Saturday, 20 December 2014 12:24

ት/ቤት ያቋቋሙት ግለሰብ የመምህራን ደሞዝ መክፈል አቅቷቸዋል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

     ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ያስተማሯት ጎበዝ ተማሪ በትዳር ሰበብ (ያውም በወላጆቿ ግፊት) ትምህርት ስታቋርጥ በጣም ነው ያዘኑት፡፡ “ልጅቷ በትምህርቷ ጎበዝ ስለነበረች ከክፍል 1ኛ ነበር የምትወጣው፡፡ አማካይ ውጤቷ 92 ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከክፍል 2ኛ ወጥታ “እንዴት ተደርጎ?” ብላ አልቅሳለች፡፡ ወላጆቿ “አንቺን ቤት አስቀምጠን አንቀልብም” በማለት ከት/ቤት አስቀርተው ሲድሯት በጣም አዘነች፡፡ ጉብዝናዋን የሚያውቁት መምህራኖቿም ሆኑ እኔ ከማዘን በስተቀር ትምህርቷን እንድትቀጥል ማድረግ አልቻልንም፡፡
“ይኼ የሆነው የአካባቢው ማህበረሰብ ለትምህርት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑና የቀበሌ አስተዳደሩም ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ ቅስቀሳና ግፊት ስለማያደርግ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት 40 ልጃገረዶች ትምህርት አቋርጠው ተድረዋል ወይም ታጭተዋል፡፡ ሌሎች ያቋረጡ ወንዶችም አሉ፡፡ በአጠቃላይ 50 ይደርሳሉ፡፡ በየዓመቱ ይህን ያህል ያቋርጣሉ፡፡ ይህ ባይሆን የተማሪዎቻች ቁጥር 350 ሳይሆን 400 በላይ ይደርስ ነበር” ያሉት በትውልድ ቀያቸው ት/ቤት የከፈቱት አቶ ዘውዱ ዳባ ቀነኒ ናቸው፡፡
አቶ ዘውዱ ከ40 ዓመት በኋላ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወረዳ፣ ሎያ ጀጎላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የሄዱት ከተወለዱበት ስፍራ የወጡት በሕፃንነታቸው ስለሆነ አካባቢው ምን እንደሚመስል ለማየት እንጂ ት/ቤት ለማቋቋም አስበው አልነበረም፡፡
የባላገር ልጆች ከከተማ የመጣና ካሜራ የያዘ ሰው ሲያዩ ብርቃቸው ስለሆነ አቶ ዘውዱ ወደ ስፍራው እንደደረሱ ከበቧቸው፡፡ ልጆቹ ተዳጊዎች ነበሩ፡፡ ወላጆቻቸው ለእረኝነት ፈልገዋቸው ያስቀሯቸው መስሏቸው በማዘን “ለምን ት/ቤት አልሄዳችሁም?” በማለት ጠየቁ፡፡ ት/ቤት የሚገኘው ከቀበሌው ሩቅ ስለሆነ፣ መንገዱም ዳገትና ቁልቁለት በመሆኑ ከ2 እስከ 4 ሰዓት ስለሚፈጅ ወላጆች ወደ ጉሮ ከተማ ለ1ኛ ክፍል የሚልኩት ልጆቹ ከ13 ዓመት በላይ ሲሆናቸው እንደሆነ ነገሯቸው፡፡ በሰሙት ነገር በጣም አዘኑና “እኔ እዚህ ት/ቤት እሰራላችኋለሁ” አሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ድሆች ስለሆኑ፣ እኛ የምናዋጣው ነገር የለንም አሉ፡፡ “ግድ የለም፤ እኔ አስፈላጊውን ነገር አሟላለሁ፤ እናንተ በጉልበት (በማዋቀሩ) ትረዱኛላችሁ” አሏቸው፡፡ ነዋሪዎችም በጣም ደስ ብሏቸው ተስማሙ፡፡ በሳምንቱ ቃላቸውን ጠብቀው ቆርቆሮ፣ ሚስማር፣ …አስጭነው ይዘው ሄዱና ት/ቤቱ ተሰራ፡፡
 በከተማ ሕጻናት 1ኛ ክፍል የሚገቡት ለሶስት ዓመት ከፈደላትና ከቁጥሮች ጋር ከተዋወቁ በኋላ በ7 ዓመታቸው ነው፡፡ በሎያ ጀጎላ ግን ልጆች 1ኛ ክፍል የሚገቡት የፊደልና የቁጥር ዘር ሳያውቁ በ13 ዓመታቸው ነው፤ ያውም የታደሉትና ዕድሉን ያገኙት፡፡
