Saturday, 13 December 2014 10:51

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

መቼ ነው ያለሁት?
ዛሬ ነግቶ መሽቶ ቀኑን አልፈውና፣
ሌላው ቀን ሲተካ ሲሆን ትናንትና፣
ይኸው እኖራለሁ አለሁ እኮ ዛሬ፣
ደግሞም ለዓመታት  ተስፋ አለኝ መኖሬ፣
    እያልሁ አስብና፣
    ሞቴን እረሳና፣
    እቅዴን አውጥቼ፣
    ምኞቴን አስፍቼ፣
ደጉን ተመኝቼ፣
ክፉውን ዘንግቼ፣
ሞትን ተሸክሜ ግን እየረሳሁት፣
ጎንበስ ቀና እያልሁ ይኸውና አለሁት፡፡
ምንም ባላውቀውም ቀኑን መሻገሬ፣
የነገን እንጃ እንጂ አለሁ ግን ለዛሬ፡፡
ሞት ትዝ ቢልም፣ ከራርሞ ከራርሞ …
    ከስንት ቀን አንዴ፣
መች ተስፋ ቆርጬ፣ ሰብዓዊ ፍጡር…
        ሰው አይደለሁ እንዴ!
ሃሳብ አይገባኝም፣ ባስብስ ምን ልሆን …
           ከቶ የማይቀረውን፣
ስለዚህ ማሰብስ፣ ዛሬን እንጂ ኑሮን …
    ፋታ የማይሰጠውን፡፡
ግን ታዲያ! …
    ማለፌን ሳስታውስ እንደገና ደግሞ፣
    ከውጥኔ በፊት ሞት ሲመጣ ቀድሞ፣
        ድንገት ፀጥ እልና፣
        ክልትው እለውና፣
        ሁሉም ይቀርና፣
        ጣጣዬ  ያከትምና፣
        ክርችም ብሎ ቁልፉ፣
        ይዘጋል ምዕራፉ፡፡
ቀነ - ሞታችንን እኔም ሆንኩ ሌላው …
          ጨርሰን አናውቀው፣
ስለዚህ ነው ሰዎች፣ “መቼ ነው ያለሁት?”
    ብዬ የምጠይቀው፡፡
                  * * *
አምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
ህዳር 2007 ዓ.ም

Read 3647 times