Saturday, 27 December 2014 16:26

የእብዶች ሸንጎ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

    አፈጉባኤው የጫት ገረዊናውን እያነሳ የንግግር ማድረጊያውን ጉብታ መሬት እየደጋገመ ያጎነዋል። ለፓርላማው አባላቱ  ስለ ስብሰባው ፍሬ ነገር ሹክ ለማለት በእጅጉ እየተጣደፈ ነው። ጉሮሮውን በልቅላቂ የሀይላንድ ውሀ እያጠበ የመክፈቻውን ንግግር ጀመረ፤
“ከጊዜ ግሳንግስ ውስጥ ይህቺን ቅጽበት ብቻ ተውሰን እብዳታችንን ፊት መንሳት እንጀምራለን። ከእብደታችን ጋር ለመፋታት ስንዳዳ ማንገራገሩ ሊከፋብን ይችል ይሆናል፡፡ ማንገራገሩ ግን ግፋ ቢል አፍታን ነው የሚሻገረው። ጉባኤውን ከእብድ ጉባኤነት ልንታደገው ይገባል፤ ከተተመነለት የሰዓት ኮታ ውጭ ውልፊት የሚል ተሰብሳቢ ካለ ጫንቃችን ሊሸከመው ዝግጁ አይደለም።” አለ ጭንቅላቷ ከጣቱ መሀል የደረሰችን ኒያላ ሲጋራን በፍቅር እየማገ፡፡
ስብሰባው ከጅመሩ ያልተዋጠለት እብድ፤ የንግግሩን ቅድሚያ በጉልበት ወሰደ፤፡፡ በሱስ ካበደው ወገን ነው። ይህ ወገን የሽንጎውን ሲሶ ክፍል ይሸፍናል። እብዱ የያዘውን የብረት ቁርጥራጭ እያንኳኳ ልፍለፋውን ተያያዘው፤
“ገደብ፣ ክልከላህን ፊት ንሳና ፍሬነገርህን ሹክ በለን። ቆይ … ቆይ … ዘንግቼው … እንደውም ... ስብሰባውን ለምን በህሊና ጸሎት አንጀምረውም……”
“የህሊና ጸሎት ከእዚህ ምን ዶለው?” አፈጉባኤው በሀይለ ቃል እያበሻቀጠ የመልስ ምት ሰጠው
“ክቡር-አፈጉባኤ…….ይህንን ማዕረግ ተሸክመህ ለህሊና ጸሎት….እንግዳ መሆንህ …ደንቆኛል፤ ለማንኛውም… የአብራካችን ክፋይ የሆኑ ...በተከርቸም አባዜ የሚናውዙ… የእግረ-ሙቅ…ሲሳዮችን…. ለማሰብ ሁላችንም ከተንጋለልንበት እንነሳ” አለ በስሜት ወዲህ ወዲያ እየተወዛወዘ፡፡
ከተንጋለለበት የተነሳ እብድ ግን ማየት አልቻለም። በተሰብሳቢው ልግምተኝነት የተነሳ እብደቱ ሊያገረሽበት ከአፋፍ ላይ ደርሶ ተናነቀው ፤ከውስጥ ሱሪው ውስጥ የተጎመደች ሲጋራውን አውጥቶ አየር ላይ ለመለኮስ ይጣጣር ጀመረ፤ መለፍለፉን ሳያቋርጥ፡፡
“እናንተ ብሎ እብድ ፤ይሄኔ ለቀፈታችሁ ውትወታ ጥሞና ስጡ ቢሏችሁ በአደባባይ ላይ ትበዙ ነበር፤ ዝንተአለም ጎብጣችሁ ብታዘግሙ ግድ አይሰጠኝም፤ እኔ እንደሁ..አንድ ለራሴ አላንስም” በንዴት ስብሰባውን እረግጦ ተፈተለከ፤ግድ ያለው እብድ አልነበረም።
