Saturday, 20 December 2014 12:35

ሰርካለማዊ እጆች

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(4 votes)

አንድ ወዳጄ መጥቶ “እንዋብማ” አለኝ፡፡ ወዴት እንደምንዋብ ሳልጠይቅ “ቅደምማ” አልኩት፡፡ ወዳጄ የአራት መፃህፍት ደራሲ ነው፡፡ የመንፈስ ትርፉን ሳያሰላ በከንቱ ተውቦ የሚያስውብ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ከእኔ ቤት እምብዛም እርቀን ሳንዋብ እቦታው ደረስን - Economic Commission of Africa ግቢ፡፡ ለካ መዋባችን የአጋጣሚ አልነበረም፡፡ ቀደም ብሎ አስመዝግቦኝ ኖሮ፣ ከመዝገቡ ሥሜ ተፅፎ ተገኘ፡፡ ፍተሻው በምንጣሮ ተካሂዶብን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡
ይሄን ግቢ ከ10 ዓመት በፊት አውቀዋለሁ፡፡ African Development Forum (ADF) ስብሰባ እዚህ ሲካሄድ በዘጋቢ ጋዜጠኝነት ደጋግሜ ተገኝቻለሁ፡፡ አካባቢው እንጂ እርሱ አልተለወጠም፡፡ ግቢው አንዳች አውሮፓዊ መንፈስ የረበበበት ነው፡፡ “አፍሪካ ሆይ የት ነሽ?” ብዬ መጮህ አሰኘኝ፤ አፍሪካ ጉያ ውስጥ ነህ እየተባልኩ አፍሪካዊ ጠረን ማጣት ምን ይሉት ፌዝ ነው? Jean - Paul Sartre እንዲህ ሲል የተነበየው ለዛሬይቱ አፍሪካም ይሰራ ይሆን? “Negritude is destined to destroy itself”
ወደ ውስጥ ዘለቅን …
… የመሰብሰቢያ አዳራሾቹ አንድ ትልቅ የጋራ እልፍኝ አላቸው፡፡ መገናኛ ዕልፍኙ፤ ምሰሶ አልባ ግዙፍ የመስታወት ጎጆ ነው፡፡ ግዝፈቱ ይጫናል፡፡ እዚህ እልፍኝ የገባ የሰው ልጅ የማነስ ስሜት ይደቁሰዋል ልበል? እንደዚያ ተሰማኝ፡፡ የእልፍኙ ዙሪያ ገባ በመሰብሰቢያ አዳራሾች ተሞልቷል፡፡ Conference Room 1, 2, 3, 4…
ወደ ወዳጄ ዞሬ “ለምን፣ እንዴት ነበር የመጣነው?” ስል ጠየቅሁት፡፡ ነገረኝ፡፡ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያው ቅርንጫፍ፣ በቢዝነስ አድምኒስትሬሽን ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ያስመርቅ ኖሯል፡፡
“በወዳጄ የተደገሰልኝ አዲስ ነገር ምን ይሆን? መቼም የምረቃ ስነ ስርአቱን እንድከታተል ብቻ ይዞኝ አልመጣም” ስል አሰብኩ፡፡ ቀስ በቀስ መገናኛ እልፍኙ በርከት ያሉ ሰዎችን ማስተናገድ ጀመረ፡፡ በዚያውም ግዝፈቱና ልቅ ባህሪው እየታረመ ከርከም፣ ሰብሰብ ያለ እየመሰለኝ መጣ፡፡ ሁሉም ነገር ልክ እንዳለው የሚያስገነዝብ ብዙ ብሒል አለን፡፡ “ዶሮ በጋን” እንላለን፤ ላልተመጣጠነ ጥምረት ሰውም ቢሆን ልክ አለው፡፡ ያለበት ያለቅጥ ከገዘፈ “ዶሮ በጋን” ሊያስመስለው ሊያሳንሰው፣ ብሎም ለራሱ ያለውን ሰዋዊ ግምት ሊጫጫነው ይቻላል፡፡ የሰው ልጅ በሳይንስ ሰማይ ዋሾ ግርዶሽ መሆኑንና ፅንፍ አልባ ግልጥጥ ህዋ ውስጥ መኖሩን ሲገነዘብ፣ ለራሱ ያለው ነባር ግምት እንደወደቀው ማለት ነው፡፡ ከመሰብሰቢያ አዳራሾቹ ወደ አንዱ ዘለቅን፡፡ አዳራሹ የብርቱካን አንዲት ዘለላ ቅርፅ አለው፡፡ ግማሽ ክብ፡፡ በስተግራ ጥግ ላይ ሶስት ሴቶች የቫዮሊን ዕቁብ ይጣጣላሉ፡፡ የጥዑመ ዜማ መዋጮው “ተማር ልጄ” የተሰኘ የአለማየሁ እሸቴን ተወዳጅ ዘፈን ዳግም ፈጥሯል፡፡
