Monday, 29 December 2014 07:45

መሰላል ያላንሸራተተው ሁሌ ጫፍ የሚወጣ ይመስለዋል የህንዶች አባባል

Written by 
Rate this item
(10 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የውሃ ኤሊ የመውለጃዋ ጊዜ ደርሶ ኖሮ ከውሃው ወጥታ ወደ ባህሩ ዳርቻ ትሄዳለች፡፡ይቺ ኤሊ ቀስ እያለች በረጅሙ የአሸዋ መንገዷ ስታዘግም ሁለት ጓደኛሞች ያዩዋታል፡፡
አንደኛው ፤ “ይቺ ዔሊ ወዴት ነው የምትሄደው?” ይላል፡፡
ሁለተኛው፤ “የመውለጃ ጊዜዋ ደርሶ ይሆናል”
አንደኛው፤ “የመውለጃዋ ጊዜ ቢደርስ ወደ አሸዋው ምን ያስኬዳታል? መኖሪያዋ ውሃ ውስጥ ነው፡፡ እዚያው ወልዳ ተገላግላ እርፍ አትልም እንዴ?”
ሁለተኛው፤ “ለምን ውሃ ውስጥ እንደማትገላገል አላውቅም፤ የማውቀውና ሰዎች ሲሉ የሰማሁት ግን፤ ኤሊ የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ ወደ ባሕሩ ቅርብ ዳርቻ አይደለም የምትጓዘው፡፡ ከውሃው እጅግ እርቃ ወደማይታይ አቅጣጫ ነው የምትሄደው”
“ልጆችዋን እሩቅ ቦታ ሄዳ የምትገላገል ከሆነ፤ በኋላ እንዴት አድርገው ልጆችዋ ከሷ ጋር ይገናኛሉ? እናታቸው በባሕሩ ውስጥ መሆኗንስ እንዴት ያውቃሉ?”
ይህ ጥያቄ በጣም ውስብስብና በቀላሉ የሚፈታ ስላልሆነላቸው በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ጠቢብ ዘንድ ሄደው ሊጠይቁ ይስማማሉ፡፡
ጠቢቡ ቤት ሄደውም፤ “ጠቢብ ሆይ! አንዲት የውሃ ኤሊ አየን፤ ከውሃው ወጥታ ወደ አሸዋው ዘልቃ እርቃ ሄደች፡፡ በኛ ግምት የመውለጃዋ ቀን ደርሶ ይሆናል ተባባልን፡፡ ግን አንድ ጥያቄ አነሳን፡፡ ወልዳ ወደ ባሕር ስትመለስ ልጆችዋን ማን ያመጣላታል? መቼም ህፃናት ናቸውና አውቀው ወደ ባሕሩ አይመጡም፡፡ ደግሞስ ያን ያህል ሰፊ ባሕር ውስጥ እናታቸው የት ትኑር የት እንደምን ያውቃሉ” ሲሉ ጠየቁት፡፡ ጠቢቡም “የአምላክን ተአምር የምታደንቁት እነዚህን አይነት ጉዳዮችን ለመመርመር ስትችሉ ነው፡፡ ኤሊዋ ልጆችዋን የምትወልደው እንዳላችሁት ከባሕሩ ራቅ ያለ ቦታ ሄዳ ነው፡፡ እንዳላችሁትም ከተገላገለች በኋላ የባሕሩ ዳርቻ አሸዋ እንዲሞቃቸው እዚያው ትታቸው ነው ወደ ባሕሩ የምትመለሰው፡፡ ልጆችዋ እስኪጠነክሩ ድረስ እዚያው አሸዋው ላይ ይቆዩና ሰፊውን አሸዋ አቋርጠው ወደ እናታቸው ይመለሳሉ፡፡ የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ ያለ ጥርጥር በባሕሩ ውስጥ እናታቸው የቱ ጋ እንዳለች ያውቃሉ፡፡ ዋና አስገራሚ ነገር ግን ወደ ባሕሩ በሚመጡ ጊዜ መንገድ ላይ አደጋ መኖሩ ነው፡፡ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የኤሊ ጫጩት እየተመገቡ የሚኖሩ ወፎች አሉ፡፡ ከጫጩቶቹ መካከል በወፎቹ ከመበላት ተርፈው እናታቸው እቅፍ ውስጥ ለመግባት የሚችሉት ጥቂቶቹ የታደሉቱ ናቸው፡፡ ይህ የአምላክ ስርዓተ ተፈጥሮ ነው፡፡ ትላንት እንደዚያ ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም በአግባቡ ይቀጥላል፡፡” አላቸው፡፡
የፍጥረታትን ተዓምር እያደነቁ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡
***
በዓለም ላይ በዚህም ቢሉት በዚያም ከመሆን የማይቀር ነገር አለ፡፡ መንግስታት ይለወጣሉ፤ አገሮች ባሉበት ይቆያሉ፡፡ የሚሠሩ ያገኛሉ፡፡ ዳተኞች ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ፡፡ የሚጥሩ ዳር ይደርሳሉ፡፡ የተኙ ወደ ኋላ ይሄዳሉ፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ የሆነው ነገር አይቀሬ ነው፡፡ ከኤሊ ጫጩቶች መካከል ተርፈው ለእናታቸው የሚኖሩ ጥቂቶቹ ይሁኑ እንጂ ይኖሩ ዘንድ የተፈቀደላቸው የታደሉ ናቸው፡፡ ያልታደሉት ባጭር ይቀጫሉ፡፡ ይህ ህግ ሁሌም የሚኖር ነው፡፡ ሰው የሚሰራው ነገር ተጨማሪ ነው፡፡ ያም ሆኖ
“አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር”  ይላሉ ደራሲ ከበደ ሚካኤል፡፡ በዚህ ውስጥ የተቃራኒዎች አንድነትና ትግል ሁሌም አይቀሬ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ መግዛቱን ለመቀጠል ተገዢዎች የኛም ፓርቲ የገዢነት ቦታ ሊኖረው ይገባል በማለት እስኪሸናነፉና እስኪለይላቸው ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ፡፡
“ልምድን ከሩቅ ሆነህ አታየውም፤ ሲከሰት ግን መኖሩን ታውቃለህ” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ለመማር ዝግጁ የሆነ ባወቀው ይጠቀማል፡፡ አትማር ያለው ባወቀውም ይደነቁራል፡፡ በሀገራችን ብዙ ፓርቲዎች ተወልደዋል፡፡ ብዙዎች ሞተዋል፡፡ አንዳንዶች ቀንቷቸዋል፡፡ አንዳንዶች በአጭር ተቀጭተዋል፡፡ የሁሉም የጋራ ሀብት ግን ከኖሩት አለመማር ሆኖ ታዝበነዋል፡፡ አሸናፊው ድሉን ከማሸብረቅ በቀር የሄደበትን መንገድ ዳግመኛ ለመመርመር አይቃጣውም፡፡ ተሸናፊው ቂም በቀሉን ከማመንዠክ እና ጊዜ ከመጠበቅ በቀር ያለፈውን ሁኔታ አጥንቶ በወጉ ለነገ ለመዘጋጀት ከቶም ልቦና የለውም፡፡ ይህ ሀቅ ሁሌም ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚያጋጥመው እውነታ ነው፡፡ ትላንት በምርጫው አሸናፊ ነኝ የሚለው ወገን ለአሸናፊነት ሁሌም የታጨሁና ሁሌም የሚሳካልኝ ነኝ የሚለውን አስተሳሰብ የማይለወጥ እውነታ አድርጐ መውሰዱን አይን ካለን እናያለን፡፡ በአንፃሩ ትላንት በምርጫው ተሸናፊ የሆነው ወገን ደግሞ በመጭበርበር ተሸነፍኩ እንጂ ልክ ነበርኩ የሚለውን ሃሳቡን ሳይለውጥ አምስት አመት ይኖራል፡፡ በኢትዮጵያ ሠርጉ ካልደረሰ በርበሬ አይቀነጠስም ይባላል፡፡ አድፍጦ፣ አሳቻ ጊዜ መርጦ ለማነቅ ጀግና መባል አንዱና ዋነኛው የትግል ዘዴ በሆነበት ሀገር፣ የዲሞክራሲ እውንነት ሁሌም ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡
ያለ ዲሞክራሲያዊ መስተጋብር ህይወት የአዘቦት መንገዷን እንጂ የተለወጠ ጐዳና ወይም እግረ መንገድ እንኳ ልትቀዳጅ አይቀናትም፡፡ የትግሉን ሂደት ከማየት ይልቅ ስወለድም እንዲህ ነበርኩ ማለትም አጉል መመካት ነው ይሉናል አበው ጠበብት፡፡ እኛ ብቻ ነን ለዚህ ስልጣን የተቀባን የሚለው ሃሳብ ግዘፍ ነስቶ የምናየው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን ብለን እናማትብ፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በእውነትም ሆነ በውሸት ምርጫ ሲያሸንፍ “ፍፁም ስለሆንኩ አሸነፍኩ” የሚል አስተሳሰብ ውስጥ መዋኘቱ አይገርሜ ነው! ግቡን መምታቱ ያላጋጠሙትን አሊያም አጋጥመውት ያልዘገባቸውን መንሸራተቶችና መሰናክሎች ወይም ሰንካላ እድሎች እንዲረሳ የደረሰበት ወንበር ክፉ ንቀት ይሰጠዋል! ዛሬ እዚህ የደረስከው በሠራኸው ጥሩም፣ መጥፎም ነገር  ነው፡፡ የሚለውን ልብ አይልም፡፡ “መሠላል ያላንሸራተተው ሁሌ ጫፍ የሚወጣ ይመስለዋል” የሚለው ተረት ከላይ የተጠቀሰውን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
“ጥሩው ብቻ አይደለም እዚህ ያደረሰህ
መጥፎም ነው እኮ ያንተ ማንነትህ” እንደማለት ነው በግጥም ሲለገጥ፡፡  
Read 4791 times