የጉባኤው አየር ሊረግብ አልቻለም። አየሩም የተሰብሳቢው መንፈስ ተጋብቶበት በላይ በላይ እያበደ ነው። የሚንሸዋሸው የፌስታል ድምጽ ከርቀት እየሰነጠቀ መጣ። የሚታይ ሰው  የለም። ድምጹ ግን እየቀረበ ነው። ትንሽ ሰከንድ ፈቀቅ እንዳለ ከድምጹ አቅጣጫ የተበጠሰ ኤርጌንዶ ነጠላ ጫማ ውስጥ የተቸረቸፉ የእግር ጣቶች ብቅ አሉ። ለጥቆ ቀርፋፋ ቀውላላ ሰው እንደ ጅብራ ተገተረ። ጅብራው በቀጣጠለው የላዉንደሪ ላስቲክ ውስጥ የጫት ገረባ፣’የመከኑ ሲጋራዎችና ክዳን አልባ የሀይላንድ ላስቲኮችን ሰብስቧል። ያዘለውን ኮተት ለፓርላማው ታዳሚዎች ከፈተላቸው። በሙሉ  ሰፈሩበት። ከቅራቅንቦው ብፌ የየፍላጎታቸውን ለመቃረም እጃቸውን ሰደዱ። ጅብራው በፌስታሉ ውስጥ ያሉት ኮተቶች የእብዶቹ ሲሳይ ሲሆኑ ደንታ ባይሰጠውም፣ በማሳረጊያው ላይ ግን  ለአንድ ነገር ስስት ያዘው:: የገነፈለ ብዕር ነበር፡፡ ብዕሩን ሊያጋፍፍ እጁን የዘረጋውን እብድ አፈፍ አደረገው፡፡ ጅብራው ለወረቀትና ለብዕር ነክ ነገሮች በሚሰጠው ክብር ከዘመኑ እብዶች ለየት ይላል፡፡ “ምሁር እብድ ነኝ” ብሎ ስለሚያስብ ሌሎችን በንቀት ነው  የሚመለከተው። በፈረንጅ አፍ ሲያወራ አላፊ አግዳሚው ሳይወድ በግዱ ቀልቡን ሰብስቦ ጆሮውን ያውሰዋል። ዛሬ እነዚህን የዘመኑ እብዶች ምን እንዳሰባሰባቸው ግር ተሰኝቷል። የገነፈለውን ብዕር ከደረቱ ላይ እንደለጠፈ ባለበት ተቸንክሮ ሁኔታውን ለመከታተል ወሰነ።
ብቸኛዋ የሴት እብድ ተወካይ እጇ ላይ የሚያንኮራፋ ጨቅላ እንደታቀፈች ብድግ አለች። የተኛውን ጨቅላ ላለመቀስቀስ በጣም በዝግታ ታንሾካሹካለች። ለጨቅላዋ ምቾት እብደቷም አንዳንዴ ታጋሽ ይሆናል። የተነሳችበትን ፍሬ ሀሳብ በሹክሹክታ ድምጽ እየሰነዘረች ነው። ንግግሯ ለእብዶቹ ሊሰማቸው ስላልቻለ ባለ በሌለ ሀይላቸው  ጆሯቸውን አስግገው ወደ ሹክሹክታው አዘነበሉ።
“የጾታ እኩልነት ለምን በእብድ አለም አይሰራም። ጤነኛ ሆናችሁ የተጠናወታችሁ ንቀት አብዳችሁ እንኳ አይለቃችሁም፤ እብደት ማለት የጾታና የዘር  አጥር የሌለው ልቅና ዝርግ ህይወት ነው፤ እናንተ እብድ አይደላችሁም። አውቆ አበድ ናችሁ። ማበዳችሁን ያወቃችሁ። ለእብደታችሁ ጤነኞች እውቅና እንዲሰጧችሁ የምትንገበገቡ የታይታ እብዶች። ጉስቁላናችሁን እንደ ቀብድ አሲዛችሁ ትርፍ ለማጋበዝ የምትታትሩ ከንቱዎች፤ከንፈር እንዲመጠጥላችሁ ላይ ታች የምትሉ አስመሳይ ቀውሶች!” ብላ በበለዘ ሻሿ ፊቷን አበሰችው፡፡
ቀውሶች የሚለውን ቃል ስታወጣ  እልህ ቢጤ ስለተናነቃት፣ ድምጿ ከተኛው ጨቅላ ጆሮ ሰርስሮ ገባ። ጨቅላው በጩኸቱ አካባቢውን እውነተኛ የእብድ ሰፈር አስመሰለው። እብዷ ወዲያው ወደ ቀልቧ ተሰብስባ፣ ግቷን ለጨቅላው ስታቀብልና ጩኸቱ ሲረግብ አንድ ሆነ።
ምሁሩ እብድ የሴትየዋን ተሳልቆ በጥሞና ተከታትሎታል።
“We need to revolutionize our thinking behavior” አለ በሚታወቅበት የእንግሊዘኛ ችሎታው። እብዶቹ በሙሉ የተናገረውን ወደ ሀበሻ አፍ እንዲለውጥላቸው በአንድ ላይ ተንጫጩበት፤ ግድ አልሰጠውም…..ጉራማይሌ እያደረገ ንግግሩን ቀጠለ፤