ተማር ልጄ
ተማር ልጄ፣
ወገን ዘመድ የለኝ
ሐብት የለኝም ከእጄ፣
አፍሪካ መሰለችኝ፣ ኢትዮጵያ መሰለችኝ …
… በእያንዳንዱ መቀመጫ ፊት ለፊት የመመረቂያ መፅሔትና የፕሮግራም መግለጫና ማስተዋወቂያ ፅሁፍ ተቀምጧል፡፡ አንስቼ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ ወዳጄም እንዲያ እያደረገ ነበር፡፡ የመፅሔቱ መክፈቻ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የዶ/ር ሚካኤል ብሮድስኪ መልእክት ነው፡፡ እጥር ምጥን ያለና ሁለት ሰዎችን ያጣቀሰ መልዕክት፡፡ አንዱ የ1987 ዓ.ም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ባለቅኔ ጆሴፍ ብሮድስኪን ንግግር ያጣቀሰ ሲሆን ሌላኛው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊኒስተን ቸርችልን የሚያስታውስ ነው፡፡
በወዳጄ የተደገሰልኝ አዲስ ነገር የቱ ነው? ….
…. ገለጥኩ፤ በሊንከን ዩኒቨርሲቲ የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኢትዮጵያ፣ መስራችና ዳይሬክተር የሆኑት የአቶ አቤቶ መላኩ መልዕክት ነው፡፡ በፈጣሪና በራስ በመተማመን ከፊት የሚጋረጥን መሰናክል በቆራጥነት መጋፈጥ እንደሚገባ ተማሪዎችን ያስገነዝባል፡
በወዳጄ ተሸፋፍኖ የተቀመጠልኝ አዲስ ነገር የት አለ?
የኮሌጁ መምህራንና ሐላፊዎች እንዲሁም ተማሪዎች ፎቷቸውና መልእክታቸው ተደርድሯል፡፡ ይሄን ሳገላብጥ ወዳጄ ጎሸም አድርጎ፣ የራሱን መፅሔት አሳየኝ፡፡ አንዲት ፈረንጅ በደቡብ የባህል ልብስ ተውባ፣ በተንሰራፋ ሥርዓት ቡና ስታፈላ የተነሳችው ፎቶ ይታያል፡፡
የራሴን መፅሔት ገለጥኩ “The Challenge” (ተፈታታኙ) በሚል ርዕስ ጥቂት የአማርኛ ዘይቤዎች፣ ምሳሌዎችና የዘፈን ግጥሞች ከእነ እንግሊዝኛ ፍቺዎቻቸው ንዑስ ርዕስ ሆነው፤ የተጣቀ    ሱበት ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ “ትምህርትና መንገድ ማለቂያ የለውም”፣ “የተማረ ይግደለኝ” ፣ “አሳድገውናል በማር በወተት - አባባ ጃንሆይ የሁሉም አባት” ፣ “ተምሮ ያላስተማረ ዘርቶ ያላጠረ” … ፅሁፉ የቡና አፍይዋ ፈረንጅ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ሥሟ ተጠቅሷል፡፡ ሥሟም እንግሊዝኛና አማርኛን ያጣቀሰ ነው - LaDena - “Serkalem” (ሰርካለም) Scnapper …
… “እና” በሚል ጠያቂ አይን ወዳጄን አየሁት፡፡ አፉን ወደ ጆሮዬ አስጠጋ …
“ወ/ሮ ሰርካለም፤ የአቶ አቤቶ መላኩ እናት ኛቸው፡፡ አስተምረው ለዚህ ያበቁት፡፡ ውለታቸው ሀገር ጠቀስ ነው፡፡ ይሄ ኮሌጅ ኢትዮጵያ የመጣው በአቶ አቤቶ ብርታት ከዩጋንዳ ተነጥቆ ነው፡፡ እዚያ እፊት ይታይሃል?” በአገጩ ጠቆመኝ “ወ/ሮ ሰርካለም ልዩ እንግዳ ሆነው ከአሜሪካ መጥተዋል፤ እኛውልህ”
አንገቴን አንጠራርቼ አየሁ፡፡ ወርቃማ ጥለት ያለው የሐበሻ ልብስ ለብሰዋል፡፡ ጥለቱ ከትከሻቸው እስከ ወገባቸው ወርዶ፣ ከፊታቸው ቀለም ጋር ይፎካከራል፡፡ ሸበቶ ፀጉራቸው በአጭሩ ተከርክሞ የጐጃም ሴቶችን ያስታውሳል፡፡
እስካሁን የባዘነው መንፈሴ መስመሩን ለየ….
