Saturday, 27 December 2014 16:02

ያለፈው ሥርዓት “አስማተኛ” ሳይሆን አይቀርም!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

እኔ የምላችሁ ግን … ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ስንት ዓመቱ ነው? ይሄንን ቀላል ጥያቄ የምጠይቃችሁ ወድጄ እንዳይመስላችሁ፡፡ ግራ ቢገባኝ ነው፡፡ ሌላም ጥያቄ አለኝ - ያለፈው ሥርዓት ከተገረሰሰ ምን ያህል ጊዜ ሆነው? (ውዥንብሩ መጥራት አለበት!) አንዳንዴ ያለፈው ሥርዓት “አስማተኛ” ይመስለኛል፡፡ ለምን መሰላችሁ? አንዳንድ ሰዎች አሁንም ከ24 ዓመት በኋላ እንኳን ስለሱ ማውራት አልተዉም፡፡ ለሁሉ ነገር ያለፈውን ሥርዓት ካልጠሩ አይሆንላቸውም - በተለይ የኢህአዴግ ካድሬዎች፡፡ (ፍሬሾቹን ማለቴ ነው!)
 ሰሞኑን EBC ባቀረበው የዜና ዘገባ ላይ “…የሴቶች ጥቃት ያለፈው ሥርዓት ችግር ስለሆነ እንታገለዋለን…” (really?!) የሚል ነገር የሰማሁ መሰለኝ፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … ራሱ ኢህአዴግም እንኳን  የሴቶች ጥቃት “ያለፈው ሥርዓት” ችግር ነው አይልም፡፡ እንዲያ ካለማ--- ያለፈው ሥርዓት አልተገረሰሰም ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ እንዳልኩት “አስተማኛ” ነው፡፡ (መቃብር እየፈነቀለ የሚወጣ!)
ይሄውላችሁ --- በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓይነትም በመጠንም እየጨመሩ ለመምጣታቸው ከፖሊስ ፕሮግራም የበለጠ ማስረጃ የለም፡፡ (የሴቶች መብት ተሟጋቾችም ምስክር ናቸው!) አስገድዶ መድፈር፣ አሲድ መድፋት፣ ከባድ ድብደባና የአካል ማጉደል እንዲሁም አሰቃቂ ግድያዎች…በእጅጉ በርክተዋል፡፡ (ሰብዓዊ ልማት ተዘንግቷል!)
እናም--- የሰሞኑ የEBC ዘገባ blame shifting (“የእምዬን ወደ አብዬ”) እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ሃቁን እንነጋገር ከተባለ --- የሴቶች ጥቃት  “ያለፈው ሥርዓት” ችግር ሳይሆን የእኛው የራሳችን ችግር ነው፡፡ (የኋላ ቀርነት፣ የትምህርት አለመስፋፋት፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የአመለካከት ችግር ወዘተ…) ነገርዬው እምብዛም ከስርዓት ጋር የሚያያዝ አልመሰለኝም (ፖለቲካ እኮ አይደለም!) የግድ የሥርዓት ችግር ነው ከተባለም ባለቤቱ የአሁኑ ሥርዓት ነው፡፡ እናሳ? … እናማ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ወዳለፈው ሥርዓት ለማሻገር ከመታተር ይልቅ እውነታውን ተቀብሎ ለመፍትሄ መትጋት ይሻላል፡፡ (ያለፈው ሥርዓት ከበቂ በላይ የራሱ ኃጢያቶች እንዳሉት አንዘንጋ!!)
ይሄውላችሁ ----- እንኳንስ በቅርብ ዓመታት እየተባባሰ የመጣው “የሴቶች ጥቃት” ይቅርና በእርግጥም ካለፈው ሥርዓት የተወረሱ ናቸው የሚባሉት (እነ ድህነት፣ ሙስና፣ የስልጣን ጥመኝነት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የነፃነት አፈና፣ የፍትህ መጓደል ወዘተ…) ቢሆኑም እንኳ --- 20 ዓመት ስላለፋቸው  ውርስነታቸው አብቅቷል፡፡ (ከአባት የተወረሰ ንብረትም እኮ ለዘላለም በውርስነት አይጠራም!) ከምሬ እኮ ነው… ከአሁን በኋላ ችግሮችን ባለፈው ሥርዓት ማሳበብ ራስን ለትዝብት ማጋለጥ ነው፡፡
በመጨረሻ አንድ ሃሳብ ላቅርብ፡ ከፆታዊ ጥቃቶች አንዱ የሆነው አስገድዶ መድፈር፣ ለምን በፀረ ሽብር ህጉ ውስጥ አይካተትም? ይሄ እኮ… ሥርዓቱን ወይም ህገመንግስቱን በኃይል ለመናድ ከመሞከር ፈፅሞ አይተናነስም፡፡ ሴቶች ላይ ጥቃት መፈጸም - ቤተሰብን --- ህዝብን --- መንግስትን ---- አገርን --- ማሸበር ነው!!

Read 4343 times