Saturday, 13 December 2014 10:45

ወጣቱን በቅኔ

Written by  አስረስ አያሌው (አዲስ አበባ) ኢሜል፡- asrinholeo@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

         በአገራችን “ወጣት የነብር ጣት” የሚል አባባል አለ፤ ወጣትነት የብርታትና የጉብዝና ዕድሜ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ነብር ጥፍሮቹን በሚያድነው እንስሳ ላይ ከሰካ፣ ሰካ ነው፣ እንስሳው የትም አያመልጥም፡፡ ከዚያ በኋላ ጉሮሮውን አልያም ማጅራቱን ባንድ ንክሻ ይዞ ሲጥ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ወጣቶችም አንድ ነገር ከያዙ፣ ያዙ ነው - ያ ነገር ይጥቀምም ይጉዳ ሁሉ ነገራቸውን ይሰጡታል፡፡ በአገራችን በ1966ቱ አብዮት ወቅት የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አደባባይ የወጡት ከመምህራኖቻቸው፣ ከወታደሩና ከፋብሪካ ሠራተኛው በፊት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ከገባቸው ነገር ያልገባቸው ቢበልጥም አብዮቱን የሙጥኝ ብለው ይዘዉት ነበር፡፡ በኋላም ኢህአፓን ተቀላቅለው ሲታገሉ የነበሩ ወጣቶች የነበራቸው ራስን እስከመሰዋት የደረሰ ድርጅታዊ ፍቅር እውነትም ወጣትነት ካልተጠነቀቁ ምን ያህል ለግብታዊነት የሚዳርግ ዕድሜ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ዛሬ የሚያስተዳድሩን ገዢዎቻችንም በወጣትነታቸው በረሃ የገቡ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ በተገቢው መንገድ የሚያደራጀውና የሚመራው ቢያገኝ ታሪክ ሊሠራ የሚችል ኃይል ዛሬ ያለበት ሁኔታ ያሳዝነኛል፡፡ የኛ ትውልድ ወጣት ግራ የተጋባ ነው፡፡
እንደ አያቶቹ አርበኛ፣ እንደ አባቶቹ ደግሞ አብዮተኛ አይደለም፡፡ ልግመኛ ነው፡፡ ልግመኛ የሆነው ግን ወዶ አይደለም፡፡ የሚያግዘው አጥቶ ነው፡፡ በአገራችን እናቶች ተሰብስበው ቡና ሲጠጡ ከመካከላቸው አዋቂ ለሚባሉት ለአንደኛይቱ የቡናቸውን አተላ የማስነበብ ልማድ አላቸው፡፡ ይህ የባለስኒውን ዕድል ፈንታ ይገልጣል ተብሎ የሚደረግ ከአጉል እምነት የመነጨ ልማድ ነው፡፡ ተከታዩዋን ቅኔ ስናነብ ይህን አጉል ልማድ ወደ ጎን ብለን ፍሬ ነገሩን ለማግኘት በመሞከር ይሁን፡-
“የቡኑን አተላ አትድፉት ብለናል
አንባቢ ጠፋ እንጂ ስኒማ ሞልቶናል”
የጠፋው የቡና አተላ የሚያነብ አይደለም፤ እሱንማ እናቶች ተክነውበታል፡፡ ይልቅ ያጣነው የሚያነብ፣ ታሪኩን የሚያውቅና የሚጠይቅ ትውልድ ነው፡፡ ያለፈው ትውልድ በበጎ ከሚነሳባቸው ነገሮች ዋነኛው ለንባብ የነበረው ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡  በአንጻሩ ዛሬ “ስኒማ ሞልቶናል፡፡” አዳዲስ ሲኒማ ቤቶች በየጊዜው ሲከፈቱ እናያለን፡፡ አዳዲስ አብያተ መጽሐፍት ግን ተከፈቱ ሲባል አንሰማም፡፡ ተከፍተውም ከሆነ ማስታወቂያ አይነገርላቸውም፡፡ እርግጥ ነው ሲኒማ ቤቶች ያስፈልጉናል፡፡ እንደውም እየተሠሩ ካሉት ፊልሞች የጥራት ደረጃ ጋር ሲነጻጸር አያንስም ካልተባለ በስተቀር፣ ካለን የህዝብ ብዛት አኳያ ሲኒማ ቤቶቻችን ቁጥራቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም አብያተ መጽሐፍት በእጅጉ ተመናምነዋል፡፡ በውጤቱም የማያነብ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ በተቃራኒው ግን በሲኒማ ቤቶች ደጃፍ ላይ ረጃጅም ሰልፍ ይታያል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ፊልም ሰሪዎቻችን ራሳቸው የሚያነቡ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍትን ወደ ፊልም ሲቀይሩ እምብዛም አይታዩም፡፡ የቱ ይቀድማል - መጽሐፍ ወይስ ፊልም? ቢያንስ ግን መጽሐፍ ወደ ፊልም እንጂ ፊልም ወደ መጽሐፍ ተቀየረ ሲባል አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
ወጣቱ እንደ ንባብ ያሉ አስተማሪ መዝናኛዎችን ብዙም እንዲወድ ባለመደረጉ ትኩረቱን ወደ አልባሌ የጊዜ ማሳለፊያዎች ለማዞር ተገዷል፡፡ እነኚህ መዝናኛዎች ገንዘብን፣ ጊዜን፣ ጤናን፣ ቤተሰባዊና ማኀበረሰባዊ ትስስርን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህይወትን የሚያሳጡ ናቸው፡፡ ዛሬ ወጣቶቻችን አደጋ ተጋርጦባቸዋል - ያውም የእሳት አደጋ፡፡ እናም ይህን ተረድቶ የተጨነቀ ወገን እንዲህ ይላል፡-
“ለማዳን ባትችል ቤት ንብረትህን
እሳቱ ሳይበላህ አሽሽ ነፍስህን”
አዎ፣ ቤቱ በእሳት የተያያዘበት ሰው በቅድሚያ ማድረግ ያለበት ማቄን ጨርቄን ሳይል ህይወቱን ለማትረፍ መሸሽ ነው፡፡ ወጣቱም በሀሺሽና በተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች ሱስ ተጠምዷል፡፡ በእኩዮች ግፊት፣ ዘመናዊነት ነው ብሎ በማሰብ ወይም መሄጃ በማጣት ተዘፍቆበታል፡፡ አንዳንድ የምሽት ክበቦች የቀን ቀን ሥራቸው ወጣቶችን ሰብስቦ ጢስ ማጠን ነው፡፡ እኔ በግሌ ቦሌ ሐያት ሆስፒታል አካባቢ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር የምሄድበት ቤት አለ፡፡ ቤቱ ጭር ያለና ሰላማዊ ነው፡፡ ሆኖም ጥቂት እንደተቀመጣችሁ ድንገት ከውስጠኛው ክፍል ከደህና ኗሪ ቤተሰብ የተገኙ የሚመስሉና ገና በታዳጊነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ተግተልትለው ሲወጡ ታያላችሁ፤ ቆይተው ደግሞ ግር ብለው ተመልሰው ይገባሉ፡፡ አኳኋናቸው ሁሉ ያፈነገጠ ነው፡፡ አንድ ቀን አስተናጋጁን ጠርቼ ብጠይቀው እየተቅለሰለሰ ልጆቹ የሚመጡት ዕፅ ለመውሰድ እንደሆነና ከነሱ በስተቀር ሌላ ሰው ወደ ውስጥ መግባት እንደማይፈቀድለት ነገረኝ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያሉ የንግድ ቤቶች በወጣት ህይወት እየቀለዱ ያለ ከልካይ ገንዘብ ያጋብሳሉ፡፡ እሺ ልጆቹ የሚያጠፉት ገንዘብ የወላጆቻቸው ስለሆነ አይቆጫቸው ይባል፣ ግን እንዴት የገዛ የራሳቸው ህይወት አያሳስባቸውም?