“ቆይ እናንተን ከእብድ ማህበረሰብ ጋር እንድትቀላቀሉ የፈቀዳለችሁ ማን ነው? የእኛ ትውልድ እብድ መለመላውን ሆኖ በእንግሊዝ አፍ እየተቀኘ የሚንጎራደድ…ወደል ነበር፤ ትንሽ እንደተጓዘ በጤነኞች አጀብ ይደረግለታል። It was so majestic………….፡፡
የእናንተ አጀብ የገዛ ጥላችሁ ነው። ቆይ እኔ የምለው ወይ በእንግሊዝ አፍ አትቀኙ፣ ወይ በሀበሻ አፍ አትቀኙ። ሁለመናችሁ የተሸበበ ልጉም ፍጡሮች! እኔ የማዝነው ያ ወርቃማ የእብድ ማህበረሰብ አልቆ እኔ ብቻ በመቅረቴ ነው። ትውልዳችንን ከመጥፋት የሚታደገው ማን ነው? በቃ የእብድ ማህበረሰብ ማለት ይህ ነው?”  ስቅስቅ እያለ ማንባት ጀመረ፡፡ የእርሱን ሀዘን የተጋሩ ሌሎች እብዶች አብረውት ተነፋረቁ፡፡
አፈጉባኤው ጸጥታ ለማስጠበቅ የጫት ገረወይናውን አንስቶ ሊደበድብ እጁን ሰደደ። ገረወይናው  የለም። ዞር ሲል ወይጦ ከሚባለው እብድ ጋር አይን ለአይን ተላተመ፡፡ ገረወይናው የወይጦ ካራ ሲሳይ ሆኗል። ብሽቀቱን ለመሸሸግ እየሞከረ ካጠገቡ ተንጋላ በተቀመጠችው ቁራጭ የሀይላንድ እቃ  ጉብታውን መሬት ልቡ እስኪጠፋ እየደጋገመ ደበደበው።
“ጸጥታ! ጸጥታ! ለመነፋረቅ አይደለም የተሰበሰብነው። መላ ልናወጣ ልናወርድ እንጂ። ጸጥታ…….ጸጥታ!” ሀይላንዷ እስክትነደል ድረስ ጉብታውን መቀጥቀጡን አላቆመም። እብዶቹ አፈጉባኤውን ብዙ ሳይንገራግሩት ቀና ምላሽ ሰጡት።
ቃለጉባኤ እንዲይዝ የታዘዘው እብድ የጨበጠው ብዕር አልፅፍ ስላለው ቅዝዝ እንዳለ በቀፎው መሬቱን ይቆረቁራል። ድንገት መሬት መቁርቆርን ገታ አደረገና እምር ብሎ ተነሳ። ሽቅብ ወደ ሰማይ አንጋጠጠ። ሁሉም እብድ በአይኑ ተከተለው። እብዱ አይኑን ከአንድ ነገር ጋር እየተከተለ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ያንከራትታል። አይኑ የሚንከራተተው በአካባቢው ቅኝት በሚያደርግ አሞራ ላይ ነው። አሞራው ያንዣብባል። አንዴ ቁልቁል እንደ ሚግ አውሮፕላን  ክንፉን ጨምቆ ይወረወርና ይመለሳል፤ በድጋሚ ክንፉን ጨምቆ ይወረወራል። ምንም የለም። ይመለሳል። መወርወር መመለስ። መወርወር መመለስ። ለሀምሳ ጊዜ ተመላለሰ። በሀምሳኛው ላይ አንዲት ግልገል አይጠ መጎጥ በጥፍሩ ጨምድዶ፣ በአሸናፊነት አየሩን እየገመሰ ከአይን ተሰወረ።
 ሁሉም እብድ  ትእይንቱን ከጅምሩ አንስቶ ነፍዞ እየተከታተለው ነበር።
“አሁን ከእዚህ ትዕይንት ለእብድ ማህበረሰብ ምን የሚፈይድ ነገር ተማርን?” አለ ቃለጉባኤ ፀሐፊው፡፡“እብድና  ብኩን አሞራ አንድ ናቸው። አሞራውስ ሀምሳ ጊዜ ተንከራቶ አንድ አግኝቷል፤ እብድ ግን ለእዚህ አልታደለም። ሀምሳ ጊዜ ተመኝቶ ሀምሳውንም የሚያጣ፤ ሀምሳ ጊዜ ጠይቆ ሀምሳ ጊዜ የሚነፈግ፤ ሀምሳ ጊዜ አንብቶ አንድ ጊዜም የማይፈግግ ብኩን አሞራ ነው፤ ስለዚህ ቢያንስ ከእዚህ አሞራ እንማር፤ ሀምሳ ጊዜ ለፍተን አንድ እንቃርም፤”
“ምንድን ነው የምንቃርመው?” አለ አፈጉባኤው ድንገት አቋርጦት
