Saturday, 27 December 2014 16:21

አማርኛ የራሱ ፊደል አለውን?

Written by  ጌታቸው አበበ አየለ
Rate this item
(25 votes)

በክፍል ፩
 ፅሑፌ፤ የአማርኛ ፊደሎች (ሆሄያት) በዝተዋልና ይቀነሱ (ይሻሻሉ) በሚሉ የቋንቋ ምሁራን የተሰነዘሩትንና እየተሰነዘሩም ያሉትን ሀሳቦች ከብዙው በጣም በጥቂቱ እንደገለጽኩ ይታወሳል፡፡
 በማጠናቀቂያዬም “ለመኾኑ አማርኛ የራሱ የኾነ ብቸኛ ፊደል (የፊደል ገበታ) አለውን?” የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ እናም በቀጠሮዬ መሰረት ይኸው የያዝኩትን ይዤ ብቅ ብያለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
“ነገርን ነገር ያነሳዋል” ይባል የለ፡፡ እናም ወደ ዋናው ጉዳይ ከመሔዴ በፊት “ፊደል” የሚለውን ቃል በተመለከተ አንድ ሐሳብ ላነሣ ፈለግሁ፡፡ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ፊደል የሚለው ቃል ሆሄ ከሚለው ቃል ጋር በተምታታ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውሉ በማየቴ ነው፡፡
በእርግጥ እንደ ልምድ ሆኖ ይመስላል ሆሄ በማለት ፈንታ ፊደል እያልን ስንጠቀም ቆይተናል፤ እየተጠቀምንም እንገኛለን፡፡ ያም ሆኖ ግን መግባባታችን አልቀረም፡፡ “ቋንቋ መግባቢያ አይደል እንዴ! እኛ ከተግባባንበት ቢባል ምን ችግር አለው?” የምትሉኝ ትኖሩ ይሆናል፡፡ ተሳስታችኋል ከሚል ድምዳሜ ፈጥኜ አልገባም፡፡
ይሁን እንጂ በሥነ ጽሑፍ ውስጥ አንድ ቃል ሊገልጸው የሚፈልገውን ነገር በትክክል ሊያስረዳ ካልቻለ ጸያፍ ከመሆን አያልፍም፡፡ “እንጀራ እየጋገርሁ ነው” ለማለት “ምጣድ እየጋገርሁ ነው፡፡” አይነት ይሆናል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ስለ ፊደልና ሆሄ ልዩነትና አጠቃቀም ብንሳሳት ወይም ባናውቅ አይፈረድብንም፡፡ ምክንያቱም ስለ ሁለቱ ቃላት ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያብራራ መዝገበ ቃላት አልተዘጋጀምና፡፡ አንዳንዶቹ መዛግብተ ቃላትማ ፊደልን ጠቅሰው ሆሄ የሚለውን ዘልለውት እናገኛቸዋለን፡፡
ወደ እንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት መለስ ብለን እስቲ “አልፋቤት” እና “ሌተር” የሚሉትን ቃላት ትርጉም እንመልከት፡፡
Alphabet:  The set of letters used in writing any language, esp. when arranged in order, eg. Greek alphabet, Russian alphabet. Letter: any of the sign in writing or printing that represent a speech sound. “B is a capital letter “b” is a small letter.   (Longman Dictionary of Cont. English)
እዚህ ላይ እንደምንመለከተው በእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት alphabet (ፊደል) እና letter (ሆሄ) ግልጽ ትርጉም ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ፣ ካሉት መዛግብተ ቃላት መካከል ቀረብ ያለ አተረጓጎም የያዘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታተመው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አማርኛ መዝገበ ቃላት ፊደል የሚለውን ቃል፡-
