሰብ አስተሳሰብና ስነልቡና እንዲሁም ለአገዛዙ የነበረውን ምላሽ በጉልህ ያሳያሉ ብዬ ማመኔ ነው፡፡ ነገሬን እንዲህ አስረድቼ “ይለፍ” አልነፈገምና ልቀጥል፡፡
ወታደራዊው የደርግ መንግስት የንጉሡን ስርዓት “አስወግዶ” ስልጣን በመያዝ ይህቺን ሀገር ለ17 ዓመታት ማለትም ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም አስተዳድሮአል፡፡ በእነዚህ ዓመታትም በሀገሪቱ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ከለውጦቹና ክንዋኔዎቹ መካከል ስርዓቱ ቀድሞ ያቀነቀነው የመሬት ለአራሹ አዋጅ፣ የእድገት በህብረት ዘመቻ፣ የሠፈራ ፕሮግራም፣ ቀይ ሽብር፣ ብሔራዊ ውትድርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በዘመኑ የነበረው ማህበረሰብም እንደቀደሙት ዘመናት አባቶቹ ሁሉ እነዚህና ሌሎች ከስርዓቱ መለወጥ ጋር ተያይዘው የመጡ ክስተቶች ያሳደሩበትን የአዎንታም ይሁን የአሉታ፣ የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ስሜት በስነቃል፣ ከስነቃልም በቃል ግጥም ሲገልጽ ኖሮአል፡፡ በደርግ ዘመን የተነገሩት ቃል ግጥሞች በወቅቱ በመንግስት የተከወኑ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ትኩረቴ በተቃውሞ የተነገሩት ላይ መሆኑን ቀድሜ አትቻለሁና ወደነሱ ልለፍ፡፡ ከእነሱም በዘመኑ “ጉልህ” ክስተቶች በነበሩት ማለትም “ቀይ ሽብር”፣ “ሠፈራ” እና ጦርነት ላይ የተነገሩትን ላንሳ፡፡
በደርግ ዘመን በነበረው የ“ቀይ ሽብር ዘመቻ” ሳቢያ የበርካታ ዜጎች (በተለይ የወጣቶች) ህይወት አልፎአል፡፡ ይህ “ዘመቻ” በመላው ሀገሪቱ ሊባል በሚችል መልኩ የተካሄደ ሲሆን በዘመቻውም የጠፋው የሰው ሕይወት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነው፡፡ በዘመኑ የነበረው ማህበረሰብም “ዘመቻው” ያደረሰውን ጉዳትና ጉዳቱም የፈጠረበትን ሀዘንና ስሜት በተለያዩ የስነቃል አይነቶች በተለይም በቃል ግጥም ገልጾአል፡፡ በ“ቀይ ሽብር” ላይ ከተነገሩ ቃል ግጥሞች መካከል በጎንደር ከተማ የተነገሩትን ሁለት ቃል ግጥሞች እንመልከት፡፡
መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም
የዛሬን ማርልኝ የነገን አልወልድም
(ይህንን ማርልኝ ከእንግዲህ አልወልድም)
ግጥሙ መላኩ ተፈራ ጎንደርን “ያስተዳድር” በነበረበት ዘመን የተነገረ ነው፡፡ መላኩ በጎንደር በርካታ የ“ኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ” (ኢህአፓ) አባላት የሆኑ ወጣቶች “እንዲገደሉ” እንዳደረገና “የፈለገውን የመግደልና የፈለገውን የማዳን” ስልጣን እንደነበረው ይነገራል፡፡ በዚህ ወቅት ነው አንዲት ልጇ ሊገደልባት የነበረች እናት ይህንን ግጥም የተናገረችው ይባላል፡፡ (ይባላል ነው!)