ት/ቤቱ ቢሰራም የሎያ ጀጎላ ቀበሌ ልጆች ከ14 ዓመት በላይ ቢሆናቸውም ስለ ፊደልና ስለ ቁጥር የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ አቶ ዘውዱ ልጆቹ 1ኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት፣ 12ኛ ክፍል ያጠናቀቀ ወጣት ቀጥረው 3 ወር ክረምት ከትምህርት ጋር እንዲተዋወቁ (መዋለ ህፃናት እንደማለት ነው) ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ዴስክ፣ ጥቁር ሰሌዳ፣ ቾክ … ገዝተው መምህራን ቀጥረው፣ በ2001 ዓ.ም 1ኛ ክፍል ከፍተውና 172 ተማሪዎች ተቀብለው በነፃ ማስተማር ጀመሩ፡፡ በ2001 ትምህርት የጀመሩት ልጆች ዘንድሮ የ7ኛ ክፍል ተማሪ መሆናቸውንና የት/ቤቱ ተማሪዎች ቁጥርም 350 መድረሱን አቶ ዘውዱ ገልፀዋል፡፡
ለት/ቤት ከሚያስፈልጉ ዋነኛ ነገሮች አንዱ ውሃ፣ ሌላው ደግሞ መብራት ነው፡፡ ስለዚህ የት/ቤቱ መስራች ዳገት ላይ ጉድጓድ አስቆፍረው በ6 ባንቧ ውሃ ለት/ቤቱ አስገቡ፡፡ ሌላው የመንደሩ ነዋሪዎች ዋነኛ ችግር በአካባቢው የወፍጮ ቤት ያለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ በግላቸው ትራንስፎርመር ገዝተው፤ በ1,500 ሜትር ርቀት ፖል ተክለውና ሌሎች ወጪዎችን ጨምረው በ250 ሺህ ብር በማውጣት መብራት አስገቡ፡፡
የመብራቱ መግባት ወፍጮ ቤት እንዲተከልና ት/ቤቱ መብራት እንዲያገኝ አስቻለ፡፡ መብራቱ በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎች ቤትም ስላስገቡ ተማሪዎች ከኩራዝ ተላቀው በኤሌክትሪክ ብርሃን ማጥናት፣ መምህራንም የትምህርት ዕቅድ ማዘጋጀት እንደቻሉ፣ ነገር ግን ኤሌክትሪክ ሲያስገቡ የተበደሩትን 170 ሺህ ብር ዕዳ መክፈል እንዳልቻሉ፣ … መስራቹ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዘውዱ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት የተረፋቸው ባለሀብት ሆነው አይደለም፡፡ የእሳቸው ሀብት የ6 ዓመት ህፃን ሳሉ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ካሳደጓቸውና ካስተማሯቸው “ባለ ውለታዬ ናት” ከሚሏቸው ከአክስታቸው ከወ/ሮ አልማዝ ጌታቸው ጋር አንድ ቤት ለሁለት ተካፍለው የሚሰሩባት አነስተኛ ሱቅ ናት፡፡
ት/ቤት ለመስራት የተነሳሱት ገንዘብ ኖሯቸው ሳይሆን የት/ቤት ደጅ ያልረገጡ የገጠር ታዳጊ ልጆችን ለማስተማር ባደረባቸው ጥልቅ ፍላጐት የተነሳ ነው፡፡ “የእኔ ልጆች ይማራሉ፡፡ እነዚህ ልጆች የትምህርት ዕድል ቢያገኙ እንደማንኛውም ልጅ የመማር፣ የማደግ፣ የመለወጥ፣ … ራዕይ ይኖራቸው ነበር፡፡ እኔ በምችለው አቅም ት/ቤት ሰርቼላቸው ለምን ምኞትና ራዕያቸው እውን እንዲሆን አልደግፋቸውም?” …በሚል ሃሳብ ተነሳስቼ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ዘውዱ በቅንነት የጀመሩት ነገር በአንድ በኩል ዋጋ እያስከፈላቸው በሌላ ወገን ደግሞ እያስደሰታቸው ነው፡፡ የደስታቸው ምንጭ የልጆቹ የእውቀት ብርሃን ማየት ነው፡፡
ይህም ልጆቹን የበለጠ በመደገፍ ምኞታቸውን ለማሳካት እንዲያቅዱ አድርጓቸዋል፡፡ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-ሙከራ ለመስራትና 8ኛ ክፍል ለመክፈት አስፈላጊ ቁሶች አዘጋጅተው ቤቱን ለማዋቀር የአካባቢውን ህብረተሰብና የሌላውንም ድጋፍ እየጠበቁ ነው፡፡