“ፊደል፡- ንግግርን በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችልና ድምጽን ወክሎ የሚቆም ምልክት (ለምሳሌ ሀ፣ ለ …) በማለት ተርጎሞታል፡፡ ሆሄ ለሚለው ቃል ደግሞ “ሆሄ (ብዙ ሆህያት) ስ. ከግእዝ እስከ ሳብዕ (ለምሳሌ ከሀ-ሆ ወይም ከሀ-ፐ) ያለው የፊደላት ስምና መልክ ወይም ቅርፅ” የሚል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡
ለማንኛውም ፊደል ንግግርን በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችሉና ድምፅን ወክለው የሚቆሙ ምልክቶች (ሆሄያት) ስብስብ ሲሆን ሆሄ ግን ለአንድ ድምፅ የሚወከል ምልክት ነው የሚለውን ትርጉም በመያዝ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ልመልሳችሁ፡፡
እዚህ ዝርዝር ውስጥ የገባሁት ወደፊት ባለው ጽሑፌ የሁለቱ ቃላት አገባብ አንባቢዎችን ግር እንዳያሰኝ በማሰብ ነው፡፡ እናም “አማርኛ የራሱ የሆነ ፊደል አለውን?” የሚለውን እንመልከት፡፡
አማርኛ የራሱ የሆነ ፊደል አለው ወይም የለውም የሚል ብያኔ ከመስጠታችን በፊት ግን የት መጣነቱን ማየት ወይም ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህንንም ለመረዳት ከኢትዮጵያዊው ፊደል ማለትም ከግዕዝ ታሪካዊ አመጣጥ መነሣቱ ለግንዛቤ ይጠቅማል፡፡
ስለ ግዕዝ ፊደል አመጣጥ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ እነዚህም ሃይማኖታዊና ሳይንሳዊ አመለካከቶች ናቸው፡፡ የሃይማኖት ሊቃውንት ስለ ፊደል አመጣጥ ሲገልጹ፣ ፊደል ከአዳም ሦስተኛ ትውልድ በሆነው በሄኖስ አማካይነት ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ ነው፡፡ በልሳን ተውጦና ተሰውሮ የነበረው አካሉ በሰማይ ገበታነት ተጥፎ፣ ተቀርጦ የተገለጠ ነው በማለት፤ (ኩፋሌ 5፥18)ን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ ፊደሉም ግዕዝ ነው ይላሉ፡፡
የፊደሉም ሆሄያት መደበኛ ቁጥራቸው ከእሁድ እስከ ዐርብ በተፈጠሩት ፍጥረታት ልክ 22 ናቸው፡፡ በእነሱ ላይ ደግሞ በመጥበቅና በመመሳሰል ምክንያት ተደራራቢ ሆሄያት (ሰ፣ኃ፣ዐ፣ፀ) ሲጨመሩ ኻያ ስድስት ይሆናሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡
በሳይንሳዊ አመለካከት በኩል የሚቀርበው የግዕዝ ፊደል አመጣጥ ታሪክ ግን ከሃይማኖት ሊቃውንት አባባል የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እንደ ሳይንሳዊ ጥናት አድራጊ ምሁራን አባባል፤ የሰው ልጅ ፊደልን በሚሊዮኖች ዓመታት የዕድገት ደረጃዎች ለውጡ ቋንቋውን ከሥልጣኔ ዕድገቱ ጋር አብሮ እያራመደ ሲመጣ ያገኘው ውጤቱ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በዚህም መሰረት አስቀድሞ ሸክላ፣ ቆዳ፣ ብረት፣ እንጨትና የመሳሰሉት ልዩ ልዩ ቅርፃቅርፆችንና ምልክቶችን በመጠቀም መልእክት ለማስተላለፍ ቻለ፡፡ በእነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች (Pictographic Symbols) ከመጠቀም አልፎም ወደ ጽሑፍ ቋንቋ (Writing Language) በቅቷል የሚል ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