በግጥሙ ሴቲቱ “ማንም ከልካይ የሌለበትንና የፈለገውን የሚያደርገውን” መላኩን “የእግዜር ታናሽ ወንድም” አድርጋዋለች፡፡ ከዚህም ሌላ “ይህንን ማርልኝ” እንጂ “ከእንግዲህ አልወልድም” በማለት ሌላ ልጅ ላለመውለድ ቃሏን እስከመስጠት ደርሳለች፡፡ ይህ ግጥም የዘመኑ ማህበረሰብ በዘመቻው የደረሰበትን ጉዳትና ሰቀቀን በሚገባ ማሳየት የሚችል ነው፡፡ በዚያው በጎንደር (ቀይ ሽብር ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ከተሞች አንዷ ጎንደር መሆኗን ልብ ይሏል፡፡) የተነገረ አንድ ሌላ እንጨምር፡፡
የማራኪ ጎመን አልበላም እርሜ ነው
ያባሳሜል ጎመን አልበላም እርሜ ነው
 እሱ የበቀለው በወጣቶች ደም ነው፡፡
ሁለቱ (የተሰመረባቸው) በጎንደር በ“ቀይ ሽብር” የተገደሉ ወጣቶች በጅምላ ይቀበሩባቸው የነበሩ ቦታዎች ናቸው፡፡ ይህንን የሚያውቀው ሀገሬው በሁኔታው የተሰማውን የመረረ ሀዘን ፊት ለፊት ሳይሆን አዙሮና አጠይሞ በግጥሙ ገልጾአል፡፡ የሀገሬው ጉዳይ ወይንም ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ስለሚበላው ጎመን አይደለም፡፡ እሱን ያስቆጨውና ያስመረረው በሁለቱ ቦታዎች ላይ የፈሰሰው የወጣቶቹ (የልጆቹ) ደም ነው፡፡ ሆኖም ይህንን ድርጊት በግልጽ ለመቃወምና ለመውቀስ ፍርሀት ስለነበረበት ጎመንን ጠርቶ ቁጭቱን ገልጾአል፡፡
ግጥሞቹ በዘመኑ የነበረው ማህበረሰብ በቀይ ሽብር የደረሰበትን ፍራት፣ ጉዳትና ሰቀቀን እንዲሁም ለክስተቱ የነበረውን ምላሽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ግጥሞቹ የተነገሩት በጎንደር በነበረው ሁኔታ መነሻነት ነው ቢባልም የዘመቻው ጉዳት በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም የነበረ በመሆኑ የምንደርስበት መደምደሚያ የተለየ አይሆንም፡፡
“ሠፈራ” ላይ የተነገሩ ቃል ግጥሞችን እንመልከት፡፡ “የሠፈራ ፕሮግራም” በደርግ ዘመነ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ተካሂዶአል፡፡ በዚህም በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች በተፈጠረ “የተፈጥሮ ችግርና ድርቅ” ምክንያት መንግስት የአንዳንድ አካባቢ ነዋሪዎችን ከነበሩበት ቦታ አንስቶ የተሻለ ነው ወደአለው ቦታ እንዲሠፍሩ አድርጎአል፡፡ የሠፈራው ተገቢነት አከራካሪ ቢሆንም ማህበረሰቡ “እትብቴ ተቀብሮበታል!” ከሚለውና ተኩሎና ተድሮ ልጆች ካፈራበት ርስቱ ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ በመሆኑ፣ ተነስተህ ወደ ሌላ ቦታ ሥፈር ሲባል የደረሰበት የስነልቡና እና “የማንነት ጥያቄ” ቀውስ ቀላል አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ግን በአንድ በኩል በልቶ ህይወቱን ለማቆየት ከነበረው ተስፋና ጉጉት፣ በሌላም በኩል በመንግስት ተፅእኖ የኖረበትን መሬት ለቅቆ ወደተባለው ቦታ ሄዶ ሠፍሮአል፡፡ ሠፈራው ያሳደረበትንም ከቀዬው የመነጠል መሪር ስሜት በቃል ግጥሞች ገልጾአል፡፡ እንዲህ እያለ:-
የኮምሽን ስንዴ ጣዕሙ ጥሩ ነበር
ውለው እያደሩ ስፈሩ ባልነበር!
ግጥሙ ምንም እንኳን በወቅቱ በመንግስት ለማህበረሰቡ ይታደል ስለነበረው “የኮሚሽን ስንዴ” የሚናገር ቢመስልም ጉዳዩ ሠፈራው ነው፡፡ ማህበረሰቡ በየጊዜው ያላችሁበትን ለቅቃችሁ ወደ ሌላ ቦታ “ሥፈሩ” በመባሉ የነበረውን ተቃውሞ ግጥሙ በሚገባ ያሳያል፡፡ ሆኖም በወቅቱ ይህንን ተቃውሞውን በግልጽ ለመናገር የማይችል በመሆኑ (አሁን ይችላል አላልኩም!) ቃላዊ ሀብቱን ተጠቅሞ፣ ስለ ስንዴ ያወራ በመምሰል በሠፈራው ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልጾአል፡፡
ምንድን ነው ሠፈራ ዶሮ ይመስል
ላከኝ ከጦር ሜዳ ከወንዶች ሰፈር
ይህ ደግሞ ከቀደመው ቃል ግጥም በከረረ መልኩ ማህበረሰቡ ለሠፈራው የነበረውን ተቃውሞ የገለጸበት ነው፡፡