እንደ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የባዕድ ፍቅር የተቸረው በዓለም የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንፃር ያልዘራነውን ስናጭድና ስናፍስ ኖረናል ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ባዕዳን በሰላም ጊዜ ጉልበታቸውን፣ በጦርነት ጊዜ ህይወታቸውን ሰጥተውናል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ባለሟል የነበረው እንግሊዛዊው ሊቀመኳስ ዮሐንስ ቤል ትዝ አለኝ…
ሊቀመኳስ በኢትዮጵያ ፍቅር ተማርኮ ጠቅልሎ እስኪገባ ድረስ የእንግሊዝ ባህር ኃይል መኮንን ነበር፡፡ ቀደም ሲል ለራስ አሊ፣ ቀጥሎም ለአፄ ቴዎድሮስ አሽከርነት በማደር የፍቅር “ከፍ - ዝቁን” ጀመረ፡፡ ሊቀመኳስ ዮሐንስ በኑሮውም ሆነ በአለባበሱ እንግሊዝን ክዶ የወቅቱን የኢትዮጵያውያን ገበሬዎች መስሎ ነበር፡፡
 አለባበሱ ብቻ ሳይሆን ጫማ አለማድረጉና ባርኔጣ አለመድፋቱ ብዙዎችን ያስገርም ነበር፡፡ መጽሐፉ፤ “ጌታ አንድያ ነፍሱን እስኪሰጥ ድረስ የሰውን ልጅ ወድዶት ነበር” እንዳለ፣ እንዲሁ በሊቀመኳስ ዮሐንስ ላይም ሆኗል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከአጐታቸው ልጅ ከደጃች ጋረድ ጋር ሲዋጉ፣ ለእሳቸው የተተኮሰው ጥይት ላይ በመጋረጥ ህይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ሊቀመኳስ ዮሐንስ ሲሞት አፄ ቴዎድሮስ ሬሣው ላይ ተደፍተው እንዲህ ሲሉ ማልቀሳቸውን ሔነሪ ዱፍተን ጽፏል፡-
“ወዳጄ ቤል፣ ደሃው ቤል፣ በወዳጅነት ክፍያ ህይወቴን ያዳንኸው ቤል…”
የችግር ወቅት አረር ከጦርነት ጊዜ ጥይት አይተናነስም፡፡ ወ/ሮ ሰርካለም፤ አቶ አቤቶን ለዚህ ለማብቃት የትኛውን የህይወት ዳገት ወጥተው፣ የትኛውን ቁልቁለት ወረዱ? ስንት ትርፍ ሥራ፣ ስንት ትርፍ ጊዜ፣ ስንት ትርፍ ሐሳብ…አፈሰሱ? ምን ያህል ጊዜ እንቅልፍ፣ ዕረፍት፣ ሠላም አጡ?