በወጣቱ ላይ ወጥመድ የሆነበት ዋናው ነገር የጃማይካውያን ተፅዕኖ ነው፡፡ በፊት በፊት እዚያው ሻሸመኔ አካባቢ ይሆናል እንጂ አዲስ አበባ ውስጥ የካናቢስ ስርጭት በግልፅ ሲካሄድ እንደነበረ አላውቅም፡፡ አሁን ግን ቦሌ ከኖክ ነዳጅ ማደያ ገባ ብሎ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ሀያ ሁለት ማዞሪያ አካባቢ አንድ የምሽት ክበብ ውስጥ አደገኛው ኮኬይን ሳይቀር በክብሪት ሳጥን ውስጥ ተደብቆ እንደሚሸጥ ሰምቻለሁ፡፡ የሚወራው ነገር ሁሉ እንዲህ ያሰኛል፡-
“ሁልጊዜ አሻጋሪ አይገኝምና
ሰምጠሽ እንዳትቀሪ ተይ ተማሪ ዋና”
ወጣቶቻችን በጃማይካውያን የአኗኗር ዘይቤና የሙዚቃ ስልት ከተመሰጡ ቆይተዋል፡፡ ሬጌ ሙዚቃ ስለ ፍቅርና ሰላም በመስበክ ቢታወቅም ሁልጊዜ እንደዚያ ነው ማለት አይደለም፡፡ ወጣቱ ከማርሎን አሸር “Ganja Farmer”፣ እስከ አፍሮማን “Before I Got High” ድረስ ማሪዋናን በግልፅ በሚያወድሱ ዘፈኖች እየተወዛወዘ ይናብዛል፡፡ ዋና መዋኘት ሳይችሉ ወንዝ ውስጥ መግባት ውጤቱ ራስን ለአስከፊ ሞት መዳረግ እንደሆነው ሁሉ በማሪዋናም ሱስ ሰምጠው የቀሩ የትየለሌ ናቸው፡፡ መቸም የፈረደበት ቤተሰብ ጦሱን ችሎ አስታምሞ አንዳንዶቹን ወደ ሰውነት ተራ ይመልሳቸው ይሆናል፡፡ ይሁንና ይህን የሱስ ወንዝ ሁሉም አይሻገሩትም፡፡ ብዙዎች ትምህርታቸውን አቁመዋል፣ ለከባድ የአእምሮ ቀውስና ባስ ሲልም ለእብደት ተዳርገዋል፡፡ በአንድ ወቅት እናደንቃቸው የነበሩ አርቲስቶቻችን ሳይቀሩ በየመንገዱ እየለፈለፉና እየተሳደቡ መሄድ ጀምረዋል፡፡በአሁኑ ወቅት የወጣቱ ብቻ ሳይሆን የመላው ኀብረተሰብ ችግር የሆነው የጫት ጉዳይም መረሳት የለበትም፡፡ በጫት የተነሳ አንድ ትውልድ ቃል በቃል እየጠፋ ነው፡፡ ስሟን በማልጠራት የጫት መዲና በሆነች ምስራቃዊ የሀገራችን ከተማ ከአምስት ሰው አንዱ አብዷል ወይም ለማበድ መንገዱን ጀምሮታል፡፡ ጫት ገሃዱን ዓለም ያስጠላል፣ ምናብ ውስጥ ይከታል፡፡ ተጠቃሚውን ከራሱና ከቤተሰቡ ጋር ያጣላል፡፡ እናም አስታራቂ እንዲህ እያለ ይለምናል፡- “እናስታርቅ ብንል አስቸገራችሁን
ምናለ ብተዉት ይህን ቂማችሁን”
ይህ ምልጃ የቀረበው ወጣቱ ከ‘ቂማ’ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ሱስ እንዲወጣ ለመወትወት ነው፡፡ በረሃብ የምትታወቀው አገራችን ‘ሪሃብ’ (Rehabilitation Center) አቋቁማ ሱሰኞች እንዲያገግሙ የምትረዳበት አቅም የላትም፡፡
መፍትሔው መጥፎውን ልማድ ሙሉ ለሙሉ እርግፍ አድርጎ መተው ብቻ ነው - የአካል ክፍልን ቆርጦ እንደ መጣል ቢከብድም፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ስለ ወጣት እህቶቻችን አለባበስ እንነጋገር፡፡ ብዙዎቹ ስርዓት ያለውና ልከኛ አለባበስ የሚከተሉ ቢሆንም ያንዳንዶቹ አለባበስ ግን ያስበረግጋል፡፡ ታላላቆቻቸው ቢያዩዋቸው እንዲህ ሳይሉ አይቀሩም፡-
“እጅግ ተጨነቀ አዘነ ልባችን
ርቃን ስትሄድ ታናሽ እህታችን”