 በግጥሙ የመጀመሪያ መስመር ላይ “ሠፈራ” ለዶሮ እንጂ ለሰው እንዳልሆነ/እንደማይሆን ያስረግጣል፡፡ ይህም “እኛ ሰዎች ሆነን ሳለ የዶሮ ያህል አሳንሰው እያሠፈሩን ነው” ወደሚል ትርጉም ያደርሰናል፡፡ ይህንን ልብ ብለን ወደ ሁለተኛው የግጥሙ መስመር ስናልፍ ግን የምናገኘው መልዕክት ከዚህም የመረረና የጠነከረ ነው፡፡ ማህበረሰቡ በግጥሙ መንግስትን “ከሰው አሳንሰህ እንደ ዶሮ ከምታሠፍረኝ ወደ ጦር ሜዳ ላከኝ” ብሎአል፡፡ በጦር ሜዳ ሞት አለ፡፡ ሆኖም እንደ ዶሮ ከመኖር ጦር ሜዳ ሄዶ መሞትን መርጦአል፡፡… ይህንን እዚህ ላይ ገተን በዘመኑ በነበረው የማያቋርጥ ጦርነት ላይ ወደተነገረው እንለፍ፡፡
የደርግ ዘመን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጊዜያት ከጦርነት የፀዳ ነበር ማለት ማበል ነው፡፡ በቀዳሚዎቹ የአገዛዙ ዓመታት ከሶማሊያ መንግስት ጋር ከባድና ብዙ ጉዳት ያደረሰ ጦርነትን አድርጎአል፡፡ እንዲሁም ከኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባሮችና ከወያኔ ሠራዊት ጋር የስልጣን ዘመኑ እስከሚያበቃበት የመጨረሻዎቹ ወቅቶች ድረስ ተዋግቶአል፡፡
 በእነዚህ ጦርነቶችም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ጦርነቱ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑም የደርግ መንግስት በተለይ በመጨረሻዎቹ ዓመታት “ብሔራዊ ውትድርና” በሚል ብዙ ወጣቶችን “አፍሶ” ወደ ጦር ግንባሮች ልኳል፡፡
ይህ ሁኔታ ልጁን ለተነጠቀው ማህበረሰብ እጅግ መራር ሀዘንን የፈጠረ በመሆኑ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ ስሜቱን በቃል ግጥም አውስቷል፡፡ ጦርነቱ ላይ የተነገረን አንድ ቃል ግጥም እንጥራ፡፡እንዴት ያል ዘመን ነው የዘመን ቆረንጮ
ወልዶ ለጦርነት ሰርቶ ለመዋጮ
በግጥሙ የመጀመሪያ መስመር ላይ ማህበረሰቡ ሆኖና ተደርጎ የማያውቅ ነገር በዘመኑ በመፈጸሙ ይህንን ሲወቅስ እንመለከታለን፡፡ በሁለተኛው መስመር ላይ በሚገኙት ሁለት ሐረጎች የምናገኘው መልዕክት ግን ሁለት ነው፡፡
ማህበረሰቡ የወለደውን ልጅ ጦርነቱ እየነጠቀው በመሆኑ ተስፋ ቆርጦአል፡፡ ሰው የሚወልደው ለጦርነት አይደለም፡፡ ለብዙ ሰዋዊ ዓላማዎች ነው፡፡
 ሆኖም ግን በወቅቱ ለነበረው ማህበረሰብ መውለድ ለጦርነት ሆኖ ተሰምቶታአል፡፡ በመሆኑም “ምናባቱ ባልወልድስ” እስከማለት አድርሶታል፡፡
 ሁለተኛው ሐረግ ደግሞ ማህበረሰቡ ለመስራትም ልቡ እንደሰነፈና ተስፋ እንደቆረጠ ያሳያል፡፡ በዘመኑ ማህበረሰቡ “ለእናት ሀገር” በሚል መዋጮ እንዲያዋጣ ይደረግ ነበር፡፡ በመሆኑም “ባልሰራስ፣ ቢቀርስ” በሚል ተስፋ ቆርጦአል፡፡
በሀገራችን በዘመነ ደርግ ስርዓቱ ላይ የተነገሩትን የተቃውሞ ቃል ግጥሞች አነሳሁ እንጂ በየዘመናቱና ስርዓቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቃል ግጥሞች ተነግረዋል፡፡ አሁንም ይነገራሉ! እነዚህ ቃል ግጥሞች ማህበረሰቡ ለየዘመኑና በዘመኑ ለነበረው ስርዓት የነበረውን ሁሉን አቀፍ ስሜትና ምላሽ የያዙ በመሆናቸው ዘመኑንና የወቅቱን ማህበረሰብ ስነልቡና የሚያሳዩ ህያው ምስክር ናቸው፡፡
ይህንን እየከተብኩ እንዲህ አሰብኩ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ እየተነገሩ ያሉ ቃል ግጥሞችስ ምን ይመስሉ ይሆን? በዘመናችን ቃል ግጥምን ሊያስነግሩ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡
 በርካታ! ስራ አጥነት፣ መልሶ ግንባታ፣ ውሃ ማቆር፣ የኑሮ ውድነት፣ ስደት፣ ምርጫና የፖለቲካ ውዝግብ… ሌሎችም ብዙ! ታዲያ ማህበረሰቡ ለእነዚህ ጉዳዮችና በአጠቃላይ ለአገዛዙ ያለውን ምላሽ በቃል ግጥሙ እንዴት ገልጾ ይሆን? ጊዜና አጋጣሚ ቢፈቅድ ሌላ ጊዜ እመለስባቸዋለሁ፡፡
መልካም ሰንበት!!

Read 11836 times