ራዕያቸው ት/ቤቱን አዳሪ ት/ቤት ማድረግ፣ ኮሌጅ ከፍተው ከ14 ዓመት በኋላ 200 ያህል ተማሪዎች በዲግሪ ማስመረቅ፣ ወደ ት/ቤቱ የሚያደርሰውንና መኪና የማያስገባውን 20 ኪ.ሜ አስቸጋሪ መንገድ ማሰራት፣ ት/ቤቱን ከ5ሺህ እስከ 10 ሺህ ለሚደርሱ ተማሪዎች ምቹ መማሪያ ማድረግ፣ ለአካባቢውና አጎራባች አርሶ አደሮች ምርጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ማቅረብ፣ … ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ምኞታቸው የሚሰምረው ግን ከአካባቢው ህብረተሰብና ከሌሎችም ግለሰቦችና ድርጅቶች ድጋፍ ሲያገኙ ነው፡፡
አሁን የአቶ ዘሪሁን  ከፍተኛ ችግር ለመምህራን ደሞዝ መክፈል ያለመቻል ነው፡፡ በየወሩ ለመምህራን ደሞዝ ከ10 ሺህ ብር በላይ ከኪሳቸው እየከፈሉ፣ የትምህርት አጋዥ ቁሳቁስ እያሟሉ የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስቀጠል እያቃታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እናም የመምህራኑን ደሞዝ፣ በሚቀጥለው ዓመት ለሚከፈተው 8ኛ ክፍል ቤተመፃሕፍትና ቤተ ሙከራ (ላቦራቶሪ) የሚያስፈልጉ እንደ ማይክሮስኮፕ ያሉ መሳሪያዎችና ኬሚካሎች፣… የሚረዳቸው አካል በጣም ይፈልጋሉ፡፡
የት/ቢሮ ጽ/ቤት የትምህርት አሰጣጡን ጥራት እየሄደ ይቆጣጠራል መማሪያ መጻሕፍትና ቾክ (ጠመኔ) ይሰጠዋል፡፡ ት/ቤቱ በስፖርት ውድድሮች ከሌሎች ት/ቤቶች ጋርም ይወዳደራል፡፡ ከዚህ ያለፈ የሚያደርግለት ነገር ግን እንደሌለ አቶ ዘውዱ ገልፀዋል፡፡
 በአንድ ወቅት አቶ ዘውዱ “ለመምህራን ደሞዝ መክፈል አቅቶኛልና ት/ቤቱን ተረከቡኝ” በማለት ለወረዳው ትምህርት ቢሮ ጽ/ቤት አመለከቱ፡፡ “ለማመልከቻዬ ምን ምልስ  ሰጣችሁ?” በማለት ሲጠይቁ “እኛ በጀት የለንም፤ ከፈለክ ዝጋው” እንዳሏቸው ያስታወሳሉ፡፡
እሳቸው ግን እንደአብራካቸው ክፋይ የሚያዩትን ት/ቤት መዝጋት አቃታቸው፡፡ ስለዚህ የት/ቤቱን ፎቶ ግራፍ በየመጠጥ ቤቱ፣ በየካፌው … ለማያውቋቸው ሰዎች እያሳዩ፣ “ለመምህራም ደሞዝ መክፈል ስላቃተኝ እርዱኝ” ብለው ሲጠይቁ፣ አንድ  ሺህ፣ ሁለት ሺህ፣ አምስት ሺህ ብር… ባደረጉላቸው ድጋፍ ት/ቤቱን ከመዘጋት አትርፈው ይኸው እስካሁን እንዲቀጥል በማድረጋቸው እነዚያን ሰዎች በተማሪዎቹ ስም ከልብ አመስግነዋል፡፡
አቶ ዘውዱ ድጋፍ ካልተደረገላቸው በስተቀር እንደበፊቱ ብቻቸውን መቀጠል እንደከበዳቸው ነው የሚናገሩት፡፡ ሦስት ልጆቻቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ነው፡፡
እነሱን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እስካሁን ት/ቤቱን የሚያንቀሳቅሱት፣ ከሱቋ በተጨማሪ የባህር ዛፍ ተክል ስለነበራቸው እሱን እየቆረጡ በመሸጥ ነበር፡፡ አሁን ግን አልቋል፡፡ የወረዳውን አስተዳደር ጠፍ መሬት እንዲሰጣቸው ጠይቀው የተፈቀደላቸው 29 ሄክታር መሬት ቢኖርም የአካባቢው ነዋሪዎች ሊያርሱላቸው አልቻሉም፡፡ በግላቸው እንዳያርሱ ደግሞ አቅም አነሳቸው፡፡ በእነዚህና በብዙ ሌሎች ምክንያቶች ድጋፍ እንዲደረግላቸው አበክረው ጠይቀዋል፡፡
የሜታ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤትም ለአቶ ዘውዱ ሥራ እውቅና ሰጥቶ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ከዚህ በታች የቀረበውን ደብዳቤ ጽፎላቸዋል፡፡   

Read 5004 times