የምረቃው ፕሮግራም መካሄድ ጀመረ፡፡ እኔ ግን ከዘመትኩበት መመለስ ተስኖኛል፡፡ የሚጣል የሀሳብ ግዳይ ላይኖር እባዝናለሁ፡፡ ብዙ ባዕዳን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ፍቅር የዋተቱበት ጊዜ፣ ጉልበትና ልፋት የማይራገፍ የዕዳ ሸክም ሆኖ ይታየኛል፡፡ በሥነ ፅሁፍ እና በነገረ - ቋንቋ ረገድ እንኳን ስንት የሠላም ጊዜ ታጋዮች እኛ አዝረክርከን የተውነውን ሲሰድሩ ህይወታቸውን ገብረዋል? ኢዮብ ሎዶልፍ፣ ኦገስት ዲልማን፣ ዎልፍ ሌስሎው፣ አግናቲዎስ ጉይዲ የሰሩትን የትኛው ኢትዮጵያዊ ሞክሮታል? በግዕዝ፣ በትግርኛና በአማርኛ ያደረጉት ጥናት ዛሬም የምንመካበት ጥሪታችን አይደለምን?በዘመናዊ ሥነ - ፅሁፍም ቢሆን እራሳችንን ያላስቻሉን ምሁሮች ሲያንጐላጁ፤ ብዙ ሥራ የሰሩት እነዚያው ባዕዳን አጥኚዎችና አፍቃሪዎቻችን ናቸው፡፡ “Ethiopian Literature in Amharic” የሚል መፅሐፍ ያቀረበው ቶማስ ኬን፤ “Tradition and Change in Ethiopia” የተሰኘ መፅሐፍ ያለው ኑት ሞልቬር፤ “Four African literatures”ን የደረሰው ፕሮፌሰር አልቤርት ዤራር እዚህ ቢጠቀሱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
የምረቃ ፕሮግራሙ በብዙ ተናጋሪዎች ታጅቦ እየተከናወነ ነው፡፡ ድንገት አቶ አቤቶ መላኩ ወደ መነጋገሪያው ወጥተው፣ አንድ ልዩ እንግዳ በመካከላችን እንዳለ አበሰሩን፡፡ ጆሮዎቼ ነቁ፡፡ ልዩ እንግዳዋ La Dena (ሰርካለም) Schnaper እንደሆኑ ገለፁ፡፡ አቶ አቤቶ የሀበሻን ሁሉ ሆድ በሚያላውስ መልክ “እናቴ” እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ወ/ሮ ሰርካለም በአፍላ ዕድሜያቸው ከ1963 እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ለአራት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም ጓድ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት በፊት የአንድ ረድኤት ድርጅት ሠራተኛ ሆነው ዳግም በመጡበት ወቅት ነበር ከአቶ አቤቶ ጋር የተገናኙት፡፡ “አስተምሪኝ” ስል ተማፀንኳት ይላሉ፡፡
 መንገድ ላጋጠመን ተማፅኖ ቀርቶ ሥጋችን ላቋጠረን ልመና እንኳ ጆሮ የምንነፍግ ስንት ነን፡፡ ወ/ሮ ሰርካለም ግን ለዚያ ባዕድ ልጅ ቃል - ገቡ፡፡ ቃላቸውንም ጠብቀው ወደ አሜሪካ ወሰዱት - አስተማሩትም፡፡ ትሩፋቱ ለእኛም ተረፈ፡፡ ባዶ እጁን የሄደው ልጅ፣ ለወገን መመኪያ የሚሆን ድርጅት ይዞ ተመለሰ፡፡ ውለታቸው ለሀገር ተረፈ፡፡ ወ/ሮ ሰርካለም ወደመነጋገሪያው ተጋበዙ፡፡ እንደ ሊቀመኳስ ዮሐንስ በአለባበሳቸውም በዘይቤአቸውም እኛን ሆነው ቀረቡ፡፡ “አቤት - አቤት - አቤት፤ እንዴት ደስ ብሎኛል” ብለው ጀመሩ፡፡ አማርኛቸው ተውተርታሪ ይሁን እንጂ ፍሬ ጉዳይ የሚስት አልነበረም፡፡ ብዙዎቻችን በተዘነጋን የአማርኛ ተረቶች እያዋዙ የልጅ ልጆቻቸውን (ተመራቂዎቹን) አበረታቱ፡፡ “ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል ይባላል፡፡ እናንተ ተመራቂዎች ግን ዕንቁላልነታችሁ አብቅቷልና ታሽጋችሁ አትቀመጡም፡፡ ዶሮ ሆናችኋል፡፡ ወደየአካባቢያችሁ እየተዘዋወራችሁ የሚያስፈልጋችሁን የምትሰበስቡበት ሁኔታ ተፈጥሮላችኋል” ወ/ሮ ሰርካለም ደጋግመው “የእኔ ልጅ” ሲሉ አሁንም ሆድ ያገላብጣሉ፡፡ “ደፋርና ጭስ መውጪያ አያጣም” አሉ፡፡ ደገሙና “አንድ ብርቱ ለሺህ መድኃኒቱ” አሉ፡፡ ይሄንን በእርሳቸው ድርጊት እንፈክራለን፡፡ አንድ ብርቱዋ ወ/ሮ ሰርካለም፤ ለሺህዎቹ ለእኛ መድኃኒት ሲሆኑ ተመልክተናልና፡፡ ኧረ መለስ ብለን እራሳችንን እንመልከት፡፡ ስንት ሊያፈሩ የሚችሉ ህፃናት ሰርካለማዊ እጆች በመንፈጋችን እንዲሁ ጎዳና ላይ ባክነው ሲቀሩ እያየን አይደል? እስኪ ልቦና ይስጠን፡፡    

Read 2734 times