ወጣቷ ከምትኖርበት ኀብረተሰብ ባህል በመንፈስ መራቋ ሳያንሳት በአደባባይ ርቃን ሊባል የሚችል አለባበስ ለብሳ ስትሄድ በቤተሰቧ ላይ የሚፈጠረው መሸማቀቅ ከፍ ያለ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደዚያ ለብሳ ስትወጣ ያልከለከለ ወላጅ ከእሷ ባይሻል ነውም ያስብላል፡፡ እንዴት መልበስ እንዳለብኝ ማንም አይነግረኝም የሚሉ በበረከቱ ቁጥር እነሱን አይቶ ስሜቱ የተነሳሳ አለሌ መጫወቻ የሚሆኑት ሚስኪን ልጃገረዶች ዕጣ ያሳዝናል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየተዛመተ የመጣ አንድ ክፉ ወረርሽኝም አለ፡፡ ያየውን ሁሉ ሳያመዛዝን ለቀም የሚያደርገው ወጣትም የወረርሽኙ ዋነኛ ተጠቂና አስፋፊ ሆኗል፡፡ እስቲ ቀጣዩዋን ቅኔ አንብበን የወረርሽኙን ምንነት እንድረስበት፡-
“በዱላ ምክቶሽ ፈሪው እየገባ
ሲያቀምሱት ይሸሻል አልቅሶ ደም እንባ
የዛሬው ግን ፍልሚያ ዋለ ተፋፍሞ
መንደሩ ቀለጠ ወንድ ከወንድ ገጥሞ”
ዱላ ምክቶሽ በገጠር የተለመደ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ለነገሩ ጨዋታ ይባል እንጂ አልፎ አልፎ ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የሱርማዎችን ‘ዶንጋ’ እናስታውሳለን፡፡ ታዲያ ሁለት ጀግኖች የተጋጠሙ እንደሆን ፍልሚያው ምንም አሰቃቂ ቢሆን ተመልካች ግን ምርጥ ነው ብሎ ያሞካሻል፡፡ የላይኛው ቅኔ የሚናገረው ግን ስለ ዱላ ምክቶሽ ሳይሆን ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ነው፡፡ ዛሬ “ወንድ ከወንድ ገጥሟል፡፡” በርካታ ወጣቶች በዚህ አደጋ እንደተያዙ በተለያዩ ሚዲያዎች እንሰማለን፡፡ ግብረ ሰዶማውያን አደን ላይ ናቸው፡፡ እኔ እንኳ ባለኝ ጠባብ ማኀበራዊ ግንኙነት እኔን ጨምሮ ሦስት ጓደኞቼ በተለያየ ጊዜ በግብረ ሰዶማውያን ትንኮሳ ተፈጽሞብናል፡፡ ብዙ ጓደኞች፣ ያሏቸው ደግሞ ብዙ ገጠመኝ ሊሰሙ ይችላሉ፡፡ ግብረ ሰዶም በሴቶችም በኩል የተለመደ ሆኗል፤ የፌስ ቡክ ግሩፕ እስከ መመስረት ደርሰዋል፡፡ እንግዲህ የዘመናችን ወጣት ያሉበት ጋሬጣዎች በጥቂቱ እነዚህን ይመስላሉ፡፡ በራሱ ዕድል ላይ እንዲወስን አልተፈቀደለትምና መፍትሔ ከሌላ ወገን ይጠብቃል፡፡ ይህን ጊዜ መከፋቱን በቅኔ እንዲህ ይተነፍሰዋል፡-
“ጽናትን ከውድቀት ህልምን ከሌት ወርሶ
የኑሮን አቀበት ወጣት አጎንብሶ”
አዎንታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ከመጥፎ ነገር ጥሩ ነገርን ያወጣል - ከውድቀት ጽናትን ይማራል፣ ከአስፈሪው ሌሊትም ህልም አልሞ ያድራል፡፡ በስተመጨረሻም ባለድል ይሆናል፡፡ ለዚህ የታደሉ ብዙ ወጣቶች ከመካከላችን ይገኛሉ - ብንከተላቸው አርአያ የሚሆኑን፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የትውልዴ ወጣት አንገቱን አጎንብሶ ነው ያለው፡፡ አገር ተረካቢ የሚባለው ወጣት አንገቱን ካጎነበሰ እንግዲህ አገር ምን ተስፋ አላት? እኛ ወጣቶች ከወደቅንበት መሬት ተነስተን፣ አቧራውን አራግፈን፣ ቀጥ ብለን መሄድ መጀመር አለብን፡፡ መንግሥትም ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ወጣቱን የአገራችን ዕድገት ዋነኛ ተዋናይ ለማድረግ ከልቡ ሊሠራ ይገባል፡፡
(ማስታወሻ፡- በጽሑፉ ላይ የቀረቡት ቅኔዎች በሙሉ የጸሐፊው ናቸው፡፡)

Read 2518 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.