Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 06 January 2012 11:32

ማራኪዕርገት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የቀበሌ አርባ ሁለት ፅህፈትቤት ፀጥ ብሏል …

ሰፊ ግቢ ነው፡፡ የግቢውን የጀርባ አጥር የኋላ ግድግዳዉ አድርጎ የተነሣ ትልቅ፣ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ የግቢውን አጋማሽ ይዞታል፡፡ ከሲሚንቶ ይልቅ ብረትና መስታወት የሚበዛበት ብርሀናማ፣ ግሩም ሕንፃ ነው፡፡

ከኮብላይ የተወረሰ፡፡

የግቢውን ግራና ቀኝ የግንብ አጥር ተደግፈው በሸካራ ብሎኬት የተሰሩ በርከት ያሉ ደጃፍ ቤቶች ተደርድረዋል፡፡ አያምሩም፡፡ በጥበብና በጥንቃቄ ከታነጸው ትልቅ ፎቅ ቤት እግሮች ላይ የበቀሉ ዕጢዎች ይመስላሉ፡፡ ከፎቁ አጠገብ በስተቀኝ - መጀመሪያ ካለው ጠባብ የእስር ቤት ክፍል የምስራች ብቻዋን በጀርባዋ ተኝታ ጣራ ጣራውን እያየች በሃሳብ ተመስጣለች፡፡ ራሷን ያስደገፈችበት ቀኝ እጇ ስለ ዛለባት በቀስታ አሾልካው የግራ እጅዋን በቦታው ተካችና በረጅሙ ተነፈሰች፡፡

መወሰን አልቻለችም፡፡

ከሰሞኑ በአንደኛው፣ በማንኛውም ቀን ለምርመራ እንደምትጠራ አውቃለች፡፡ ምርመራ ክፍል ውስጥ ከተናገረች ትኖራለች፡፡ ካልተናገረች ትሞታለች፡፡

ምርጫው አጭር እና ግልፅ ነው፡፡ ከመታሰሯ በፊት እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ቢገጥማት ምርጫዋ የቱ እንደሚሆን አስባውም አታውቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ምርጫዋ በእርግጥ ግልጽ ነበርና፡፡ አትናገርም፡፡ እነዚህ ባንዳዎች እጅ ከመግባትዋ አስቀድማ ነፍሷን በገዛ እጇ ታጠፋለች፡፡ “ግን አልረባም እኮ!” አለች ለራሷ፡፡ “ሁልጊዜ ሰው ዝቅ አድርጌ መገመት እወዳለሁ፡፡ ይሄ የፊውዳል አስተዳደጌ መሆን አለበት፣” አለችና ከነሕይወቷ ልትያዝ የምትችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል አስቀድማ ባለማሰቧ ራሷን ወቀሰች፡፡ “ግን አስቀድሜ አስቤበትም ቢሆን እኮ ምርጫዬ አልናገርም ነበር የሚሆነው፡፡ እነዚህ ደደቦች ያሰሩኝ ዕለት ቢመረምሩኝ - ጥሩ ነበር፡፡ አሁን ሳምንት ሙሉ ጨለማ ቤት ውስጥ ብቻዬን ሳሰላስል ልሰንፍ ነው መሰለኝ …”

መወሰን በእርግጥ አልቻለችም፡፡

“እንዴት! ለምንድን ነው መወሰን የማልችለው?” እራስዋን ጮክ ብላ እየተናገረች ተቆጣችው፡፡ ከተጋደመችበት ዘላ ተነሳችና ቀጥ ብላ ቆመች፡፡ ክፍሉ ድፍን ጨለማ ነው፡፡

ጨለማው ላይ ፊት ለፊት አፍጥጣ ለጥቂት ደቂቃ ፀጥ አለች፡፡ የልቧ ምት ብቻ ነበር የሚሰማው፡፡

ፀጥታ፡፡

ድንገት ለምን መወሰን እንዳልቻለች ግልጽ ሆነላት፡፡ እና ፈራች …፡፡ ፅኑ አላማና፣ ፅኑ ፍቅር …፡፡

ዓላማዋ እንድትሞት ያስገድዳታል፡፡

ፍቅር እንድትኖር ይጠራታል፡፡

በኃይል ፈራች፡፡

ለምን መወሰን እንዳልቻለች ስትረዳ ደንግጣለች፡፡

ይህንን በእርግጥ እሷ መወሰን አትችልም፡፡ ማንም ቢሆን ለመወሰን አይችልም፡፡ እሺ! - ሌላው ይቻል፡፡ እሷ ግን አትችልም፡፡ በቃ፡፡

መንፈሰ-ጠንካራነቷና በራስ መተማመኗ ሲከዷት ይታወቃታል፡፡

በቀስታ ሲሚንቶው ወለል ላይ ተቀመጠች፡፡

ጉልበቶቿን በሁለት እጆቿ ይዛ “ጋሽዬ” እያለች ማልቀስ ጀመረች፡፡ አባቷን ነው፡፡ ሴትነቷ ለብዙ ዓመታት ተቀብሮ ከቆየበት በቀስታ ወጥቶ መንፈሰ-ጠንካራነቷና በራስ የመተማመን ስሜቷ የለቀቁትን ደም ስሮቿን ጨምድዶ ይይዝ ጀመር፡፡

 

(“የትሮይ ፈረስ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” ከሚለው የደራሲ አሳምነው ባረጋ መድበል የተቀነጨበ - 1994 ዓ.ም)

 

 

Read 2770 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:43