የሳይንሳዊ ጥናት ተመራማሪዎች ከላይ እንደተገለጸው፤ የሰው ልጅ ለንግግሩ ጽሑፋዊ መግለጫ የሆነውን ፊደል መፍጠር እንደቻለ አረጋግጠዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ልንገነዘበው የሚገባን ነገር ይኖራል፡፡ ሃይማኖታዊም ሆነ ሳይንሳዊ አመለካከት ያላቸው ሁለት ክፍሎች፤ በፊደል ታሪካዊ አመጣጥ ላይ የተለያየ አቀራረብ ቢኖራቸውም በአጠባበቅና በአጠቃቀም በኩል ግን በአብዛኛው አንድነት ያላቸው መኾኑን ልንረዳ ይገባል፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው፤ የሰው ልጅ ፊደልን ከማግኘቱ በፊት ለፊደል መፈልሰፍ መሰረት የሆኑት ሥዕላዊ ምልክቶችን ይጠቀም እንደነበረ ተገንዝበናል፡፡ እነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች የግብፅ ሂሮግሊፊክ እና የመሶጶታሚያው ኩኒፎርም በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡ በዓለም ውስጥ ያሉት ፊደሎችም በሙሉ ከእነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች የተገኙ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
የግብፅን ሂሮግሊፍክ (ሥዕላዊ ጽሑፍ) መሠረት በማድረግ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት 1800-1500 በሴማውያን ከተፈለሰፈው ጥንት ሲናዊ (Proto - sinaific) ፊደል፣ በርካታ ሌሎች ፊደላት መገኘት ችለዋል፡፡ ከተፈለሰፉት መካከል ግን እንደ ዐረብኛ፣ ዕብራይስጥኛና ኢትዮጵያዊኛ ያሉት እናት ፊደላቸውን መምሰል እየተውና እየራቁ በመሔድ የተገኙ ናቸው፡፡
የሴም ፊደሎች ሰሜን ሲናዊ እና ደቡብ ሲናዊ በመባል በሁለት  ወገን ይከፈላሉ፡፡ እናም ለኢትዮጵያዊው ፊደል (ግዕዝ) መነሻ ሆኖአል የተባለው የሳባ ፈደል በደቡቡ ሴማዊ ክፍል የሚገኝና በደቡብ ዐረብ የነበረ ነው፡፡
ይህ በደቡብ ዐረብ ይሰራበት የነበረውና ኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተሻግሮ የግዕዝን ፊደል ያስገኘው የሳባ ፊደል፣ ሃያ ዘጠኝ ሆሄያት እንደነበሩት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ግዕዝ ይኸንን የአጻጻፍ ስልት በወረሰበት ጊዜ ሁሉንም አልተቀበላቸውም፡፡ ምክንያቱም በሁለቱ ቋንቋዎች ማለትም በሳባና በግዕዝ ድምፀ ልሳኖች ውስጥ አንዳንድ ድምፆች ልዩነት ስለነበራቸው ነው፡፡
ከዚህም የተነሣ ግዕዝ አምስቱን በመተው፣ ሃያ አራቱን የሳባ ፊደል ሆሄያት ሊወርስ ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከንፈራዊ ደወል የለሽ (ፐ) እና አንድ ከንፈራዊ ፈንጂ (ጰ) የተባሉትን ሁለት ድምፀ ወካይ ምልክቶች በማከል የፊደል ሆሄያቱን ቁጥር ኻያ ስድስት አድርሶታል፡፡ እንዲሁም ኻያ ስድስቱ ሆሄያት ድምፅ ሰጪ እንዲኖራቸው በመደረጉ፣ በጠቅላላው (26x7) አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የግዕዝ ዲቃላ የሚባሉ ሌሎች አራት ሆሄያትም በመኖራቸውና እነሱም በበኩላቸው አምስት ድምፅ ሰጪዎች ስላሏቸው (4x5) ሃያ ዲቃላ ሆሄያት ስለሚሆኑ፣ የግዕዝ ፊደል በጠቅላላው 202 ሆሄያት ነበሩት፤ አሉትም፡፡
የግዕዝ ፊደል የሚባሉት 26ቱ ድምፆችና አራቱ ዲቃሎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ፣ ሠ፣ ረ፣ ሰ፣ ቀ፣ በ፣ ተ፣ ኀ፣ ነ፣ አ፣ ከ፣ ወ፣ ዐ፣ ዘ፣ የ፣ ደ፣ ገ፣ ጠ፣ ጰ፣ ጸ፣ ፀ፣ ፈ፣ ፐ እንዲሁም ኰ፣ ጐ፣ ቈ፣ ኈ ናቸው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በተለይም 26ቱ የግዕዝ ፊደል ተነባቢ ድምፆች የየራሳቸው የሆነ ትርጉምና የአጠቃቀም ህግ አላቸው፡፡ የጋዜጣውን ዓምድ ላለማጣበብ ሲባል እንጂ ሁሉንም መዘርዘር በተቻለ ነበር፡፡