“እብደታችንን ነዋ፤ እውነተኛ እብድ እንሁን፤ እስካሁን እብድ ለመሆን ተንከራተናል፤ በእርግጥ ቆሽሸናል፤ አዳፋ ተከናንበናል፤ ከገንዳ ውስጥ ፍርፋሪ እየለቀምን እድሜያችንን ቀጥለናል፤ ግን አሁንም ከትክክለኛው እብደታችን ጋር በአይነ ስጋ አልተያየንም። እውነተኛው እብደታችን ከእቅፋችን ውስጥ የሚገባው እንዲህ በረባው ባልረባው ብርክ የሚይዘው ልባችን መጀገን ሲጀምር ነው።
እስቲ የትኛው እብድ ነው ጤነኞች የሚወረውሩበትን  ፍላጻ  ለመመከት ደረቱን በጀግንነት ገልብጦ የሚሰጠው፤ የትኛው እብድ ነው እጁን ወደ የሚንቀለቀል እሳት የሚልከው፤ የትኛው እብድ ነው አንድዬ ብርቅዬ ህይወቱን እየሳቀ የሚሸኘው ፤ አያችሁ እኛ እብዶች አይደለንም፤ ምስኪን ጤነኞች እንጂ፤ ምስኪን ጤነኛ ደግሞ ከእብድ እግር ጋር አይተካከልም? እንዴት ይተካከላል…” ጠየቀ ተሰብሳቢውን፡፡የጉባኤውን መንፈስ ለማረጋጋት ሌላ እብድ ከተቀመጠበት ተነሳ። በመስተፋቅር ካበደው የፓርላማው ወገን ነው። አናቱ ላይ ብጭቅጫቂ ዳንቴል አጥልቋል፤ አንገቱ ላይ  ሻሽ ጠምጥሟል፤ የደረቱን እኩሌታ በእሳት በተበላ  ጡት መያዣ ሸፍኖታል፤ ሚጢጢዬ ጠጠር ድንጋይን እንደ ክሬን እየተጎተተ ከመሬት በማንሳት በጩኸት መናገሩን ቀጠለ፤ “ለምንድን ነው ግን ወደ ራሳችን የማንመለከተው፤ ድሮ ድሮ እብድ ሲባል የጠገበ ዱላ ይዞ የሚንጎራደድ ወጠምሻ ነበር፤ የእብድ ስም ሲነሳ የማይሸበር ጤነኛ አልነበረም፤ እንደውም እስከነተረቱ….“እብድ የተናገረው መሬት አያርፍም” ይባላል፡፡
ፍልስፍናው ዝብርቅርቅ፣ ወሬው የጤነኞችን የማሰብ አቅም የሚፈታተን ነበር፤ ዛሬስ? ዛሬማ ተንቀናል፤ እስቲ ተመልከቱን …..ለአይን የሚያጠግብ እብድ ከእዚህ ውስጥ ይፈለግ ቢባል አይገኝም፤ በአካልም በመንፈስም ደቀናል። አንደበታችን ዲዳ፤ አካላችን ለንቋሳ ሆኗል። እጃችን በዱላ ፋንታ የተጣለ ሀይላንድ መለቃቀም ከጀመረ ሰነባብቷል።
 ፍልስፍናችን በዝምታ ተቀይሯል። የድሮ እብደታችንን ማምጣት ለነገ የምንለው ስራ መሆን የለበትም።”ቀኝ እጁን ወደ ላይ እየሰቀለ መፈክር ማሰማት ጀመረ፤ “እብደታችን እንደ ድሮ ይሆናል! እብደታችን እንደ ድሮ ይሆናል!” አስደንጋጭ መፈክር ከሞቀ ጭብጨባ ጋር አጀበው። ጭብጨባውን ሰምቶ ይሁን ድንገት… ስጋ የጠገበ መለዮ ለባሽ ዱላውን አክሮባት እያሰራ ከርቀት ወደ ስብሰባው ሲመጣ ታየ፡፡ ሁሉም ተሰብሳቢ በፍርሀት ልቡ ይርድ ጀመረ።
አፈጉባኤው በእዚህ ጊዜ፤
“አንድ ጊዜ ……አንድ ጊዜ፤ አሁን ጤነኛውን ከእብድ፣ ፍሬውን ከገለባ መለየት ቸለናል፡፡ በአንድ መለዮ ለባሽ  እንዲህ የሚርድ ልብ ካለን፣ ጤነኛ የመሆናችን ፋይዳው ምኑ ላይ ነው። …ኸረ.. እብደት በስንት ጣዕሙ….. በሉ ወደ የሚያዋጣን እብደታችን እንመለስ” ብሎ በንዴት ስብሰባውን በተነው።

Read 2226 times