የግዕዝ ፊደል ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ በር ከፋች ሆኖ በስፋት ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ በኋላ እጅግ በርካታ ድርሳናት ተደርሰውበታል፡፡ በግዕዝ ቋንቋና ፊደል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ቅዱሳት መጻሕፍትዋ ላይ የጻፏቸውን ጨምሮ  የአያሌ መጣጥፎችና መጻሕፍት ደራሲ የሆኑት ምሁር ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ በሐመር መጽሔት ሐምሌ/ነሐሴ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም እትም፤ “… ኢትዮጵያ በጥንታዊው የሥነ ጽሑፍ ታሪክ በዓለም የመጀመሪያውን ረድፍ የምትይዝ አገር ናት፡፡ በእንግሊዝ፤ በፈረንሳይ፣ በጀርመን ዛሬ የሚፃፉት ሁሉ ከኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጋር የሚወዳደሩት ትልልቆቹ የግሪክ፣ የአራማይክ፣ የላቲን፣ የመሳሰሉቱ ናቸው፡፡ …” በማለት ኢትዮጵያን ታላቅ ከሚያደርጓት ሀብቶቿ አንዱ ይኸው የግዕዝ ሥነ ፅሑፍ መሆኑን በዝርዝር መግለፃቸውን እናያለን፡፡
በጥቅሉ ስለ ግዕዝ ፊደል የትመጣነትና አገልግሎት በዝርዝር ለማስቀመጥ ሰፊ ቦታና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ለመግቢያ ያህል ይህችን ታህል ካልን የሚበቃ ይመስለኛል፡፡ እናም ዘመቻ ወደበዛበት ወደ አማርኛ ፊደል መለስ ብለን ማየት እንሞክር፡፡
የአማርኛ ፊደል ለአማርኛ ቋንቋ መጻፊያነት እንዲያገለግል ሆኖ ሥራ ላይ መዋል የጀመረው በ1270 ዓ.ም የዛጌ ሥርወ መንግስት ማብቂያ ዘመን አካባቢ መኾኑ ይነገራል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ፊደሉን የወረሰው በቀጥታ በግዕዙ ከሚገኙት ሆሄያት ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን ሃያ ስድስቱንም የግዕዝ ሆሄያት አንድም ሳያስቀር ሁሉንም ተቀብሏቸዋል፡፡
ያደረገው አዲስ ነገር ቢኖር ለቋንቋው የሚያገለግሉ 7 ድምፃዊ ምልክቶችን (የድምፅ ወካዮችን) ጨምሮ የፊደሉን ቁጥር ወደ 33 ከፍ አድርጎ መጠቀም መቻሉ ነው፡፡
እነዚህም ተጨማሪ ያደረጋቸው ሆሄያት “ሸ”ን ከሰ፣ “ቸ”ን ከተ፣ “ኸ”ን ከከ፣ “ኘ”ን ከነ፣ “ዠ”ን ከዘ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ በመጨረሻም ከ“በ” ሆሄ “ቨ” የሚለውን ወካይ ጨምሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ ስንመለከተው፣ አማርኛ የራሱ የሆነ ፈደል አለውን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይከብዳል ተብሎ አይገመትም፡፡ አንድ ቋንቋ ወይም አገር የራሱ ፊደል አለው ብሎ መናገር የሚቻለው የቋንቋውን ድምፆች የሚወክሉ ሆሄያትን  የያዘ ፊደል መፈልሰፍ ሲችል ነው፡፡ ስለሆነም አማርኛ የሚጠቀምበት ፊደል 78.8% የግዕዝ በመሆኑ ፊደሉ የአማርኛ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ከዚህም የተነሣ አማርኛ በግዕዝ ፊደል ላይ በጨመራቸው 7 ሆሄያት ብቻ የቋንቋውን ድምፆች በጽሑፍ መግለጽ ስለማይችል የራሱን ፊደል ይዟል አይባልም፡፡
ከዚህም ላይ አማርኛ ከግዕዝ የወረሰው ፊደሉን ብቻ አይደለም፡፡ ከቋንቋውም ቀላል የማይባሉ ቃላትን በመዋስ ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፤ እየተጠቀመባቸውም ነው፡፡ ይህ ከሆነ ታድያ “የአማርኛ ፊደል ይሻሻል፤ ፊደላት በዝተዋልና ይቀነሱ” ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችና ዘመቻዎች ለምን ይነሳሉ? በቀጣይ የምንመለስበት ይሆናል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡  

Read 16915 times